Friday, September 22, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከ1.2 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች ለማፍራት ቢያቅድም በኮንቴይነር እጥረት ምክንያት ዕቅዱ መክሸፉን አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ባለፈው ዓመት ከህንድ ኩባንያ ጋር ውል የገባበት የኤሌክትሪክ ኬብል በኮንቴይነር እጥረት ምክንያት አገር ውስጥ ባለመግባቱ፣ በተጠናቀቀው በጀት ዓመቱ የኤሌክትሪክ መስመር የዘረጋላቸው አዲስ ደንበኞች ቁጥር 367 ሺሕ ብቻ መሆኑ ተገለጸ፡፡ ይህ ቁጥር አገልግሎቱ በበጀት ዓመቱ ለማፍራት ካሰበው 1.2 ሚሊዮን አዲስ ደንበኞች ጋር ሲነፃፀር የዕቅዱን 32.84 በመቶ የሚሸፍን ነው ተብሏል፡፡

ከህንድ ወደ ኢትዮጵያ መግባት የነበረበት የኤሌክትሪክ ኬብል፣ አገር ውስጥ ላለመድረሱ የኮንቴይነር እጥረት ምክንያት እንደሆነ ተገልጿል፡፡ የማጓጓዝ ሥራውን የሚያከናውነው የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት በበኩሉ፣ የኮንቴይነር እጥረት በከፊል አጋጥሞ እንደነበር አረጋግጦ፣ ችግሩ ሲቀረፍ  አቅራቢው ድርጅትም ምርቱን በሚፈለገው መጠን ለጉዞ እያዘጋጀ አለመሆኑን  ገልጿል፡፡

ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሽፈራው ተሊላ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የአገልግሎቱ ለደንበኞች አገልግሎት ላይ የሚውለውን የኤሌክትሪክ ኬብል (Concentrate Electrical Cable) ለመግዛት በ2013 ዓ.ም. ሌሰር ፓወር ኤንድ ኢንፍራ (Laser Power and Infra Pvt.Ltd.) ከተባለ የህንድ ኩባንያ ጋር የግዥ ውል ፈጽሟል፡፡ ግዥ የተፈጸመበትን የኤሌክትሪክ ኬብል ለማጓጓዝ 400 ኮንቴይነሮችን እንደሚፈልግና አገልግሎቱ ከህንዱ ኩባንያ 16 ሚሊዮን ዶላር ውል እንደገባ አቶ ሽፈራው ተናግረዋል፡፡

እንደ አቶ ሽፈራው ገለጻ፣ የተገዛው የኤሌክትሪክ ኬብል ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ ተመርቶ ቢያልቅም፣ በወቅቱ የኮንቴይነር እጥረት በማጋጠሙ በምሥራቅ ህንድ ከሚገኘው ኮልካታ ወደብ (Kolkata Port) ማንሳት አልተቻለም፡፡ በዚህም ሳቢያ የኤሌክትሪክ ኬብሉ በመስከረም 2014 ዓ.ም. አገር ውስጥ እንዲገባና በመላ ኢትዮጵያ ለሚገኙ 1.2 ሚሊዮን ለአዲስ ደንበኞች መስመር ዝርጋታ እንዲደረግ የተያዘው ዕቅድ መሳካት እንዳልቻለ አስረድተዋል፡፡

የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት በበኩሉ፣ ‹‹በኮንቴይነር እጥረት ምክንያት የኤሌክትሪክ ምርቱ ወደ አገር ውስጥ መግባት አልቻለም፤›› የሚለውን ሐሳብ ሙሉ ለሙሉ አይቀበልም፡፡

የድርጅቱ የሺፕመንት አገልግሎት ዘርፍ ምክትል ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወንድወሰን ካሳ፣ ‹‹በእርግጥ ከአንድ ዓመት በፊት ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋር ተይይዞ ተግዳሮት ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ቅድሚያ ሰጥተን እየሠራን ነው፤›› ብለዋል፡፡ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ 40 ጫማ ከፍታ ባላቸው 14 ኮንቴይነሮች የኤሌክትሪክ ኬብል የጫነች መርከብ መነሳቷንና በቀናት ውስጥም 14 ኮንቴይነሮች የጫነች መርከብ እንደምትንቀሳቀስ አስታውቀዋል፡፡

‹‹ችግሩ የኮንቴይነር ብቻ አይደለም፣ አቅራቢው ዘንድ ችግር ነበር፡፡ ጭነቱን በሰዓቱ ዝግጁ አላደረገም፤›› ያሉት አቶ ወንድወሰን፣ አሁን በጉዞ ላይ ያለችው መርከብ ከመነሳቷ በፊት የመርከብ ድርጅቱ 50 ኮንቴይነር ቢያቀርብም፣ አቅራቢው ማቅረብ የቻለው በ14 ኮንቴይነሮች የተጫነውን ኬብል መሆኑን አስረድተዋል፡፡

እንደ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገለጻ፣ ድርጅቱ አሁንም ከአቅራቢው ዘንድ መቼ እንደሚነሱ ቀጠሮ ያልተያዘላቸው 22 ባለ 20 ጫማ ኮንቴይነሮች እንዳሉት አክለው፣ ‹‹መቼ እንደሚጫን ማረጋገጫ አልተሰጠንም፣ እነሱ ዝግጁ ከሆኑ ከቀናት በኋላ የምትነሳው መርከብ ላይም መጫን እንችላለን፤›› ብለዋል፡፡

ሪፖርተር ከባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት የተነሳውን ሐሳብ በተመለከተ፣ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሽፈራውን ሐሳብ ለማካተት ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው ሌላ የአገልግሎቱ ኃላፊ በበኩላቸው፣ አቅራቢው ኩባንያው ባለፈው ዓመት አምርቶ እንዲነሳ የጠየቀው ምርት ሳይነሳ ሲቀር ሸጦት ሊሆን እንደሚችል፣ አሁን በቀረበለት ኮንቴይነር ልክ ምርቱን አለማቅረቡ ከዚህ ጋር ሊያያዝ እንደሚችል አስረድተዋል፡፡

የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎቱ በበጀት ዓመቱ ይዟቸው ከነበሩ ዕቅዶቹ ውስጥ ዝቅተኛ አፈጻጸም የተመዘገበው፣ በኤሌክትሪክ ኬብል መዘግየት ምክንያት ያልተሳካው አዲስ ደንበኞችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ የማድረግ ዕቅድ ላይ ነው፡፡ ሌላው ዝቅተኛ አፈጻጸም የተመዘገበው የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነትን ለማሳደግ ተይዞ በነበረው ዕቅድ ላይ ነው፡፡ በ2014 ዓ.ም. 425 አዳዲስ የገጠር፣ ከተሞችና መንደሮች ኃይል እንዲያገኙ ታቅዶ በ204 ከተሞች ዕቅዱን ማሳካት መቻሉ ተገልጿል፡፡ ይህም የዕቅዱን 48 በመቶ የሚሸፍን ነው ተብሏል፡፡

በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ከኃይል ሽያጭ 23.84 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ የነበረው አገልግሎቱ 20.94 ቢሊዮን ብር በመሰብሰብ የዕቅዱን 88 በመቶ መሳካቱን ገልጿል፡፡ አገልግሎቱ በበጀት ዓመቱ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለገዛው ኃይል የፈጸመው ክፍያ 9.92 ቢሊዮን ብር መሆኑን፣ ይህም ሌሎች ወጪዎችን ሳይጨምር 13.92 ቢሊዮን ብር ብልጫ ያለው ገንዘብ ከሽያጭ እንዲሰበስብ እንዳደረገው፣ ሌሎች የገቢ ምንጮችን ጨምሮ በአጠቃላይ ከ27.7 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን ተወስቷል፡፡

የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በአንፃሩ አገልግሎቱ ውድመትና ዝርፊያ፣ እንዲሁም ከኃይል ሽያጭ ይገኝ የነበረ 1.24 ቢሊዮን ብር ኪሳራ እንዳደረሰበት ታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች