የአገሪቱ ባንኮች ዋነኛ ተግባራቸው የሆነው ብድር የማቅረብ አገልግሎት እንከን የሚታይበት መሆኑን፣ ይኸውም ሁሉም ባንኮች በሚባል ደረጃ የሚያቀርቡት ብድር የተወሰኑ ዘርፎችንና አካላትን ብቻ ትኩረት ማድረጉን በመተቸት ዕርማት እንዲያደርጉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አሳሰበ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) ይህንን የተናገሩት ሰሞኑን ከሁሉም የአገሪቱ ባንኮች ፕሬዚዳንቶች ጋር በነበራቸው የውይይት መድረክ ላይ ነው። የውይይት መድረኩ የአገሪቱ ባንኮች ላለፉት አራት ዓመታት ያደረጉትን ውጤታማ እንቅስቃሴ ለመዘከርና የዘርፉን እንቅስቃሴ በጋራ ለመገምገም የተዘጋጀ ቢሆንም፣ ሊስተካከሉ ይገባቸዋል የተባሉ የባንክ ኢንዱስትሪው ጉደለቶችም ተነስተው ዕርምት እንዲደረግባቸው ዘርፉን በሚቆጣጠረው ብሔራዊ ባንክ ምክረ ሐሳብ የተሰጠበትም ነበር።
‹‹ሁሉም ባንኮች ውጤታማ ቢሆኑም፣ ምንም ዓይነት ጉድለት የለባቸውም ማለት አይደለም፤›› ያሉት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) በተለይም የአገሪቱ ባንኮች የተቋቋሙበት ዋነኛ ዓላማና የትርፋማነታቸው ምንጭ በሆነው የብድር አቅርቦት አገልግሎት ላይ ችግሮች እንደሚስተዋሉ ገልጸዋል።
‹‹የባንኮች የብድር መጠን የመጨመሩን ያህል ብድር እየተሰጠ ያለው ግን ለተወሰኑ አካላት ብቻ መሆኑ አግባብ አይደለም፤›› ሲሉ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር (ዶ/ር) በመድረኩ ለታደሙት የሁሉም ባንኮች ፕሬዚዳንቶች አስረድተዋል፡፡ የብሔራዊ ባንክ ገዥው እንደተናገሩት ሁሉም የአገሪቱ ባንኮች የሚሰጡት የብድር አገልግሎት ትልልቅ ባለሀብቶች ላይ ትኩረት ያደረገና በከተሞች አካባቢ ብቻ የተገደበ ነው።
‹‹የሚሰጠው ብድር በትልልቅ ባለሀብቶች አካባቢና በከተማ አካባቢ የታጠረ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል፤›› ያሉት ይናገር (ዶ/ር)፣ ባንኮች ይህንን አዝማሚያ ማረም እንደሚገባቸውና የተበዳሪዎቻቸውን ስብጥር በማስፋት ኢኮኖሚያዊ ትርጉም ያላቸው ዘርፎችን እንዲደግፉ አሳስበዋል።
‹‹ባንኮች የሚሰጡትን ብድር ወደ ገጠር በተለይም አነስተኛ ገቢ ላላቸው፣ በመካከለኛው ገቢ ለሚተዳደሩ ሰዎችና ለአነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ብድር ማቅረብ ይገባቸዋል፤›› ብለዋል። አክለውም ‹‹ይህ ቁልፍ ጉዳይ ነው›› ሲሉ አሳስበዋል።
ከዚሁ ጎን ለጎን የፋይናንስ ተደራሽነትን ማሳደግ አሁንም ብዙ የሚቀረው በመሆኑ በዚህ ረገድ ባንኮች ትኩረት እንዲያደርጉ መክረዋል። የብሔራዊ ባንክ ገዥ ያስገነዘቡት ሌላው ጉዳይ በባንኮች ውስጥ ከሚታይ ምዝበራና ማጭበርበር ጋር ተያይዞ ያለውን ችግር በተመለከተ ነው፡፡
‹‹በባንኮች ውስጥ ያሉ ግለሰቦችም ሆነ ከባንክ ውጪ ያሉ አንዳንድ ሰዎች የማጭበርበር፣ የሥርቆትና የኮንትሮባንድ በፋይናንስ ተቋማት ላይ የመፈጸም ሁኔታዎችና አዝማሚያዎች እየታዩ በመሆኑ፣ እዚህን በመከላከል ረገድ የሁሉም ባንኮች አመራሮች በየተቋሞቻቸው እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችን ማጠናከር ይጠበቅባቸዋል፣›› ብለዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የባንክ ሱፐርቪዥን ዳይሬክተር አቶ ፍሬዘር አያሌው በበኩላቸው፣ የአገሪቱ ባንኮች በቀጣይ ትኩረት ሰጥተው ሊሠሩባቸው ይገባል ብለው በዝርዝር ካስጠቀመጧቸው ውስጥ በቀዳሚነት የጠቀሱት የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ ለውጭ ተወዳዳሪዎች የመከፈቱ ጉዳይ እውነታ ሆኖ እየመጣ በመሆኑ ለማይቀረው ውድድር ከወዲሁ ዝግጅት ማድረግ እንዲጀምሩ የሚመክር ነው።
አቶ ፍሬዘር እንዳሉት፣ የባንክ ዘርፍ ለውጭ ኩባንያዎች ሊከፈቱ የሚችል በመሆኑ፣ የአገሪቱ ባንኮች ለዚህ ስትራቴጂካዊ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። አክለውም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክም ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ የሱፐር ቪዥንና (የክትትልና ቁጥጥር) አቅሙን እንዲሁም፣ የባንክ ዘርፍ አቅምን ማጎልበት ላይ በሰፊው ሊሠራ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ከላይ የተገለጸው እንዳለ ሆኖ፣ የአገሪቱ ባንኮች ባለፉት አራት ዓመታት ከሌሎች ዘርፎች በተለየ አትራፊና ውጤታማ ሆነው መቀጠላቸው በውይይት መድረኩ በጥንካሬ ተነስቷል።
በ2014 የሒሳብ ዓመት 16ቱ የግል ባንኮችና ሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች ከታክስና ከሌሎች ተቀናሾች በፊት ከ70 ቢሊዮን ብር በላይ ማትረፋቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ከዚህም ውስጥ 16ቱ የግል ባንኮች ከ40 ቢሊዮን ብር በላይ ትርፍ ሲያስመዘግቡ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የኢትዮጵያ ልማት ባንክ እንደቅደም ተከተላቸው 27.5 ቢሊዮን ብር እና 3.4 ቢሊዮን ብር ከታክስና ከሌሎች ተቀናሾች በፊት ማትረፍ ችለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ በውይይት መድረኩ እንደገለጹትም፣ ባለፉት አራት ዓመታት በዘርፉ የተደረጉት ሪፎርሞች የባንክ ኢንዱስትሪውን በከፍተኛ ደረጃ እያሳደገው መጥቷል፡፡ ይህ ዕድገት የተመዘገበው ደግሞ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ተግዳሮቶች ጎልተው በታዩበት ወቅት በመሆኑ የነበሩት ተደራራቢ ተግዳሮቶች ባይኖሩ ዘርፉ ከዚህም በላይ ውጤት ባስመዘገበ ነበር ብለዋል፡፡ ውጫዊም ሆነ ውስጣዊ ችግሮች እጅግ ፈታኝ ቢሆኑም የባንክ ኢንዱስትሪው እያደገና ለአገራዊ ኢኮኖሚያዋ ዕድገት ከፍተኛ የሚባል አስተዋጽኦ እያደረገ መቀጠሉንም አመልክተዋል፡፡ ይህ ያልተቋረጠ ዕድገት የተገኘው ባንኮች ባደረጉት ያላሰለሰ ጥረት በመሆኑ ምሥጋና ይገባቸዋል ተብለዋል፡፡
የአገሪቱን የባንኮች እንቅስቃሴና በተለይ ባለፉት አራት ዓመታት የታየውን ዕድገት አኃዛዊ መረጃዎችን በማስደገፍ ማብራሪያ የሰጡት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የባንክ ሱፐርቪዥን ዳይሬክተር አቶ ፍሬዘር አያሌው እንዳመለከቱት በሁሉም ረገድ ባንኮች ከፍተኛ የሚባል ዕድገት ያሳዩ መሆናቸውን ነው፡፡ ለዚህም ማሳሪያ የሆኑ አኃዛዊ መረጃዎች በማጣቀስ ገለጻ ያደረጉት እጥፍ ነበር እንደ ምሳሌ ካነሱት ውስጥ ከአራት ዓመት በፊት በ2011 የሒሳብ ዓመት 18 የነበሩት ባንኮች ቁጥር በዚህ ዓመት መጨረሻ ላይ 30 መድረሳቸው አንዱ ነው፡፡ እነዚህ ባንኮች በ2011 የነበራቸው የቅርንጫፎች ብዛት 5,564 የነበረ ሲሆን ይህ ቁጥር በ2014 መጨረሻ ላይ 8,944 ደርሷል፡፡ ይህም በአራት ዓመት ውስጥ 61 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡
የባንክ ኢንዱስትሪው ማደጉን የሚያመላክተውና በተለይም በአራት ዓመታት ውስጥ ለውጥ ማሳየቱን ሌላው አመላካች የሆነው የባንክ ተደራሽነት ዕድገት ማሳየቱ ነው፡፡ አቶ ፍሬዘር እንደገለጹት በ2011 የሒሳብ ዓመት አንድ ቅርንጫፍ ለ16,957 ሰው ሲሆን ይህ ቁጥር በ2014 የሒሳብ ዓመት መጨረሻ ላይ ወደ 11,516 ወርዷል፡፡ ይህ ትልቅ ለውጥ ተደርጎ የሚታይ ነው ተብሏል፡፡
የአገሪቱ ባንኮች ከሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች በተለየ ዕድገት የታየባቸው ስለመሆኑ ማሳያ ሆኖ የቀረበው ሌላው አኃዛዊ መረጃ ደግሞ የባንኮቹ የሀብት መጠን ዕድገት ነው፡፡ የሰጡት የብድር መጠን፣ የተቀማጭ ገንዘብ፣ ካፒታልና የአስቀማጭ ደንበኞቻቸው ቁጥር መጨመር ዘርፉ ላስመዘገበው ዕድገት ሌላው ማሳያ ነው፡፡
በእነዚህ ዋና ዋና የዘርፉ መመዘኛዎች ሲታዩ በተለይ ባለፉት አራት ዓመታት ባንኮቹ ከ73 እስከ 108 በመቶ ዕድገት አሳይተዋል፡፡ በእነዚህ ወሳኝ መመዘኛዎች ዙሪያ ማብራሪያ የሰጡት አቶ ፍሬዘር የባንኮች አጠቃላይ የሀብት መጠን ባለፉት አራት ዓመታት በአማካይ 24.5 በመቶ እያደገ በ2014 መጨረሻ ላይ 2.5 ትሪሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ይህ አኃዝ ከ2011 የሒሳብ ዓመት ከነበረው የ1.3 ትሪሊዮን ብር የሀብት መጠን ጋር ሲነፃፀር የ92 በመቶ ዕድገት ያሳየ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
እነዚህ ባንኮች የብድር ክምችታቸውም በአማካይ በ20 በመቶ እያደገ የመጣ መሆኑን ያመለከቱት አቶ ፍሬዘር በ2011 የሒሳብ ዓመት 952.08 ቢሊዮን ብር የነበረው የባንኮች የብድር ክምችት በ2014 መጨረሻ ላይ 1.64 ትሪሊዮን ብር ደርሷል ብለዋል፡፡ በተቀማጭ ገንዘብ ረገድም ባለፉት አራት ዓመት በአማካይ 25 በመቶ እያደገ መጥቶ አሁን ላይ 1.73 ትሪሊዮን ብር መደረሱን ያመለከቱት አቶ ፍሬዘር ይህ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን በ2011 የሒሳብ ዓመት ከነበረበት 899.8 ቢሊዮን ብር አንፃር ሲታይ በአራት ዓመታት ውስጥ 93 በመቶ ማደጉን ያመለክታል ብለዋል፡፡
የአገሪቱ ባንኮች በተለየ ከፍተኛ ዕድገት ያስመዘገቡበት ተብሎ የተጠቀሱት ሌሎች ማሳያዎች ደግሞ የካፒታል መጠንና የቁጠባ ሒሳብ የከፈቱ ደንበኞች ቁጥር ነው፡፡ ዳይሬክተሩ እንዳመለከቱትም በ2011 የሒሳብ ዓመት የሁሉም ባንኮች ካፒታል መጠን 98.9 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ ይህ የካፒታል መጠን በየዓመቱ በአማካይ 27 በመቶ እያደገ መጥቶ በ2014 መጨረሻ ላይ 199.1 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ አኃዛዊ መረጃው መረዳት እንደሚቻለው ባንኮቹ ባለፉት አራት ዓመታት ካፒታላቸውን በእጥፍ ማሳደግ መቻላቸውን ነው፡፡ በ2014 የደረሱበት የካፒታል መጠን ከ2011 የሒሳብ ዓመት ከነበረው ጋር ሲነፃፀርም የ101 በመቶ ዕድገት የታየበት መሆኑን አቶ ፍሬዘር ተናግረዋል፡፡
በባንኮች የተቀማጭ ሒሳብ የከፈቱ ደንበኞች ቁጥርም በአራት ዓመታት ውስጥ በእጥፍ ጨምሯል፡፡ ሁለትና ከሁለት በላይ ደብተር ያላቸው ደንበኞች ታሳቢ ተደርጎ በ2011 የሒሳብ ዓመት 40.04 ሚሊዮን የበረው የአስቀማጮች ቁጥር በአራት ዓመት ውስጥ በየዓመቱ በአማካይ በ28 በመቶ ዕድገት እያስመዘገበ 2014 ላይ 83.3 ሚሊዮን ደርሷል፡፡ ይህ የ108 በመቶ ዕድገት የታየበት እንደሆነም ዳይሬክተሩ አመልክተዋል፡፡
የአገሪቱ ባንኮች በእርግጥም አድገዋል ውጤታማም መሆን ችለዋል የሚለውን የበለጠ የሚገልጸው ዓመተዊ የትርፍ ምጣኔያቸው እንደሆነ ያስታወሱት አቶ ፍሬዘር ሁሉንም ባንኮች አትራፊ ሆነው ቀጥለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ባንኮች በተለየ የማይታይበት ነጥብ አንድም ባንክ ኢትዮጵያ ውስጥ ከስሮ የተዘጋ ያለመሆኑን ነው፡፡
ባለፉት አራት ዓመታትም የባንኮች የተጣራ ትርፍ ወይም ከታክስ በኋላ ያስመዘገቡትን ትርፍ በአኃዝ በምሳሌነት ቀርቧል፡፡ በ2011 የሒሳብ ዓመት ሁሉም ባንኮች ከታክስ በኋላ ያስመዘገቡት የትርፍ መጠን 22.48 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ በ2012 ደግሞ 21.86 ቢሊዮን ብር ሲያገኙ በ2013 ከታክስ በኋላ ያገኙትን ትርፍ ወደ 33.54 ቢሊዮን ማድረስ መቻላቸውን ጠቅሰዋል፡፡ በ2014 ደግሞ ከታክስ በፊት 49.9 ቢሊዮን ብር በማድረስ ችለዋል፡፡ ይህ የትርፍ መጠን ዕድገት ከ2011 አንፃር ሲታይ የ122 በመቶ ዕድገት የታየበት መሆኑንም አቶ ፍሬዘር አመልክተዋል፡፡
የአገሪቱ የፋይናንስ ተቋማት በተለያዩ መለኪያዎች ጤናማ ሆነው ስለመቀጠላቸው በርካታ ማሳያዎች እንዳሉም ተጠቅሷል፡፡ ጤናማነታቸውን ማሳያ ተደርጎ የቀረበው የተበላሸ የብድር መጠናቸው ዝቅተኛ መሆን ነው፡፡ ባለፉት አራት ዓመታት ኢኮኖሚው ላይ ብዙ ጫና ቢኖርም የባንኮች የተበላሸ የብድር መጠን 3.87 በመቶ ነው፡፡ የተበላሸ ብድር መጠን ከአምስት በመቶ መብለጥ የለበትም ብሎ ካስቀመጠው መጠን በታች በመሆኑ ጤናማነታቸውን ያሳያል ተብሏል፡፡
በሌሎች መለኪያዎችም የንግድ ባንኮች ጤናማ ሆነው እየሠሩ ነው መሆኑን የገለጹት አቶ ፍሬዘር ከፍተኛ የተበላሸ ብድር ይዞ የቆየው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የተበላሸ ብድር መጠኑን በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱን በሚመለከት የኢትዮጵያ ባንኮች ጤናማና ውጤታማ ሆነው እየቀጠሉ ነው ብለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ወደ 47 በመቶ የነበረውን የተበላሸ ብድር መጠን ወደ 15 በመቶ ማውረድ መቻሉና የ3.4 ቢሊዮን ብር ትርፍ በ2014 የሒሳብ ዓመት ማትረፉ ታውቋል፡፡
ከሌላው ጊዜ በተለየ ባንኮች ያስገኙት ውጤት በተወደሰበት መድረክ ላይ ‹ይህ ውጤት እንዴት ተገኘ?› የሚለው ጥያቄም መልስ የተሰጠበት ነበር፡፡ አቶ ፍሬዘር ለዘርፉ ዕድገት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጀው በርካታ ለውጦችና ሪፎርሞች ትልቅ አስተዋጽኦ ነበረው፡፡ ባለፉት አራት ዓመታት አጠቃላይ የባንክ ሥርዓቱ የሚመራበትን የባንክ ሌጋልና ሌጋል ፎርም ወርክ ሪቪው የማድረግ ሥራ መሠራቱ፣ ተንቀሳቃሽ ንብረትን በዋስትና አስይዞ መበደር እንዲቻል የሚያስችል አዋጅና መመርያ መውጣቱ፣ የካፒታል ሕግ እንዲወጣ መደረጉ፣
ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት መፍቀድ፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን በባንክ ዘርፍ ላይ ኢንቨስት እንዲያደጉት መፈቀድ፣ አቅም ያላቸው ማክሮ ፋይናንሶች ወደ ባንክ እንዲያድጉ መፍቀድ፣ ትልቁ ሪፎርም ደግሞ የፋይናንስ ዘርፍ ሲባል፣ በአብዛኛው ባንክና ማክሮ ፋይናንስ የሚጠቀስ ሲሆን፣ አሁን ግን የተለያዩ ዘርፎች ተካተዋል፡፡ ባንኮች ካፒታላቸውን እንዲያሳድጉ መወሰኑና ሌሎች በርካታ ማሻሻያዎች ለዘርፉ ዕድገት አስተዋጽኦ ነበረው ተብሏል፡፡ የባንክ ፕሬዚዳንቶችም የብር ኖት ለውጡ በአንዳንድ መመርያዎች ላይ ብሔራዊ ባንክ ባንኮችን ማማከሩና ሌሎች ዕርምጃዎችም ለዘርፉ ዕድገት አበርክቶ እንደነበረው ጠቁመዋል፡፡