Sunday, February 5, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ልማት ባንክ በቤኒሻንጉል በዕዳ ለያዛቸው መሬቶች 105 ሚሊዮን ብር ግብር እንዲከፍል ተጠየቀ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባለሀብቶች ለእርሻ ኢንቨስትመንት ከክልሉ መንግሥት የተረከቡትን መሬት በዕዳ የያዘው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ፣ 105 ሚሊዮን ብር የመሬት ኪራይ ግብር እንዲከፍል ተጠየቀ፡፡ ግብር እንዲከፈል የተጠየቀበት መሬት 69 ሺሕ ሔክታር ስፋት ያለው ሲሆን ለ114 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ተሰጥቶ የነበረ ነው፡፡

የክልሉ መንግሥት ባንኩ መሬቶቹን በዕዳ በያዘባቸው ዓመታት ከመሬቶቹ ማግኘት የነበረበትን የመሬት ኪራይ ግብር ገቢ ብቻ አስቦ ጥያቄውን እንዳቀረበና የግብሩን ወለድና ቅጣት ሒሳብ ውስጥ እንዳላከተተ አስታውቋል፡፡ ልማት ባንክም ጥያቄውን ተቀብሎ ክፍያውን ለመፈጸም መስማማቱን የክልሉ ገጠር መሬትና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ አመንቴ ገሺ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

የክልሉ መንግሥት በመሬቶቹ ላይ መከፈል የነበረበትን ውዝፍ ሒሳብ ለልማት ባንክ ያቀረበው ግንቦት 2014 ዓ.ም. በሁለቱ አካላት መካከል ከተደረገ ንግግር በኋላ ነው፡፡ በንግግሩ ላይ ባንኩ ግብሩን ለመክፈል በመስማማቱ የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ኮሚቴ አዋቅሮ መሬቶቹን ኦዲት በማድረግ ከአንድ ወር ገደማ በፊት 105 ሚሊዮን ብር ውዝፍ ሒሳብ ማቅረቡን አቶ አመንቴ አስረድተዋል፡፡

‹‹ይህ ሒሳብ ሲቀርብላቸው ተስማምተው በአካባቢው ያሉት ቅርንጫፎዎች ክፍያ እንዲፈጽሙ ጽፈውላቸዋል፤›› ያሉት አቶ አመንቴ፣ የመተከል አካባቢ ደንበኞችን ከሚያስተናግደው የባህር ዳር ቅርንጫፍና ካማሺና አሶሳን ከሚሸፍነው የወለጋ ቅርንጫፍ ክፍያውን መፈጸም እየተጠበቀ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የክልሉ መንግሥት በሰፋፊ እርሻዎች ላይ መሰማራት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች ሰፋፊ መሬቶችን ሲሰጥ የነበረ ሲሆን፣ ብዙዎቹ ባለሀብቶች ግን ከክልሉ በነፃ የወሰዱትን መሬት አስይዘው ከኢትዮጵያ ልማትና ንግድ ባንኮች ብድር ከወሰዱ በኋላ፣ የተበደሩትን ገንዘብ ይዘው መጥፋታቸውን አቶ አመንቴ ገልጸዋል፡፡ አንዳንዶቹ ባለሀብቶች ብድሩን የወሰዱት የደን ምንጣሮ እንኳን ሳያካሂዱ መሆኑን የጠቀሱት ኃላፊው፣ ጥቂቶቹ ሥራ ከጀመሩ በኋላ የመክፈል አቅም አጥተው ከስረው እንደወጡም አንስተዋል፡፡

ልማት ባንክ እነዚህን መሬቶች ማስያዣ አድርጎ ለባለሀብቶቹ የሰጠው ብድር ሁለት ቢሊዮን ብር ነው፡፡

እንደ ኃላፊው ገለጻ፣ ባንኩ ባለሀብቶቹ ከወጡ በኋላ አንዳንዶቹን መሬቶች ለአራት ዓመት ለሚሆን ጊዜ ይዟቸው ቆይቷል፡፡ ልማት ባንክ የሰጠውን ብድር ለማካካስ በዕዳ የያዛቸውን እነዚህ መሬቶች አጫርቶ በሊዝ ለመሸጥ ቢፈልግም፣ የክልሉ መንግሥት ለኢንቨስተሮች በነፃ መሬት የሚያቀርብ በመሆኑ እነዚህን መሬቶች ተጫርቶ የሚገዛ አለመገኘቱን ተናግረዋል፡፡

በዚህ ምክንያት መሬቶቹ ባዶ ሆነው መቆየታቸውንና ክልሉ ማግኘት የሚገባውን ጥቅም እንዳላገኘ ገልጸዋል፡፡ ይኼንንም ሲያስረዱ፣ ‹‹የክልሉ መንግሥት መሬቱን ለባለሀብቶች ሲሰጥ የሚጠብቃቸው ጥቅሞች አሉ፣ ግብር፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርና የመልማት ደረጃ ሁሉ አጥተናል፡፡ ለክልሉ የመጣ ልማት የለም፣ ግብርም አልተከፈለም የቴክኖሎጂ ሽግግርም አልመጣም፤›› ብለዋል፡፡

አክለውም፣ ‹‹መንግሥት ከእያንዳንዱ ኩንታል የሚሰበስበው የምርት ግብር አለ፣ ከ69 ሺሕ ሔክታር መሬት ምን ያህል ይሰበሰባል የሚለውን ማሰብ ቀላል ነው፤ እኛ ጋር ቢያንስ በሔክታር 50 ኩንታል ይመረታል፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

አሁን በቀረበው የመሬት ኪራይ ውዝፍ ግብር ላይም ቅጣትና ወለድ ቢታሰብ እስከ 200 ሚሊዮን ብር ሊደርስ እንደሚችል ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡

እንደ አቶ አመንቴ ገለጻ የክልሉ መንግሥት መሬቶቹ በአጭር ጊዜ ውስጥ በጨረታ እንዲተላለፉ አልያም ለክልሉ መንግሥት እንዲመለሱ ፍላጎት አለው፡፡

‹‹በመስማማት ደረጃ ግብሩን ብቻ ክፈሉና መሬቱን ደግሞ ወደ ልማት አስገቡ ነው ያልናቸው፤›› በማለት የግንቦት ወሩን ንግግር ያስታወሱት ኃላፊው፣ ግንቦት ወር ላይ በነበረው ንግግር በስድስት ወር ውስጥ የመሬቶቹ ጉዳይ መፍትሄ እንዲሰጠው ጥያቄ መቅረቡን አስታውሰዋል፡፡

አቶ አመንቴ፣ የክልሉ መንግሥት መሬቱ በባንኩ ሲያዝ የፕሮጀክቱ ባለቤት እንደተቀየረ እንጂ፣ ባንኩ የመሬቱ ባለቤት እንደሆነ እንደማይቆጠር ገልጸዋል፡፡ መሬት የሚሰጣቸው ፕሮጀክቶች በምርታማነትና ባቀረቡት ዕቅድ መሠረት ያላቸው አፈጻጸም እንደሚታይና ችግር ከተገኘ ተነጥቆ ለሌላ ባለሀብት እንደሚተላለፍ አስረድተዋል፡፡

ክልሉ ለዓመታት ያለ ሥራ የተቀመጡት መሬቶች ወደ ሥራ እንዲገቡ አልያም እንዲመለሱ እየጠየቀ ያለው በዚህ አግባብ እንደሆነም አብራርተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች