Tuesday, December 10, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የህንዱ ሥጋ አምራች ኩባንያ ከወጪ ንግድ 37 ሚሊዮን አገኘሁ አለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

መንግሥት የሥጋ ወጪ ንግድ አፈጻጸም አነስተኛ ነው ብሏል

በኢትዮጵያ ሁለት ድርጅቶችን የሚያንቀሳቅሰው የህንዱ ግዙፍ ሥጋ አምራች የሆነው አላና ግሩፕ፣ ለሁለት ዓመት ያህል ያቋረጠውን ሥራውን እንደገና በመጀመር በ2014 ዓ.ም. ከወጪ ንግድ 37 ሚሊዮን ዶላር ማግኘቱን አስታወቀ፡፡

ከወጪ ንግድ የተገኘው ገቢ ከህንድ ወደ ተለያዩ አገሮች በዓመት እስከ 204 ቢሊዮን ዶላር ድረስ የሚያወጣ የሥጋ ምርት የሚልከው አላና ግሩፕ፣ ከሰባት ዓመታት በፊት በ100 ሚሊዮን ዶላር በሞጆና በአዳሚ ቱሉ ዘመናዊ ቄራዎችና የተረፈ ምርት ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች መገንባቱ ይታወቃል፡፡

በአላና ግሩፕ ሥር የሚገኙት ሁለት ድርጅቶች ያለ ምንም የብድር አገልግሎት በግል ባለሀብት የተገነቡት ሞጆ የሚገኘው ‹‹አክሰከር ኢትዮጵያ›› እና ዝዋይ አዳሚ ቱሉ የሚገኘው ‹‹ፍሪጎሪፊክ ቦራን ፉድስ›› ኩባንያዎች መሆናቸውን፣ የአላና ግሩፕ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ከሊፋ ሁሴን ተናግረዋል፡፡

ሁለቱም ድርጅቶች በግብዓት እጥረት፣ ኮቪድ-19 በመከሰቱና የውጭ አገሮች የገበያ መዳረሻ ዝቅተኛ በመሆኑ ምክንያት በ2012 ዓ.ም. ተዘግተው ከቆዩ በኋላ ከሁለት ዓመታት በኋላ ተከፍተው ሥራ መጀመራቸውን አቶ ከሊፋ አስረድተዋል፡፡

ዘንድሮ የግብዓት እጥረት ሙሉ በሙሉ ባይፈታም፣ መንግሥት በሥጋ ዘርፍ ላይ የሚስተዋለውን ችግር ለመፍታት ቃል በመግባቱና የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በአንፃራዊነት ስለቀነሰ ወደ ምርት በመግባት ወደ ውጭ መላክ መቻሉን አቶ ከሊፋ ገልጸዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ በአገር ደረጃ ከሥጋ የወጪ ንግድ 119 ሚሊዮን ዶላር የተገኘ መሆኑን፣ አላና ግሩፕ ከአጠቃላይ የሥጋ የወጪ ንግድ ገቢ ውስጥ 31 በመቶ ድርሻ መያዙ ተጠቁሟል፡፡

ሁለቱ የአላና ግሩፕ ድርጅቶች በአገሪቱ ከሚገኙት 11 ቄራዎች ውስጥ እንደሚካተቱ፣ ሁለቱም በሙሉ አቅማቸው ቢያመርቱ በዓመት እስከ 500 ሚሊየን ዶላር ማስገኘት እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡

ድርጅቶቹ በሙሉ አቅማቸው ቢያመርቱ በቀን እስከ 9,000 በጎችና ፍየሎች እንዲሁም 3,000 የቀንድ ከብቶች በማረድ ሥጋዎችን መላክ እንደሚችሉ፣ ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ በቀን የ1,500 እንስሳት ሥጋ እንደሚያመርቱ ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ አክለዋል፡፡

የአላና ግሩፕ ድርጅቶች ከአቅም በታች የሚያመርቱበት ዋነኛ ምክንያት የሥጋ ምርቶቹ የሚላኩት ወደ ሳዑዲ ዓረቢያና ዱባይ ብቻ በመሆኑ፣ ይህ ደግሞ ድርጅቱ ቀድሞ ሲመሠረት ካቀዳቸው የገበያ መዳረሻዎች ማለትም በእስያ ከቻይናና ከማሌዥያ  ጋር የንግድ ግንኙነት ባለመፈጠሩ መሆኑን አቶ ከሊፋ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ እ.ኤ.አ. የ2021 መረጃ እንደሚያሳየው ኢትዮጵያ 42 ሚሊዮን በጎች፣ 52.5 ሚሊዮን ፍየሎች፣ 70.2 ሚሊዮን የቀንድ ከብቶች፣ 58 ሚሊዮን ዶሮዎች፣ እንዲሁም ስምንት ሚሊዮን ግመሎች አሏት፡፡

‹‹ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ የእንሰሳት ሀብት ያላት ቢሆንም የሚፈለገውን ያህል የወጪ ንግድ አልተመዘገበም›› ሲሉ የተናገሩት፣ በኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን የኤክስፖርት ቄራ ኢንስፔክሽንና ሰርተፊኬሽን ዳይሬክተር አያሌው ሹመቴ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

በ2014 ዓ.ም. ከሌሎች ዓመታት አንፃር ከፍተኛ የወጪ ንግድ ተደርጓል ተብሎ 22 ሺሕ ቶን የተላከ መሆኑን ያስረዱት አያሌው (ዶ/ር)፣  ነገር ግን በዓመት 300 ሺሕ ቶን ሥጋ መላክ የምትችል በመሆኑ አሁንም አነስተኛ አፈጻጸም እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በተለያዩ ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች ምክንያት ኢትዮጵያ ከሥጋ ወጪ ንግድ ማግኘት የሚገባትን ገቢ እያገኘች አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

የገበያ መዳረሻ ውስንነት፣ መንግሥት ለዘርፉ የሰጠው ትኩረት አነስተኛ መሆን፣ የቁም እንስሳት አቅርቦት ችግር፣ የበሽታ ቁጥጥር ሥርዓት ደካማ መሆንና እንስሳት ከተወለዱ ጀምሮ እስከ መጨረሻቸው ያለቡት ሁኔታና የደረሰባቸው ችግር ምዝገባ አለመኖር ከችግሮች መካከል እንደሚገኙ አያሌው (ዶ/ር) አክለዋል፡፡

የኢትዮጵያ የሥጋ ምርት በስፋት ወደ ዱባይና ሳዑዲ ዓረቢያ አገሮች የሚላክ ሲሆን፣ በተወሰነ ደረጃ ደግሞ ኳታር፣ ኮሞሮስና ቬትናም ተቀባይ አገሮች ናቸው፡፡

‹‹የሥጋ ምርት የወጪ ንግድ በዓረብ አገሮች ብቻ የተገታው በኢትዮጵያ ያለው የበሽታ ቁጥጥር ሥርዓት ደካማ በመሆኑና እንደ ቻይና ያሉ አገሮች ያወጡትን የምርት ደረጃ ማሟላት ስላልተቻለ ነው›› ሲሉ አያሌው (ዶ/ር) ምክንያቱን አስረድተዋል፡፡

በአገሪቱ የሚፈለገውን የሥጋ ምርት የወጪ ንግድ ለማግኘት በቀጣይ መንግሥት ከአርብቶ አደሮች የሚገኘውን አቅርቦት በስፋት በማገዝ፣ ዘርፉን መደገፍ እንደሚገባው አቶ ከሊፋ ጠቁመዋል፡፡

በሥጋ የወጪ ንግድ ያለውን ችግር ለመፍታት በመንግሥት በኩል የባለድርሻ አካላት ውይይት መደረጉን የገለጹት አያሌው (ዶ/ር)፣ የሚመለከታቸው መሥሪያ ቤቶች የየራሳቸውን ድርሻ እንዲወስዱና ወደፊት የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች የመግባቢያ ሰነድ በመፈራረም የሚመለከታቸውን የሚሠሩበት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር መታቀዱን ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች