Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የኢኮኖሚ ዕድገቱ የዜጎችን ኑሮ ያሻሽል!

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከስድስት በመቶ በላይ የሚመዘገብበት እንደሆነ በመንግሥት በኩል እየተነገረ ነው፡፡ ገለልተኛ የሚባሉ አካላት ትንበያም ቢሆን ይህንኑ የሚያመላክቱ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ የኢኮኖሚውን ዕድገት የሚያመላክቱ አንዳንድ አፈጻጸሞችም ይህንኑ የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ለምሳሌ የአገሪቱ የወጪ ንግድ ከ4.6 ቢሊዮን ዶላር በላይ ያስገኘ መሆኑ አንዱ ነው፡፡ የአገሪቱ የፋይናንስ ተቋማት ወደ ኢኮኖሚው ያሠራጩት የብድር መጠንና ያሰባሰቡት የብድር መጠን ከተጠበቀው በላይ መሆኑን በራሱ የሚያሳየው ነገር አለ፡፡ የብር የመግዛት አቅም መዳከም እንደተጠበቀ ሆኖ መንግሥት ያሰባሰበው የግብር መጠን በተከታታይ ዓመታት ከተገኘው ገቢ ብልጫ ያለው ነው፡፡ ይህ ገቢ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን መሠረት አድርጎ የተገኘ ገቢ በመሆኑ በጥቅል አገራዊ ኢኮኖሚ ዕድገት ቁጥር ጥያቄ ካላስነሳ በቀር ዕድገቱ አለ ለማለት የሚያስችል ተጨባጭ መረጃዎች መኖራቸውን ያረጋግጣል፡፡

ይሁን እንጂ ይህ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት አሁን ካለው ሥር እየሰደደ ከወጣው የኑሮ ውድነትና የዋጋ ንረት አንፃር ስንመዝነው ብዥታ መፍጠሩ አይቀርም፡፡ በመንግሥትም ደረጃ ቢሆን ለዓመታት እየተንከባለለ የመጣው የዋጋ ንረት በሚፈለገው ደረጃ ለመቆጣጠር አለመቻሉን አምኗል፡፡

ስለዚህ በዚህ ወቅት ስለ አገር ኢኮኖሚ ዕድገትና ብልፅግና ስናወራ ቀድሞ ጥያቄ የሚሆንብን በዚህ ለከት ባጣው የኑሮ ውድነትና የዋጋ ንረት መካከል ሆነን ኢኮኖሚያችን አደገ መባሉ ነው፡፡

እንደ ተራ ሸማች ይህንን ማሰባችን ግድ ነው፡፡ አገር ማደጓና መመንደጓም እንደ መልካም ዜጋ ሆነን ስናየው እሰየው ማለታችን አይቀርም፡፡ ቀና ዜና የአገርን ዕድገት ሁሌም ይሻል፡፡ ነገር ግን ይህ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የበለጠ ትርጉም የሚኖረው ልጓም ያጣን የዋጋ ንረት መቆጣጠር ሲቻል ነው፡፡

ዜጎች አሁን እየታየ ያለውን የዋጋ ንረት ለመቋቋም ተስኗቸዋል፡፡ በሰበብ አስባቡ በየዕለቱ በሚባል ደረጃ የሚታየው የሸቀጥና የምርቶች ዋጋ ጭማሪዎች ከአቅም በላይ ሆነዋል፡፡ አብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍል ከዓመታት በፊት በቋሚነት ያገኘው የነበረ ገቢ ላይ ቆሞ ሳለ የዋጋ ንረቱ ፍጥነት ከሚያገኘው ገቢ ጋር የሚመጣጠንለት አልሆነም፡፡

ከሸመታ ባሻገር በየትኛውም መስክ የሚፈለገውን አገልግሎት ለማግኘት የሚጠየቀውንም ዋጋ ስናስብ ፈቀቅ ያላለው ገቢ የሚቋቋመው አልሆነም፡፡ ችግሩ እየሰፋ መጥቷል፡፡ በተለይ ተቀጣሪዎች መሽቶ በነጋ ቁጥር በአዳዲስ ዋጋ የሚቀርቡለትን ምርቶችና አገልግሎቶች ለመጀመር ተቸግሯል፡፡ የአዲስ አበባ አስተዳደር አከራዮች የቤት ኪራይ ዋጋ አትጨምሩ ብሎ በተከታታይ ያስተላለፈው ማስጠንቀቂያ እንኳን በአግባቡ ባለመተግበሩ የቤት ኪራይ ዋጋ ያለ ከልካይ እየጨመረ መምጣቱም ወር ጠባቂ ደመወዝተኛ ችግር ከድጡ ወደ ማጡ እንዲሆን አድርጓል፡፡

ስለዚህ ኢኮኖሚያዊ ዕድገታችን የበለጠ ትርጉም እንዲኖረው ከተፈለገ ይህንን የብዙዎች ችግር የሆነውን የኑሮ ውድነትና የአገልግሎት ዋጋ ንረት መቆጣጠር ግድ የሚል መሆኑን መግለጽ ተገቢ ነው፡፡

ሌላው ቀርቶ መረን እየለቀቀ ያለውን የመኖሪያ ቤቶች ዋጋ ንረት አደብ ማስገዛት የሚቻልበት ዕድል እያለ በዚህ ዕድል አለመጠቀም ትል ግድፈት ነው፡፡

መንግሥት እንዲህ ያሉ የሕዝብ ሸክም እየሆኑና እያማረሩ ያሉ ጉዳዮችን ልጓም እንዲኖረው የሚያስችል አቅም እያለው አልተጠቀመበትም ወይም አልሠራበትም፡፡  

በእርግጥ ችግሩ የአንድ የኢትዮጵያ ባይሆንም የዋጋ ንረቱ ከሕዝብ አቅም በላይ ሆኖ የበለጠ ችግር እንዳይኖር ቢያንስ ያሉትን ሕጎች በማስከበር እንዲሁም ወሳኝ የሚባሉ ምርቶችን በአዋጅ በቁርጥ ዋጋ እንዲሸጡ በማድረግ ችግሩ ከዚህም በላይ ሰፍቶ ሌላ ጦስ እንዳይመዘዝ ማድረግ ይቻል ነበር፡፡ ግን ማን ይሥራ?

ከአገልግሎት አሰጣጥ አንፃርም የገዛ መብቱን ለመጠቀም በየቦታው የነጠቃ ያህል እየተጠየቀ ያለው ጉቦም የዚሁ አካል ነው፡፡ ሌብነት ሰፍቶ የሚታይባቸው አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ውስጥ አገልግሎት ለማግኘት በሃላል ጉቦ እየተጠየቀ ሕዝብ ሲማረር መንግሥት አሁንም ዛቻ ላይ ነው፡፡  

የኑሮ ውድነት በመሆኑ ዜጋ በሚከፍለው ታክስ ደመወዝ የሚቆረጥላቸው ሹመኞች በሃላል ጉቦ ሲጠየቅ ያሳዝናል፡፡

ይህ ማለት ሕገወጥነት እንዲሰፋ እንደመፍቀድ ይቆጠራል፡፡ በአደባባይ ሌብነት ላይ ዕርምጃ ይወሰዳል ተብሎ እየተስፋፋ ጭራሽ ነገሮች ሲባባሱ ማየት ያሳዝናል፡፡

በመሆኑም መንግሥት የኑሮ ውድነቱንና ሌብነቱን የሚቆጣጠርበት ሥልት እስካልነደፈ ድረስ ሕዝብ እየተበደለ የዋጋ ንረቱ እያሻቀበ መቀጠሉ አይቀርም፡፡

እውነት እንነጋገር ከተባለ የዋጋ ንረቱ ቢያንስ ባለበት ለማስቆም በሕግ ኃላፊነት የተሰጣቸው የመንግሥት ተቋማት ሥራቸውን በአግባቡ ቢሠሩ ከሙስና በፀዳ ሁኔታ ኃላፊነታቸውን ቢወጡ ችግሩን ረገብ ማድረግ የሚችሉ ቢሆንም ሕገወጥ ተግባራት እንዲበራከቱ በራፍ በመክፈታቸው ችግሩ እየሰፋ መጥቷል፡፡

ስለዚህ የዋጋ ንረት መንስዔዎች ብዙ ቢሆኑም እንዲሁም አሁንም የሚወሰን የዋጋ ንረት ለማስተካከል የማይቻል ቢሆንም ወግ ያለው የግብይት ሥርዓት እንዲፈጠር በማድረግና እንዲሁም ወሳኝ የሚባሉ ምርቶችን ዋጋ መቁረጥ፣ የቤት ኪራይ ዋጋ አማካይ ተመን ማውጣትና የተከራይ አከራይ ሕግን ሥራ ላይ ማዋል አንድ መፍትሔ ይሆናል፡፡

የዋጋ ንረቱን ለመቆጣጠር አለመቻሉን የሚገልጽልን መንግሥት ለምን እንዳልቻለ ፈትሾና ችግሩን ለይቶ የተሻለ መፍትሔ መለፈግ አለበት፡፡ የኢኮኖሚ ዕድገታችንም የኑሮ ውድነትን የሚታደግ መሆኑን ማረጋገጥም ይገባል፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት