የጠቅላይ ሚንስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢልለኔ ስዩም ዛሬ ሐሙስ ነሐሴ 12/2014 ዓ.ም. ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ የአገሪቱ መከላከያ ሠራዊት በትግራይ ኃይሎች ላይ ተኩስ ከፍቷል መባሉ ሐሰት ነው ብለዋል።
ቢልለኔ ይህን ያሉት የትግራይ ኃይሎች የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በተለያዩ ግንባሮች ጥቃት ፈጽሞብናል ካሉ በኋላ ነው።
የትግራይ ኃይሎች ረቡዕ ነሐሴ 11/2014 ዓ.ም. ባወጡት መግለጫ የፌደራል መንግሥቱ ጦር በምዕራብ ትግራይ በኩል በከባድ መሳሪያ የታገዘ ጥቃት ፈጽሟል ሲሉ ከከሰሱ በኋላ ነው።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በሰሜን ምዕራብ ትግራይ ደደቢት አካባቢ ባሉ የትግራይ ኃይሎች ላይ በከባድ መሳሪያ ለአንድ ሰዓት የቆየ ድብደባ አድርሷል ሲሉም ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
በዚህም ለወራት ታውጆ የነበረው የሰብዓዊ እርዳታ የተኩስ አቁም አዋጅ ተጥሷል ብሏል ከትግራይ ወታደራዊ ዕዝ የወጣው መግለጫ።
ይህን መግለጫ ተከትሎ የጠቅላይ ሚንስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪያት በትግራይ ኃይሎች የተሰነዘረው ክስ ከሰላም ንግግር ለመሸሽ እንደ ምክንያት የቀረበ ነው ብለዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ፕሬስ ሴክሬተሪያት ቢልለኔ ስዩም የሰላም ረቂቅ ሰነዱ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ለተከሰተው ግጭት ሰላማዊ መፍትሄ ለመስጠት፤ በመጪዎቹ ሳምንታት የተኩስ አቁም እንዲደረስ፣ የሰላም ውይይት እንዲሁም ሌሎች በእንጥልጥል የቀሩ ጉዳዮች ደግሞ በብሄራዊ ምክክሩ እንዲዳሰሱ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል።
ሰነዱ መንግስት ግጭቱ በሰላማዊ መንገድ በሚፈታበት ሁኔታ ላይ እያደረገ ያለውን ከፍተኛ ጥረት አመላካች ነው ሲሉ ገልፀዋል።
በሌላ በኩል በትግራይ ክልል መላሶ ግንባታ እና መሰረታዊ ድጋፎች ላይ መንግስት እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
መንግስት ባለሙያ በመላክም ሆነ እዛው ያለውን የሰው ኃይል በመጠቀም በክልሉ መሰረታዊ የህዝብ አገልግሎት ለመመለስ ፍላጎት እንዳለውና ለዚህም ደግሞ አንዳንድ በመሬት ላይ ያሉ ሁኔታዎች እንዲሻሻሉ እንደሚፈልግ ገልፀዋል፡፡
መንግስት በአፍሪካ ህብረት መሪነት በማንኛውም ጊዜና ቦታ የሰላም ድርድር ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል።