Monday, December 4, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የብሽሽቅ ፖለቲካ ውጤቱ ኪሳራ ነው!

በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ጠቃሚ የሆኑና ያልሆኑ ጉዳዮችን የመለየት ችግር በስፋት እየተስተዋለ ነው፡፡ የትኛው ከየትኛው ቢቀድም ለዕድገት ይጠቅማል ከማለት ይልቅ፣ በዘፈቀደ የሚከናወኑ ነገሮች እየበዙ ነው፡፡ ምክንያታዊ ሆኖ በማስተዋል መመራት እየተቻለ፣ በስሜታዊነት በሚወሰዱ ዕርምጃዎች ሳቢያ ቅራኔ የሚፈጥሩ ጉዳዮች ቁጥራቸው እየጨመረ ነው፡፡ አገር ወደፊት እንዳትራመድ ከሚያደርጉ አዋኪ ነገሮች መሀል በሚገባ ማቀድ አለመቻል፣ ሳያቋርጡ ስለትናንት ሁነቶች ብቻ ማሰብ፣ ለአሉታዊ መረጃዎች ትኩረት መስጠት፣ በሌሎች ላይ ጥገኛ መሆን፣ የማኅበራዊ የትስስር ገጾች እስረኛ መሆን፣ እርስ በርስ አለመስማማት፣ ራስን ከሌሎች ጋር ተገቢ ባልሆኑ ጉዳዮች ማወዳደር፣ ተቃርኖ የሚፈጥሩ ጉዳዮችን ማግዘፍና የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡ ፖለቲካው የሚመራው በብሽሽቅ በመሆኑ ብቻ ከሐሳብ ልዕልና በላይ ጎልቶ የሚሰማው አሽሙርና ስድብ ነው፡፡ ለአገር ዕድገት የሚጠቅሙ ሐሳቦች ላይ ማተኮር እያቃተ፣ አብዛኛው ጊዜና ጉልበት የሚባክነው ፋይዳ ለሌላቸው ጉዳዮች ነው፡፡ ለአገር የሚጠቅሙ ብርቱ ሐሳቦች ከመሀል እየተገፉ ብሽሽቅ የአገሪቱን የፖለቲካ ምኅዳር ሲቆጣጠር፣ ብሔራዊ ምክክርም ሆነ ድርድር ለማድረግ የሚኖረው ተስፋ ጉዳይ ያሳስባል፡፡

ብልጥ ፖለቲከኞች በአገኙት አጋጣሚ ሁሉ የሚፈልጉትን መልዕክት ማስተላለፋቸው አዲስ ነገር አይደለም፡፡ አጋጣሚው ይገኝ እንጂ ወቅቱን የሚዋጅ ወይም ፍላጎታቸውን የሚያንፀባርቅ ንግግር ማድረጋቸውም የሚጠበቅ ነው፡፡ ከብልጠቱም ሆነ የተገኘ አጋጣሚን ለመጠቀም ዳተኛ ወይም ቀርፋፋ የሆኑት ደግሞ፣ እንኳንስ ፍላጎታቸውን ለማስተጋባት ሌሎች የሚሉትን ለማዳመጥ ዝግጁ አይደሉም፡፡ በዚህም ምክንያት አጀንዳ ከመቅረፅና ከማሠራጨት ይልቅ፣ የሌሎች አጀንዳ አራጋቢ ሆነው ይቀራሉ፡፡ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ፖለቲካ ውስጥ እየተስተዋሉ ካሉ በጣም አሳሳቢ ጉዳዮች ውስጥ፣ አጀንዳ ሰጪውና ተቀባዩ ያሉበት ርቀት ከመጠን በላይ መለጠጡ ነው፡፡ ከአጀንዳ ሰጪው ወገን በማያቋርጥ ሁኔታ የተለያዩ መልዕክቶች በተለያዩ ይዘቶችና ቅርፆች ሲተላለፉ፣ ከተቀባዩ ወገን ያለው ተመሳሳይ ማባሪያ የሌለው ንትርክ ፖለቲካውን እያደር ቁልቁል እየሰደደው ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ በዚህ ሁኔታ ወደፊት ይራመዳል ለማለት በሚያዳግት ነባራዊ ሁኔታ ውስጥ፣ የአጀንዳ ተቀባዩ ባህሪ መለወጥ ካልቻለ ባለህበት እርገጡ በሚያሳዝን ሁኔታ መቀጠሉ አይቀሬ ነው፡፡ የቃላት ብሽሽቅ ላይ የተቸከለ የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ ሆኖ ለውጥ መጠበቅ ፈፅሞ አይቻልም፡፡

ኢትዮጵያ ለላፉት ሁለት ዓመታት ያህል ከነበረችበት አውዳሚ ጦርነት ውስጥ ወጥታ ሰላም መስፈን ሲገባው፣ አሁንም በሚያሳዝን ሁኔታ ወደ ጦርነቱ የሚመልሱ ምልክቶች እየታዩ ነው፡፡ ማንም ጤነኛ አስተሳሰብ ያለው ሰው ጦርነትን እንደገና ለዓላማ ማስፈጸሚያ ማድረግን ይደግፋል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ያ ሁሉ ዕልቂት፣ ውድመት፣ መፈናቀልና ሥቃይ ታልፎ ጦርነት ሊነሳ ይችላል የሚል ሥጋት ሲፈጠር ያሳዝናል፡፡ ሰላምን ለማስፈን ያሉ አማራጮችን በቀኝም በግራም አማትሮ መፍትሔ ላይ ለመድረስ መማሰን ሲገባ፣ ለጦርነት ታጥቆ መነሳት የሚያገለግሉ የተቃርኖ ግብዓቶችን ማሰባሰብ ከጤነኛ አዕምሮ የሚጠበቅ አይደለም፡፡ ለአገር ፋይዳ በሌላቸው ነገሮች በመተነኳኮስ የቃላት ጦርነት ውስጥ ከመግባት ጀምሮ፣ አገር ሊያፈርስ የሚችል አውዳሚ ውጊያ ለመጀመር ማሰፍሰፍ የሚጠቅመው ታሪካዊ ጠላቶችን ብቻ ነው፡፡ እነሱ ደግሞ ይህንን አጋጣሚ ለመጠቀም ኢትዮጵያውያንን በሚችሉት ሁሉ ይከፋፍላሉ፡፡ አጀንዳ ሰጪው አስከፊ ንግግር እንዳያደርግና ተቀባዩ እንዳይከፋ ጥንቃቄ መደረግ አለበት፡፡ የፖለቲካ አቋም ልዩነት ተከብሮ መፎካከር የሚቻለው፣ በመከባበር ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ ምኅዳር እንዲፈጠር የጋራ ጥረት ሲደረግ ነው፡፡

የአገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ድክመት በፖለቲካ ምኅዳሩ ውስጥ ለሚስተዋሉ እያደር ማነሶች ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው መካድ አይቻልም፡፡ በጣም ከተወሰኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች በስተቀር አብዛኞቹ እንደሌሉ ነው የሚቆጠሩት፡፡ አሉ ከሚባሉት ውስጥም ቢሆን እየታየ ያለው መፍረክረክ ድክመቱን እያጠናከረው ነው፡፡ ብዙዎች ከፍተኛ የሆነ የፋይናንስ እጥረት ስላለባቸው ከበስተጀርባቸው ሆነው ለሚዘውሯቸው ጉዳይ አስፈጻሚ ሆነዋል፡፡ በስንት ልፋት የሚገኘው የድጎማ ገንዘብ ፓርቲዎቹን ከማጠንከር ይልቅ የንትርከ ምንጭ ይሆንባቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት በአኩራፊዎች ስብስብ የሚመሠረቱ ፓርቲዎች ዕድሜያቸው ያጥራል፣ ወይም ቀንጭረው ይቀራሉ፡፡ በዚህና በሌሎች መሰል ምክንያቶች የፖለቲካ ምኅዳሩ የሐሳብ ድርቅ ገጥሞታል፡፡ በአገሪቱ ዙሪያ ገብ ጉዳዮች ላይ አቅጣጫ ማመላከት የሚገባቸው ፓርቲዎች እየሟሙ፣ የፖለቲካ ምኅዳሩ የተሞላው በማኅበራዊ የትስስር ገጾች ተንታኞችና አስተንታኞች ነው፡፡ እዚህ ሠፈር ውስጥ ካሉት ብዙዎቹ ምንም ዓይነት ኃላፊነት የማይሰማቸው፣ ከኋላ ሆነው የሚገፏቸውን ቀለብ ሰፋሪዎች ፍላጎት ለማስፈጸም የሚሯሯጡና በአገኙት አጋጣሚ ሁሉ ተቃርኖውን ለማስፋፋት የሚቅበዘበዙ ናቸው፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩ በሐሳብ ድርቅ እየተጠቃ ብሽሽቁ የተስፋፋው በዚህ ሳቢያ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡

ኢትዮጵያ በተለያዩ ምክንያቶች ከባድ ውጥንቅጥ ውስጥ ሆና ልዩነትን ይዞ በብሔራዊ ጉዳዮች ላይ መስማማት እየተቻለ፣ ከሦስት ቀናት በላይ ዕድሜ የሌላቸው የንትርክ አጀንዳዎች ላይ መጣድ ተገቢ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ መልማትና ማደግ የምትችለው ልጆቿ ልዩነታቸውን ይዘው የሐሳብ ፍልሚያው ላይ ሲያተኩሩ ነው፡፡ የሐሳብ መፋለሚያ ሜዳው ላይ በጨዋና በታረመ ቋንቋ መነጋገር ሲቻል፣ ለሐሳብ ልዕልና የሚደረገው ፉክክር ፈር ይይዛል፡፡ ሕጋዊና ሰላማዊ የፖለቲካ ፉክክሩ የብዙኃንን ቀልብ ሊገዛ የሚችለው፣ ለሕገወጥነትና ለሥርዓተ አልበኝነት የሚዳርጉ ብሽሽቆች ሲወገዱ ነው፡፡ አሁን በግልጽ እንደሚታየው ከአንድ ሥፍራ አንድ መናኛ አጀንዳ ሲለቀቅ፣ ከዳር እስከ ዳር ከሚያስተጋቡት ጀምሮ ውለው የሚያድሩበት ድረስ የሚጠፋው ጊዜና ጉልበት ያሳዝናልም፣ ያስተዛዝባልም፡፡ ይህንን ችግር በውል ተገንዝበው መፍትሔ መፈለግ የሚገባቸው የአገሪቱ የፖለቲካ ልሂቃንም ሆኑ ምሁራን፣ ልዩነቶቻቸውን መልክ አስይዘው የሚበጀውን መፍትሔ ማፍለቅ ይጠበቅባቸዋል፡፡ አንድ አጀንዳ ሲለቀቅ ራስን እዚያ ውስጥ ከቶ መብሰልሰል ፋይዳ ቢስ ነው፡፡ ቢዘገይም አልረፈደምና ነቃ ማለት ተገቢ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ አሁንም ድረስ እንደ አንድ ችግር የሚታየው ጉዳይ ካለፉ ስህተቶች ለመማር ፈቃደኛ አለመሆን ነው፡፡ ሥልጣን ላይ የወጡ ከእነሱ በፊት የነበሩት በፈጠሩት ስህተት ወይም ጥፋት ምክንያት ምን እንደ ደረሰባቸው ለማጤን በአብዛኛው ፍላጎት አይታይባቸውም፡፡ ሥልጣን ለመያዝ የሚፈልጉትም ቢሆኑ ከእነሱ በፊት የነበሩት ያልተሳካላቸው በምን ምክንያት እንደሆነ ለመረዳት አይፈልጉም፡፡ አንዱ ከሌላው ጥፋት ወይም ውድቀት እየተማረ የተሻለ ነገር ማሳየት ሲገባው፣ ራሱ መልሶ የሌላውን ስህተት ሲደግም ማየት ከማስገረም አልፎ ያሳዝናል፡፡ በዘመነ ነጭና ቀይ ሽብር ተዋንያን የነበሩ ጭምር “ዓይኔን ግንባር ያድርገው” እያሉ ጥፋታቸውን ማመን ስለማይፈልጉ፣ በዚህ ዘመን ያሉ የፖለቲካ ተዋንያን ያንን ዓይነት የውድመት መንገድ እየተከተሉ ነው፡፡ ፖለቲካው ከአራት አሥርት ዓመታት በኋላም እያደር የሚቀነጭረው ስህተትን መደጋገም ልማድ በመሆኑ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታስ አገራዊ ምክክሩ እንዴት ወደፊት ሊራመድ ይችላል ተብሎ ካልታሰበበት፣ የብሽሽቅ ፖለቲካው የበላይነቱን እየያዘ ውድቀቱ እየተባባሰ ይቀጥላል፡፡ ለአገር ፋይዳ የሌላቸው ከንቱ አጀንዳዎች ብሽሽቁን እያፋፋሙ የሚያስከትሉት ኪሳራ ነው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...

በሲሚንቶ ፋብሪካ ላይ የታየው ተሞክሮ በሌሎች ምርቶች ላይም ይስፋፋ!

ሰሞኑን በኢትዮጵም ሆነ በአፍሪካ ደረጃ ግዙፍ ስለመሆኑ የተነገረለትን የለሚ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአስተሳሰብና የአስተዳደር ዘይቤ ለውጥ ያስፈልጋል!

ኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝቡን በጋራ አስተሳስረው የሚያኖሩ በጣም በርካታ ማኅበራዊ እሴቶች አሉ፡፡ እነዚህ ለዘመናት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገሩ የኖሩ እሴቶች አገር ለማቆም ትልቅ አስተዋፅኦ ነበራቸው፣...

ድጋፍና ተቃውሞ እኩል ይስተናገዱ!

ኢትዮጵያ ውስጥ ለረዥም ዓመታት ለመንግሥት ከሚቀርቡ ጥያቄዎች መካከል አንዱ የመብት መከበር ጉዳይ ነው፡፡ ዜጎች ተፈጥሯዊም ሆኑ ሕጋዊ መብቶቻቸው እንዲከበሩላቸው ለመንግሥት ጥያቄ ሲያቀርቡ፣ ጥያቄው የቀረበለት...

ፖለቲካዊ ችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሔ ይፈለግላቸው!

መንግሥት ከኦነግ ሸኔ ጋር በታንዛኒያ ዳሬሰላም ከተማ ሲያካሂድ የነበረው ንግግር ያለ ውጤት መጠናቀቁን ካስታወቀ በኋላ፣ በኦሮሚያ ክልልም ሆነ በሌሎች ቦታዎች ሰላም ለማስፈን የነበረው ተስፋ...