- ኬንያ በዚህ ደረጃ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ታደርጋለች ብዬ አላሰብኩም ነበር ክቡር ሚኒስትር።
- አዎ። ጥሩ ዝግጅት አድርገውበታል። ቢሆንም…
- ቢሆንም ምን ክቡር ሚኒስትር?
- እባክህ ክቡር ሚኒስትር የምትለውን ነገር አቁም። ወዳጅ አይደለንም እንዴ?
- እሱማ ልክ ነው። ለተቋሙ ክብር መስጠት ስላለብኝ ነው።
- ቢሆንም… አሁን ያለነው ከተቋሙ ውጪ ነው።
- ይልቅ እሱን አርሳውና ያቋረጥነውን ጨዋታ ቀጥል። ቢሆንም ብለህ ነበር ያቋረጥነው። ምን ልትል ነበር?
- እ… አዎ። የኬንያ ምርጫ ጥሩ እንደነበረ እያወራን ነበር።
- ጥሩ ብቻ ክቡር ሚኒስትር ለቀጣናው ጭምር ተምሳሌት የሚባል ነው እንጂ?
- አንተ ደግሞ በጣም አጋነንከው። በምንም መመዘኛ ከስድተኛው የእኛ ምርጫ ውድድር አይበልጥም።
- እኔ ግን በእኛ አገር የምርጫ ውድድር ተካሂዶ ያውቃል ለማለት እቸገራለሁ። ብቻችሁን አይደል እንዴ የተወዳደራችሁት? የእነሱ ግን …
- የእነሱ በምን ከእኛ በምን ይለያል?
- በተተኪው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሳይቀር ስንት ጫና ሲደረግባቸው የነበሩት ግለሰብ ጫናውን ተቋቁመው ለማሸነፍ የቻሉት ጥሩ የምርጫ ሥርዓት ስለገነቡ እንጂ እንደ እኛ ቢሆን ውጤቱ ሌላ ነበር የሚሆነው።
- ለማንኛውም ዊሊያም ሩቶ ቀጣዩ የኬንያ ፕሬዚዳንት ሆነው በማሸነፋቸው እኛም ልዩ ደስታ ተሰምቶናል።
- የእናንተን ደስታ ምን ልዩ ያደርገዋል?
- ሰውዬው ምን እንደሆኑ አታውቅም እንዴ?
- ዊሊያም ሩቶ?
- እህሳ?
- ምንድናቸው?
- የእኛው ብሔር እኮ ናቸው?
- አይ እናንተ… መቼም አትለወጡም በቃ?
- እንዴት?
- ምን ልትሉ እንደሆነ ገብቶኛል?
- ምን እንላለን?
- ሩቶ ኬኛ!
[ክቡር ሚኒስትሩ በስንዴ ምርት ራስን የመቻል ጥረትን በተመለከተ የተላለፈውን የምሽት ዜና ከባለቤታቸው ጋር ተመልክተው በዚህ ዙሪያ እየተጨዋወቱ ነው]
- ትልቅ ስኬት እንደምናስመዘግብ ጥርጥር የለውም።
- በምን ጉዳይ?
- በስንዴ ምርት ነዋ? ዜናውን እየተከታተልሽ መስሎኝ ነበር እኮ? እንደ ቀልድ የተቆጠረው ጥረታችን ዛሬ የት እንደደረሰ አላየሽም?
- እሱስ ተመልክቻለሁ። ጥሩ ጅምር ይመስላል ግን…
- ግን ምን?
- አሜሪካ ግን ይህንን ጥረት ለማቆሸሽ ይመስላል፡፡
- እንዴት?
- እናንተ ዘንድ ምንም ዓይነት የስንዴ ምርት ከውጭ አልሸመትንም እያላችሁ አይደል?
- ትክክል ነው! እንደውም ከመጪው ዓመት ጀምሮ ወደ ጎረቤት አገሮች ኤክስፖርት ማድረግ እንጀምራለን።
- እናንተ ዘንድሮ ስንዴ ከውጭ አናስገባም ብትሉም አሜሪካ ግን ለኢትዮጵያ የተገዛው ስንዴ ወደ አገሪቱ እየተጓጓዘ ነው የሚል መረጃ እያሠራጨች ነው።
- መቼ ነው ይህንን መረጃ ያሠራጨችው?
- ጠቅላዩ በስንዴ ማሳዎች ጉብኝት እያደረጉ በነበረበት ቀን መሰለኝ፡፡ አዎ በዚያው ቀን ነው።
- ከዚህ ሴራ ጀርባ ማን እንዳለ ግልጽ ነው።
- ሴራ? ማነው ያለው?
- ጁንታው ነዋ!
- መረጃውን ያሠራጨችው እኮ አሜሪካ ነች?
- ያው ናቸው! ለማንኛውም …
- እህ… ለማንኛውም? ስንዴውን አንቀበልም እንዳትለኝ ብቻ?!
- ለምን አንቀበልም …እንቀበላለን እንጂ፡፡
- እኮ…
- ግን አንድ ነገር መታወቅ አለበት።
- ምን?
- እኛ ያዘዝነው ስንዴ የለም! ከመጣ ግን አንቀበልም አንልም።
- ዋናው እሱ ነው። ስንዴውን ተቀብሎ የተጀመረውን በስንዴ ራስን የመቻል ጥረት መቀጠል።
- ትክልል ነው። አየሽ አይደል ምን ያህል ማሳ በበጋ ስንዴ እንደተሸፈነ?
- ምን ያህል ተሸፈነ?
- በሶማሌ ክልል ብቻ 127 ሺሕ ሔክታር በስንዴ እየለማ ነው።
- ስንት ማለት ነው 127 ሺሕ ሔክታር? ብዙ ነው እንዴ?
- አንቺና ቁጥር መቼም አትዋደዱም።
- ምን ያህል እንደሆነ ለምን አታስረዳኝም?
- ቆይ… እንዴት ላስረዳሽ? አዎ… ስንት መሰለሽ…?
- እህ… ስንት ነው?
- የአዲስ አበባ ከተማን በሁለት እጥፍ የሚበልጥ የስነዴ ማሳ እንደ ማለት ነው።
- አትቀልድ?!
- የምሬን ነው!
- በአዲሱ ነው፣ በድሮው ስፋቷ?
- አዲሱ ደግሞ ምንድነው?
- የከተማዋ አከላለል ማለቴ ነው።
- ቁምነገር እያወራን ለምን ትቀልጃለሽ?
- ቀልዴን አይደለም? እንደውም ካነሳነው አይቀር ልጠይቅህ?
- ምን?
- አሁን እኛ የምንኖርበት ቤት አዲስ አበባ ውስጥ ነው?
- ዛሬ ምን ሆነሻል? ስለ በጋ ስንዴ ስኬታችን እንዲወራ አልፈለግሽም?
- ኧረ እንደዚያ አይደለም።
- ታዲያ ምን እየሆንሽ ነው?
- የበጋ ስንዴው ስኬትማ በሌሎች ምርቶችም ቢደገም ጥሩ ነው።
- እሱማ አይቀርም። ይደገማል!
- በተለይ ነዳጅ ላይ ብትረባረቡ ጥሩ ነው።
- ነዳጅ?
- አዎ።
- የምን ነዳጅ?
- የበጋ ነዳጅ!