Thursday, September 21, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የቅድመ ሕክምና አገልግሎትን ለማጠናከር››

ቢኒያም ዓለሙ (ዶ/ር) የብሉ ሄልዝ ሕክምና አማካሪ ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅና የአሜሪካ ኸርት አሶሴሽን ኢንተርናሽናል ቤዚክ ላይፍ ሰፖርት ኢንስትራክተር ናቸው፡፡ በድንገተኛ ሕክምና አገልግሎት፣ በድርጅቱ እንቅስቃሴና ሌሎችም ተጓዳኝ በሆኑ ሥራዎች ዙሪያ ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ብሉ ሔልዝ የሕክምና አማካሪ ድርጅት ከተቋቋመ አንድ ዓመት አልፎታል፡፡ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በጤናው ዙሪያ ለኅብረተሰቡ ካበረከታቸው ሥራዎች መካከል ቢገልጹልን?

ዶ/ር ቢኒያም፡- ድርጅቱ ከተመሠረተ ጊዜ አንስቶ በጤናው ዙሪያ ያተኮሩ ልዩ ልዩ ጠቃሚ ተግባራትን አከናውኗል፡፡ ካከናወናቸው ተግባራት መካከል አንዱና ዋነኛው በቅድመ ሕክምና አገልግሎት (የመጀመርያ የሕክምና ዕርዳታ) ዙሪያ ላይ ያተኮረ ሥልጠና መስጠት ይገኝበታል፡፡ በዚህም ሥልጠና ከአንድ ሺሕ በላይ ሰዎች ተሳትፈው ጠቃሚ ዕውቀትን ቀስመዋል፡፡ ሠልጣኞቹ የተውጣጡት ከልዩ ልዩ ኩባንያዎችና የትምህርት ተቋማት ነው፡፡ ከዚህም ሌላ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና ተቀብለው ፈተናውን በጥሩ ውጤት አልፈው ሕክምና ኮሌጅ በመግባት የሕክምና ትምህርት የመማር ፍላጎት ላላቸው ተማሪዎችም የተዘጋጀው የክረምት ኮርስ ሌላው የሥልጠና ዓይነት ነው፡፡ ኮርሱ የተዘጋጀው በሁለት ዙር ነው፡፡ የመጀመርያው ኮርስ ባለፈው ወር የተጠናቀቀ ሲሆን፣ ሁለተኛው ኮርስ ደግሞ ከያዝነው ወር ጀምሮ በመከናወን ላይ ነው፡፡ በመጀመርያው ዙር ላይ 75 ተማሪዎች የሠለጠኑ ሲሆን፣ በሁለተኛው ዙር ደግሞ 67 ተማሪዎች በመሠልጠን ላይ ናቸው፡፡ ይህ ኮርስ እየተካሄደ ያለው በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ነው፡፡ በኮርሱ ላይ እየተሰጡ ያሉ ሥልጠናዎችም በጤና ኮሌጁ ውስጥ የመማር ማስተማር ሥራ በምን መልኩ እየተካሄደ እንደሆነ የሚያሳይ ነው፡፡ የሕክምና ትምህርት በጣም ከባድና ሥራውም ከሰው ሕይወት ጋር የተያያዘ በመሆኑ ተማሪዎቹ ይህንኑ ተገንዝበው ተግተው እንዲያጠኑና ትምህርቱንም በጥሞና ለመከታተል ከወዲሁ ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ ሥልጠናው አነቃቅቷቸዋል ማለት ይቻላል፡፡ ከመምህራኖቻቸው ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት ጤናማና ወንድማማችነት እንዲኖረው ለማድረግ የሚያስችላቸውን አካሄድ ቀስመዋል፡፡ ይህ እንደጠበቀ ሆኖ ጤና ሚኒስቴር በሥራ ላይ ላሉ ሐኪሞች ያወጣውን የሙያ ማጎልበቻ ሥልጠና ከ2000 በላይ ለሆኑ ጠቅላላ ሐኪሞች ሰጥቷል፡፡ ወደ 17 የሚሆኑ ቨርቿል ሥልጠናም ተከናውኗል፡፡ ይህንንም ሥልጠና ለመስጠት የሚያስችለን ላይሰንስ ከኢትዮጵያ የሕክምና ማኅበር ተሰጥቶናል፡፡ በሥልጠናውም የተለያዩ ሰብ ስፔሻሊስቶችና ስፔሻሊስት ሐኪሞች እየጋበዝን ልምዳቸውን እንዲያካፍሉ አድርገናል፡፡

ሪፖርተር፡- ባዘጋጃችኋቸው ሥልጠናዎች ላይ ከመንግሥትም ሆነ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች የተደረገላችሁ ዕገዛና ድጋፍ አለ?

ዶ/ር ቢኒያም፡- ከመንግሥት በኩል የጤና ሚኒስቴር የኢመርጀንሲ ዳይሬክቶሬት ተባበሯቸው የሚል ደብዳቤ በመጻፍ ረድቶናል፡፡ በተረፈ አዲስ አበባ ውስጥ ሲኤምሲ አካባቢ የሚገኘው ሎርካን የግል ጤና ኮሌጅ የክረምት ኮርሱ የተሳካ እንዲሆን በሚቻለው መልኩ ተባብሮናል፡፡

ሪፖርተር፡- እስካሁን ድረስ ሥራ ያላገኙ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ተመራቂ ሐኪሞች አሉ፡፡ በምታዘጋጁት ሥልጠና ላይ እነሱን ለመቅጠር ያደረጋችሁት ጥረት አለ?

ዶ/ር ቢኒያም፡- የሥልጠናውን ሥራ በጀመርን በሦስት ወራችን ከእኛ ጋር ተመርቀው ሥራ ያጡ ሐኪሞችን ለመቅጠር የሚያስችል ማስታወቂያ አወጣን፡፡ በዚህም ተመርቀው ሥራ ያላገኙ፣ ሥራ አግኝተው አንድና ሁለት ዓመት ያገለገሉ 290 ሐኪሞች ለሥራው አፕላይ አደረጉ፡፡ እኛ ግን አቅማችን በሚፈቅደው መሠረት 15 ሐኪሞችን ተቀብለን በቅድመ ሕክምና አገልግሎት ላይ ያተኮረ ሥልጠና እንዲሰጡ አድርገናል፡፡ የድርጅታችን አቅም ተጠናክሮ ሲወጣ ወደፊት 50 ጠቅላላ ሐኪሞችን ለመቅጠር አቅደን ለተግባራዊነቱ ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ እያደረግን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሥራ አጥ ለሆኑ ተመራቂ ሐኪሞች የምታስተላልፉት ምክር አለ?

ዶ/ር ቢኒያም፡- ሕክምና የተከበረ ሙያ ነው፡፡ በዚያው ልክ ደግሞ የተለያዩ ችግሮች አሉበት፡፡ ችግሮቹን እንደ ፀጋ ማየት ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ከችግሮቹ በመነሳት ሥራን መፍጠር ያስችላል፡፡ እኛም በቅድመ ሕክምና አገልግሎት ዙሪያ የታየውን ክፍተት በማየትና ከችግሩም በመነሳት በአገልግሎቱ ዙሪያ ያተኮረ የሥራ ፈጠራ አዘጋጀን፡፡ በዚህም ዝግጅት ተቀጥሮ ከመሥራት ይልቅ የራሳችንን ሥራ መፍጠር ይሻላል በሚል ሐሳብ ተነስተን አሁን ያለውን ድርጅታችንን ለማቋቋም በቅተናል፡፡ የቀሩትም ተመራቂ ሐኪሞች የእኛን ፈለግ በመከተልና ከጤና ችግሮች በመነሳት የሥራ ፈጣሪ ለመሆን ቢጥሩ መልካም ነው፡፡ በእርግጥ ሒደቱ ቀላል አይደለም፡፡ ብዙ ውጣ ውረድ አሉት፡፡ ለዚህም ሳይንበረከኩ በአሸናፊነት ለመወጣት መንቀሳቀስ ይገባቸዋል ብለን እናምናለን፡፡

ሪፖርተር፡- አማካሪ ድርጅቱን ስንት ሰዎች/ባለሙያዎች ሆናችሁ ነው ያቋቋማችሁት? ለማቋቋሚያ የሚውል ገንዘብ ከየት አገኛችሁ?

ዶ/ር ቢኒያም፡- ድርጅቱን ያቋቋምነው አራት ሆነን ነው፡፡ አብሮኝ የተመረቀው ጓደኛዬ ኤሊያስ ታደሰ (ዶ/ር) እንዲሁም የኢመርጀንሲና የፅኑ ሕመም ስፔሻሊስት የሆኑት መምህራችን ናታን ሙሉብርሃን (ዶ/ር) እና የሁላችንም ጓደኛ የኮምፒዩተር ኢንጂነሪንግ ባለሙያ የሆነው አዳም ጌታቸው በአንድ ላይ ሆነን ነው ያቋቋምነው፡፡ ከሃረማያ ዩኒቨርሲቲ ከተመረቅን በኋላ ሳንውል ሳናድር ነው ያቋቋምነው፡፡ በእኔ በኩል የሕክመና ትምህርት ላይ እያለሁ እናቴ በስሜ በከፈተችው የባንክ ሒሳብ በየወሩ 50 ብር ከፍ ሲል ደግሞ 70 ብር ታስገባልኝ ነበር፡፡ ሰባት ዓመት ሞልቶች ስመረቅ ከባንክ ያለው ተቀማጭ ሒሳብ 20,000 ብር ደረሰ፡፡ በቤታችን ውስጥ ምረቃን አስመልክቶ በተከናወነው ድግስ ላይ እናቴ 20,000 ብር የያዘውን የባንክ ደብተር በስጦታ አበረከተችልኝ፡፡ ጓደኛዬ ኤልያስም (ዶ/ር) ወንድሙ 20,000 ብር ሰጠው፡፡ የሁለታችንንም ገንዘብ በአንድ ላይ አድርገን፣ ከዚያም በአንድ ጠባብ ቤት ውስጥ ሆኖ የራሱን ሥራ ከሚያከናውነውና የኮምፒዩተር ኢንጂነር ከሆነው ጓደኛችን ጋር ተዳብለን መንቀሳቀስ ጀመርን፡፡ አስተማሪያችን ናታን ሙሉብርሃን (ዶ/ር) በቅድመ ሕክምና አገልግሎት ዙሪያ በአማርኛና በኦሮምኛ ያዘጋጀውን መጽሐፍ ለሕትመት አብቅተን ገበያ ላይ እንዲውሉ አደረግን፡፡ ከዚህም ሌላ አዲስ አበባ የሚገኘው ኦርቢት ኢኖቬሽን ኸብ የተባለው ድርጅት የኢንተርፕረነርሽፕ ሐሳብ ያላቸውን እያወዳደረ ሥልጠናና የመነሻ ገንዘብ ይሰጥ ነበር፡፡ እኛም ሐሳባችን ይዘን ተወዳደርን፡፡ በውድድሩም ከተመረጡት አሥሩ መካከል አንዱ ሆንን፡፡ በዚህም ለሐሳባችን መነሻ የሚሆን 85,000 ተሰጠን፡፡ የሥልጠናውም ተሳታፊ ሆንን፡፡ ቀደም ሲል ያዋጣነውን 40,000 ብር እና ለመነሻ የተሰጠን ገንዘብ አዋህደን ለሥልጠና የሚያስፈልገንን ልዩ ልዩ መሣሪያዎችና የመገልገያ ዕቃዎች ገዛን፡፡ ከጠባቡ ቤት ወጥተን ሰፋ ያለ ቤት ተከራየን፡፡ የሦስት ወር የቤት ኪራይ በቅድሚያ ከፈልን፡፡

ሪፖርተር፡- ትኩረታችሁ ወይም መነሻችሁ በዋነኝነት በቅድመ ሕክምና አገልሎት ዙሪያ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ በዚህ ላይ ትኩረት እንድታደርጉ ያነሳሳችሁ  ምክንያት ምንድነው?

ዶ/ር ቢኒያም፡- እኔና ጓደኛዬ የሕክምና ትምህርት ተከታትለን ያጠናቀቅነው ወይም የተመረቅነው በሃሮማያ ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ የሰባተኛ ዓመት የመጨረሻ ዓመት ተማሪ ሆነን ሕይወት ፋና ጠቅላላ ሆስፒታል ድንገተኛ ሕክምና ክፍል ኢንተርንሽፕ እንሠራ ነበር፡፡ በቆይታችንም ወቅት በድንገተኛ ሕመም የሚመጡ ሕሙማንን የማየትና የማከም ዕድል አጋጥሞናል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን አንዲት ነፍሰጡር በባጃጅ ተሽከርካሪ ተገጭተው ሕክምና ላይ እያሉ ሕይወታቸው ማለፉ በእጅጉ ከንክኖናል፡፡ አደጋው የደረሰው ነፍሰ ጡሯ ተገቢውን የሕክምና አገልግሎት አግኝተው ከሆስፒታል ሲወጡ፣ ባጃጁ ደግሞ ጉዳት የደረሰበትን ታካሚ ለሆስፒታሉ አስረክቦ ሲመለስ ሆስፒታሉ በራፍ ላይ ነፍሰ ጡሯን ክፉኛ ገጭቶ ጉዳት አደረሰባቸው፡፡ በአካባቢው ያሉትም ሰዎች እፍስፍስ አድርገው ይዘዋቸው ድንገተኛ ሕክምና ክፍል አመጧቸው፡፡ ከወደቁበት ሥፍራ ያነሷቸው ሥርዓትና ጥንቃቄ በተሞላበት አኳኋን አይደለም፡፡ የቅድመ ሕክምና አገልግሎት ሥልጠና ያልወሰዱ ሰዎች ናቸው ያነሷቸው፡፡ በዚህም የተነሳ መተንፈስ አቅቷቸው ሕይወታቸው ሊያልፍ ችሏል፡፡ ይህ ክስተት ለምን ሆነ? የሚል ጥያቄ በጭንቅላታችን አቃጨለብን፡፡ ከምርቃታችን በኋላም በዚህ አገልግሎት ዙሪያ መሥራት አለብን ብለን ተስማማን፡፡ ምክንያቱም የቅድመ ሕክምና አገልግሎት ለቀጣይ ሕይወት መሠረት ነውና፡፡

ሪፖርተር፡- ከስምምነቱ በኋላ ምን ዓይነት ዕርምጃ ወሰዳችሁ?

ዶ/ር ቢንያም፡- በቀጣይ ያደረግነው ማኅበረሰባችን በቅድመ ሕክምና አገልግሎት ዙሪያ ምን ዓይነት ሐሳብ አለው? የሚለውን ለማወቅ ቀደም ሲል የተሠሩ ጥናቶችን መዳሰስ ጀመርን፡፡ ባካሄድነውም ዳሰሳ ጤና ሚኒስቴር በ2021 ባወጣው ሪፖርት ላይ በተጠቀሰው አገልግሎት ዙሪያ 100,000 ሰዎችን ለማሠልጠን አቅዶ 33,000 ሰዎችን ብቻ እንደሠለጠኑ ተረዳን፡፡ ከአጠቃላዩ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር አንፃር ሥልጠናውን ያገኘ ሰው ብዛት ኢምንት ነው፡፡ ሆኖም ሕዝቡ ሥልጠናውን ይፈልገዋል ወይ? የሚለውን ለማወቅ ደግሞ አዲስ አበባ ውስጥ 580 ሾፌሮች የተካተቱበት ጥናት በ2018 ተካሂዶ ከተሳታፊዎች መካከል 80 ከመቶ ያህሉ ሥልጠናውን እንደሚፈልጉ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ያደጉ አገሮችን ልምድና ተሞክሮ ስናይ ደግሞ አገልግሎቱ በሁሉም የትምህርት ተቋማት እንደሚሰጥ፣ በአንድ ቤተሰብ ውስጥ በቅድመ ሕክምና አገልግሎት የሠለጠነ አንድ ሰው መኖር እንዳለበት፣ መንጃ ፈቃድ ለማውጣት በቅድሚያ የቅድመ ሕክምና አገልግሎት ሥልጠና ማግኘት አስገዳጅ መሆኑን የሚገልጹ መረጃ አገኘን፡፡ ሌላው የተመለከትነው ቢኖር በሠለጠኑት አገሮች አደጋ የደረሰበትን ሰው ከወደቀበት ሥፍራ አንስቶ አቅራቢያው ወደሚገኘው ጤና ተቋም በስንት ደቂቃ መድረስ አለበት የሚለውን ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ሲንጋፖር በ10 ደቂቃ፣ በአውሮፓ አገሮች 15 ደቂቃና በአሜሪካ 20 ደቂቃ እንደሚፈጅ ተረዳን፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ከሁለት ሰዓት በላይ እንደሚፈጅና 93 በመቶ ያህሉ የተጎዳ ሰው ወደ ጤና ተቋም የሚመጣው በአምቡላንስ ሳይሆን በሕዝብ ትራንስፖርት መሆኑን ለማወቅ በቅተናል፡፡ በዚህም ብዙዎቹ ዕርዳታ በወቅቱ ሳያገኙ ለሕልፈተ ሕይወት እንደሚዳረጉ ተመልክተናል፡፡

ሪፖርተር፡- ይህንን ከተገነዘባችሁ በኋላ ድርጀቱን ወደ ማቋቋም ነው ያመራችሁት ወይስ ተጨማሪ ማስረጃዎችን ፍለጋ ነው ያማተራችሁት?

ዶ/ር ቢንያም፡- ቀደም ሲል የተሠሩትን ጥናቶች ከዳሰስንና ልዩ ልዩ መረጀዎችን ካጠናቀርን በኋላ መፍትሔ ፍለጋ ነው የገባነው፡፡ ለዚህም ዕውን መሆን መምህራኖችንን ማማከር ቀጠልን፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ መፍትሔ እንዲሰጡን ካማከርናቸው መምህራኖቻችን መካከል ናታን ሙሉብርሃን (ዶ/ር) እና የሕፃናት ኢመርጀንሲ ሰብ ስፔሻሊስት ትዕግሥት ባጫ (ዶ/ር) አነጋገርን፡፡ ጠቃሚ ምክሮችንም ለገሱን በተለይ ናታን (ዶ/ር) የቅድመ ሕክምና አገልግሎት የተመለከተ መጽሐፋቸውን ሰጡን፣ መጽሐፉንም ለሥራችን አንዱ መመርያ (ጋድላይን) ተጠቀምንበት፡፡ አሁን ያለንበት የቴክኖሎጂ ዘመን በመሆኑ የተነሳ ሰው የአምቡላንስ ቁጥሮችን ማወቅ አለበት፡፡ በሠለጠነ ዓለም ግን 911 የሚባለውን ሁሉም ያውቀዋል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ግን አንድ አደጋ ቢከሰት ወይ ዘመድ ወይ ጓደኛ ዘንድ ነው የሚደወለው፡፡ የእሳት አደጋ ቁጥር 939 በተወሰነ መልኩ በሕዝብ ዘንድ ይታወቃል፡፡ የቀይ መስቀል አምቡላንስ ቁጥር የሆነው 907 ማንም የሚያውቀው የለም፡፡ ጤና ሚኒስቴር ከዚህ ግንዛቤ በመነሳት በሁሉም የክልል ከተሞች የሚተገበር አዲስ ያስጀመረው ፕሮጀክት አለ፡፡ ፕሮጀክቱም ‹‹ሜጀር ሲቲ ኢንተርናሽናል አምቡላንስ ሰርቪስ›› ይባላል፡፡ ፕሮጀክቱም በአራት ዲጂት የተካተቱና ነገር ግን የተለያዩ አምቡላስ ቁጥሮችን የያዘ ነው፡፡ ፕሮጀክቱ በባህር ዳር፣ ጅማ፣ ሐዋሳ፣ ሐረርና መቀሌ ከተሞች ውስጥ ለመጀመርያ ጊዜ ሥራ ላይ እንዲውል ተደርጓል፡፡ መቀሌ ላይ ግን በተፈጠረው ችግር ሳቢያ አይሠራም፡፡ በተረፈ በሌሎቹ ከተሞች ሥራ ላይ ቢውልም ሕዝቡ ግን አያውቃቸውም፡፡  

ሪፖርተር፡- ከዚህ ችግር ተነስታችሁ ምን ዓይነት መፍትሔ ወሰዳችሁ?

ዶ/ር ቢንያም፡- ከዚህ ችግር በመነሳት የአምቡላንሶቹን ቁጥር መለየት የሚያስችል አንድ የሞባይል አፕሊኬሽን (መተግበሪያ) ለማዘጋጀት በቅተናል፡፡ ‹‹ደራሽ›› በሚል መጠሪያ የሚታወቅ ይህ አፕሊኬሽኑ የመንግሥትና የግል አምቡላንሶችን ቁጥር ያለምንም ችግር በቀላሉ እንዲገኝ ያስችላል፡፡ አፕልኬሽኑ የተዘጋጀው በአማርኛ፣ በኦሮምኛና በእንግሊዝኛ ነው፡፡ ሌላው ሰው ወደ ትልልቅ ሆስፒታል ከመውሰድ ይልቅ በአቅራቢያው ወደሚገኘው ጤና ተቋም መውሰድ ጠቃሚ ነው፡፡ ይህም በሞባይል አፕሊኬሽን ውስጥ ተካቷል፡፡ ከአቅም በላይ ሆኖ ከተገኘ በሪፈር ወደ ትልቅ ሆስፒታል መውሰድ ይቻላል፡፡ ይህ ዓይነት ሞባይል መተግበሪያ በአሁኑ ጊዜ እየሠራ ያለው አዲስ አበባ ውስጥ ብቻ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በሕክምና ተማሪዎቹና መምህራን መካከል ጤናማ የሆነ ግንኙነት እንደሌለ አንዳንድ ፍንጮች እየጠቆሙ ነው፡፡ በዚህ ዙሪያ ከተማሪዎቹ ማኅበር መረጃ ለማግኘት ሞክረን ነበር ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ በዚህ ላይ የተረዱት ነገር ካለ ቢያካፍሉን?

ዶ/ር ቢንያም፡- ችግሩን ከማኅበራዊ ሚዲያ ለማወቅ ችያለሁ፡፡ የችግሩን መንስዔ በተመለከተ ግን ምንም የማውቀው ነገር የለም፡፡ ግን እንደ አጠቃላይ ሁኔታ ሲታይ የሕክምና ትምህርት ከባድ ነው፡፡ እንደ ዋዛ የሚታይም አይደለም፡፡ ትምህርቱ በሰው ሕይወት ዙሪያ ያተኮረ ስለሆነ በርካታ ችግሮ ይኖሩታል፡፡ እነኛን ችግሮች በብልኃት፣ በጥበብና በትዕግሥት ማለፍ ግድ ይላል፡፡ በተለይ ከአንድ ትንሽ ክስተት በመነሳት አንድ ዓመት የሚያስደግሙ ከፍተኛ (ሲኒየር) ሐኪሞች አይታጡም፡፡ ከፍተኛ ሐኪሞች ክብራቸው ይሰፋል፡፡ ከፍተኛ ሐኪም ያለበት ካፌ ውስጥ አንድ ተማሪ ለመግባት ፍርኃት ይሰማዋል፡፡ ይህ ሁሉ በግንኙነት ላይ የራሱ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡ ስለሆነም ሁሉንም ችግር እንደ አመጣጡ ተቀብሎ በትዕግሥት ማለፍና ለምረቃ መብቃት ነው ዋናው ቁም ነገር፡፡

ሪፖርተር፡- የሐኪሞችን ደመወዝ እንዴት ይገመግሙታል?

ዶ/ር ቢንያም፡- ደመወዛቸው ከሥራቸው አንፃር ሲታይ በጣም ኢምንትና ፍፁም የማይገናኝ ነው፡፡ የወር ደመወዝ 9,056 ብር ነው፡፡ በዚያ ላይ ተቀናንሶለት የሚደርሰው ወደ 6,000 ብር ነው፡፡ ይህ የቤት ኪራይ ወጪ እንኳን የሚሸፍን አይደለም፡፡ የራይድ ሾፌር በወር ከ15,000 እስከ 20,000 ብር በላይ ነው የሚከፈለው፡፡ የደመወዝ ጉዳይ የሐኪሞችን ሞራል የሚገድል ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ብዙ ሐኪሞች ከፕሮፌሽናቸው ውጭ የሆነውን ሥራ ለመሥራት እንደተገደዱ ነው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች