Friday, April 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

መንግሥት ለግንባታ ግብዓቶች የገበያ ችግር ትኩረት እንዲሰጥ ተጠየቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የዋጋ ንረት በከፍተኛ ሁኔታ ተፅዕኖ እያሳደረባቸው ከሚገኙ የኢኮኖሚ ዘርፎች ውስጥ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ተጠቃሽ ነው፡፡ ኢንዱስትሪው ለአገራዊ ኢኮኖሚው አስተዋጽኦ ያለው ድርሻ ከፍተኛ የሚባል የነበረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ግን ከዋጋ ንረት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ችግር ውስጥ መዘፈቁ እየተነገረ ነው፡፡ 

ቀድሞም ቢሆን ብልሹ አሠራሮች የነበሩበት ይህ ዘርፍ ለተከታታይ ዓመታት በኮንስትራክሽን ግብዓቶች ላይ ፍጹም ተጠባቂ ባልሆነ ሁኔታ የታየው የግብዓቶች የዋጋ ጭማሪ ኢንዱስትሪውን በእጅጉ ስለመጉዳቱ የኢትዮጵያ ኮንትራክተሮች ማኅበር በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቆይቷል፡፡ 

የማኅበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ግርማ ሃብተማርያም (ኢንጂነር) እንደገሉጸትም በተለይ ባለፉት ሁለት ሦስት ዓመታት በግንባታ ግብዓቶች ላይ እየታየ ያለው የዋጋ ጭማሪ ብዙ ፕሮጀክቶች እንዲቋረጡ ምክንያት ከመሆኑም በላይ ብዙ ኮንትራክተሮችንም ለኪሳራ የዳረገ እስከመሆን ደርሷል፡፡ ችግሩ በዚህ ብቻ የማይገለጽ መሆኑን የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ በግንባታ ዕቃዎች መወደድ ሳቢያ የኮንስትራክሽን ድርጅቶች ብዙ ሠራተኞችን ለመቀነስ መገደዳቸውንም ይጠቁማሉ፡፡ 

ኪሳራ ውስጥ ላለመግባት የዋጋ ጭማሪውን ተቋቁመው በእጅ ያሉ ሥራዎቻቸውን ለማጠናቀቅ የሚተጉትም ቢሆኑ ዕድለኛ ሆነው ሥራቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ቀጣይ ህልውናቸው ምን ሊሆን እንደሚችል እንኳን ለመገመት ያዳግታል ይላሉ፡፡ በሁሉም የግንባታ ዕቃዎች ላይ ዋጋ ጭማሪው ተገማች ያልሆነ መሆኑን የሚጠቅሱት አቶ ግርማ በተለይ ብረትና ሲሚንቶ ዋጋውም ሆነ አጠቃላይ የግብይት ሒደቱ የተበላሸ ሆኖ መቀጠሉ ለዚህም ሁነኛ መፍትሔ ሊበጅ አለመቻሉ ችግሩን የበለጠ እንዳባባሰው አመልክተዋል፡፡

ማኅበራቸው ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ ከዋጋና ከግብይት ጋር የተያያዙ ችግሮች እንዲፈቱ ለመንግሥት አቤቱታ የቀረበ ቢሆንም መፍትሔ የተባሉ ውሳኔዎች በተግባር ሊቀየሩ ባለመቻላቸው በተለይ የብረትና የሲሚንቶ የግብይት ሥርዓት ብልሽት ከድጡ ወደ ማጡ እየሆነ መሄዱንም በምሬት ገልጸዋል፡፡ 

ሌላው ቀርቶ በቅርቡ በተከታታይ የሲሚንቶ ጉዳይ መፍትሔ ተበጅቶለታል፣ የተለያዩ ዕርምጃዎች ተወስደዋል እየተባለ እንኳን የታየ ለውጥ አለመታየቱን ፤ ይባስ ብሎ አሁን ላይ የአንድ ኩንታል ሲሚንቶ ዋጋ 1,800 ብር መድረሱን በምሳሌት ጠቅሰዋል፡፡ 

አሁን ደግሞ በብረት ገበያ ውስጥ ተመሳሳይ ችግር እየታየ ስለመሆኑ የሚጠቁሙት ያነጋገርናቸው ኮንትራክተሮች የዋጋ ጭማሪው ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የብረት ግብይት ሕገወጥ አሠራሮች እየታዩበት መሆኑን ይገልጻሉ። የብረት ዋጋው ዓለም አቀፍ ገበያን ያላገናዘበ እየሆነ መምጣቱንም ያስረዳሉ፡፡ እንደ አቶ ግርማ ገለጻ ከሆነ ደግሞ ከአራትና አምስት ዓመት በፊት የገባ ብረት ሳይቀር ተሸሽጎ ቆይቶ አሁን በተጋነነ ዋጋ በመሸጥ ላይ ነው።

አምስትና ስድስት ዓመት አንድ ኪሎ አርማታ ብረት 20 እስከ 25 ብር ያስገቡ ሰዎች አሁን 122 ብር እየሸጡ ነው መባሉንም ይጠቅሳሉ፡፡

‹‹በአጠቃላይ የዚህን አገር ገበያ አለመጠየቅ ይሻላል፤›› የሚሉት አቶ ግርማ በገበያው ብዙ ነገር እየተበላሸ በመሆኑ ኢንዲስትራውን እየጎዳና ሠራተኞችንም እየተፈናቀለ እንደሚገኝ በመጥቀስ አፋጣኝ መፍትሔ ይበጅለት ይላሉ፡፡ በዋግ ጭማሪና በተወነባበደው የገበያ ሥርዓት ብቻ ከደረጃ አንድ ኮንትራክተሮች ውስጥ ጥቂት የማይባሉ ሥራ አጥተው አራትና አምስት ዓመት እንዳለፋቸው ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ለባለሙያዎች ክፍያ እየከፈሉ የተቀመጡ ቢሆንም አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ማግኘት አለመቻላቸውን ጠቅሰዋል፡፡ 

የኮንስትራክሽን ሥራ ተቀዛቅዟል እየተባለ በሌላ በኩል ደግሞ የግንባታ ግብዓቶች ዋጋ እያሻቀበ መምጣት ብዙዎችን እያነጋገረ ሲሆን፣ በተለይ የብረትና የሲሚንቶ ዋጋ ፈጽሞ አልቀመስ ያለበት ምክንያት ግንባታዎች በዝተው ሳይሆን የግብይት ግብዓቶች መበላሸት ያመጣው ችግር መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ የአገር ውስጥ ብረት አምራቾች ግብዓት የሚሆናቸውን ጥሬ ዕቃ ከውጭ የሚያስመጡ ቢሆንም በትክክል ወጪያቸውን አስልተው ትክክለኛ የትርፍ ህዳግ ይዘው እየሸጡ ነው ብሎ ለማመን እንደሚከብድ አቶ ግርማ ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን ከውጪ የሚመጣው የጥሬ ዕቃው ቀረጥ ይታወቃል ማምረቻ ወጪያቸውና የሚሸጥበትን ዋጋ በአማካይ መገመት ቢቻልም የተጋነነ ትርፍ ተይዞ ሲሸጥ መንግሥት ቁጥጥር አለማድረጉ ትልቅ ችግር እየፈጠረ እንደሆነ ይገልጻሉ።

ስለዚህ አጠቃላይ የማምረቻ ዋጋው እየታወቀ ከውጭ የሚገባውም ከማንም የተሸሸገ ሳይሆንም መንግሥት ገበያውን ለማረጋጋት የሚያስችል ዕርምጃ ባለመወሰዱ ችግሩ መባባሱንም ያመለክታሉ፡፡ ዋጋን ለመቆጣጠር የተቋቋሙ እንዲሁም የሙስና ኮሚሽን አሉ ቢባልም እነዚህ ተቋማት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ባለመወጣታቸው ለችግሩ መባባስ ተጠቃሽ ያደርጋሉ፡፡ 

በአሁኑ ወቅት የአርማታ ብረት ከውጭ በኮንትሮባንድ እየገባ መሆኑን በመጥቀስ ገበያው ጤናማ እንዳልሆነ ያነጋገርናቸው ገልጸዋል። እንደ አቶ ግርማ ምልከታም ብረትን የሚያህል ነገር በኮንትሮባንድ መግባቱ የግብይት ሥርዓቱን መስመር ማስያዝ ካለመቻል የሚመነጭ ነው፡፡ 

‹‹በቀደመው ጊዜ አንድ ቤተሰብ ነበር ብረት የሚያስመጣው›› ያሉት አቶ ግርማ አንድ ሰሞን ደግሞ ደረሰኝ አትጠይቁን የግንባታ ቦታ (ሳይት) ድረስ በቅናሽ እናመጣለን የሚሉ ሁሉ መምጣታቸውን በመጥቀስ የችግሩን ደረጃ ያሳያሉ፡፡ 

አንድ የደረጃ አንድ ኮንትራክተር ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ የብረት ዋጋ የቀነሰ ቢሆንም ኢትዮጵያ ውስጥ እየተሸጠበት ያለው ዋጋ አሁንም ሊቀንስ አለመቻሉና በሕገወጥ መንገድ የሚገቡ የብረት ምርቶች ገበያ ውስጥ ችግር እየፈጠሩ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ 

ከወቅታዊው የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው እንቅስቃሴና በተለይ ከሲሚንቶና ብረት ግብይት ጋር በተያያዘ ያነጋገርናቸው አንድ የአማካሪ ድርጅት ባለቤትና መምህር ችግሩ አሳሳቢ መሆኑንና በርካታ ኮንትራክተሮችን ከጨዋታ ውጪ እያደረጋቸው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ነገሩን ጠቅለል አድርጎ ለተመለከተው አንዳንዴ ምርቱ ጠፍቶ ሳይሆን ገበያውን ጉልበተኞች ይዘውት ነው የሚል እምነት አላቸው፡፡ መፍትሔ ተወስዷል ተብሎ ውጤት የማይገኘውም ገበያ ውስጥ ያሉ ጉልበተኞች የሚፈጥሩት ቀውስ ነው ብለው ያምናሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች