Wednesday, June 12, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ፋና የሚያስተዳድራቸው ሁለት የመዝናኛ ማዕከላት መሬት ለኢንቨስተር ሊሰጥ ነው

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የማዕከላቱ ሠራተኞችና የአካባቢው ማኅበረሰብ ድርጊቱን ተቃውመዋል

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቦሌ ክፍለ ከተማ በፋና ሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ሥር የሚተዳደሩት 17/19 እና 17/23 መዝናኛ ማዕከላትን መሬት፣ ሞል፣ አፓርትመንት፣ እንዲሁም ለባለአምስት ኮከብ ሆቴል ግንባታ፣ ለኢንቨስተሮች ለመስጠት እንደሚፈልግ አስታወቀ፡፡

ማዕከላቱ የሚገኙበት የቦሌ ወረዳ ሦስት የመሬት ልማትና አስተዳደር ጽሕፈት ቤት፣ ፓርኮቹን ለሚያስተዳድረው ለቦሌ ፋና ሸማች በጻፈው ደብዳቤ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ መጋቢት 17 ቀን 2014 ዓ.ም. መሬቱ እንዲሰጠው መጠየቁን አስታውቋል፡፡

ደብዳቤው እንደሚያስረዳው የሁለቱ መዝናኛ ማዕከላት፣ መሬቱ የተፈለገው በኤምደብልዩኤስ (MWS) ትሬዲንግ ለሚገነባ ሞልና አፓርትመንት፣ እንዲሁም በበቀለ ለገሰና አገሩ አበበ ለሚገነባ ባለአምስት ኮከብ ሆቴል ነው፡፡

የቦሌ ወረዳ ሦስት ሥራ አስፈጻሚ አቶ አብርሃም ጀባሞ፣ የሁለቱ መዝናኛ ማዕከላት መሬት በኢንቨስተሮች ለሚደረጉ ግንባታዎች መፈለጋቸውን አረጋግጠዋል፡፡

‹‹እንደ አዲስ አበባ ከተማ፣ በካቢኔው ለኢንቨስተር ለመስጠት የተወሰኑ ቦታዎች አሉ፡፡ ከእነሱ ውስጥ አራቱ የሚገኙት በእኛ ወረዳ ነው፤›› ያሉት ሥራ አስፈጻሚው፣ በወረዳው ውስጥ የተፈለገው መሬት ሁለቱን ማዕከላት እንደሚነካ አስታውቀዋል፡፡

አራት ሺሕ ገደማ አባላት ያሉት የፋና ቦሌ ሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበር በሥሩ 17/17 (ሻላ መናፈሻ)፣ 17/18፣ 17/19 እና 17/23 የመዝናኛ ማዕከላትን ያስተዳድራል፡፡ አሁን መሬታቸው ከተፈለጉት ውስጥ አንዱ የሆነው 17/19 መዝናኛ ማዕከል 7,524 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን፣ 17/23 ማዕከል ደግሞ ከዚህም የበለጠ ስፋት እንዳለው ከማኅበሩ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

ሁለቱ መዝናኛ ማዕከላት በውስጣቸው የቴኒስ ሜዳዎችና የሠርግ አዳራሾች ያሏቸው ሲሆን፣ 17/19 መዝናኛ ማዕከል ብቻ 207 ሠራተኞች አሉት፡፡

የሙዚቃ ኮንሰርቶችን ጨምሮ የተለያዩ ሁነቶች የሚካሄዱበት የፋና ፓርክ የሚተዳደረው በ17/23 የመዝናኛ ማዕከል ሥር ነው፡፡ ለኢንቨስትመንት የተፈለገው መሬት ኮንሰርት የሚዘጋጅበትን ፓርክ የሚነካ ባይሆንም፣ ፓርኩ የሚተዳደርበት ጽሕፈት ቤት የያዘውን መዝናኛ ማዕከል ግን ይነካል፡፡

የወረዳ ሦስት ሥራ አስፈጻሚ አቶ አብርሃም፣ ለኢንቨስትመንት የተፈለገው መሬት የመነሳቱን ጉዳይ ከመዝናኛ ማዕከሉ ኮሜቴዎች ጋር ውይይት እንደተደረገበት ተናግረዋል፡፡ በቀጣይ የአካባቢውን ማኅበረሰብ ለማወያየት ቀጠሮ እንደተያዘም አስረድተዋል፡፡

የፋና ኅብረት ሥራ ማኅበር ቦርድ አመራሮች በበኩላቸው መሬቱ እንደሚፈለግ ከተደረገላቸው ገለጻ ውጪ፣ ከወረዳው አመራሮች ጋር ውይይት እንዳላካሄዱ ተናግረዋል፡፡

ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የኅብረቱ አመራር፣ ‹‹ካቢኔው ቀጥታ ይኼ መሬት ይሰጥ ብሎ አይወስንም፤›› በማለት አካሄዱ ልክ አይደለም የሚል መከራከሪያ አቅርበዋል፡፡ ወረዳው ለማኅበሩ በላከው ደብዳቤ፣ የከተማው ካቢኔ በወረዳ ሦስት ለኢንቨስትመንት የሚሆን ቦታ እንዲሰጥ መወሰኑን እንጂ፣ የ17/19 እና የ17/23 የመዝናኛ ማዕከላት መሬት እንዲሰጥ ስለመጠየቁ እንዳልተጠቀሰ ገልጸዋል፡፡

በአራቱ መዝናኛ ማዕከላት አካባቢዎች የሚገኙ ማኅበረሰብ ተወካዮች ዓርብ ነሐሴ 13 ቀን 2014 ዓ.ም. ለቦሌ ክፍለ ከተማና ለወረዳ ሦስት መሬት ልማትና አስተዳደር ጽሕፈት ቤቶች፣ እንዲሁም ለወረዳው ሥራ አስፈጻሚ ጽሕፈት ቤት በጻፉት ደብዳቤ ተቃውሟቸውን ገልጸዋል፡፡

የሊዝ አዋጅ ቁጥር 721/2011 አንቀጽ አራት ንዑስ አንቀጽ አራትን በመከራከሪያነት ያነሳው የተወካዮቹ ደብዳቤ፣ በዚህ አንቀጽ ላይ መሬት ያለ ጨረታ የሚሰጠው ለመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች እንደሆነ መደንገጉን አስታውሷል፡፡ በዚህ ዝርዝር ውስጥ አሁን በሁለቱ መዝናኛ ማዕከላት መሬት ላይ ይገነባሉ የተባሉት ሆቴልና የንግድ ማዕከል እንዳልተካተቱ ጠቅሰው ተቃውመዋል፡፡

‹‹መሬት በምደባ ያለ ጨረታ የሚሰጥ ቢሆንም እንኳን ባዶ መሬት ተፈልጎ እንጂ፣ የኅብረተሰብ ማዕከል ፈርሶ አለመሆኑ ሊታወቅ ይገባል፤›› ሲሉ በደብዳቤው ላይ አስፍረዋል፡፡

የወረዳው ሥራ አስፈጻሚ አቶ አብርሃም መሬቶቹ ለኢንቨስትመንት የመፈለጋቸው ጉዳይ ላይ ስለተነሳው ተቃውሞ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ፣ ‹‹እስካሁንም ሲሠራበት የነበረ ሕግ አለን፣ መመርያው ካርታ ያላቸው የካሳ ክፍያና ተመጣጣኝ ቦታ እንዲሰጥ ያዛል፣ ጉዳዩ በዚህ መመርያ በኩል ይስተናገዳል›› ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች