በዳኝነት አካላት ውስጥ የሚፈጸም የሙስና ተግባራትን አስመልክቶ የሚቀርቡ ጥቆማና አቤቱታዎች፣ ከአራት ወራት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ምርመራ ተደርጎ፣ የውሳኔ ሐሳብ እንዲቀርብባቸው የሚደነግግ ደንብ ፀደቀ፡፡
ምርመራውን የሚያደርገው የጥቆማ ተቀባይ ክፍል፣ ጥቆማውን ለማጣራት ተጨማሪ ጊዜ የሚያስፈልገው ከሆነ ለዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ጥያቄ የሚያቀርብ ሲሆን፣ ተጨማሪ ሁለት ጊዜያት ሊፈቀዱለት ይችላል፡፡
በፌዴራል የዳኝነት አካል ውስጥ ስለሚታዩ የሙስና ተግባራት ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣው የማስፈጸሚያ ደንብ ከመፅደቁ በፊት፣ ከዳኝነት ጋር በተያያዘ ለፌደራል ዳኞች አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ለሚቀርቡ የሙስና ጥቆማዎች የጊዜ ገደብ አልነበረባቸውም፡፡ ደንቡ መፅደቁ ከዚህ ቀደም ጥቆማዎች ተመርምረው ለፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ እስከሚቀርቡ ይወስድ የነበረውን ሁለትና ሦስት ዓመት ያስቀራል የሚል እምነት ተጥሎበታል፡፡
የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዘሪሁን ጌታሁን፣ ከዚህ ቀደም የጊዜ ገደብ ባለመኖሩ በ2010 ዓ.ም. ለጽሕፈት ቤቱ ቀርበው ምርመራ ያልተደረገባቸው አቤቱታና ቅሬታዎች ጭምር እንዳሉ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ‹‹ከዚህም አንፃር አሁን በደንቡ የተቀመጠው አራት ወራት በጣም የተሻለ ነው፤›› ብለዋል፡፡
በዚህ ሐሳብ የሚስማሙት የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትና የጉባዔው አባል አቶ ፉአድ ኪያር በበኩላቸው፣ ጉባዔው የተከማቹ ጥቆማዎች ላይ ውሳኔ በማሳለፍ የማፅዳት ሥራ ላይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ጉባዔው አሁን እየተመለከታቸው ካሉ ጉዳዮች ውስጥ አብዛኛው ‹‹አሁን ያለው አመራር ከመምጣቱ በፊት›› የተመዘገቡ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
‹‹አራት ወራት የተቀመጠው ውስብስብ የሆኑ የሙስና ጉዳዮች ቢያጋጥሙ ለማጣራት፣ ከፖሊስና ከዓቃቤ ሕግ ጋር መጻጻፍ የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ቢኖሩ ለእነሱ ተብሎ ነው፤›› ያሉት አቶ ፉአድ፣ አራት ወራት የመጨረሻው የጊዜ ገደብ መሆናቸውን አውስተዋል፡፡
የፌደራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ባለፈው ሳምንት ነሐሴ 9 ቀን 2014 ዓ.ም. ያፀደቀው ይህ ደንብ በጉባዔው ሥር በሚሆንና ሹመት በሚሰጠው ዳኛ የሚመራ የጥቆማ ተቀባይ ክፍል የሚያቋቁም ነው፡፡ ይህ ደንብ ከመውጣቱ በፊት ጥቆማ የሚቀበል ራሱን የቻለ ክፍል እንዳልነበረና ጥቆማዎች የሚቀርቡት ለጉባዔው ጽሕፈት ቤት መሆኑን አቶ ፉአድ ተናግረዋል፡፡
ደንቡ በፀደቀ በ15 ቀናት ውስጥ ይህ የጥቆማ ክፍል መቋቋም እንዳለበት የተደነገገ ሲሆን፣ ጉባዔውም ቅዳሜ ነሐሴ 14 ቀን 2014 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ የሆኑት ዳኛ በረከት ሠይፉ ክፍሉን እንዲመሩ መድቧል፡፡
የጥቆማ ክፍሉ ከቅሬታ አቅራቢዎች የቀረቡለትን መረጃና ማስረጃዎች ተንትኖ ተደማጭነታቸውን በበቂ ማስረጃዎች የተደገፉ መሆናቸውን የማረጋገጥ ኃላፊነት አለበት፡፡ ክፍሉ ባረጋገጠው መሠረት የዲሲፕሊንና የወንጀል ተጠያቂነት የሚያስከትሉ አቤቱታዎችን የጉባዔው ሰብሳቢ ለሆኑት ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ ያቀርባል፡፡
በአዲሱ ደንብ መሠረት ለጥቆማ ማስረጃ የሚያቀርቡ ግለሰቦችና አካላት በራሳቸው ወይም በቤተሰባቸው ላይ የበቀል ወይም መሰል ተግባራት እንዳይፈጸምባቸው ጥበቃ የማግኘት መብት አላቸው፡፡ መረጃ ለመስጠት በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ለወጪ የሚዳረጉ ከሆነ ተመጣጣኝ ማካካሻ እንደሚደረግላቸው ደንቡ አስቀምጧል፡፡
ይሁንና ማንኛውም ጥቆማ ሰጪ ሐሰተኛ ማስረጃ የሚያቀርብ ወይም ያለ ምንም ተጨባጭ ማስረጃ ጥቆማ የሰጠ እንደሆነ በወንጀል ሕግ ተጠያቂ እንደሚሆን ተደንግጓል፡፡ የጥቆማ ክፍሉም ከተረጋገጡ ጥቆማዎች ውጪ በማስረጃ ያልተደገፉትን በመለየት ከውሳኔ ሐሳብ ጋር ለጉባዔው የማቅረብ ኃላፊነት ተጥሎበታል፡፡
ከዚህ ቀደም ከነበረው አሠራር በተለየ አሁን የሚቋቋመው የጥቆማ ክፍል በአጭር ቁጥር ጥሪ በማድረግ ጥቆማ ለመስጠት የሚያስችል የራሱ የሆትላይን ቁጥር ይኖረዋል፡፡
የፌዴራል ዳኞች አስተዳዳሪ ጉባዔ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዘሪሁን እንደሚያስረዱት፣ ጽሕፈት ቤቱ በ994 ቁጥር ላይ ሲደወል ካሉት አማራጮች ውስጥ ጥቆማ ክፍሉንም ማግኘት የሚያስችል አማራጭ እንዲካተት ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር ንግግር እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ጽሕፈት ቤቱ ሌሎች ለጥቆማ ክፍሉ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን አሟልቶ እያጠናቀቀ መሆኑንና ጥቆማ አቅራቢዎች እንዲመጡ በቅርቡ ማስታወቂያ እንደሚያስነግር አክለዋል፡፡
የፌደራል ዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ነሐሴ 14 ቀን 2014 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባው፣ የሥነ ምግባር ጥሰት በፈጸሙ ሁለት የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዳኞች ላይ ቅጣት ጥሏል፡፡
አንድ መቶ ሺሕ ብር ጉቦ እንደተቀበሉና በአካል ከባለ ጉዳይ ጋር በመገናኘት ስለያዙት ጉዳይ በመወያየት ከባድ የሥነ ምግባር ደንብ ጥሰት መፈጸማቸው የተረጋገጠባቸው ዳኛ ከሥራ እንዲሰናበቱ ተወስኖባቸዋል፡፡
በአንድ የክስ መዝገብ ላይ ግልጽ የሆነና ተደራራቢ የሥነ ሥርዓት ሕግ ጥሰት መፈጸማቸው የተረጋገጠባቸው ሌላው ዳኛ ደግሞ፣ የአምስት ወራት ደመወዝ እንዲቀጡ ጉባዔው ወስኗል፡፡