በያሬድ ኃይለ መስቀል
የመጽሐፉ ደራሲ ሰለሞን በላይ ፋሪስ (ዶ/ር) ሲሆኑ፣ መጽሐፉ 180 ገጾች አሉት። በመጀመሪያ ከመጽሐፉ ጀርባ ጀምሮ ወደ 65 የሚደርሱ ማጣቀሻ ጽሑፎች አሉት። ስማቸውን ወረድ ብዬ ሳይ በጣም የማከብራቸውን እንደ ተከስተ ነጋሽ (ፕሮፌሰር) ያሉ ኤርትራ ተወልደው በጠንካራ ኢትዮጵያዊነት የሚታወቁ ምሁር ናቸው። ቀድመውም የኢትዮጵያ ትምህርት ችግር እንዳለበትና ችግር ፈቺ ሳይሆን ችግር ፈጣሪ ነው ብለው የተቹ ናቸው። ወንድሜ ሰለሞን (ዶ/ር) የእነሱን ፈለግ መከተሉ ትልቅ ኃላፊነት በትከሻው ላይ እንደጣለ ተሰማኝ። ከዚያም ከእነ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት አንስቶ እስከ ገጣሚና ወግ አዋቂ ‹‹ደብተራ›› በዕውቀቱ ሥዩም ድረስ ተጣቅሰዋል። ይህ በፍጥነት ወደ ንባቡ አስገባኝ። ይሁንና ሥጋት ነበረኝ።
ይህ ለመመረቂያ ጽሑፍ የተዘጋጀ ነው። የመመረቂያ ጽሑፍ ደግሞ በሕግና በአጥር የተከፋፈለ ደረቅ እውነታ ነው። እንኳን ላልተማረና ኑሮውንም ማስተማር ላደረገ ፕሮፌሰርም አሰልቺ ነው። ስለዚህ ይህ ንባብ ይከብደኝ ይሰለቸኝ ይሆን ብዬ ራሴን ጠየቅኩ።
የቋንቋ ችሎታ
ጽሑፉ የዶክትሬት መመረቂያ የሳይንሳዊ ምርምር ትርጉም ይሁን እንጂ፣ ወደ አማርኛ ሲመለስ እንደ አዲስ እንደተጻፈ መረዳት ይቻላል። ማንም ማንበብና መጻፍ የሚችል ሁሉ አንብቦ ሊረዳው በሚችል ቋንቋ፣ ትርክት፣ ቀልድና ቁም ነገር የተሞላ ነው። ሲጀምር በዕውቀቱ ሥዩም ግጥም ይጀምራል፡፡
‹‹ህልም አለህ ይላሉ
ራዕይ ያዘለ
ኮከብ አለህ አሉ
ትንቢት የታደለ
ህልምህን ንገረኝ
ኮከብህን አሳየኝ
ተርጉሜው ልጽናና
መነሻዬን ልወቅ መድረሻዬን ላጥና
ባንት ዕጣ ፈንታ ውስጥ ርስት አለኝና››
መጽሐፉን ጠበቅ አድርጎ ለያዘው በአንድ ቀን ወይም እንደ እኔ ላለ ዳዊት ሳይደግም ዘመናዊ ትምህርት ለጀመረ አንባቢ ደግሞ ሁለት ቀን ቢወስድ ነው።
መጽሐፉ ብዙ የሚገርሙና ራሳችንን ቆም ብለን እንድንመረምር ‹‹አሃ›› እንድንል የሚያስችል ነው። ከአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እስከ ‹‹ደብተራ›› ይቅርታ ‹‹ፕሮፌሰር›› ቢያነበው በቀላል መረዳት በሚያስችል አማርኛ ነው የተጻፈው።
የመጽሐፉ ጭብጦች
ትምህርት በኢትዮጵያ የሺሕ ዓመት ታሪክ አለው። ያለ ትምህርትና ዕውቀት አክሱምም፣ ላሊበላም፣ ፋሲለደስ፣ የሐረር ግንብ አልተገነባም። ይሁንና የፈረንጅ ወይም ዘመናዊ ትምህርት በአፄ ምንሊክ ጊዜ ከገባ ይኸው መቶ ዓመት አለፈው። ይሁንና ሰለሞን (ዶ/ር) ‹‹የተማሩ ኢትዮጵያውያን አገሪቷን ለማሳደግ ሊረዳቸውን የሚችለውን አገር በቀል መንፈሳዊ ቁሳዊ ዕውቀት በመነጠቃቸው›› አገር ማልማት ቀርቶ ሦስት ጊዜ መመገብ አልቻሉም የሚል ጥያቄ ያነሳል?
አባቶቻችን በኩራት የጠበቋቸውንና የተናገሩባቸውን መሠረታዊ መንፈሳዊና ባህላዊ እሴቶች የአሁኖቹ ምሁራን የት አደረሷቸው ብሎ በመጠየቅ ነው። ልጆች በአፍ መፍቻ ቋንቋ ይማሩ እያልን በሌላ በኩል ደግሞ የቤተሰቦቻቸውን እምነት፣ ሐሳብ፣ ባህልና አኗኗር እንዴት ከዘመናዊ ትምህርት ጋር አይቀላቀል እንላለን?
ሕይወት ሁሉ የመንፈሳዊና yቁሳዊ ውጤት ነው። ታድያ በሴኩላሪዝም (ዓለማዊ) ምክንያት የኢትዮጵያዊውን መንፈሳዊ ዕውቀትና ሀብት ወደኋላ ጥለን እንዴት መራመድ እንችላለን?
ከኢትዮጵያ ሕዝብ 97 በመቶ የሚሆነው ሃይማኖታዊና መንፈሳዊ ሕይወት አለው። መንፈስና ሥጋ ደግሞ ከዚያ አልፎ ተዋህዶ (Dualism) የሚል የጠለቀ እምነትና ፍልስፍና ያለበት አገር ነው። ስለዚህ ቁሳዊ ብቻ ብሎ ማስተማር እንዴት ዕድገት ሊያመጣ ይችላል የሚል ጥያቄዎች ያነሳል። መንፈሳዊ ሀብታችንን ይዘረዝራል። ለምሳሌ መንገደኛ በማያውቀው ጎጆ ሄዶ ያንኳኳል። ‹‹የእግዚአብሔር እንግዳ ነኝ አሳድሩኝ›› ይላል። ያስገቡታል፣ እግሩን አጥበውና እራት አብልተው ያሳድሩታል።
ኢትዮጵያዊ ክፉ መሥራት በልቡ ቢመጣም እንኳን ‹‹እሱ ባያየኝ አምላክ ያየኛል›› ብሎ ከክፉ ተግባር ራሱን ያቅባል። ይህንን እሴት ከጣልነውና በቁስ ላይ ከተንጠለጠልን ሰዎች ማንም በማያያቸው ሰዓት… ሌሎችን ከመንጠቅ አይቆጠቡም?
ጀግናና ቅዱስነት በሚለው ክፍል ኢትዮጵያውያን ‹‹ጀግናና ቅዱስ›› የሚሉ ትምህርቶችና እሴቶች አሉዋቸው፡፡ ሁለቱም አንድ ናቸው። ራስን ለሌሎች አሳልፎ ከመስጠት ከሚመጣ ነፃ ስሜት ነው።
ሪቻርድ ፓንክረስት ‹‹ኢትዮጵያዊያን ሽንፈትን አይቀበሉም››፣ በዚህ የተነሳ ‹‹ወራሪዎች ለማጥቃት በሞከሩ ቁጥር ተሸንፈዋል››፣ ‹‹የኢትዮጵያ ነፃነት ተዋጊዎች ተስፋ አይቆርጡም፣ ተስፋ አለመቁረጥ፣ አለመሸነፍ›› የቁሳዊ አቅም ነፀብራቅ ሳይሆን፣ የመንፈሳዊ ጥንካሬ ነው። ስለዚህ ቢሸነፉም፣ ‹‹ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች›› መዝሙረ ዳዊት 68:13 ብለው ይቀጥላሉ። ‹‹ያሉት ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፉ›› ይላሉ፡፡ በሕግ አምላክ በማለት የነጠላ ጫፋቸውን አስረው ወደ ዳኛ እንዲሄዱ ከተደረገ ፈተው አይጣሉም።
ጽላተ ሙሴ፣ የአክሱም ሐውልት፣ ላሊበላ፣ ግማደ መስቀል፣ የመጀመርያው የሙስሊሞች ስደትና የኢትዮጵያውያን ወንድማዊ አቀባበል ትርክቶች የሞራል ልዕልና አስተምህሮዎች ናቸው (Ethics and Moral Philosophy)፡፡ እውነት፣ ታጋሽነት፣ ታማኝነት፣ ርህራሔ፣ አክብሮት፣ ጠንክሮ መሥራት፣ ‹‹በዓርያ ሥላሴ አምሳልና ተግባር መፈጠር›› (Equality of the Human Race) ናቸው፡፡
አለባበሳችንና የሕይወታችን አመራር ሃይማኖታዊ መሠረት አለው፡፡ ይህ መሠረት ደግሞ እንደ የጋራ ፍቅርና መከባበር፣ ጀግንነት፣ አገር ወዳድነትና የመሳሰሉት ባህላዊ ተግባሮች በቀድሞው ሃይማኖታዊ ልምምዶች ላይ ማደጋቸው ጥርጥር የለውም። ሠርግ፣ ቤተ ክርስቲያን፣ ጦርነት ሲኬድ የሚለበሰው ይለያያል።
የኢትዮጵያ መንፈሳዊና ባህላዊ እሴቶች የሚመነጩት የእግዚአብሔርን መኖር ከማመንና ፈቃዱን ለመፈጸም ካለ ፍላጎት ነው።
የኢትዮጵያ ሥልጣኔ ከመንፍሳዊና ከሳይንሳዊ ትስስር እንጂ መነጣጠል አይደለም። ላሊበላ የተገነባው ለፈጣሪ ክብር ቢሆንም በሳይንስ ነው። ያለ ጂኦሎጂ፣ ኢንጂነሪንግ፣ ካለብረት ጥንካሬ፣ ያለ ሒሳብ፣ ያለ መለኪያ፣ በአጠቃላይ ያለ ሳይንስ ዕውቀት አልተገነባም። ሃይማኖት የመንፈሳዊ መነሳሳቱን ብቻ ሳይሆን ሳይንሳዊ አቅሙንም የመመርመር መብት ይሰጣል።
‹‹የዘርዓያዕቆብ ዳግም ውልደት›› በሚለው ወግ ውስጥ እንደታየው፣ ኢትዮጵያን በመንፈሳዊውና በቁሳዊው መካከል ያለውን ግንኙነት ይገነዘባሉ። የኢትዮጵያውያን ፍልስፍና መነሻ፣ ለምናውቀውና ለምናደርገው ነገር ሁሉ መሠረቱ መንፈሳዊነትና ጥብቅ እምነት መሆኑን ከሚረዱት ፈላስፎች ዘርዓያዕቆብ›› አንዱ ነው።
መደምደሚያው በዚህ ረገድ የምንተገብረው፣ ተያያዥነት ያለው የኢትዮጵያ መለኮታዊ ሳይንስ በእነዚህ የተለያዩ ደረጃዎች ስላለው፣ ኃይልና በመካከላቸው ስለሚኖረው ሚዛንና ስምምነት የሚያጠና ሲሆን ይገባናል፡፡
ይህ መጽሐፍ የትምህርት ፖሊሲያችንን እንድንመረምር የሚያስገድድ የፍልስፍና መጽሐፍ ነው።
ቁሳዊ ድህነታችን የመንፈሳዊ እሴታችንን አለመጠቃማችን ነው። ሥርዓተ ትምህርት በአጭሩ ፍልስፍና ነውና የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅት ከሁሉም በላይ አንደኛ ርዕዮተ ዓለም የሚያደርገው፣ ከለጋ ሕፃን ጀምሮ የአገሪቱ ዜጎች እንዲያልፋበት የሚደረግ ቁርባን ስለሆነ አብሮ አድጎ አብሮ የሚያረጅ ማንነት የሚፈጥር መሣሪያ በመሆኑ ነው
እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን ዘመናዊ ትምህርትና አገራችን ገብቶ የማያልቅ ጦሱን እስከ ተክል ድረስ አስደናቂ ጠለቅ ያለ ባህላዊ ትምህርት ነበረን። ኢትዮጵያ ደክማ አስተማርኩ የምትላቸው ትውልዶች ከድህነት ሳይታደጓት በየአገሩ እንደ አሸዋ ተበትነው የሰው አገር አገልጋይ ሆነዋል።
ምክር
ለረዥም ዓመታት አብረው በኖሩት በኖሩዋቸው ሃይማኖታዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ሕይወት የተነሳ ኢትዮጵያውያን በታሪካዊ ክፍተኛ ውጤት ያስገኙላቸው አገር በቀል መንፈሳዊና ባህላዊ ዕውቀቶች አሏቸው። እነዚህ መንፈሳዊኔ ባህላዊ ዕውቀቶች ተበጥረው ታውቀው ለትምህርት ሥር ዓይነት ሊዘጋጁ ይችላሉ፡፡ ከእነዚህም ዕውቀቶች ለአገራችን የሚስማማ የሳይንስ ትምህርት ለመፍጠር በሚችል ሥልታዊ በሆነ ሁኔታ፣ በሥርዓት ትምህርቱ ውስጥ ሊካተት ይችላልን? የኢትዮጵያውያን መንፈሳዊና ባህላዊ እሴቶች ወደ ሳይንስ ሥርዓተ ትምህርት ማምጣት ነው።
ተዋህዶ (Dualism)፣ ዕውቀት የሚመነጨው ከእግዚአብሔር ነው። ሰው ሥጋና ነፍስ ነው። ትምህርት ይህንን ተፈጥሮ ማገናዘብ አለበት። በእርግጥ ማንነትን ከመረዳት የበለጠ ምን ጥልቅ ቅውነተኛ ዕውቀት አለ? የራሱን ማንነት ያወቀ ሰው ዓለምንና ፈጣሪውን ማወቅ ይችላል፡፡ የምዕራባውያን ትምህርት አግባብነት ለሌለው የባሪያ ንግድ፣ ጦርነት፣ ለቅኝ ግዛት፣ ለባሪያ ፍንገላም አስተዋጽኦ አድርጓል
አሁን ያለው የትምህርት ዓላማዎችና ፍላጎቶች ከምዕራባውያን አገሮች ፍላጎቶችና ፍልስፍናዎች ነው። የምዕራባዊ ትምህርት የእነሱን የበላይነትና የእኛን የበታችነት የሚያሰርፅ ነው። ትምህርት ችግር ለመፍታት ነው፣ ታዲያ ለምን ችግራችን በዛ?
‹‹ስትሄድ ስከተላት››
ሳይንስ በራሱ ዓላማና ግብ የለውም። ሳይንስን የሚያውቁትና የሚጠቀሙበት ናቸው ለሳይንስ ዓላማ የሚሰጡት። ስለዚህ ዕውቀት አንቱ ለመባያ ሳይሆን የችግር መፍቻ እንዲሆን የራሳችንን የትምህርት ዓላማ መፍጠር አለብን። ይህንን ለማድረግ ደግሞ መንፍሳዊ እሴቶች ማስተማር የግድ ይላል። ሥነ ምግባር ያላቸው ሰዎች ብቻ ናቸው ሥነ ምግባራዊ ሳይንስ የሚፈጥሩት።
ስለዚህ ሳይንሳዊና መንፈሳዊ ሒደቶችን ጎን ለጎን መውሰድ አለብን። ዘመናዊነት ማለት መጀመርያ ራስን ማጥናትና ማወቅ ነው። ከዚያ እንደ ኢትዮጵያ የመሰለ ብዙ አቅም ያለው አገር ዓለም ዕውቀት ገበያ ተሳታፊ መሆን ትችላለች፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የዋይኤችኤም ኮንሰልቲንግ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ፣ ዓለም አቀፋዊ የፕራይቬት ኢኩቲ ኢንቨስተር በማምጣት የኢትዮጵያን ኩባንያዎች ለኢንቨስትመንት በማብቃት የማማከር ሥራ በማከናወን ላይ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡