Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምበሱዳን ቤቶችን እያፈራረሰና ሕይወት እየነጠቀ የሚገኘው የጎርፍ  መጥለቅለቅ

በሱዳን ቤቶችን እያፈራረሰና ሕይወት እየነጠቀ የሚገኘው የጎርፍ  መጥለቅለቅ

ቀን:

ለሱዳናውያን ከግንቦት እስከ ጥቅምት የሚዘንበው በተለይም ከኢትዮጵያ ከዘጠኝ ወንዞች ተቀባብሎ ከዓባይ እስከ ዋይት ናይል የሚዘልቀው ወንዝ ይዞት የሚነጉደው ውኃ  ጎርፍ ሆኖ የሚያጥለቀልቅ መሆኑ አዲስ ክስተት አይደለም፡፡

ሱዳኖች ለዘመናት ሲቸገሩበት ግብርናቸውን፣ መሠረተ ልማታቸውን፣ የሰዎችን መኖሪያ፣ ከብቶቻቸውንና ሰዎቻቸውን ሲያጡ የኖሩት ከዚሁ ከዓባይ በሚገሰግሰውና ከዋይት ናይል ተጋብቶ ጉልበቱን በሚያጠናክረው ጎርፍ ነው፡፡

በ2003 ዓ.ም. የመሠረተ ድንጋዩ የተቀመጠለትና ዛሬ ላይ ሦስተኛው ዙር የውኃ ሙሌት የተጠናቀቀለት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሲጀመር፣ ሱዳናውያን ደስተኛ ነበሩ፡፡

የግብርናና የውኃ ባለሙያዎቻቸውንና ሚኒስትሮቻቸውን ጨምሮ ሱዳን ከጎርፍ አደጋ ትላቀቃለች፣ በየዓመቱ ውኃ የሚበላው ግብርናዋ ይጠበቃል፣ መሠረተ ልማቶች በጎርፍ አይወድሙም ሲሉም በዓለም አቀፍ ሚዲያ ጭምር ቀርበው መስክረዋል፡፡ ዶክመንተሪ ተሠርቶ ሲተላለፍም ነበር፡፡

የሱዳን ጋዜጠኞችና በርካታ ምሁራንም አሁንም ድረስ ከግድቡ ተጠቃሚ መሆናቸውን በተደጋጋሚ ቢገልጹም፣ ግንባታው ሲጀመር ከኢትዮጵያ ጎን የነበረችው ሱዳን ዛሬ ላይ ከግብፅ ወግና አንዳንዴም መሀል ሰፋሪ በመሆን የግድቡን ግንባታ በአስገዳጅ ሕግ እንዲታሰር ኢትዮጵያ ላይ ጣት መቀሰር ከጀመረችውም ከርማለች፡፡

በተለይ ግብፅ በየጊዜው የምታነሳውን ‹‹የውኃ ያጥረናል›› አጀንዳ ሱዳንም ታቀነቅናለች፡፡ ምንም እንኳን በኢትዮጵያ በኩል ፍትሐዊ የውኃ ክፍፍል ይኑር የሚለው አቋም የፀና ቢሆንም፣ ግብፅ ፍላጎቷን ብቻ አስጠብቃ የተናገረችውን ሱዳን ትደግፋለች፡፡ ሱዳን ከራሷ ይልቅ የግብፅን አጀንዳ ማስጠበቁ ላይ ትኩረት አድርጋለች፡፡

ኢትዮጵያ ከምትሠራው ግድብ ባለፈ የዓባይ ውኃ ሱዳን ግድብ እንድትሠራ፣ ግብርናዋን ሆነ የዓሳ ሀብቷን እንድታስፋፋ በየዓመቱ የሚጠራርጋትን ጎርፍ የሚታደጉ ግንባታዎች እንድታደርግ ዕድል የሚሰጥ የተፈጥሮ ፀጋ ቢሆንም፣ ከዚህ ይልቅ በኢትዮጵያ የግድብ ሥራ ላይ ገደብ እንዲደረግ ትለፋለች፡፡ የዘወትር ውትወታዋም ወደፊት ውኃ ይቸግረናል የሚል ሆኗል፣ ልክ እንደ ግብፅ፡፡

ይሁን እንጂ የግብፅና የሱዳን ባለሥልጣናት ‹‹ግድቡ በበጋ ወቅት ብቻ ሳይሆን በክረምትም ውኃ ያሳጣናል፤›› እንዳሉት ሳይሆን ቀርቶ የውኃ ሙሌቱ ከተያዘበት ከዛሬ ሦስት ዓመት ጀምሮ እንኳን ቢታይ፣ ሱዳን በጎርፍ ያልተጥለቀለቀችበት ጊዜ የለም፡፡

የህዳሴ ግድቡ ሦስተኛ ዙር ሙሌት ከመጀመሩ በፊትና አሁንም ‹‹ኢትዮጵያ አስገዳጅ ማዕቀፍ ውስጥ ትግባ›› በማለት ከግብፅ ጋር በመሆን አሜሪካን ጭምር ስትማልድ የከረመችው ሱዳን ዘንድሮ ከባድ በተባለ ጎርፍ እየተመታች ነው፡፡

ኤቢሲ ኒውስ እንዳሰፈረው፣ በሱዳን እየተባባሰ የመጣው የጎርፍ መጥለቅለቅ ቤቶችን እያፈራረሰ ሕይወትን እየነጠቀ ነው፡፡

እስከ ነሐሴ 10 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ 66 ሰዎች በጎርፍ የሞቱ ሲሆን፣ 24 ሺሕ ቤቶችና ከሃያ በላይ የመንግሥት ሕንፃዎች ሙሉ ለሙሉና በከፊል ወድመዋል፡፡

የሱዳን ናሽናል ካውንስል ፎር ሲቪል ዲፌንስ ቃል አቀባይ ብርጋዴል ጄኔራል አብዱል ጀላል አብዱል ራሂም እንዳሉት፣ በሱዳን ከሚገኙት 18 ግዛቶች በ12ቱ ከባድ ዝናብና ጎርፍ እየተከሰተ ሲሆን፣ ይህም 136 ሺሕ ሰዎችን ለችግር ዳርጓል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ዕርዳታ ጉዳዮች (ኦቻ) በበኩሉ፣ 238 የጤና አገልግሎት መስጫዎች ከሥራ ውጭ ሆነዋል ብሏል፡፡

ምዕራብ ዳርፉር፣ የዓባይ ወንዝን የሚዋሰኑ ግዛቶች፣ የዋይት ናይልና የደቡብ ዳርፉር አካባቢዎች በጎርፍ በከፍተኛ ሁኔታ የተመቱ ሥፍራዎች ናቸው፡፡

ዓምና በጎርፍ ምክንያት 80 ዜጎችን ያጣችው ሱዳን፣ በጎርፍ መጥለቅለቅ ምክንያት ካችዓምና የሦስት ወራት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጃ ነበር፡፡ በወቅቱ 100 ዜጎቿ የሞቱባት ሱዳን፣ ከ100,000 በላይ ቤቶች በጎርፍ ተውጠውባት ነበር፡፡ ዘንድሮ ብቻ በ540 ሔክታር መሬት ላይ የተዘራ ሰብልም ወድሟል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...