የጉምሩክ ኮሚሽን ወደ አገር ውስጥ የሚገቡና የሚወጡ ዕቃዎችን ከጉምሩክ ውጪ ለማስፈተሽ ፈቃድ የተሰጣቸው አስመጪ ድርጅቶችና ዕቃዎች ላይ ገደብ አስቀመጠ፡፡
ከዚህ ቀደም ዕቃዎቻቸውን በውጭ ለማስፈተሽ ፈቃድ የነበራቸው አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ድርጅቶችና የወጪ ንግድ ማበረታቻ ሥርዓት ተጠቃሚ ግለሰቦችና ድርጅቶች፣ ዕቃዎቻቸውን ከጉምሩክ ውጪ እንዳያስፈትሹ ተከልክለዋል፡፡ የልማትና የሲቪክ ማኅበራትም ይኸው ክልከላ ከተደረገባቸው ውስጥ ናቸው፡፡
ኮሚሽኑ ይህንን ውሳኔ ያስተላለፈው፣ የውጭ ምርመራ አሠራር የተዘረጋበትን መመርያ ዓላማ የሚፃረሩ እንቅስቃሴዎች በመታየታቸው መሆኑን አስታውቋል፡፡ የጉምሩክ ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቃበታ ባለፈው ሳምንት ለጉምሩክ ጽሕፈት ቤቶች በጻፉት ደብዳቤ፣ በውጭ ፍተሻ ምክንያት ‹‹ሊሰበሰብ የሚገባው የመንግሥት ቀረጥና ታክስ እንዳይሰበሰብ እየተደረገ›› መሆኑ እንደታወቀ ገልጸዋል፡፡
በዚህም ምክንያት መመርያው ማስተካከያ እስከሚደረግበት ድረስ ገደቦች መቀመጣቸውን ያስታወቁት ኮሚሽነሩ፣ ከዚህ ውጪ የሚሠሩ ‹‹አካላት ካሉ በተቋሙ የዲሲፕሊን ደንብና መደበኛ ሕጎች መሠረት ተጠያቂ እንዲደረጉ፤›› በማለት በደብዳቤው አሳስበዋል፡፡
ሪፖርተር በውጭ ፍተሻ ላይ የተላለፈውን ገደብ አስመልክቶ ጥያቄ ያቀረበላቸው አንድ የኮሚሽኑ ኃላፊ ገደቡ መጣሉን አረጋግጠው፣ ‹‹የተወሰኑ የሚጣሩ ጉዳዮች አሉ፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹በቅርቡ ኮሚሽነሩ ወይም ምክትሉ ማብራሪያ ይሰጣሉ፤›› በማለት ዝርዝር ጉዳዮችን ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ዕቃዎች ፍተሻን ጨምሮ የቅድሚያ የጉምሩክ ሥነ ሥርዓት የሚፈጸምበት ዕቃ ጉዳዮች የሚመሩት፣ የገቢዎች ሚኒስቴር በ2011 ዓ.ም. መጨረሻ ባወጣው መመርያ ነው፡፡
የጉምሩክ ኮሚሽን ወደ አገር ውስጥ የሚገቡና የሚወጡ ዕቃዎችን በጉምሩክ መውጫና መግቢያ በሮች፣ በተፈቀዱ የጉምሩክ መጋዘኖች፣ በመተላለፊያ መንገዶችና መዳረሻ ቦታዎች ላይ ይፈትሻል፡፡
የጉምሩክ ኮሚሽን ባለሙያዎች በሚወጡና በሚገቡ ዕቃዎች ላይ ፍተሻ የሚያደርጉት የሥጋት አመላካች ሁኔታዎች ለመየት ሲሆን፣ ይህም በዋነኛነት ይገባል ወይም ይወጣል የተባለው ዕቃ ዝርዝርና የሚገባው ወይም የሚወጣው ዕቃ መካከል ልዩነት እንዳይኖር ለማድረግ ነው፡፡
ይኼ ፍተሻ የሚደረገው በጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ወይም ጣቢያዎች ቢሆንም፣ በመመርያው የተፈቀደላቸው ድርጅቶችና ዕቃዎች በውጭ ይፈተሻሉ፡፡ የውጭ ፍተሻው የሚካሄደው በመንግሥት መሥሪያ ቤት፣ በድርጅት ቅጥር ግቢ፣ በመጋዘን ወይም ፕሮጀክት በሚገኝበት አከባቢና በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ እንደሆነ መመርያው ዘርዝሯል፡፡
የኮሚሽኑ ባለሙያዎች ከጉምሩክ ውጪ ፍተሻ የሚያደርጉበት ዋነኛ ምክንያት በፍተሻ ቁጥጥር ምክንያት የሚባክነውን ጊዜ ለመቆጠብና በዕቃዎች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለማስቀረት ነው፡፡
በዚህም መሠረት በውጭ እንዲፈተሽ የተፈቀደለት ወደ አገር ውስጥ የሚገባ ዕቃ በደርጅቱ መጋዘን ውስጥ እንዲራገፍ የሚደረግ ሲሆን፣ ኮሚሽኑ በመጋዘኑ ፍተሻ የሚያደርግ ባለሙያ ይመድባል፡፡
ሪፖርተር ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው ባለሙያዎች እንደተረዳው፣ በውጪ ፍተሻ እንዲያደርጉ በተፈቀደላቸው ድርጅቶችና በጉምሩክ ባለሙያዎች በሚደረግ ድርድር ለመንግሥት መከፈል የነበረበት ቀረጥና ታክስ የማይከፈልባቸው አጋጣሚዎች አሉ፡፡
ባለሙያዎቹ እንደሚገልጹት፣ የጉምሩክ ባለሙያ አንድ ድርጅት ወደ አገር ውስጥ ያስገባቸው ዕቃዎችን በሚፈትሽበት ጊዜ በዕቃው ዝርዝር መግለጫ ላይ ከሰፈረው የዕቃ ብዛት የበለጠ ቁጥር ያለው ዕቃ ወደ አገር ውስጥ ገብቶ ሊያገኝ ይችላል፡፡ ድርጅቱ ባስገባው ዕቃ ልክ ቀረጥና ግብር መክፈል ያለበት ቢሆንም፣ ከባለሙያው ጋር በሚደረግ ድርድር መግለጫው ላይ በሰፈረው የዕቃ ብዛት ብቻ ቀረጥና ግብር እንዲከፈል ይደረጋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ከባለሙያ ጋር በሚደረገው ድርድር በዝርዝር መግለጫ ላይ ከሰፈረ የዕቃ ዓይነት ውጪ፣ ሌሎች ዕቃዎችም ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ እንደሚደረግና ቀረጥና ታክስ ሳይከፈልባቸው እንደሚያልፉ ባለሙያዎቹ አስረድተዋል፡፡
በዚህ አሠራር ምክንያት መሰብሰብ የነበረበት ቀረጥና ታክስ እንዳይሰበሰብ እየተደረገ መሆኑን ያስታወቀው ጉምሩክ ኮሚሽን፣ በመመርያው ላይ ‹‹አስፈላጊው ማስተካከያ›› እስከሚደረግ ድረስ የቀድሞው አሠራር ላይ ገደብ ጥሏል፡፡
ከዚህ ቀደም በውጭ መፈተሽ ይችሉ የነበሩት የፋብሪካ ጥሬ ዕቃዎችና ኬሚካሎች በጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ወይም ጣቢያዎች ውስጥ እንዲፈተሹ ኮሚሽነር ደበሌ በደብዳቤው ትዕዛዝ አስተላልፈዋል፡፡ አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ድርጅቶች፣ የወጪ ንግድ ማበረታቻ ሥርዓት ተጠቃሚ ግለሰቦችና ድርጅቶች፣ እንዲሁም የልማትና የሲቪክ ማኅበራት ዕቃዎቻቸውን ከጉምሩክ ውጪ እንዳያስፈትሹ ተከልክለዋል፡፡
ትዕዛዙ ከተላለፈበት ጊዜ ጀምሮ በአስመጪዎች የሚቀርቡ የውጭ ፍተሻ ጥያቄዎች፣ በኮሚሽነሩ ውሳኔ ከተሰጠበት ብቻ ተፈጻሚ እንደሚሆን በደብዳቤው ላይ ተጠቅሷል፡፡
በመመርያው ላይ በውጭ እንዲፈተሹ ፈቃድ ተሰጥቷቸው አሁንም ገደብ ያልተጣለባቸው ዕቃዎችና ድርጅቶችም፣ መረጃቸው ለብቻ እንዲያዝና የአፈቃቀድና የአፈጻጸም ሁኔታው በተከታታይ እንዲመረመር ትዕዛዝ ተላልፏል፡፡