Sunday, April 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊመቶ ሺዎችን የሚደርሰው ነፃ የጤና ምርመራና ሕክምና

መቶ ሺዎችን የሚደርሰው ነፃ የጤና ምርመራና ሕክምና

ቀን:

ኢትዮጵያን ከድህነት አረንቋ ለማውጣትና መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለማሠለፍ ጤንነቱ የተጠበቀ ዜጋ ማፍራት ግድ ይላል፡፡ ለዚህም ዕውን መሆን የጤናው ዘርፍ ተጠናክሮ መውጣት አለበት፡፡ የዘርፉ መጠናከር የጤና አገልግሎትን በመደበኛና በዘመቻ መልክ ተደራሽ ለማድረግ ያስችላል፡፡

በመደበኛው አገልግሎት የመክፈል አቅም ያላቸውን ዜጎች ተጠቃሚ ማድረግ የሚቻል ሲሆን፣ በዘመቻ መልክ የሚከናወነው አገልግሎት ደግሞ የመክፈል አቅም የሌላቸውን አቅመ ደካማ ዜጎች ለመድረስ ነው፡፡

አቅም የሌላቸውን በነፃ ሕክምና የመደገፉ ሥራ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ አጋርነትን የሚጠይቅና አገልግሎቱም በጥራትና በብቃት መሰጠት ያለበት ነው፡፡ ይህንንም ከግምት በማስገባት ከግል፣ መንግሥታዊ ካልሆኑና ከመንግሥታዊ ጤና ተቋማት የተውጣጡ በጎ ፈቃደኛ ባለሙያዎች ተሳታፊ የሆኑበት ነፃ የጤና ምርመራና የሕክምና አገልግሎት በዘመቻ መልክ እየተሰጠ ነው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የጤና ሚኒስትር ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) የነፃ ሕክምና መርሐ ግብሩን በዘውዲቱ አጠቃላይ ሆስፒታል ሲያስጀምሩ እንደገለጹት፣ ከነሐሴ 16 ቀን እስከ ነሐሴ 21 ቀን 2014 ዓ.ም. እየተካሄደ ባለው በዚሁ ዘመቻ ከፍለው መታከም ለማይችሉ አቅመ ደካሞች፣ የጎዳና ተዳዳሪዎችና ሌሎች ተጋላጭ የኅብረተሰብ ክፍሎች ነፃ የምርመራ፣ የሕክምናና ሌሎች የጤና አገልግሎቶች ተጠቃሚ እየተደረጉ ነው፡፡

‹‹በጎነት ለጤናችን›› በሚል መሪ ቃል በኢትዮጵያ ለአራተኛ ጊዜ እየተካሄደ ባለው በዚሁ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ዘመቻ ለ100,000 ዜጎች ነፃ የሕክምና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ታቅዷል፡፡

ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች፣ የኮሌራና ሌሎች ውኃ ወለድ በሽታዎች፣ ወባ፣ ኤችአይቪ፣ ኮቪድ-19፣ የካንሰር ሕመምና የደም ግፊት፣ የደም የስኳር መጠን፣ ከአንገት በላይ፣ የዓይን፣ የቆዳ፣ የሥነ ምግብ፣ አዕምሮ ጤናና በሌሎችም የተጠናከረ የጤና አጠባበቅ ትምህርትና የምክር አገልግሎትም እየተሰጠ ነው፡፡

የበጎነት ትግበራንና ማኅበራዊ አገልግሎትን እንደ ዋና የሥራ ዘርፍ አድርገው መሥራት ከጀመሩ መቆየታቸውን የገለጹት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ አየለ ተሾመ (ዶ/ር) በርካታ ሥራዎች ቢከናወኑም እንደ አገር የሕዝብ እሴት የሆነውን የመረዳዳት፣ የበጎነትና የማኅበራዊ አገልግሎት ባህርያትን ከማስቀጠል አንፃር ብዙ ክፍተቶች አሉት ብለዋል፡፡

በጎነትንና ማኅበራዊ ዕሴቶችን ተንከባክቦ በማቆየት ለሚቀጥለው ትውልድ የማስተላለፉ ሥራ በተሳካና ውጤታማ በሆነ መልኩ ከተከናወነ ችግሮችን መቀነስ እንደሚቻልም አክለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ ዮሐንስ ጫላ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት 17,000 ያህል የከተማዋ ነዋሪዎች በነፃ ከሚሰጠውን የምርመራና የሕክምና አገልግሎት ተጠቃሚ እንደሚሆኑ፣ ነዋሪዎችም በየአቅራቢያቸው በሚገኙ ሆስፒታሎች፣ ጤና ጣቢያዎች፣ አረጋውያንና ሕፃናት ማሳደጊያ ማዕከላት እየቀረቡ የአገልግሎቱ ተቋዳሽ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ቢሮው በርካታ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን ገልጸው፣ በአሁኑ ወቅት ለአንድ ሳምንት ያህል እየተካሄደ ባለው በዚሁ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተጠቃሚ የሚሆኑት ነዋሪዎችም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙና ከፍለው መታከም የማይችሉ አቅመ ደካሞች ብቻ መሆናቸውን አሳስበዋል፡፡

ከቂርቆስ ክፍለ ከተማ ተውጣጥተው በዘውዲቱ ሆስፒታል የነፃ ምርመራና የሕክምና አገልግሎት ለማግኘት በመጠባበቅ ላይ ከነበሩት ወገኖች መካከል ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ አንዲት እናት በሰጡት አስተያየት፣ አገልግሎቱ ጥሩ ሆኖ ሳለ በዓመት አንዴ፣ እንዲያውም ለአምስት ቀናት ብቻ መሆኑ የተደራሽነቱንና አገልግሎቱን ፋይዳ እንደሚያሳሳው ገልጸዋል፡፡

በቀጣዩ ዓመት የተጠቃሚዎችን ቁጥር ከፍ በማድረግና የአገልግሎት ጊዜውንም በማራዘም ተደራሽነቱ እንዲሰፋ ቢደረግ መልካም ነው የሚል እምነት እንዳላቸውም ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ከሴራ ፖለቲካ በስተጀርባ ጥቅማቸውን የሚያስጠብቁ ኃይሎች

በመኮንን ሻውል ወልደ ጊዮርጊስ የአፄ ቴዎድሮስ መንግሥት የወደቀው ከመቅደላ በፊት...

ስለዘር ፖለቲካ

በሀብታሙ ኃይለ ጊዮርጊስ  ‹‹በቅሎዎች ዝርያችን ከአህያ ነው እያሉ ይመፃደቃሉ›› የጀርመኖች...

አማርኛ ተናጋሪዋ ሮቦት

በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው የሳይንስ ሙዚየም፣ ሚያዝያ 2 ቀን...

ወዘተ

ገና! ከእናቴ ሆድ ሳለሁ፤ ጠላት ሲዝትብኝ ሰምቻለሁ። በዳዴ ዘመኔም፣ በ'ወፌ ቆመችም!'፤ አውዴ ክፉ ነበር...