Saturday, May 25, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አዲስ በድርና ቁጠባ በተያዘው የበጀት ዓመት አምስት ቢሊዮን ብር ለማበደር ማቀዱን አስታወቀ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ካገኘው 1.2 ቢሊዮን ብር ገቢ ውስጥ 709 ሚሊዮን ብር ያልተጣራ ትርፍ ማግኘቱን ያስታወቀው አዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም በተያዘው የበጀት ዓመት አምስት ቢሊዮን ብር ለማበደር ማቀዱን አስታወቀ፡፡

የብድርና ቁጠባ ተቋሙ በ2014 የበጀት ዓመት ለኢንተርፕራይዞች፣ በቡድን ለተደራጁ ሴቶችና ወጣቶች ባጠቃላይ ለ41,715 ደንበኞቹ 3.72 ቢሊዮን ብር ብድር ማቅረቡ የታወቀ ሲሆን፣ ይህንን መጠን በማሳደግ በአዲሱ የበጀት ዓመት ለ58,750 ተበዳሪዎች አምስት ቢሊዮን ብር የሚያበድር መሆኑ ተገልዷል፡፡

በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ተቋሙ ካቀረበው አጠቃላይ ብድር 3.23 ቢሊዮን ብር የሰበሰበ ሲሆን፣ ይህም በበጀት ዓመት ለመሰብሰብ ከወጠነው 3.39 ቢሊዮን ብር 95.4 ከመቶ ያህሉ የተሳካበት መሆኑ ታውቋል፡፡

ላለፉት 22 ዓመታት የማይክሮ ፋይናንስ አገልግሎቶችን ለአዲስ አበባና አጎራባች ከተሞች ሲያቀርብ የቆየው የአዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም፣ በ2014 የበጀት ዓመት በቁጠባ አሰባሰብ፣ በብድር መስጠትና አሰባሰብ በካፒታልና ትርፍ ከፍተኛ የሚባል ዕድገት ማሳየቱን የተቋሙ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ዳምጠው ዓለማየሁ ተናግረዋል፡፡

ተቋሙ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ከ9.2 ቢሊዮን ብር በላይ የተቀማጭ ገንዘብ መሰብሰቡን የታወቀ ሲሆን፣ አምና ከነበረው አኃዝ ጋር ሲነፃፀር የ156 በመቶ ጭማሪ የታየበት ነው ተብሏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የባንኩ የካፒታል መጠን 4.91 ቢሊዮን ብር መድረሱን ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡

ወደ ባንክ ለመሸጋገር ከሚያስፈልጉት መስፈርቶች አንዱ የካፒታል ጣሪያ እንደሆነ ያስታወቁት አቶ ዳምጠው፣ ይህንን ተቋሙ በዚህ ወቅት እንዳሟላና ከስያሜ ጋር ተያይዞ ብሔራዊ ባንክ ለሰጠው አስተያየት ምላሽ ተሰጥቶ የባንኩን ይሁንታ እየተጠበቀ ይገኛል ብለዋል፡፡

በተያዘው የበጀት ዓመት ተቋሙ ወደ ባንክ የሚያደርገውን ሽግግር ሲጨርስ ከ70 እስከ 80 የሚደርሱ ቅርንጫፎችን በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች እንደሚከፍት የተገለጸ ሲሆን፣ በዚህም አገልግሎቱን ከአዲስ አበባና አጎራባች ከተሞች ውጭ ለማዳረስ የሚያስችለው ይሆናል ተብሏል፡፡

ከማይክሮ ፋይናንስ ወደ ባንክ የሚያደርገው ሽግግር በተያዘው የበጀት ዓመት ዕውን እንደሚሆን የሚጠበቀው አዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም፣ በ2015 የበጀት ዓመት ከቁጠባ 10 ቢሊዮን ብር ማሰባሰብ ዋና ግቡ መሆኑን አስታውቆ፣ ከዚህ በሻገር ወደ ባንክ የሚደርገውን ሽግግር በማጠናቀቅ 50 በመቶ ቅርንጫፎቹን የባንክ ሥራ ለማስጀመር መታቀዱ ተመላክቷል፡፡

ከዚህ ቀደም ተቋሙ የነበሩት ባለአክሲዮኖች አምስት ብቻ እንደነበሩ የሚታወስ ሲሆን፣ ይህንንም በዚህ ወቅት  ወደ 26 በማሳደግ  የተቋሙን ካፒታል 4.91 ቢሊዮን ብር እንዳደረሰ፣ በቀጣይ አክሲዮኖችን ሸጦ የተሻለ ካፒታል የማሳደግ ሥራ እንደሚሠራ ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

አቶ ዳምጠው እንዳስታወቁት፣ ከቴክኖሎጂ ጋር ተያይዞ የኮር ባንኪንግ ሶፍትዌር ግዥ ፈጽሞ 40 ቅርንጫፎች ላይ ትግበራ ያከናወነ ሲሆን፣ በ2015 የበጀት ዓመት 80 በመቶ የሚሆኑ ቅርንጫፎቹን በዚሁ ሲስተም ሥራ የሚያስጀምር ይሆናል፡፡

የብድርና ቁጠባ ተቋሙ ያሉት ቅርንጫፎች 145 የደረሰ ሲሆን፣ የደንበኞቹ ቁጥር በ2013 ዓ.ም. ከነበረበት 350,000 በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት 440,000 መድረሱ ተገልጿል፡፡

በተያያዘም ተቋሙ በ2014 የበጀት ዓመት የነበረውን አፈፃፀም መሰረት በማድረግ ከሌሎች ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ልቀው የተገኙ ናቸው ላላቸው ቅርንጫፎች ነሐሴ 13 ቀን 2014 ዓ.ም. በኢንተር ኮንቲኔንታል ሆቴል ዕውቅና የሰጠ ሲሆን፣ ከዚህ በሻገር በቦርድ አባላት ውሳኔ ለሠራተኞች የሁለት ወር ከግማሽ ቦነስ ክፍያና የሦስት እርከን የደመወዝ ጭማሪ ማድረጉ ታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች