Friday, December 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናአዲስ አበባና ኦሮሚያ ወሰን ለማካለል ተስማሙ

አዲስ አበባና ኦሮሚያ ወሰን ለማካለል ተስማሙ

ቀን:

  • ኮዬ ፈጬ፣ ቱሉዲምቱ፣ ጀሞ ቁጥር 2 ወደ ኦሮሚያ
  • ለቡ፣ ፉሪና ሃና ወደ አዲስ አበባ ይካለላሉ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት አጨቃጫቂ ሆኖ የከረመውን የወሰን ጉዳይ በአስተዳደራዊ የወሰን ማካለል ለመፍታት ስምምነት ላይ መድረሳቸውን አስታወቁ፡፡

በስምምነቱ መሠረት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተገነቡ የኮዬ ፈጬ፣ የቱሉ ዲምቱና በከፊል ጀሞ ቁጥር ሁለት ኮንዶሚኒየሞች የሚገኙባቸው አካባቢዎች ወደ ኦሮሚያ እንዲካለሉ ተወስኗል፡፡ በሌላ በኩል የኦሮሚያ መንግሥት የገነባቸው ለቡ ወይም ቆጣሪ ኮንዶሚኒየም፣ ፋሪና ሃናን ጨምሮ እስከ ቀርሳ ወንዝ ያሉ ቦታዎች ወደ አዲስ አበባ እንዲካለሉ ተወስኗል፡፡

ትናንት ማክሰኞ ነሐሴ 10 ቀን 2014 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፣ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣ እንዲሁም ከፌዴራል ተወካዮችና ከኦሮሚያ ልዩ ዞን ነዋሪዎችና ከአዲስ አበባ ነዋሪዎች ጋር ባደረጉት ምክክር ውሳኔውን ይፋ አድርገዋል፡፡

‹‹ለሰባት ዓመታት በጋራ የቴክኒክ ኮሚቴ ተዋቅሮ ሲሠራበት የቆየውና የአስተዳደራዊ ወሰን ጉዳይ በሕገ መንግሥትና በአዲስ አበባ ከተማ ቻርተር መሠረት ወሰን ጉዳይ በሁለቱ አስተዳደር አካላት ይፈታሉ ብሎ በሚያስቀምጠው መሠረት፣ ዛሬ ላይ ስምምነት ላይ ደርሰናል፤›› በማለት፣ ወ/ሮ አዳነች በመግለጫቸው ላይ ቀኑን፣  ‹‹ታሪካዊና በስኬት የተጠናቀቀ፤›› ብለውታል፡፡

የጋራ ኮሚቴው ከኦሮሚያ ልዩ ዞኖችም ከአዲስ አበባ ከተማ የተውጣጡ ሰዎችን ያቀፈ ሲሆን፣ ውሳኔው ላይ ከመድረሱ በፊት ለዓመታት ጥናት ማድረጉ ተገልጿል፡፡ የፌዴራል መንግሥት የኦሮሚያና የአዲስ አበባ ቻርተሮች እንደ መነሻ መጠቀማቸው ተገልጿል፡፡ 

ኮሚቴው ሁለቱ መንግሥታት ወሰን ዘልቀው የሠሯቸው ኮንዶሚኒየሞች ከመለዋወጥ ውጪ ሌሎች አካባቢዎች ባሉበት እንዲቀጥሉ ወስኗል፡፡ ኦሮሚያና አዲስ አበባ ከተገለጹት አካባቢዎች ውጪ በነባሩ ወሰናዊ አስተዳደር እንዲቀጥሉ ተስማምተዋል፡፡

በምሥራቅና በምዕራብ አዲስ አበባ ሁለቱ አስተዳደሮች ወሰን ያለፉትን ወደ ነበሩበት መወሰኑ ግን፣ የአዲስ አበባን ይዞታ በምን ያህል እንደሚቀንስ ወይም እንደሚጨምር አልታወቀም፡፡

የአስተዳደር ወሰኑ በሚያርፍባቸው አካባቢዎች አዲስ አበባና ኦሮሚያ በጋራ ፀጥታ እንደሚያስጠብቁ፣ መንግሥታዊ አገልግሎቶች እንደሚቀጥሉ፣ የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶች በፍጥነት እንደሚጠናቀቁና የትምህርትና የሥራ ቋንቋ ባለበት እንደሚቀጥል ተገልጿል፡፡

በተጠቀሱት ኮንዶሚኒየሞች ዕጣ የወጣላቸው አዲስ አበባ ነዋሪዎች ግን ምንም ለውጥ እንደማይኖርና ባለቤትነታቸው እንደማይቀለበስ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት፣ የአዲስ አበባ ከንቲባ ጽሕፈት ቤትና የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ባወጡት መግለጫ አሳውቀዋል፡፡

ይህም ማለት አዲሱ የአስተዳደር ወሰን መሬት ላይ ወርዶ እስኪተገበር ድረስ ሁሉም አሁን ባለበት መደበኛ ሁኔታ ይቀጥላል፡፡

‹‹በሁለቱ መካከል እስከዛሬ አስተዳደር ወሰን ባለመደረጉ፣ የመሬት ወረራን ጨምሮ ሌሎች ሕገወጥ ተግባራትን ለመቆጣጠር፣ የሕግ የበላይነትን ለማስከበርና ተጠያቂነትን ለማስፈን አዳጋች ሆኖ ቆይቷል፣ ነዋሪዎች ያለግባብ ተፈናቅለዋል፡፡ ለኢኮኖሚያዊና ለማኅበራዊ ቀውስ ዳርጎናል፡፡ ከዚህም አልፎ ችግር ለፖለቲካ ቀውስም ዳርጎናል፡፡ የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ልዩ ዞኖች ተቀናጅተውና ተደጋግፈው አብረው በጋራ እንዳያድጉ እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል፤›› በማለት፣ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎቶች በበኩሉ ውሳኔውን፣ ‹‹ለዘመናት ለቆየው ማነቆ ዘላቂ መፍትሔ ነው፤›› ሲል አወድሷል፡፡ የፌዴራል መንግሥትም የቅርብ ክትትል ሲያደርግ ቆይቷል፡፡

ይሁን እንጂ የአካባቢው ነዋሪዎች በውሳኔው ከመስማማታቸው ውጪ ውሳኔው ለአዲስ አበባ ምክር ቤትና ለኦሮሚያ ጨፌ ቀርቦ መፅደቁ አልተገለጸም፡፡    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...