Tuesday, March 5, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበአፋር ሰመራ ካምፕ ውስጥ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች ወደ አብአላ መጓጓዝ ጀመሩ

በአፋር ሰመራ ካምፕ ውስጥ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች ወደ አብአላ መጓጓዝ ጀመሩ

ቀን:

በአጋቲና ካምፕ የሚገኙት በቀጣይ እንደሚጓጓዙ ተሰምቷል

ከታኅሳስ 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ በሚገኝ ካምፕ ውስጥ የእንቅስቃሴ ገደብ ተጥሎባቸው የቆዩ የትግራይ ተወላጆች ወደ አብአላ ከተማ መጓጓዝ መጀመራቸው ተገለጸ፡፡

በትናንትናው ዕለት ማክሰኞ ነሐሴ 10 ቀን 2014 ዓ.ም. በተጀመረው የማጓጓዝ ሥራ፣ በሰመራ ካምፕ ይገኙ የነበሩ ከ400 በላይ ሰዎች በአራት መኪናዎች እንደተጓጓዙ ሪፖርተር በካምፑ ከሚገኙ ነዋሪዎች አረጋግጧል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት (ኦቻ) በካምፑ የሚገኙ ሰዎችን የማጓጓዝ ሥራ መጀመሩንና ለቀጣዮቹ ሁለት ሳምንታት እንዲሚቀጥል ትናንት በትዊተር ገጹ አስታውቋል፡፡ ጽሕፈት ቤቱ አክሎም፣ ‹‹ኦቻ ተመላሾች ደኅንነቱ የተጠበቀ ሽግግር እንደሚኖራቸው ለማረጋገጥ ከአጋሮቹ ጋር እየሠራ ነው፤›› በማለት የማጓጓዝ ሥራውን ገልጿል፡፡

ኦቻ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እየተጓጓዙ እንደሆነ ከመግለጽ በቀር ያስቀመጠው ቁጥር ባይኖርም 9000 የሚጠጉ የትግራይ ተወላጆች ሰመራና አጋቲና ካምፖች እንደሚገኙ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ሰኔ 22 ቀን 2014 ዓ.ም. ሰኔ እና 2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አስታውቆ ነበር፡፡

መድህን የተባለና በሰመራ ካምፕ ውስጥ የሚገኝ ነዋሪ ለሪፖርተር እንደገለጸው፣ በካምፑ ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎችን ወደ መኖሪያ መንደራቸው ለመመለስ እንቅስቃሴ የተጀመረው ከሐምሌ ወር አንስቶ ነው፡፡ በካምፑ ውስጥ ያሉ ሰዎች ይኖሩበት የነበረው አከባቢ፣ መመለስ የሚፈልጉበት ቦታና የነበራቸውን ንብረት የሚገልጹ መረጃዎችን እንዲሞሉ ተደርጓል፡፡

በካምፑ ውስጥ ያሉት ነዋሪች ከአንድ ወር በፊት ወደ አካባቢያቸው ሲመለሱ ሊያገኙ የሚችሏቸውን የጦር መሣሪያ ቅሪቶችና ማድረግ የሚገባቸውን ጥንቃቄዎች በተመለከተ ገለጻ እንደተደረገላቸው ስሙ እንዳይጠቀስ የገለጸ ነዋሪ ለሪፖርተር ተናግሯል፡፡

ከነዋሪዎቹ የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው በሰመራ ካምፕ ውስጥ የሚገኙት አብዛኛዎቹ ነዋሪዎች በአብአላ ከተማ ነዋሪ የነበሩ የትግራይ ተወላጆች ናቸው፡፡ እነዚህ ነዋሪዎች አሁን አብአላ እየተጓጓዙ ያሉት በአራት ቀጣናዎች ተከፍለው ነው፡፡

ትናንት ጉዞአቸው የተጀመረው አሳሌ ወደሚባለው የመጀመሪያው ቀጣና የሚሄዱ ነዋሪዎች መሆኑንና ‹‹እንገላ፣ ኢድሞና ዳርአራ ቀጣናዎች በየተራ ይሄዳሉ ተብሏል፤›› ሲል አስረድቷል፡፡

በመጀመሪያው ጉዞ ሰዎችን ከጫኑት አራት የሕዝብ ማመላለሻ መኪናዎች ባሻገር በካምፑ የነበሩ ሰዎችን ዕቃዎች የያዙ ሁለት ተሳቢ መኪናዎች አብረው እንደተጓዙ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው ነዋሪዎች እንደሚያስረዱት፣ ወደ የሚጓጓዙበት ሥፍራ ከደረሱ በኋላ ስለሚኖረው ሁኔታ የተደረገላቸው ገለጻ የለም፡፡ በአጋቲና ካምፕ የሚገኙ ሌሎች የትግራይ ተወላጆች እስካሁን ጉዞ አለመጀመራቸውንም ሪፖርተር ለማወቅ ችሏል፡፡

በዚህ ካምፕ ውስጥ የሚገኙ ሰዎችም የነበሩበትንና የሚመለሱበትን አካባቢ የሚገልጽ መረጃ በተሰጣቸው ፎርም ላይ እንደሞሉና ‹‹የሰመራ ካምፕ ነዋሪዎች ጉዞ ሲጨርስ የአጋቲና ካምፕ ያሉት ይቀጥላል፤›› የሚል መረጃ እንደተሰጣቸውም ለማወቅ ተችሏል፡፡

በአብአላ ከተማ በኪራይ ቤት ውስጥ ይኖር እንደነበር የገለጸው አንድ ግለሰብ፣ አሁን የሚመለስበት ቦታ ባለመኖሩ ወደ ትግራይ ክልል ለመመለስ ፎርሙ ላይ እንደሞላ ተናግሯል፡፡ ‹‹አብአላ ቤት የሌላቸው ወደ ትግራይ ለመመስ ነው የሞሉት፣ ሰመራ ካምፕ ያሉት ብዙዎቹ ግን አብአላ ቤት አላቸው፤›› ሲል ግለሰቡ ተናግሯል፡፡

ሪፖርተር ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ወደ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽንና አፋር ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ያደረጋቸው የስልክ ጥሪዎች ባለመሳካታቸው ከመንግሥት በኩል ስለ ማጓጓዝ ሥራው መረጃ ማግኘት አልተቻለም፡፡

ኢሰመኮ ሰኔ ወር ላይ ባወጣው መግለጫ በሁለቱ ካምፖች የሚገኙት ነዋሪዎች የትግራይ ክልል አዋሳኝ ከሆኑ ከአባአላ፣ ከኮነባና ከበረሃሌ የተሰኙ ሦስት የአፋር ክልል ወረዳዎች የመጡ መሆናቸውን አስታውቆ ነበር፡፡

ነዋሪዎቹ ከአካባቢያቸው እንዲወጡና በእነዚህ ካምፖች ውስጥ እንዲቆዩ የተደረጉት ‹‹ከፈቃዳቸው ውጪ›› መሆኑን የገለጸው ኢሰመኮ፣ በካምፖቹ ውስጥ የሰብዓዊ ዕርዳታና የሕክምና አገልግሎት አቅርቦት እጅግ ውስን መሆኑን ተናግሮ ነበር፡፡

ከዚህም ባሻገር፣ በካምፖቹ ውስጥ የተከሰተ ወረርሽኝ መሰል በሽታ ለሕይወት መጥፋት ጭምር ምክንያት እንደሆነና በሰመራ ካምፕ ብቻ በበሽታ ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎች መኖራቸውን ገልጿል፡፡

አክሎም፣ ‹‹የቆዳ ወረርሽኝ የተባለው በሽታ ወደ ሌሎች ሰዎች በመዛመቱ አጠቃላይ ደኅንነታቸውና ሕይወታቸው ጭምር አደጋ ላይ መውደቁን ለመረዳት ተችሏል፤›› ሲል ሁኔታውን አስረድቶ ነበር፡፡

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) ‹‹በመጠለያ ጣቢያ ስም የተፈጸመ፣ በብሔር ማንነት ላይ የተመሠረተ ሕገ ወጥና የዘፈቀደ እስር፤›› በማለት በካምፑ ያሉ ሰዎችን ሁኔታ መግለጻቸው በዚህ መግለጫ ላይ ተጠቅሷል፡፡

ዋና ኮሚሽነሩ፣ ‹‹የአሁኑ አያያዝ የሕግ መሠረት የሌለው ከመሆኑም በተጨማሪ በካምፑ የሚገኙትን ሰዎች ለተደራረበ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት እያጋለጠ በመሆኑ በአፋጣኝና ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ሊያበቃ ይገባል፤›› በማለት አሳስበው ነበር፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...