Wednesday, April 17, 2024

አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ወደ ትግራይ ክልል ለመሄድ ዕቅድ መያዙን አስታወቀ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ባለፉት ወራት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተንቀሳቀሰው የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ወደ ትግራይ ክልል ለማቅናት ዕቅድ እንዳለው አስታወቀ፡፡

የምክክር ኮሚሽኑ አባልና የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ የሆኑት ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኮሚሽኑ በመቀጠል ወደ ትግራይ ክልል ለማምራት ዕቅድ እንዳለው፣ ዝግጅቱ ሲጠናቀቅም ለሚዲያ ይፋ እንደሚደርግ አስታውቀዋል፡፡

አገራዊ ምክክሩ ሁሉን አቀፍ እንዲሆን የተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም፣ በግጭት አካባቢዎች ያሉ አካላት ጭምር የሚገናኙበትን መድረክ ለመፍጠር መታሰቡን፣ በአገር ሽማግሌዎችና በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ትብብር ሁሉንም ወገኖች በማሳተፍ ኢትዮጵያን የሚያሻግር የውይይት መድረክ ለማዘጋጀት ኮሚሽኑ እየተዘጋጀ ነው ብለዋል፡፡

ወደ ትግራይ ክልል ለመሄድ አስቻይ ሁኔታ አለ ወይ ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ ውይይት የሚያስፈልገው አመቺ ሁኔታ ሳይኖር ሲቀር መሆኑን አዳዬ (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡

ኮሚሽነሩ ይህን የተናገሩት  የኢትዮጵያ  ሲቪል  ማኅበረሰብ  ድርጅቶች  ምክር ቤትና  የኢትዮጵያ  ፖለቲካ  ፓርቲዎች  የጋራ  ምክር ቤት፣ በአገራዊ ምክክሩ ላይ ማክሰኞ ነሐሴ 17 ቀን 2014 ዓ.ም. ውይይት ባደረገበት ወቅት ነው፡፡

ኮሚሽኑ እስካሁን ባለው ሒደት በሥራው ጣልቃ የገባባት የውጭም ሆነ የአገር ውስጥ ኃይል እንደሌለ፣ በቀጣይም ይህንኑ ያስቀጥላል የሚል እምነት እንዳላቸው ዮናስ (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡

ሁሉም ኢትዮጵያውያን ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ያሳዩትን ኅብረት ለአገራዊ ምክክሩ በድጋሚ እንዲያሳዩ ጥሪ ያቀረቡት ኮሚሽነሩ፣ ልሂቃንም ከእንግዲህ ብዙ ተሞክሮ የሚያወጣው መንገድ ሰላም ብቻ ስለሆነና ለሰላም ያለው ብቸኛ አማራጭ ራሱ ሰላም በመሆኑ፣ ለዚህ መሳካት ሰላማዊ ውይይትን ባህል ማድረግ እንዳለባቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ከአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድ አዲስ የፖለቲካ ባህል ያገኛል የሚል እምነት እንዳላቸው የገለጹት ኮሚሽነሩ፣ ሁሉም በጋራ አሸንፎ አዲስና የጋራ የፖለቲካ መሠረት የሚጥልበት ጊዜ ይፈጠራል ብለዋል፡፡

መንግሥትና የተለያዩ ታጣቂ ኃይሎች ለድርድር ሲንቀሳቀሱ ለአገራዊ ምክክሩ ትልቅ አስተዋጽኦና ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑን፣ በተመሳሳይ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተፈጠሩት ችግሮችና ግጭቶች ምንጊዜም ለአገራዊ ምክክሩ እንቅፋትና ተግዳሮት ስለሚሆኑ፣ ግጭቶቹ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ለማድረግ ኮሚሽኑ የተለያዩ ዘዴዎችን እንደሚጠቀም አስረድተዋል፡፡

አክለውም የፖለቲካ ድርድሩ የብሔራዊ ምክክር አንዱ አካል እንደሆነ፣ አገራዊ ምክክር መዋቅራዊ ለሆኑና ዘላቂ መፍትሔ ለሚሹ ችግሮች መፍቻ እንደሚሆን፣ አሁን የተጀመሩትን የሰላም እንቅስቃሴዎች ሁሉ በመደገፍ ሰላምን የሚያደናቅፉ እንዳይኖሩ እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡

የፌዴራል መንግሥትና ሕወሓት መካከል የፖለቲካ ድርድር ይጀምራሉ ተብሎ በሚጠበቁበት ጊዜ የፖለቲካ ቃላት መወርወር ውስጥ መግባታቸው ለአገራዊ ምክክር ዝግጅቱ ላይ ስለሚኖረው ተፅዕኖ ሲያስረዱ፣ ‹‹በበለጠ ጥንቃቄና ማስተዋል በተሞላበት ሁኔታ እንድንሄድ ያደርገናል እንጂ፣ ይህን ፈርተን ወደኋላ የምንልበት ምክንያት የለም፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹በአንድ በኩል ግጭትና ጦርነት እየታየ ውይይትና ምክክር የተለመደና የሚደረግ በመሆኑ ለእኛ ጥንቃቄ በተሞላበት አካሄድ እንድንሠራ ይረዳናል፤›› ብለዋል፡፡

በውይይቱ  የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢ አብዱልቃድር አደም (ዶ/ር)፣ ከአሥር በላይ የሚሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች በኮሚሽኑ አመሠራረትና ቁመና ላይ ተቃውሞ ለማሰማት ተደራጅተው እየጠየቁ መሆኑን በመጥቀስ በቀጣይ የእነዚህን ፓርቲዎች ጥያቄ ማድመጥ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡ ነገር ግን ፓርቲዎቹ የማይደመጡ ከሆነ በአገራዊ ምክክር ሒደቱ ላይ የራሱ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚኖረው አስታውቀዋል፡፡

የአገራዊ ምክክር ሒደቱ በስምምነት ላይ የተመሠረተ መሆን እንደሚኖርበት የገለጹት ምክትል ሰብሳቢው፣ ለአገራዊ ምክክሩ እንቅፋት ያሏቸውን ሁለት ጉዳዮች ፖለቲካዊና ሒደት ተኮር በሚል አቅርበዋቸዋል፡፡

ፖለቲካዊ ምክንያት የተባሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች የአጀንዳ ቅርርብ፣ የፖለቲካ ፍላጎት መኖርና አለመኖር፣ የምሁራን ድጋፍና ተቃውሞ፣ ሕዝብ ለአገራዊ ምክክሩ ያለው ድጋፍ፣ እንዲሁም የውጭ ኃይሎች ሚና ለአገራዊ ምክክሩ መሳካትና አለመሳካት ትልቅ ሚና እንደሚኖራቸው አስረድተዋል፡፡

ሒደት ተኮር በሚል ያቀረቧቸው የተሳታፊዎች አመራረጥና ቁጥር፣ መተማመን ለመፍጠር የሚከናወኑ ሥራዎች፣ የውሳኔ አሰጣጥ መንገዶች፣ የአመቻቾች አመራጥ፣ ለሒደቱ የሚደረግ የቴክኒክ ድጋፍና በተሳታፊዎች መካከል የሚኖር ግንኙነት ለምክክሩ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት አብራርተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ታሪክ ተከናውኗል የሚባል የአገራዊ ምክክር ሒደት አልነበረም ያሉት ምክትል ሰብሳቢው፣ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ሥር ነቀል የኢኮኖሚ ለውጥ ለማምጣት፣ ፖለቲካዊ ቀውስን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠርና ለማስቆም ከተፈለገ አገራዊ ምክክሩ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በአገራዊ ምክክር የዝግጅት ምዕራፍ ሥራዎች ውስጥ የፖለቲካ እስረኞችን መፍታት፣ የትጥቅ ትግል ለሚያደርጉ ይቅርታ ማድረግ፣ ከታጣቂዎች ጋር ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነት ማድረግና የሚዲያ ነፃነትን ማረጋገጥ አጋዥ ፖለቲካዊ ሁኔታዎች መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -