የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዲት ብሔራዊ የደኅንነት አማካሪ ቱት ጋትሉክ ሚናሜ፣ ሰሞኑን በሱዳን በነበራቸው ጉብኝት ካደረጉት ንግግር የተወሰደ፡፡ የደኅንነት አማካሪው ከሱዳን ጊዜያዊ ሉዓላዊ ምክር ቤት ሊቀመንበር ጄኔራል አብዱልፈታህ አል ቡርሃን ጋር በሁለቱ አገሮች የፖለቲካና የድንበር ጉዳዮች ላይ በተወያዩበት ወቅት፣ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ከኢትዮጵያና ከሱዳን መሪዎች ጋር የሦስትዮሽ ውይይት የሚደረግበት ስብሰባ በማዘጋጀት የድንበር ውዝግቡን ለመፍታት ዕቅድ እንዳላቸው እንደ ነገሯቸው ዢኑዋ ከካርቱም ዘግቧል፡፡ ሱዳን የኢትዮጵያን ድንበር ጥሳ ገብታ ሰፋ ያለ መሬት በወረራ በመያዟ ምክንያት፣ በሁለቱ አገሮች መካከል መቃቃር መፈጠሩ ይታወሳል፡፡ በተለይ ኢትዮጵያ ችግሩ በዲፕሎማሲ ተፈቶ የሁለቱ አገሮች ወዳጅነት ወደ ነበረበት እንዲመለስ በተደጋጋሚ ማስታወቋ አይዘነጋም፡፡ በምሥሉ ላይ የሚታዩት የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡