Friday, December 1, 2023

የኬንያ ምርጫ ቀጣናዊ አንድምታው

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በዘመናት ውስጥ ሳይናወጥ መዝለቅ የቻለ ይሉታል አንዳንዶች፡፡ የአገሮቹ መሪዎች መፈራረቅም ሆነ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም መለዋወጥ ሳይጫነው ረዥም ጊዜ መዝለቅ የቻለ መሆኑንም ብዙዎች ይናገራሉ፡፡ የኬንያና የኢትዮጵያ ግንኙነት በአገሮቹ ውስጥ በየዘመናቱ የተፈጠሩ ለውጦችን ተሻግሮ ሳይሻክር መዝለቅ የቻለ የሰመረ መሆኑን በርካቶች ይስማሙበታል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ለአዲሱ ተመራጭ የኬንያ ፕሬዚዳንት ለዊሊያም ሩቶ ፈጥነው የእንኳ ደስ አለዎት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ ከተሳናባቹ ፕሬዚዳንት ከኡሁሩ ኬንያታ ጋር መልካም ግንኙነት ለመመሥረት ያልተቸገሩት ዓብይ (ዶ/ር)፣ ከአዲሱ ተመራጭ ፕሬዚዳንት ጋር መልካም ግንኙነት ለመመሥረት ያላቸውን ተስፋ በዚህ የደስታ መልዕክታቸው ገልጸው ነበር፡፡

በኢትዮጵያና በኬንያ አዋሳኝ የድንበር ከተሞች የጋራ የኢኮኖሚና የንግድ ቀጣና በመመሥረት ሞያሌ ላይ ከኡሁሩ ጋር ሲጨባበጡ የታዩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር)፣ ከተተኪው ተመራጭ ፕሬዚዳንት ጋር ተመሳሳይ የሁለትዮሽ ግንኙነት ለመፍጠር አይቸገሩም የሚል ግምት አሳድሯል፡፡ ዓብይ (ዶ/ር) ከሁለትዮሽ ባለፈም ከተመራጩ ፕሬዚዳንት ጋር በቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመሥራት ተስፋ እንዳላቸውም ነው በመልዕክታቸው የጠቀሱት፡፡

ታሪክ እንደሚያስታውሰው ኢትዮጵያ ለኬንያ ከቅኝ ተገዥነት የመላቀቅ ተጋድሎ በርካታ ድጋፎች አድርጋለች፡፡ የማኦ ማኦ ነፃ አውጪ ንቅናቄ ተዋጊዎችን በማስታጠቅና በማስጠጋት ቀደምት የኢትዮጵያ መሪዎች ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደነበራቸው ታሪክ ከትቦ አስቀርቶታል፡፡ በቅርብ ጊዜ ለንባብ የበቃው በባህሩ ዘውዴ (ፕሮፌሰር) የቀረበው የፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ (አባመላ) ግል ታሪክ መጽሐፍ፣ የኢትዮጵያና የኬንያ ግንኙነትም ሆነ የወሰን ጉዳይ ከየት እንደሚጀምር በሰፊው ያትታል፡፡

ረዥም ዘመናት ያሳለፈው የሁለቱ አገሮች ወዳጅነት በብዙ የታሪክ አጋጣሚዎች መፈተኑ ባይቀርም፣ በአፍሪካ ቀንድ ካሉ አገሮች የተሻለውና በበጎነት የሚወሳ ግንኙነት መሆኑ በሰፊው ይወሳል፡፡

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ዳይሬክተር ጄኔራል ሆነው እያገለገሉ የሚገኙትና ለረዥም ዓመታት በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው የሠሩት ዲና ሙፍቲ (አምባሳደር)፣ ኢትዮጵያ ከኬንያ ጋር ያላት ግንኙነት ከሌሎች ጎረቤቶቿ ጋር ካላት ግንኙነት የተለየ ገጽታ እንዳለው ይናገራሉ፡፡

‹‹ኢትዮጵያ ከኬንያ ጋር ካልሆነ በስተቀር ከሌሎቹ ጋር በሆነ ወቅት በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ መቀያየም ውስጥ ገብታ ነበር፡፡ ሱዳን፣ ሶማሊያና ኤርትራን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ከኬንያ ጋር ኢትዮጵያ ተቀያይማም ሆነ ተጋጭታ አታውቅም፡፡ የግንኙነቱ መጥበቅና መላላት በየወቅቱ የሚነሳ ካልሆነ በስተቀር በአመዛኙ የሁለቱ ግንኙነት በጥንካሬ የሚነሳ ነው፤›› በማለት ነው ዲና (አምባሳደር) የሚያስረዱት፡፡

የአዲሱ ተመራጭ ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ ወደ ሥልጣን መምጣት የሁለቱን አገሮች ግንኙነት የበለጠ የማጠናከር ዕድሉ የሰፋ እንደሆነ ዲና (አምባሳደር) ግምታቸውን ይናገራሉ፡፡ ምርጫውን ተከትሎ በኬንያ የሚፈጠረው ፖለቲካዊ ለውጥ አገሪቱ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ያሻክረዋል የሚል እምነት አለመኖሩንም ያክላሉ፡፡

የሁለቱ አገሮች የቀደሙ መሪዎች በተለያዩ ጊዜያት በመገናኘት በሁለቱ አገሮች መካከል ወዳጃዊ ግንኙነት ለመፍጠር ጥረት ማድረጋቸው ይነገራል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1964 እና በ1970 ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ኬንያን ጎብኝተዋል፡፡ ጆሞ ኬንያታ እ.ኤ.አ. በ1967 በአዲስ አበባ ያደረጉትን ታሪካዊ ጉብኝት ጨምሮ፣ የናይሮቢ ቤተ መንግሥትን የተፈራረቁበት አምስቱም ፕሬዚዳንቶች በየጊዜው ወደ ኢትዮጵያ ተመላልሰዋል፡፡ ፕሬዚዳንት ዳንኤል አራፕ ሞይ እ.ኤ.አ. በ1979 እና በ1991 አዲስ አበባን እንደረገጡት ሁሉ፣ ኢትዮጵያን ከዓለምና ከቀጣናዊ ፖለቲካ በማግለል የሚታሙት ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ጭምር እ.ኤ.አ. በ1980 የናይሮቢ እንግዳ ነበሩ፡፡

የኬንያና የኢትዮጵያ ግንኙነት በየዘመናቱ የሁለቱ አገሮች መሪዎች ሲለዋወጡም ሆነ ፖለቲካቸው ሲቀያየር ሳይስተጓጎል ቀጥሏል፡፡ በአገሮቹ መካከል የሚኖረውን ግንኙነት ከዚህ ይልቅ ቀጣናዊ የፀጥታና የጂኦ ፖለቲካዊ ሁኔታ ሲወስነው ነው የቆየው ይባላል፡፡

‹‹የሁለቱ አገሮች ግንኙነት በዋናነት በሁለቱ መካከል ባለው ፍላጎት ሊቀየር የሚችልበት ዕድል የጠበበ ነው፡፡ በኬንያም ሆነ በኢትዮጵያ ማንም ወደ ሥልጣን ቢመጣ የግንኙነቱ ፍጥነት መጨመርና መቀነስ ካልሆነ በስተቀር በሁለቱም በኩል የሚፈጠር ነገር የለም፤›› ይላሉ ዲና (አምባሳደር) ግንኙነታቸውን ስለሚወስነው ጉዳይ ሲያስረዱ፡፡ በአንድ ወቅት ኬንያ በቀጣናው የጂኦ ስትራቴጂክ ተፈላጊነት ያላት አገር እንደነበረችው ሁሉ፣ በሌላ ጊዜ ደግሞ ኢትዮጵያ ከዓለም ጋር ያላት ግንኙነት ተጠናክሮ የወጣበት ሲሆን፣ ከመታየቱ በስተቀር በሁለቱ መካከል ግንኙነት የማሻከር ፍላጎት ኖሮ እንደማያውቅ ያክላሉ፡፡

‹‹ኢትዮጵያ በቀጣናው ጂኦ ፖለቲካ ተፅዕኖዋ እየጨመረ ነው፣ ኢኮኖሚዋ እየፈጠነ ነው፣ በዕድገትም እየተለወጠች ነው የሚለው ትርክት በተለይ በኬንያ ልሂቃን ዘንድ የፉክክር መንፈስ ከመፍጠር ውጪ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ጠንካራ ሆኖ ነው የዘለቀው፡፡ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ፣ የድንበሩ፣ የቋንቋና የባህል ግንኙነታቸው ጠንካራ በመሆኑ ሁለቱ አገሮች ሊለያዩ የማይችሉ አገሮች ሆነው ነው የዘለቁት፤›› በማለትም ዲና (አምባሳደር) የግንኙነቱን ሁኔታ ያሰምሩበታል፡፡

ሰኞ ነሐሴ 9 ቀን 2014 ዓ.ም. ምሽት ውጤቱ የተበሰረው የኬንያ ምርጫ ከመቼውም ጊዜ በላይ ጠንካራ ፉክክር እንደታየበት ተነግሯል፡፡ ዊሊያም ሩቶ 50.5 በመቶ ድምፅ በመሰብሰብ ማሸነፋቸው በታወጀበት ወቅት በተቃራኒው ከሰባቱ የምርጫ ኮሚሽነሮች አራቱ የምርጫ ውጤቱን አንቀበለውም የሚል መግለጫ ይሰጡ ነበር፡፡ ተሸናፊ የተባሉት ራይላ ኦዲንጋ የምርጫውን ውጤት ተቃውመዋል፡፡ በዚሁ ዕለት ተቃውሞ መቀስቀሱ የተነገረ ሲሆን፣ ዴሞክራሲያዊና ፉክክር ታይቶበት የነበረው እ.ኤ.አ. በ2007 ወደ 1,200 ዜጎች ያለቁበት ዓይነት የምርጫ ቀውስ እንዳይፈጠር ሥጋት ተፈጥሯል፡፡

ለምርጫ ማግሥት ቀውሶች አዲስ ያልሆነችው ኬንያ እ.ኤ.አ. በ2017 የፍርድ ቤት ጭቅጭቆችን ያስተናገደው ምርጫዋ የመቶ ዜጎችን ሕይወት መንጠቁም ይነገራል፡፡ ከትናንት በስቲያ ውጤቱ ይፋ የሆነው የዘንድሮ ምርጫም ተመሳሳይ የፖለቲካ ቀውስ እንዳያስከትል እየተሠጋ ሲሆን፣ ኅትመት እስክንገባ ድረስ ይወጡ የነበሩ መረጃዎችም ይህንኑ ፍንጭ የሚሰጡ ሆነው ነው የተገኙት፡፡

ለአምስተኛ ጊዜ በፕሬዚዳንታዊ ፉክክር ተሳትፏቸው የሚታወቁት በ48.5 በመቶ ድምፅ ተሸንፈዋል የተባሉት የአንድ ወቅት የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት የ77 ዓመቱ አንጋፋ ፖለቲከኛ ራይላ ኦዲንጋ፣ የምርጫውን ውጤት እንደማይቀበሉት ማክሰኞ ምሽት ላይ አስታውቀዋል፡፡ ኦዲንጋ እንደ ከዚህ ቀደሞቹ ምርጫዎች ሁሉ የአሁኑን ምርጫም ውጤት ወደ ፍርድ ቤት ለሙግት ይዘውት እንደሚሄዱ ይጠበቃል፡፡ ብዙዎች በኬንያ ምርጫው ቀውስ ይዞ ሊመጣ እንደሚችል ቢገምቱም፣ አገሪቱ የተፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት የሚያስችል ተቋማዊና ሥርዓታዊ አቅም እንዳላት የሚናገሩ በርካታ ናቸው፡፡

ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ የውጭ ግንኙነት ባለሙያ፣ ‹‹ኬንያውያን የፈለገ ቢጣሉም ሆነ ቢጋጩ እንደ ሌላው አገር አይጨካከኑም፤›› ይላሉ፡፡ ተቃዋሚዎቹ ማለትም የኦዲንጋ ወገን ለጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ይግባኝ እንደሚሉ የገመቱት ባለሙያው፣ ‹‹የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ስለማይታወቅ ውጤቱ ምን ይሆናል የሚለው ላይ መጣደፍ አያስፈልግም፤›› ሲሉ ያክላሉ፡፡

‹‹የታንዛኒያም ሆነ የሩዋንዳና የሌሎች ምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ምርጫዎች ተገማች ቢሆኑም የኬንያ ግን አንገት ለአንገት ትንቅንቅ የሚታይበትና የማይገመት ነው፡፡ በኬንያ የሚደረጉ ምርጫዎችም እጅግ ውድ ናቸው፡፡ እ.ኤ.አ. በ2017 ለምርጫ አገሪቱ 499 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ያደረገች ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥም 53 ሚሊዮን ዶላሩ ለፀጥታ ጥበቃ የዋለ ነው፡፡ በኬንያ በምርጫ ወቅት ገንዘብ ይበተናል፡፡ አገሪቱ የምታወጣው ከጎረቤቶቿ ድምር የምርጫ ወጪ የበለጠ ነው፡፡ ሆኖም ይህ ሁሉ ወጥቶበትም ውዝግብ አያጣውም፡፡ ውጤቱ በወጣ በአንድ ሳምንት ውስጥ ለፍርድ ቤት ይግባኝ መቅረብ ስለሚችል፣ ውጤቱን ከመናገራችን በፊት ሊኖር የሚችለውን የፍርድ ቤት ውዝግብ መጠበቅ ይኖርብናል፤›› ሲሉም የውጭ ጉዳይ ባለሙያው ይመክራሉ፡፡

ይሁን እንጂ በኬንያ በምርጫ ሒደት የፈለገ ቀውስ ቢከሰትም ሆነ ውዝግብ ቢፈጠር፣ የከፋ አደጋና መተላለቅ ይኖራል የሚል እምነት እንደሌላቸው ነው ባለሙያው የሚናገሩት፡፡

‹‹በኬንያውያን ዘንድ የከፋ መካረር ብዙ የለም፡፡ የፖለቲካ ባህላቸው ነውጠኝነት አያጠቃውም፡፡ ዘላቂ ጥቅም እንጂ ዘላቂ ወዳጅ የለም የሚል ብሂል አላቸው፡፡ እ.ኤ.አ. በ2013 እና በ2017 ኡሁሩ ኬንያታና ዊሊያም ሩቶ በአንድ ጎራ፣ ራይላ ኦዲንጋ ደግሞ በተቃራኒው ነበሩ፡፡ አሁን ደግሞ ተገልብጦ ኡሁሩ ኬንያታ ራይላ ኦዲንጋን ደግፈው በመቆም የዊሊያም ሩቶ ተቀናቃኝ ሆነዋል፤›› በማለት የሚያክሉት ባለሙያው፣ ይህን መሰሉ ፖለቲካዊ ባህላቸው አንዳቸው በሌላቸው በከፋ ሁኔታ እንዳይጨካከኑ እንደሚያደርጋቸው ተናግረዋል፡፡

የኮሮና ወረርሽኝ የቱሪዝም ገቢዋን ያወረደባትና ኢኮኖሚዋ ክፉኛ የተጎዳው ኬንያ፣ አሁን ልክ እንደ ሌላው ጊዜ የምርጫ ውዝግብ ቀውሶችን እያስተናገደች ለመቀጠል የምትችልበት ዕድል አለመኖሩ ይነገራል፡፡ በቀጣናው በአንፃራዊነት የተሻለ ፖለቲካዊ መረጋጋት አላት የምትባለዋ ኬንያ በምርጫ ውጤት መዘዝ ወደ ቀውስ ካመራች፣ የምሥራቅ አፍሪካ ቀውስ ከድጡ ወደ ማጡ ሊያመራ እንደሚችል መገመት ቀላል መሆኑን ብዙዎች እየተናገሩ ነው፡፡

አራት ሚሊዮን የምግብ ዕርዳታ ፈላጊ ሕዝብ ባላት ኬንያ ምርጫው ሥራ የሚፈጥር፣ ኢኮኖሚውን እንዲያነቃቃና ኢንቨስትመንት እንዲያስፋፋ ዕድል የሚያመቻች መሪ ይዞ እንዲመጣ የሚጠበቅ ነው፡፡

 አገሪቱ በቂ ቀውስ እንዳላት የሚናገረው በናይሮቢ መቀመጫውን ያደረገ አንድ የሚዲያ ባለሙያ፣ በምርጫው ወቅት ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ዋና መፎካከሪያ እንደነበሩ ይጠቅሳል፡፡ ኢኮኖሚውን ማን በተሻለ ከቀውስ ያላቅቃል? በተለይ ከፍተኛ ችግር እየሆነ የመጣውን የኑሮ ውድነት ችግር ማን ይቀርፋል? እንዲሁም ደሃውን የማኅበረሰብ ክፍል ያማከለ ፖሊሲ ማን ያመጣል? የሚሉ ጥያቄዎች የመራጮችን ድምፅ ለማግኘት ወሳኝ ጉዳዮች እንደነበሩ የሚዲያ ባለሙያው ያወሳል፡፡ በምርጫው ወቅት ለድሆች ድጎማ የመስጠት ዕቅድ አንድ የፉክክር ጉዳይ ሆኖ እንደነበር በበርካታ መገናኛ ብዙኃን ተዘግቧል፡፡

አሸናፊ ተመራጭ መሆናቸው በይፋ የታወጀው ዊሊያም ሩቶ ራሳቸው ድህነትን ቀምሰው ያደጉና የደሃው ማኅበረሰብ አካል የሚባሉ ሰው ናቸው፡፡ በእንቁላል መሸጥ ንግድ ያለፉትና ተግቶ በመልፋት ለትልቅ የፖለቲካ ኃላፊነት የበቁት ሰውየው፣ ነባሩን የፖለቲካ ባህል ታግለው አልፈው አሁን ካሉበት ቦታ መድረሳቸው ይነገራል፡፡ የኬንያታና የኦዲንጋ ቤተሰቦች የተፈራረቁበትን የኬንያ ቤተ መንግሥት ዊሊያም ሩቶ በፕሬዚዳንትነት የሚገቡበት ከሆነ፣ ያልተጻፈውን ሕግ ሽረው የሰፊው ደሃ ኬንያዊ ተወካይ ለፕሬዚዳንትነት በቁ እንደሚባል ብዙዎች እየዘገቡ ነው፡፡

ልክ እንደ ኢኮኖሚው ሁሉ የምርጫ ውዝግቦቹ ዕልባት አግኝተው ሰውየው በመጨረሻ አሸናፊነታቸው የሚታወጅ ከሆነ፣ በቀጣናው ኬንያ የሚኖራት ሚና ላይ ሊያደርጉት የሚችለው ለውጥም የሚጠበቅ ነው፡፡

በሶማሊያ የተሰማራውን ሰላም አስከባሪ ጦር ኬንያ እንድታስወጣ ማድረግ/አለማድረጋቸው፣ ከምዕራባውያን ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት ብቻ ሳይሆን እንደ ኢትዮጵያ ካሉ ጎረቤት አገሮች ጋር የሚፈጥሩት ግንኙነት በእጅጉ ተጠባቂ ነው፡፡

እ.ኤ.አ. በ1963 የመከላከያና የኢኮኖሚ ትብብር ስምምነት በመፈራረም መደበኛ ግንኙነታቸውን ያጠናከሩት ኬንያና ኢትዮጵያ፣ የብዙ ቢሊዮን ብሮች ሸቀጥ በዓመት የሚነግዱ ጎረቤታሞች ሆነዋል፡፡ የብሔራዊ ባንክ መረጃ እንደሚያመለክተው እ.ኤ.አ. በ2020/21 በጀት ዓመት ኢትዮጵያ ከኬንያ የ2.2 ቢሊዮን ብር ሸቀጥ ስትገዛ፣ 1.6 ቢሊዮን ብር የሚያወጣ ዕቃ ደግሞ ወደ ኬንያ ገበያ ልካለች፡፡ ኢትዮጵያ በንግድ በኩል ከጂቡቲ ቀጥሎ ሁለተኛዋ ሸሪኳ ኬንያ ናት ይባላል፡፡

ሁለቱ አገሮች በኃይል ሽያጭ፣ በወደብና በሎጂስቲክስ አገልግሎትም የሚፈላለጉ ተጎራባቾች መሆናቸው ይወሳል፡፡ በሌላ በኩል በባህል፣ በቋንቋና በሕዝቦች ጥብቅ ትስስር ያላቸው አገሮች መሆናቸው ፈፅሞ አይታለፍም፡፡ እንደ ላሙ (LAMU) ያሉ ግዙፍ ቀጣናዊ የንግድና ሎጂስቲክስ ፕሮጀክቶችን በጋራ የጀመሩት አገሮቹ በድንበር ተሻጋሪ ንግድ ብቻ ሳይሆን፣ በቀጣናዊ የፀጥታና ደኅንነት ጉዳዮችም ተፈላላጊ መሆናቸው ይነገራል፡፡ በምርጫ ፉክክሩ ወቅት ራይላ ኣዲንጋ ኢትዮጵያን ‹‹የቀጣናው ደካማ አገር›› በማለት ኬንያን ከፍ አድርጎ ለማሳየት ማመሳከሪያ አድርገው ያቀረቡበት ንግግር፣ ሰውየው ቢመረጡ የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ሊያበላሹት ይችላል የሚል ግምት ማሳደሩ ይነገራል፡፡ ይሁን እንጂ ዊሊያም ሩቶ አሸንፈዋል መባላቸው ይህን ግምት የለወጠ ሲሆን፣ አሸናፊ የተባሉት ሩቶ ለኢትዮጵያ የተለየ ቀረቤታና አመለካከት አላቸው የሚሉ አስተያየቶች በሰፊው እየተደመጡ ነው፡፡

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ዳይሬክተር ጄኔራል ዲና (አምባሳደር) እንደሚሰጡት አስተያየት ከሆነ ግን፣ የኬንያ ፖለቲከኞች (የፖለቲካ ሊሂቃን) በምርጫ ወቅት የሚናገሩትን ወደ ሥልጣን ቢመጡ በተግባር ይተረጉሙታል ማለት አለመሆኑን ያስረዳሉ፡፡

‹‹ራይላ ኦዲንጋ አላስፈላጊ የሆነ ንግግር ተናግረዋል፡፡ ይህ ደግሞ ለእሳቸው አዲስ አይደለም፤›› የሚሉት ዲና (አምባሳደር)፣ ወደ ሥልጣን ቢመጡ ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ያሻክራሉ ማለት እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡

በሌላ በኩል ምርጫውን አሸነፉ የተባሉትን ዊሊያም ሩቶን፣ ‹‹ጠንካራ ሰብዕና ያላቸውና ከምንም ተነስተው ለስኬት የበቁ ታታሪና ጠንካራ ሰው ናቸው፤›› ብለው፣ በምርጫው ውጤት ማግስት የተፈጠረው የፖለቲካ ውዝግብ በአጭር ጊዜ ተፈቶ ኬንያም ሆነች የቀጣናው ሁኔታ ወደ መረጋጋት ይመለሳል የሚል እምነት እንዳላቸው በመጥቀስ ሐሳባቸውን አጠቃለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -