Monday, February 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየክልልነት ጥያቄ መበራከት መነሻ ምክንያት እንዲመረመር ተጠየቀ

የክልልነት ጥያቄ መበራከት መነሻ ምክንያት እንዲመረመር ተጠየቀ

ቀን:

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየጨመረ መጣ ያሉትን፣ የክልልነትና ሌሎች የአደረጃጀት ጥያቄች መነሻ ምክንያት እንዲመረመር ጥያቄ አቀረቡ፡፡

ባለፉት አራት ዓመታት በተለይ ከ56 በላይ ብሔረሰቦችን አጠቃሎ ይዞ የነበረው የደቡብ ክልል፣ እንደ አዲስ ‹‹ክልልና የዞን እንሁን›› ጥያቄ እየበረታ መምጣቱን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት ተናግረዋል፡፡

ምክር ቤቱ ሐሙስ ነሐሴ 12 ቀን 2014 ዓ.ም. ባካሄደው 6ኛው የፓርላማ ዘመን፣ አንደኛ ዓመት፣ አንደኛ አስቸኳይ ጉባዔው የቀረበውን የስድስት ዞኖችና የአምስት ልዩ ወረዳዎች በአንድ ክልል እንደራጅ ጥያቄ ተቀብሎ አፅድቋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በጉባዔው ከደቡብ ክልል የመጡ የምክር ቤት አባል፣ ከ2014 ዓ.ም. ጀምሮ እየበረታ የመጣ የመዋቅር ጥያቄ መኖሩን በመግለጽ፣ ‹‹የጥያቄው መነሻ ምንድነው?›› የሚለው ጉዳይ ምክር ቤቱ ሊገመገም እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ሕዝቡ እኩል መልማትንና ተጠቃሚነትን ይፈልጋል ያሉት የምክር ቤት አባላቱ፣ እንደ ሌላው አካባቢ ሁሉ የእነዚህ ሕዝቦች የልማት ጥያቄ እኩል ሊታይ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡ ከደቡብ ኦሞ መምጣታቸውን የተናገሩ ተወካይ ባለፉት ዓመታት በሕገ መንግሥቱና በወረቀት ላይ የሰፈረው የእኩልነት መርህ መሬት ላይ አለመውረዱን ገልጸው፣ የልማት ጥያቄ በሕዝቡ ውስጥ ቁጭት ፈጥሮ ለፀጥታ ችግር ምክንያት መሆኑንና ሕዝቡ አናሳ ብሔር በሚል በአንድ ላይ ተዳምሮ ሊለማ ባለመቻሉ፣ ብቻየን ክልል ሆኝ ብደራጅ ተሰሚነቴ ይጨምራል፣ ትኩረት ይሰጠኛል፣ ተደማጭ እሆናለሁ የሚል ዕሳቤ በመያዝ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በመሆኑም የብሔረሰብ ጠበቃ የሆነው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለእያንዳንዱ ብሔር ተቆርቋሪ ሊሆን ይገባል ያሉት ተወካይዋ፣ አሠራሩ እስካሁን በተመጣበት መንገድ ከሆነ በቀጣይ ሌላ ንትርክ መፈጠሩ አይቀሬ በመሆኑ፣ በእነዚህ አካባቢዎች የሚታየውን የልማት ሁኔታ መንግሥት ሊመረምረው ይገባል ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ ሌላ የምክር ቤት አባል፣ ሕዝቡ በልማት እኩል ተጠቃሚ አለመሆኑን፣ የፍትሐዊነት ችግር፣ የግልጽነት መጓደል በሚሉና መሰል ችግሮች የመደራጀት ጥያቄዎች እየቀረቡ መሆናቸውን በመጥቀስ፣ ችግሩ ሊፈተሽ እንደሚገባ አበክረው ተናግረዋል፡፡

ሌላው የምክር ቤት አባልና በጉባዔው አስተያየት የሰጡት ተወካይ በአደረጃጀት ምክንያት ሕዝብ መፈናቀል የለበትም ብለው፣ ለዚህም የጉራጌ ዞን የክልል እንሁን ጥያቄን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሊመለከተው ይገባል ብለዋል፡፡ የምክር ቤቱ አባሉ አክለውም፣ ‹‹አሁን ካለው ሁኔታ አኳያ ጊዜ ተሰጥቶት ውይይት ቢካሄድበት እኔ በበከሌ የጉራጌ ሕዝብ የተለየ ፍላጎት አለው ብዬ አላሰብም፤›› ብለዋል፡፡ በተለይ በዞኑ ምክር ቤት በሁለት ሦስተኛ አብላጫ ድምፅ የቀረበ በመሆኑ፣ ውሳኔው እንደሌላው ሕዝብ ጥያቄ ሊስተናገድ ይገባል ብለዋል፡፡

በደቡብ ብሔራዊ ክልል የሚገኙ አሥር ዞኖች ከአንድ ዓመት በፊት በክልል ለመደራጀት ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት የጌዶኦ፣ የወላይታ፣ የጋሞ፣ የጎፋ፣ የኮንሶና የደቡብ ኦሞ ዞኖችና የቡርጂ፣ የአማሮ፣ የደራሼ፣ የባስኬቶና የአሌ ልዩ ወረዳዎች ‹‹የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል›› ለመመሥረት ያቀረቡት ጥያቄ በምክር ቤቱ ይሁንታን አግኝቶ፣ በመጪዎቹ ሦስት ወራት በምርጫ ቦርድ አማካይነት ሕዝበ ውሳኔ እንዲሰጥበት በጉባዔው ከተገኙ 123 አባላት በአምስት ተቃውሞ በአብላጫ ድምፅ አፅድቋል፡፡

ባለፉት ሦስት ዓመታት የሲዳማና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል እንሁን ጥያቄዎች፣ በሕዝበ ውሳኔ ፀድቀው ራሳቸውን የቻሉ ክልል መሆናቸው ይታወሳል፡፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አገኘሁ ተሻገር፣ የቀረበው የአደረጃጀት ጥያቄ የዘገየ መልስ እንደተሰጠው በመግለጽ፣ የሕዝብ ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ ባለማግኘታቸው ለግጭት መንስዔ ሲሆኑ እንደቆዩ፣ በአገር ሀብትና ክቡር በሆነው የሰው ልጅ ሕይወት ላይ ከፍተኛ ውድመትና ጥፋት ምክንያት መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በቀጣይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከሕዝብ የሚነሱ ጥያቄዎች ቅድመ ሁኔታቸውን አሟልተው ሲመጡ በጥንቃቄ በመመርመር፣ ምክር ቤቱ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን አቶ አገኘው አክለው ተናግረዋል፡፡

በአዲሱ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልልነት የሚደራጁት ብሔረሰቦች የሕዝብ ውሳኔ ተካሂዶ፣ ውጤቱ ሪፖርት ለፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲቀርብ ምክር ቤቱ ወስኗል፡፡ ቀሪዎቹ  የሀድያ፣ የሀላባ፣ የከምባታና ጠምባሮ፣ የስልጤ፣ የጉራጌ  ዞኖችና የየም ልዩ ወረዳ በነባሩ የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አንድ ላይ ይቀጥሉ ተብሏል፡፡

በተመሳሳይ ዜና የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ውሳኔ ተከትሎ የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ (ወብን)፣ የወላይታ ሕዝብ በክልል ተደራጅቶ ራስን በራስ የማስተዳደር ሕገ መንግሥታዊ መብት ጥያቄ ላይ የተሰጠውን መልስ ኢሕገ መንግሥታዊ ሲል ገልጾታል፡፡ ተቃውሞውን በአዲስ አበባ ለሚገኙ ለአሜሪካ፣ ለእንግሊዝ፣ ለፈረንሣይ፣ ለጀርመንና ለጣሊያን ኤምባሲዎችና ሌሎች ተቋማት ተቃውሞውን ማሰማቱን ለሪፖርተር በላከው መግለጫ አመላክቷል፡፡

የወላይታ ብሔር ራስን በራስ ክልል የመደራጀት ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄ በራሱ ጊዜ የሕዝብ ፈቃድና ስምምነት ሳያገኝ፣ አስቸኳይ ጉባዔ ጠርቶ በድብቅ ከሕዝብ ፍላጎት ውጪ ያለ ሕዝበ ውሳኔ፣ ‹‹በክላስተር እንደራጃለን›› የማለት ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣን ሳይኖረው የሰጠው ውሳኔ ስለሆነ፣ ታርሞ የወላይታ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የሚል አማራጭ የያዘውን ሕዝበ ውሳኔ እንዲደረግ በመግለጫው ጠይቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...