Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

የ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

ቀን:

ተወጥሬ የሰነበትኩበት አንድ የፕሮጀክት ሥራ በመጠናቀቁ ምክንያት ለሦስት የሥራ ቀናት እረፍት ወስጄ ነበር፡፡ ወጥሮ በያዘኝ ሥራ ሳቢያ ብዙ ያመለጡኝ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ክስተቶች ስለነበሩ፣ የትዊተር አካውንቴን ከፍቼ ከአንዱ ወደ ሌላው እየዘለልኩ ወሬ ስቃርም ድንገት አንድ ዓይን የሚስብ ነገር አጋጠመኝ፡፡ ‹‹The 3Bs Brain, Bile and Blood›› የሚል ርዕስ ያለውን የጽሑፍ ማስፈንጠሪያ ስጫነው፣ በቅርቡ ከሴት ልጁ ጋር ሆኖ የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን የጎበኘ ሰው ጽሑፍ ተንጣሎ ይታያል፡፡ ግለሰቡ ምን ገጥሞት ይሆን በማለት ጽሑፉን በከፍተኛ ትኩረት አነበብኩት፡፡ ጸሐፊው ቀለል ያለ ኑሮ የሚኖሩትንና በቀላል አቀራረባቸው ያስደመሙትን ኢሳያስ፣ ከኤርትራ የነፃነት ትግል ጀምሮ እስካሁን ከምዕራብ ኃይሎች ጋር ዓይንና ጫና ሆነው የዘለቁበትን ታሪክ ተንትኖታል፡፡ ሰውዬውን ለማግዘፍ ሳይሆን እውነቱ ይህ ነው ያለውን የሰውየውን ሰብዕና ካላቸው ጂኦ ፖለቲካዊ ዕውቀትና የዓለም አረዳድ ጋር በሚገባ ሰድሮታል፡፡

ከጽሑፉ እኔን የሳበኝ አንድ ነገር ነበር፡፡ እሱም ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ነገሩኝ ያለው፣ ‹‹Every human being is blessed with three very important soft powers that he metaphorically coupled with three words that start with “B”: the Brain (ሓንጎል), the Bile (ሓሞት) and Blood (ደም). The Brain with its white color and complex shape stands for cognitive ability and intellect, the Bile with its green color and bitter taste stands for guts and bravery, while the Blood with its red color represents energy.›› ነው፡፡ አንድ ሰው እነዚህን ሦስት ነገሮች (soft powers) በማዋሃድ መጠቀም ከቻለ በሕይወቱ ውስጥ ልዩነት መፍጠር ይችላል እንዳሉትም ጸሐፊው አብራርቷል፡፡

እኔን ይህንን ምሳሌ ያመጣሁት የባለታሪኩንና የጸሐፊውን ቆይታ በዝርዝር ለማቅረብ ሳይሆን፣ ትምህርት እስከተገኘበት ድረስ ከየትም ቢሆን በአጋጣሚ ጭምር የሚገኝ ነገርን ማብላላት አስፈላጊ ነው በማለት ነው፡፡ ብዙዎቻችን ፈጣሪ የሰጠን አዕምሮ እያለን ከምንጠቀምበት ይልቅ የሌሎች መጠቀሚያ እንሆናለን፡፡ ከሌሎች ባልደረቦቻችን ጋር ሆነን አውጥተንና አውርደን መወሰን ሲቻለን፣ የሌሎች ውሳኔ ጥገኛ እየሆንን ራሳችንንም ሆነ በዙሪያችን ያሉትን እንበድላለን፡፡ የራሳችንን ዕምቅ አቅም አውጥተን ለመጠቀም ዳተኛ ሆነን ለጠባቂነት እንዳረጋለን፡፡ ዙሪያችንን የሞላውን የተፈጥሮ በረከት በመጠቀም ማደግ ሲገባን፣ በደካማነታችን ምክንያት ምፅዋት ጠባቂ መሆናችን ያሳዝናልም ያሳፍራልም፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

አለቃ ገብረ ሐና የሚባሉ ከዘመኑ ሰው በአዕምሮአቸው የመጠቁ ነገር አዋቂና ምሁር ብዙ ጊዜ በምሳሌ ወይም በተረት መልክ ስማቸው ሲነሳ እናውቃለን፡፡ አለቃ ከሚደነቁባቸው በርካታ ነገሮች መካከል አንደኛው ነገር አዋቂነታቸውና ተቺነታቸው ነው፡፡ እኚህ የ19ኛው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያዊ ምሁር አንድ ቀን ቤተ መንግሥት ውስጥ ድል ያለ ድግስ ተሰናድቶ፣ እሳቸውም በክብር እንዲገኙ ተጠርተው ሥፍራቸውን ይዘው ተሰይመዋል፡፡ እየተበላና እየተጠጣ ሳለ አለቃ ግን በተከፋ ስሜት ዙሪያቸውን ሲያዩ አፄ ምኒልክ አይተዋቸው ኖሮ ያስጠሩዋቸዋል፡፡ አለቃም ንጉሠ ነገሥቱ ያሉበት ዙፋን ዘንድ ደርሰው እጅ ነስተው ይቆማሉ፡፡

አፄ ምኒልክም፣ ‹‹ገብረ ሐና ምን ሆነው ነው በተከፋ ስሜት ውስጥ ሆነህ ያየሁህ…›› ብለው ሲጠይቋቸው፣ ‹‹ጃንሆይ ይህ ሁሉ ግብር ላይ የታደመ ሰው እንደ አበላሉና አጠጣጡ ሥራም ላይ ቢበረታ ኢትዮጵያ ከእንግሊዝና ከፈረንሣይ እኩል ትሆን ነበር…›› ሲሏቸው፣ ‹‹ገብረ ሐና የአገሬ ሰው ያንተን ጭንቅላት ቅንጣት ያህል ቢኖረው ኖሮ ያልከው ይሆን ነበር፡፡ ግና አታይም እንዴ ለምን ሥልጣኔ ከአውሮፓ ይገባል እያለ ይታገለኛል…›› ብለው ምሬታቸውን ገለጹላቸው ብሎ የነገረኝ አባቴ ነበር፡፡ ለምሳሌ ስልክ፣ ባቡር፣ ወፍጮ፣ መኪና፣ ሲኒማ፣ ወዘተ ኢትዮጵያ ሲገቡ የነበረውን ትግል የሚያስታውስ ይመስለኛል፡፡

አሁንም ብዙ የሚያታግሉ ነገሮች ያሉ ይመስለኛል፡፡ ሁሉንም ነገራችንን ከፖለቲካ ጋር ለውሰነው ነው መሰል ጠቃሚ ነገሮችን ሳይቀር እንጠላለን፡፡ ለምሳሌ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የማልስማማባቸው ጉዳዮች ይኖሩኛል፡፡ ነገር ግን በከተማ ግብርና ቆስጣ፣ ሰላጣ፣ ጎመን፣ ቲማቲም፣ ድንች፣ ሽንኩርትና የመሳሰሉ ምርቶችን አምርቶ መጠቀም የሚጠቅመው እኛን በመሆኑ ተቀብለን ተግባራዊ በማድረግ ከቤተሰብ አልፎ ገቢ አመንጪ ሆኖልናል፡፡ ችግኝ መትከልን የመሰለ የወደፊት የአገር እስትንፋስ ማራከስም ተገቢ አይደለም፡፡ የመስኖ ስንዴ ኢትዮጵያን በዓለም ሲያስጠራት ጠላት ይመስል ዓይንን ማቅላት አስነዋሪ ነው፡፡ ከዚህ ዓይነቱ ዕሳቤ በመውጣት ድጋፍ ለሚቸረው በቂ ዕገዛ ማድረግ፣ አላስፈላጊ ላልሆኑ ድርጊቶች ደግሞ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ የሰላ ትችት ማቅረብ ይጠቅማል፡፡ ከንቱ ወሬ ፋይዳ የለውም፣ ያስንቃል፡፡

ኢትዮጵያ የጣሊያን ወራሪን ዓድዋ ላይ አንኮታኩታ የአውሮፓ ቅኝ ገዥዎችን ካሳፈረች በኋላ፣ ለ40 ዓመታት ከነበረችበት ፈቀቅ የሚያደርጋት ሥራ ባለመከናወኑ የደረሰው መከራ አይረሳም፡፡ እኛ በዓድዋ ጦርነት ጊዜ ከጣሊያን የማረክናቸውን አሮጌ መድፎችና ጠመንጃዎች ሳንቀይር አዲሱ የፋሽስት ጣሊያን መንግሥት ግን በዘመኑ በጣም የሠለጠነ ሠራዊት፣ ዘመናዊ መድፎች፣ ታንኮች፣ የጦር አውሮፕላኖችና የመርዝ ጋዝ ጭምር ነበር ይዞ የዘመተብን፡፡ ይህንን የተደራጀ ኃይል መቋቋም ባለመቻሉ ምክንያት ፋሽስት ጣሊያን ለአምስት ዓመታት ኢትዮጵያን መያዝ ችሎ ነበር፡፡ ክብርና ምሥጋና ለጀግኖቹ ኢትዮጵያውያን ይሁንና በከፍተኛ መስዋዕትነት ነፃነት ቢመለስም፣ እኛ ግን በርካታ ዓመታትን በከንቱ አባክነናል፡፡ አሁንም በጣም ብዙ ይቀረናል፡፡ ለዚህም መሰለኝ ከተኛንበት ለመንቃት ከፈለግን ከፍተኛ የሆነ ዕውቀት፣ የዓላማ ፅናትና ኃይል የሚያስፈልገን፡፡ አገር በወሬ የትም አትደርስም፡፡

(ምናሴ ሁነኛው፣ ከሳሪስ አቦ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...