ለጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች በበቂ ሁኔታ ብድር ለመስጠት ተጨማሪ 300 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ በጥናት ተረጋገጠ፡፡
በአጠቃላይ 1.5 ሚሊዮን ለሚሆኑ ኢንተርፕራይዞች የሚያስፈልገው የፋይናንስ አቅርቦት 499 ቢሊዮን ቢሆንም በበጀት የተያዘው ግን 199 ቢሊዮን ብር መሆኑን ነሐሴ 9 ቀን 2014 ዓ.ም. በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በተዘጋጀው ሁለተኛው ብሔራዊ የሥራ ጉባዔ ላይ በቀረበው ጥናት ተገልጿል፡፡
ጥናቱን ያቀረቡት የፈርስት ኮንሰልት የማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ብሪጅስ ፕሮግራም ባለሙያ አቶ ጌታቸው መኰንን ሲሆኑ፣ ለጥቃቅን፣ ለአነስተኛና ለመካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የሚቀርበው ፋይናንስ ዝቅተኛ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
አቶ ጌታቸው እንደተናገሩት፣ በአጠቃላይ ለብድር አገልግሎት 1.3 ትሪሊዮን ብር የቀረበ ሲሆኝ፣ 94 በመቶ በባንክ አማካይነት የተሰጠ ነው፡፡
የብድር አገልግሎት የተሰጠውም ለ400 ሺህ የብድር ፋይሎች ተቋማት ወይም ለስድስት በመቶ ያህሉ ብቻ መሆኑን፣ እነሱም ዋስትና ላቀረቡ ትልልቅ ተቋማት እንደሆነ በጥናቱ ተገልጿል፡፡ በኢትዮጵያ 40 በመቶ ያህል ጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የፋይናንስ አቅርቦት እንደማያገኙ፣ ከሰሃራ በታች ካሉ አገሮች ጋር እንኳን ሲነፃፀር ዝቅተኛ መሆኑ በጥናቱ ተመላክቷል፡፡
ከሰሃራ በታች ያሉ አገሮች 30 በመቶ ለሚሆኑ ለጥቃቅን፣ ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የፋይናንስ አቅርቦት እንደማያገኙ አቶ ጌታቸው ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ከቀረበው የብድር አገልግሎት ውስጥ ለጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የቀረበው ሰባት በመቶ ብቻ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
ከቀረበው አጠቃላይ ብድር ውስጥ 85 በመቶ ቋሚ ዋስትና ላቀረቡት የተሰጠ መሆኑን፣ ለብድሩ የሚጠየቁት ዋስትና ከብዱሩ በሦስት እጥፍ እንደ የሚበልጥ ተገልጿል፡፡
በ2013 ዓ.ም. የግል ባንኮች ለብድር ያቀረቡት አጠቃላይ የገንዘብ መጠን 300 ቢሊዮን ብር መሆኑን፣ ለኢንተርፕራይዞች ሁለት በመቶ ብቻ እንደተሰጠ ጥናቱ በዝርዝር ያሳያል፡፡
ለ1.5 ሚሊዮን ጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የ300 ቢሊዮን ብር የብድር ክፍተቱ ቢሟላላቸው፣ ለ7.5 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል ማስገኘት እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡ በጥናቱ መሠረት ሲሰላ አንዱ ኢንተርፕራይዝ ከአምስት ያላነሱ ዜጎች ወደ ሥራ እንደሚያስገባ ተጠቁሟል፡፡
ለኢንተርፕራይዞቹ የብድር አገልግሎት የሚያቀርቡት ማይክሮ ፋይናንሶች እንደሆኑ፣ የሚሰጡት ብድርም እጅግ አነስተኛ መሆኑን አቶ ጌታቸው ገልጸዋል፡፡
ካሉት ጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ውስጥ 74 በመቶ ያህሉ ጥቃቅን (ማይክሮ) እንደሆኑ፣ ብዙዎቹም ያልተሸጋገሩ ወይም ካሉበት ማደግ ያቃታቸው ናቸው ብለዋል፡፡
ለእነዚህ እየቀረበ ያለው የብድር አገልግሎት 36 በመቶ መሆኑን፣ 64 በመቶ የሚሆኘው ብድር ቢመቻችላቸው ለብዙዎች የሥራ ዕድል መፍጠር የሚችሉ ናቸው ተብሏል፡፡
በጥናቱ ከቀረቡት መፍትሔዎች መካከል ብሔራዊ የብድር ዋስትና የሚሰጥ ተቋም መገንባትና አማራጭ የፋይናንስ አቅርቦትን ማስፋት እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡ ብድር ለመስጠት ለዋስትና የሚሆን ፈንድ ማዘጋጀት ከተቀመጡት መፍትሔ መካከል አንዱ ነው፡፡
በአገር አቀፍ ደረጃ ጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የሥራ ዕድል ከመፍጠር አኳያ የተሻሉ ቢሆኑም፣ የፋይናንስ አቅርቦት ስለማያገኙ መሻሻል አይታይባቸውም ሲሉ አቶ ጌታቸው አስረድተዋል፡፡