Tuesday, May 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ስፖርት‹‹ፍትሐዊ ምርጫ ተደርጎ ከተሸነፍኩ ባለኝ አቅም ሁሉ ከአሸናፊው ጎን ሆኜ እግር ኳሱን...

‹‹ፍትሐዊ ምርጫ ተደርጎ ከተሸነፍኩ ባለኝ አቅም ሁሉ ከአሸናፊው ጎን ሆኜ እግር ኳሱን ለማገዝ ዝግጁ ነኝ›› አቶ መላኩ ፋንታ

ቀን:

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የፕሬዚዳንትና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ በተባለው ቀን የሚካሄድ ከሆነ፣ እሁድ ነሐሴ 22 ቀን 2014 ዓ.ም. ይከናውናል፡፡ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ የምርጫው ቦታ አልተገለጸም፡፡ በሌላ በኩል ግን ለፕሬዚዳት ምርጫው የቀረቡት ሦስቱ ዕጩ ተወዳዳሪዎች ቢመረጡ፣ ለእግር ኳሱ የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ እያስተዋወቁ ይገኛል፡፡

ከዕጩ ተወዳዳሪዎቹ መካከል የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ተብሎ ይጠራ የነበረው ተቋም ዋና ዳይሬክተር የነበሩትና በአሁኑ ወቅት የአማራ ልማት ማኅበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ እንዱሁም የአማራ ባንክ መሥራችና የቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ መላኩ ፋንታ ይጠቀሳሉ፡፡

ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንትነት ዕጩ ተወዳዳሪ ሆነው ከመቅረባቸው በፊት እግር ኳስ ምን እንደሚፈልግ፣ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በግልና በቡድን ሰፊና ጥልቅ ውይይት ማድረጋቸውን ጭምር አቶ መላኩ ያስረዳሉ፡፡

- Advertisement -

‹‹ለእግር ኳሳችን ትንሳዔ ለውጥ የምንዘጋጅበትና የምንነሳበት ትክክለኛው ጊዜ እነሆ ከፊታችን መጥቷል፤›› የሚሉት አቶ መላኩ፣ ዓለም አቀፍ ተሞክሮ እንደሚያሳየው፣ እግር ኳስ የሁሉንም ቀልብ ከመሳቡ ባሻገር ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አበርክቶው ከፍ ያለ በቢዝነስ መርህ የሚመራ ቢሊዮን ዶላሮችን የሚያንቀሳቀስ ግዙፍ ኢንዱስትሪ ቢሆንም፣ እንደ አለመታደል ሆኖ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ለዚህ ሳይታደል ዓመታትን አስቆጥሯል ይላሉ፡፡

‹‹120 ሚሊዮን ሕዝብ አለን፣ ከዚህ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆነው የማኅበረሰባችን ክፍል ወጣትና ለእግር ኳስ ታለንት ቅርብ ነው፣ በሌላ አነጋገር ያልተነካ የእምቅ ሀብት ባለቤትም ነን፤›› የሚሉት አቶ መላኩ፣ ይህን አቅምና ብቃቱ ባለው አመራር እንዲመራ በምርጫ ወቅት የሚመጡ አጋጣሚዎችን መጠቀም፣ ፍትሐዊ፣ ተዓማኒና ተገማች ምርጫ በማድረግ፣ በሥርዓትና በሕግ የሚመራ ተቋም መፍጠር ከምንም በፊት አስፈላጊ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡

ምርጫው ፍትሐዊ መሆን እንዳለበት የሚጠይቁት አቶ መላኩ፣ ፍትሐዊነትን መልመድ የዚህ ትውልድ በተለይም በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባዔ ድምፅ የሚሰጡ አባላት፣ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ እድገት ሲሉ ታማኝና ለህሊና (መርህ) ተገዥ መሆን ግድ ይላቸዋል ብለዋል፡፡

ቀደም ሲል ከምርጫው ጋር በተገናኘ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር መወያየታቸውን የገለጹት አቶ መላኩ፣ ይህን ለማድረግ መነሻ የሆናቸው፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በእግር ኳሱ የራሱ ድርሻ እንዳለው በማመን ሲሆን፣ ይህንኑ ታሳቢ ያደረገ ፍኖተ ካርታ (ሮድ ማፕ) በማዘጋጀት፣ በሥርዓት የሚመራ ተቋም መገንባት እንደሚችሉ ጭምር ያስረዳሉ፡፡

እንደ እሳቸው እምነት ወደ እዚህ ተቋም የሚመጡ ሰዎች፣ መመረጥ ያለባቸው ባላቸው አቅምና ችሎታ እንዲሁም ለእግር ኳስ ሊያበረክቱት የሚችሉት ፋይዳ ታይቶና ተገምግሞ እንዲሆን ያሳስባሉ፡፡

ቢመረጡ የፌደሬሽኑን የማስፈጸም አቅም መገንባት፣ የተጀመሩ በጎ ነገሮችን በማስቀጠል የጎደሉ ነገሮችን መሙላት፣ የሕግ የአሠራርና የአደረጃጀት ማሻሻያ ማድረግ፣ ብሔራዊ ተቋሙ በብቁ ባለሙያ እንዲደራጅና ተከታታይ የሆነ የአቅም ግንባታ ማካሄድ፣ ማበረታቻና ተጠያቂነት ያለው እንዲሁም ክለቦች በፋይናስ የሚጠናከሩበት ሥርዓት መፍጠር፣ የፋይናንስና የኦዲት አሠራሮች ማጠናከር፣ የካፍና ፊፋን መመዘኛ የሚያሟሉ የስፖርት መሠረት ልማት እንዲሁም የተጀመሩ ስታዲየሞች በማጠናቀቅ፣ ሜዳ በማጣት የተሰደደው ብሔራዊ ቡድን ወደ አገሩ ተመልሶ እንዲጫወት ማድረግ የዕቅዳቸው አካል እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

‹‹ሳይደርሱ መድረስ፣ መድረስን ያስቀራል›› የሚሉት አቶ መላኩ፣ በተለይ ባለባቸው ተደራራቢ ኃላፊነትና ተፅዕኖ ከምርጫ ፉክክሩ ሊወጡ እንደሚችሉ የሚነገረው በፍፁም የማይታሰብ ስለመሆኑ ጭምር ተናግረዋል፡፡ እንዲያውም ለእግር ኳሱ ውድቀት ዓይነተኛ ምክንያት ተደርገው የሚጠቀሱ ማለትም ስፖርቱ ሕዝባዊ መሠረት ኖሮት፣ በቢዝነስ መርህ (ሞዴል) አስተማማኝ የገቢ ምንጭ እንዳይኖረው በአሉታዊነት የሚጠቀሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመቅረፍ፣ እግር ኳሱን ዓለም አቀፍና አኅጉር አቀፍ ተወዳዳሪ ማድረግ ይቻል ዘንድ አስፈላጊው ፍኖተ ካርታ (ሮድ ማፕ) ስለማዘጋጀታቸው ጭምር ይናገራሉ፡፡

‹‹እነሆ ይህንን የአሸናፊነት አቅም ለመገንባት የሚያስችል ወሳኝ ምዕራፍ ላይ እገኛለሁ፣ ተለውጠን ለውጥ የሚያስፈልገውን ሁሉ ለመለወጥና ወደ ተሻለው የእግር ኳሳችን የዕድገት ምዕራፍ ለመሸጋገር አብረን የምንነሳበት ትክክለኛው ሰዓት አሁን ነው፤›› የሚሉት አቶ መላኩ፣ ለዚህ ፍትሐዊ፣ ተዓማኒና ተገማች ምርጫ ማድረግ ግድ እንደሚል ቢናገሩም፣ ነገር ግን ደግሞ ሥጋታቸውን ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ስፖርት በተለይም እግር ኳስ የሕዝብ፣ ለሕዝብ፣ በሕዝብ የሚከወን እንደመሆኑ፣ በተቋማዊ ለውጥ የሚፈለገውን ተጨባጭ ውጤት ለማምጣት መርሆዎች እንዳሉ የሚናገሩት አቶ መላኩ፣ አንደኛውና የመጀመርያው፣ በአዝጋሚ ሒደቶች በተገኙ ውጤቶች በመርካት ሳይሆን ሁለንተናዊ የሆነ ተቋማዊ ለውጥ ማካሄድ፣ ሁሉም ባለድርሻ በጋራ የሚሳተፉበት በተለይ መንግሥት፣ የግሉ ዘርፍና ሕዝቡ ለእግር ኳሱ ትንሳዔ በጋራ እንዲሠሩ ማድረግ፣ የመልካም አስተዳደር እጦት በተለይም የሙስና ችግር ለስፖርቱ ውድቀት ዓብይ ምክንያት በመሆኑ መልካም አስተዳደርና ተጠያቂነትን ማስፈን፣ ለስፖርቱ ዕድገት ቀጣይነት አስተማማኝ የገቢ ምንጭ እንዲኖር ስፖርቱን በቢዝነስ መርህ (ሞዴል) መምራት፣ ስፖርቱ ከሁሉም፣ ለሁሉም እንዲሆን ተደራሽነትን ማስፋት፣ ነፃና ገለልተኛ ተቋም እንዲሆን ማስቻል፣ ስፖርቱ በዕውቀት እንዲመራ እያንዳንዱ ተግባር ብቃት ባለው ባለሙያ እንዲመራ በዘርፉ በጥናትና ምርምር የታገዘ ሥራ ማከናወን፣ ምርጥ ተሞክሮዎችን መቀመርና ማስፋት የሚሉትን ጠቅሰዋል፡፡

ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ከተቋቋመበት ተልዕኮና ዝርዝር መርሆዎች አንፃር፣ ለሌሎች ፌዴሬሽኖች አርዓያ ለመሆን የሚያስችል መሠረታዊ የተቋም ግንባታ ለውጥ በማካሄድ፣ ተልዕኮውን በብቃትና በላቀ ሁኔታ መፈጸም የሚችል ተቋም ዕውን እንደሚያደርጉ ጭምር አቶ መላኩ ተናግረዋል፡፡

መሠረታዊ የለውጥ ጥናት በማካሄድ አደረጃጀቱንና የአሠራር ማሻሻያዎችን በመቅረፅ፣ በመተግበርና በቴክኖሎጂ ግብዓት በማዘመን፣ ባለሙያ በማደራጀትና በማሳተፍ ተቋሙን ብራንድ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሠሩ ያከሉት አቶ መላኩ፣ ‹‹ያለንን የሕዝብ ብዛት የሚመጥን፣ ከእግር ኳስ ታሪካችንና ወዳድነታች ጋር የሚመጣጠን፣ በዓለም አቀፍ መለኪያዎችም ምቹና ብቁ የሆኑ ስታዲየሞችና የእግር ኳስ መሠረት ልማትን በማስፋፋት፣ የማይመጥነንን ታሪክ በዘለቄታው ለመቀየር እጥራለሁ፤›› ብለዋል፡፡

ማንነት ተኮር የሆኑ አለመግባባቶች በስታዲየም ገንፍለው የወጡትበትን ጊዜ ያስታወሱት አቶ መላኩ፣ ችግሩ ምንም እንኳ በአሁኑ ወቅት በኮቪድ-19 ምክንያት የተቀየረ ቢመስልም፣ ችግሩን ዘላቂ በሆነ መልኩ ለመቅረፍ፣ ውድድሮች በስፖርታዊ ጨዋነት ተከናውነው የመልካም ግንኙነት መድረክ እንዲሆኑና ለብልሹ አሠራር ተጋላጭ እንዳይሆኑ የሚያግዙ የአሠራር ማሻሻያዎችን እንደሚተገብሩ ነው ያስረዱት፡፡

እግር ኳስ በአሁኑ ወቅት ከአዝናኝነቱ ባሻገር በቢዝነስ መርህ (ሞዴል) ከተመራ፣ በተለይም እ.ኤ.አ. ከ2011 እስከ 2017 ባለው ጊዜ ዕድገቱ 18.3 በመቶ መሆኑ፣ እንዲሁም በእንግሊዝ 2019 እና 2020 የውድድር ዓመት ኮቪድ በነበረበት ወቅት፣ ድርሻው 10.4 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን፣ ከ92 ሺሕ በላይ የሥራ ዕድል ስለመፍጠሩ ጭምር ነው ያስረዱት፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃም ያለውን ድርሻ በተመለከተ አቶ መላኩ እንደገለጹት 185 ቢሊዮን ዶላር ዓመታዊ ገቢ ሲያመነጭ፣ አማካይ በሚባሉ ስታዲየሞች ደግሞ እስከ 145 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ ገቢ እንደሚያስገኝ ነው የሚጠቅሱት፡፡ ዘርፉ ከቢዝነሱ ባሻገር በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚጫወተው ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ድርሻውም በቀላሉ የሚታይ እንዳልሆነም አልሸሸጉም፡፡

በአፍሪካ ደረጃ ያለውን የገቢ ሁኔታ በተመለከተ አቶ መላኩ፣ የግብፁ አልሃሊ 31.8 ሚሊዮን ዶላር፣ የደቡብ አፍሪካው ማሜሎዲ ሰንዳውንስ 23 ሚሊዮን ዶላር፣ የግብፁ ዛማሌክ 21.4 ሚሊዮን ዶላር ዓመታዊ ገቢ ሲያስገኝ፣ ጎረቤቶቻችን የሱዳንና የታንዛኒያ ክለቦችም፣ ማርኬቲንግና ብራንዲግ ላይ ትኩረት አድርገው እየተንቀሳቀሱ ስለመሆናቸው ጭምር ተናግረዋል፡፡

በመጨረሻም አቶ መላኩ፣ ‹‹9 ቁጥር ላይ እንድጫወት፣ ዳኛ ወይም አሠልጣኝ መሆን አይጠበቅብኝም፤›› ብለው ባለሙያን መጠቀም፣  አስፈላጊውን ሰው በተፈላጊው ቦታ መመደብ የቅድሚያ ቅድሚያ እንደሚሰጡ፣ የእሳቸውን ድርሻ በተመለከተ፣ አስተዳደራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ በማተኮር በኅብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ያለው፣ በሥርዓት የሚመራ፣ አቅሙን ያጠናከረ ብሔራዊ ፌዴሬሽን መፍጠር ዋነኛ ዓላማቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በተረፈ ፍትሐዊ ምርጫ ተደርጎ ከተሸነፉ ከአሸናፊው ጎን ሆነው እግር ኳሱን ለማገዝ ዝግጁ ስለመሆናቸው ጭምር አስረድተዋል፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...