Wednesday, May 22, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለፌደራል መንግሥት ፕሮጀክቶች የሲሚንቶ ፍላጎት በኮንስትራክሽ ባለሥልጣን እየተጣራ ሊፀድቅ ነው

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የፌደራል መንግሥት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ለሚያከናውናቸው ፕሮጀክቶች የሚያስፈልገውን የሲሚንቶ ፍላጎት፣ በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለሥልጣን በኩል እየተመረመረ ሊፀድቅ ነው፡፡

የኮንስትራክሽን ባለሥልጣን ከነሐሴ 13 ቀን 2014 ዓ.ም. አንስቶ፣ የፌዴራል መንግሥት የግንባታ ፕሮጀክቶችን ለሚያከናውኑ ተቋማት የሚያቀርቡትን የሲሚንቶ ፍላጎት መመዝገብ ጀምሯል፡፡ በአጠቃላይ 2,500 ያህል የፌደራል መንግሥት የግባታ ፕሮጀክቶች ሲኖሩ፣ በእነዚህ ቀናት ውስጥም 80 ፕሮጀክቶች ፍላጎታቸውን እንዳሳወቁ የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር መስፍን ነገዎ (ኢንጂነር) ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ፕሮጀክቶቹ የሚያስፈልጋቸው የሲሚንቶ መጠንና ለምን ያህል ጊዜ ሊቀርብላቸው እንደሚገባ በባለሥልጣኑ ተወስኖ የሚቀበሉትን ማረጋገጫ ይዘው፣ ለንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ያቀርባሉ፡፡ ሚኒስቴሩም በማረጋገጫው መሠረት ለፕሮጀክቶቹ ኮታ በመወሰን ከፋብሪካዎች በቀጥታ እንዲገዙ እንደሚያደርግ፣ የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊዋ ወ/ሮ ቁምነገር እውነቱ ገልጸዋል፡፡ ይህንን ማረጋገጫ ያልያዙ ፕሮጀክቶች ምደባ እንደማይሰጣቸውና ሲሚንቶ እንደማያገኙ አስረድተዋል፡፡

የሲሚንቶ ሥርጭትና ግብይት መመርያ አውጥቶ የሲሚንቶ ገበያን ለመምራት እየሞከረ ያለው የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ ይህንን አሠራር የዘረጋው ከሁለት ሳምንት በፊት ከኮንስትራክሽን ባለሥልጣን ጋር የመግባቢያ ሰነድ ከተፈራረመ በኋላ ነው፡፡

ሁለቱ አካላት የመግባቢያ ሰነዱን የተፈራረሙት ለሲሚንቶ ግብይትና ሥርጭት የወጣውን መመርያ ለመተግበር እንደሆነ የሚያስረዱት ወ/ሮ ቁምነገር፣ ለፕሮጀክቶቹ ኮታ ለመመደብ የሚያቀርቡትን መጠን የሚያጠና አካል ማስፈለጉን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በነበረው አሠራር ፕሮጀክቶች የሚያስፈልጋቸውን የሲሚንቶ ብዛት ለሚኒስቴሩ ብቻ እንደሚያቀርቡና ማጣራት እንደማይደረግበት ገልጸዋል፡፡ ዓላማውም ‹‹ፕሮጀክቶቹ የፈለጉትን ያህል እየጠየቁ እንዳይሰጣቸውና ለታለመለት ዓላማ ብቻ እንዲያውሉ ማድረግ ነው፤›› ብለዋል፡፡

እንደ ወ/ሮ ቁምነገር ገለጻ፣ ከዚህ ቀደም በነበረው አሠራር ለሚኒስቴሩ ከሚቀርቡ የፍላጎት መጠን ጥያቄዎች ውስጥ አብዛኛዎቹ ‹‹ያልተገቡ›› ናቸው፡፡ ‹‹ብዙዎቹ ለፕሮጀክቱ ያልተገባ ጥያቄ ነው እያቀረቡ ያሉት፣ የሚወስዱትን ሲሚንቶም ለታለመለት ዓላማ ሳይሆን፣ ገበያ ውስጥ ለሽያጭ ነው የሚያውሉት፤›› ሲሉ ወቀሳቸውን አቅርበዋል፡፡

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር መስፍንም (ኢንጅነር) ይህንን ሐሳብ የሚጋሩት ሲሆን፣ ‹‹አንድ ሆስፒታል ካለቀ አሥር ዓመት ሆኖት በስሙ ግን ሲሚንቶ እየወጣ ተገኝቷል፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ባቀረበው ጥሪ መሠረት ፕሮጀክቶቹ የሲሚንቶ ፍላጎት መጠናቸውን አሁን ካሉበት የግንባታ ደረጃና የግንባታ ጊዜ ጋር አያይዘው እንደሚያቀርቡ፣ ይህንን የሚያደርጉትም ከአማካሪ ድርጅቶቻቸው ጋር በመመካከር መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡

መስፍን (ኢንጂነር)፣ ‹‹ከቀረበልን በኋላ እኛ ደግሞ ባለሙያዎቻችንን ተጠቅመን በኢንጂነሪንግ ስሌቶች ፍላጎቱን አስልተን ለዚህ ፕሮጀክት ይህንን ያህል ሲሚንቶ ለዚህ ጊዜ ያህል ይቅረብላቸው ብለን ማረጋገጫ እንሰጣለን፤›› በማለት ሒደቱን አስረድተዋል፡፡

ማረጋገጫው ሲሰጥ ፕሮጀክቶቹ የሚያስፈልጋቸው አጠቃላይ የሲሚንቶ ብዛት በዓመት፣ በሦስት ወርና በወር ተከፋፍሎ እንደሚቀርብ የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፣ አንድ ጊዜ የሚሰጠው ማረጋገጫ እስከ ፕሮጀክቱ ማጠናቀቂያ ጊዜ ድረስ እንደሚያገለግል ገልጸዋል፡፡

የፌደራል መንግሥት ፕሮጀክቶች ምዝገባ ከመጀመሩ አንስቶ 80 የሚደርሱ ፕሮጀክቶች ፍላጎታቸውን ቢያቀርቡም፣ ብዙዎቹ ፕሮጀክቶች ያቀረቡት ‹‹ይህንን ያህል ኩንታል ያስፈልገኛል›› የሚል ብቻ እንደሆነ መስፍን (ኢንጅነር) ተናግረዋል፡፡ እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ ፕሮጀክቶቹ ከአማካሪያቸው ጋር በመሆን የፍላጎት መጠናቸውን የወሰኑበትን ስሌት ለባለሥልጣኑ ማቅረብ አለባቸው፡፡

የኮንስትራክሽን ባለሥልጣን የፌደራል ፕሮጀክቶች ፍላጎት መቀበል ቢጀምርም፣ ፍላጎቱ በምን ያህል ጊዜ ውስጥ መቅረብ እንደሚኖርበት ገደብ አላስቀመጠም፡፡ ባለሥልጣኑም ሆነ ሚኒስቴሩ ፕሮጀክቶቹ ከሥራቸው ጋር የሚያያዝ ስለሆነ በቶሎ አቅርበው ያስወስናሉ የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች