Tuesday, November 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየፌዴሬሽኑ ምርጫ በተያዘለት ጊዜና ቦታ ይካሄዳል  

የፌዴሬሽኑ ምርጫ በተያዘለት ጊዜና ቦታ ይካሄዳል  

ቀን:

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የፕሬዚዳንትና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ በተያዘለት ጊዜና ቦታ እንደሚካሄድ ተገለጸ፡፡ አስመራጭ ኮሚቴውና ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴው ነሐሴ 9 ቀን 2014 ዓ.ም.  በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የስብሰባ አዳራሽ በጋራ በሰጡት መግለጫ፣ ምርጫውን ሊያስተጓጉል የሚችል ምንም ዓይነት የአሠራር ክፍተት እንደሌለ በጋራ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

አስመራጭ ኮሚቴውም ሆነ ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴው በተለይ ከገለልተኝነት ጋር በተገናኘ ቅሬታ ሲቀረብባቸው የነበረ ከመሆኑ ባሻገር፣ ይህንኑ ለፊፋና ለካፍ በማሳወቅ የፌዴሬሽኑ የፕሬዚዳንትና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ ሊራዘም የሚችልበት አጋጣሚ እንደሚኖር ጭምር ሲነገር መቆየቱ ይታወቃል፡፡

ግንቦት 7 ቀን 2014 ዓ.ም. በፌዴሬሽኑ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔው የተመረጡት አስመራጭ ኮሚቴና ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴው በጋራ በመሰጡት መግለጫ፣ ይህን ኃላፊነት ከተቀበሉበት ዕለት ጀምሮ የድርጊት መርሐ ግብር በማስቀመጥ፣ በተለይ አስመራጭ ኮሚቴው ከሐምሌ 5 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ነሐሴ 19 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ ዕጩዎችን ሲቀበል እንደቆየ፣ በምርጫ መመርያው መሠረት ለምርጫው ብቁ ናቸው ብሎ ያመነባቸው ለፕሬዚዳንት ምርጫው ሦስትና ለሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ደግሞ 26 አባላትን መለየቱን ነው የኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ኃይሉ ሞላ የተናገሩት፡፡

ሰብሳቢው በአሁኑ ወቅት የዕጩዎች ግለ ታሪክ እየተዘጋጀ ከመሆኑ ባሻገር፣ 14 ዓይነት የምርጫ ወረቀት፣ የምርጫ ኮሮጆ ዝግጅትና ዕጩ ተወዳዳሪዎች ምርጫው ከመደረጉ አሥር ቀናት በፊት (ነሐሴ 10 ቀን 2014 ዓ.ም.) ጀምሮ ለኅብረተሰቡ የማሳወቅ ሥራ የሚያከናውንበት ጊዜ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡

ከጥቅም ግጭትና ገለልተኝነት አኳያ እየቀረበባቸው ያለውን አስተያየት አስመልክቶ አቶ ኃይሉ፣ ‹‹ዓለም አቀፉ ተቋም (ፊፋ) ከዚህ መግለጫ በፊት አስመራጭ ኮሚቴውና ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴው የሠሩትን ሥራ የሚመረምር ቡድን እንደሚልክ ሲነገር እንደነበረ እናውቃለን፡፡ በእኛ በኩል ከፊፋም ሆነ ከሌላ አካል እያደረጋችሁት ያለው ጉዳይ ትክክል አይደለም በሚል ይህ መግለጫ እስከተሰጠበት ድረስ የቀረበልን ቅሬታ የለም፤›› ብለዋል፡፡ በአንድም ሆነ በሌላ አገር የሚያስቀጣ ሥራ ሠርተናል ብለው እንደማያምኑና ምርጫውም በተያዘለት የጊዜ መርሐ ግብር መሠረት የሚከናወን ስለመሆኑ ጭምር ተናግረዋል፡፡

ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የፕሬዚዳንትና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ ጋር ተያይዞ፣ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ባለፈው ሳምንት በሰጠው መግለጫ፣ በምርጫ አስፈጻሚ ኮሚቴውና ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴው ላይ በተለይም ከገለልተኝነትና ከጥቅም ግጭት ጋር በተያያዘ ሥጋት እንዳደረበት መግለጹ ይታወሳል፡፡

በቀረበው የተገቢነትና የገለልተኝነት ጥያቄ ዙሪያ ማብራሪያ የሰጡት የኮሚቴ ሰብሳቢ፣ ‹‹እኛን ከመረጠን ጉባዔም ሆነ ፊፋ በተለይ በዚህ ጉዳይ የቀረበልን አሉታዊ ነገር የለም፡፡ የፕሪሚየር ሊጉ አክሲዮን ማኅበር ቅሬታ በተመለከተ ግን፣ ተቋሙ የጉባዔው አባል ባለመሆኑ የምንለው ነገር አይኖርም፡፡ ሆኖም ግን ሊታወቅ የሚገባው ፊፋም ሆነ ካፍ የፌዴሬሽኑ አካላት ናቸው፡፡ ይህንን ኃላፊነት ቢረከቡ ችግር ይኖረዋል የሚላቸውና በዝርዝር ያስቀመጣቸው የፌዴሬሽኑ ኦዲት ኮሚቴ፣ የሥነ ምግባር ኮሚቴ፣ የዲሲፕሊን ኮሚቴና ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ አባላትን ሲሆን ከዚህ ውጪ ያሉትን አይከለክልም፤›› ብለዋል፡፡

ከአራት ዓመታትና ከዚያ በፊት በነበሩ ምርጫዎች በጠቅላላ ጉባዔ በአስመራጭና በይግባኝ ሰሚ ኮሚቴው የሚሰየሙ አባላት መካከል አለመግባባቶች እንዲፈጠሩ ሆን ተብሎ አሻጥር ሲሠራ የነበረ መሆኑን ያስታወሱት አቶ ኃይሉ፣ ‹‹በዚህ በዘንድሮ ምርጫ በተሰየምነው ኮሚቴዎች መካከል እንዳለፉት ዓመታት ዓይነት ክፍፍልና ክፍተት የለም፡፡ ይህ ማለት ግን ተመሳሳይና ልዩነት አልነበረንም ማለት አይደለም፡፡ በሚያግባባን ተግባብተን በሚያለያየን ደግሞ የሚሻለውን ሐሳብ በመምረጥ ቀጥለናል፡፡ ስለሆነም ሁለቱን ኮሚቴዎች ለማጣላትና ጉዳዩን ለማቀጣጠል የተሞከረው ሴራ ከሽፏል፤›› ብለዋል፡፡

የፊፋና የካፍ መርማሪ ቡድን ሊመጣ ስለመሆኑ የኮሚቴው ሰብሳቢ፣ ‹‹ሁለቱ ዓለም አቀፍና አኅጉር አቀፍ ተቋማት ይመጣሉ ብለን አንሠጋም፡፡ ምክንያቱም የሠራነው ሥራ ድብቅ አይደለም፡፡ ይሁንና በተቋማቱ ልክ አይደለም? ከተባለ ሒደቱ እንዲቆም ይደረጋል፡፡ ነገር ግን ይህንን ውሳኔ ሊያስወስን የሚችል ነገር ሠርተናል ብለን አናምንም፤›› ብለዋል፡፡

በሒደቱ ዙሪያ የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ብርሃኑ ከበደ በበኩላቸው፣ ‹‹እንደ አስመራጭ ኮሚቴው ሁሉ በጠቅላላ ጉባዔ ስለመመረጣቸው፣ በተሰጠው አቅጣጫ መሠረት ከኮሚቴው አባላት አንዱ የሕግ ሰው የነበሩ መሆኑ፣ ከእሳቸውም ጋር ልናደርገው ባሰብነው ተደጋጋሚ ስብሰባ ላይ ሊገኙ ባለመቻላቸውና በሌሉበት መሥራት ከባድ መሆኑን በመገንዘብ ጉዳዩን ያሳወቁ ከመሆኑ ባሻገር፣ ምትክ እንዲሰየም ጥያቄ አቅርበው እንደነበረ፣ ይሁንና ባላችሁት ቀጥሉ ተብለን ኃላፊነታችንን ተወጥተናል፤›› በማለት የነበረውን ሒደት አብራተዋል፡፡ ሆኖም የነበረውን የሰው ጉድለትና አጠቃላይ ሁኔታውን በተመለከተ ግን ለጠቅላላ ጉባዔ እንደሚያስረዱ ነው የገለጹት፡፡

በቅሬታነት ለፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ከቀረቡ ዕጩዎች መካከል አቶ ገዛኸኝ ወልዴ የዕጩ ክልከላ ጉዳይን በተመለከተ ሰብሳቢው፣ ‹‹አቶ ገዛኸኝ የሉበትም ብሎ አስመራጭ ኮሚቴው የወሰነውን ጉዳይ በይግባኝ ለመመልከት አልቻልንም፡፡ ምክንያቱም መመርያው ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ የሚያየው አስመራጭ ኮሚቴ የወሰነውን ብቻ ነው ይላል፤›› ብለው በተገቢነት ጉዳይ ላይ የተነሳውን በሚመለከት ግን የኮሚቴውን አባላት እንደማይመለከት አስረድተዋል፡፡

በዚህ ጉዳይ አስመራጭ ኮሚቴው፣ ‹‹ዕጩውን የላከው የሐረሪ ክልል ውክልናዬን አንስቻለሁ ብሎ ደብዳቤ መላኩ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በሕጉ መሠረት ውክልናው ተቀባይነት እንዳይኖረው ተደርጓል፤›› ብሏል፡፡ በዚሁ ጉዳይ ከክልሉ ጋር ስለመነጋገሩ ጭምር አስረድቷል፡፡

ሌላው ለአስመራጭ ኮሚቴው ከቀረቡለት ጥያቄዎች መካከል፣ ከምርጫ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ፊፋ እንዲያውቀው የሚደረገው ከስድስት ወራት በፊት ሆኖ እያለ፣ አሁን ግን ሒደቱን ፊፋ እንዲያውቀው የተደረገው በአራት ወራት በመሆኑ አሠራሩ በፊፋ ተቀባይነት ይኖረዋ ወይ? የሚለው ይጠቀሳል፡፡

ለዚህ ጥያቄ ምላሽ የሰጡት የአስመራጭ ኮሚቴው ሰብሳቢ፣ ‹‹ከስድስት ወራት በፊት የሚል ሕግ ባለበት፣ በአራት ወራት የሚለው በፊፋ ይታወቃል ወይ? ፊፋ እንኳን ይህን ቀርቶ ከጠቅላላ ጉባዔ ምርጫ ጭምር እያንዳንዱን ጉዳይ ያውቃል፡፡ አሁን ግን ሌላ ነገር ለመፈለግ ካልሆነ ጉዳዩን መደጋገሙ ጥቅም ያለው መስሎ አይታየንም፡፡ ፊፋ ምርጫውን መቼና እንዴት እንደምናካሂድ ጠንቅቆ ያውቃል፣ በመሆኑም ምንም ዓይነት ሥጋት አይገባንም፤›› ብለዋል፡፡

በጎንደር ከተማ ነሐሴ 21 ቀን 2014 ዓ.ም. በሚደረገው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባዔ፣ በዕለቱ ነባሩ የፌዴሬሽኑ አመራር ባለፉት አራት ዓመታት ያከወናቸውን ዕቅዶች ለጉባዔ እንደሚያቀርብ ይጠበቃል፡፡ በማግሥቱ ነሐሴ 22 ቀን 2014 ዓ.ም. ደግሞ ፌዴሬሽኑን በቀጣይ አራት ዓመት የሚያስተዳድሩ ፕሬዚዳንትና ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ምርጫ የሚያከናውንበት እንደሚሆን ጭምር ተነግሯል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ ሲኒመር ትሬዲንግ...

የባህር በር በቀጣናዊ ተዛምዶ ውስጥ

በበቀለ ሹሜ መግቢያ በ2010 ዓ.ም. መጋቢት ማለቂያን ይዞ ዓብይ አህመድ በጠቅላይ...

ሥጋት ያስቀራል ተብሎ የሚታሰበው የጫኝና አውራጅ መመርያ

በአዲስ አበባ ከተማ በሕገወጥ መልኩ በመደራጀት ማኅበረሰቡ ላይ እንግልትና...

ማወቅ ወይስ አለማወቅ – ድፍረት ወይስ ፍርኃት?

በአሰፋ አደፍርስ ወገኖቼ ፈርተንም ደፍረንም የትም አንደርስምና ለአገራችን ሰላምና ክብር...