Saturday, December 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ከተቋቋመ ለመጀመርያ ጊዜ አተረፍኩ አለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በ2014 በጀት ዓመት በዓለም አቀፍ ጫናዎችና ኢትዮጵያ ውስጥ በተከሰተው ጦርነት በተፈጠሩ ተግዳሮቶች ውስጥ ያለፈው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን፣ ከተመሠረተ ወዲህ ለመጀመርያ ጊዜ ማትረፉን አስታወቀ፡፡

ኮርፖሬሽኑ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ከሼዶች ኪራይ፣ ከለማ መሬት ሊዝ፣ ከምክርና ሥልጠና፣ እንዲሁም ከሌሎች አገልግሎቶችና ወጪ ቆጣቢ አሠራሮች 101.1 ሚሊዮን ብር ትርፍ ለማግኘት አቅዶ 340.3 ሚሊዮን ብር ማትረፉን ገልጿል፡፡

አገልግሎት እየሰጡ ከሚገኙት የኢንዱስትሪ ፓርኮች 1.2 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡ የተገለጸ ሲሆን፣ በበጀት ዓመቱ 1.4 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ አቅዶ ሲንቀሳቀስ እንደነበር ተጠቁሟል፡፡

በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የተሰበሰበው ገቢ ኮርፖሬሽኑ ከተመሠረተበት ጊዜ (ያለፉት ሰባት ዓመታት) አንስቶ ከነበሩት አፈጻጸሞች በመጠኑ ከፍተኛ መሆኑን፣ የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሳንዶካን ደበበ በዋና መሥሪያ ቤታቸው ሐሙስ ነሐሴ 19 ቀን 2014 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ባለፉት ዓመታት በኪሳራ ውስጥ ያለፈ መሆኑን፣ ለአብነትም በ2013 በጀት ዓመት የ70 ሚሊዮን ብር ኪሳራ የደረሰበት ተቋም እንደነበር አቶ ሳንዶካን አያይዘው ገልጸዋል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ የኮርፖሬሽኑ ገቢ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የላቀ እንዲሆን ካስቻሉት ጉዳዮች ውስጥ፣ የኢንዱስትሪ ፕሮጀክት አገልግሎት (ኢንዱስትሪያል ፕሮጀክት ሰርቪስ) በሚል ካለፉት 38 ዓመታት በላይ በዘርፉ የማማከር፣ የአዋጭነት ጥናት፣ የሀብት ግመታ፣ እንዲሁም የሥልጠና ሥራዎችን ሲሠራ የቆየው የመንግሥት የልማት ድርጅት በመንግሥት ውሳኔ እ.ኤ.አ. በ2019 ወደ ኮርፖሬሽኑ ተጠቃሎ ሰፊ አገልግሎት በማቅረቡ ጭምር ነው ብለዋል፡፡ አገልግሎቱ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ በተናጠል ካስመዘገበው ገቢ ከፍተኛውን በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት እንዳገኘ ታውቋል፡፡

በትርፍ ረገድ ለተገኘው ውጤት ኮርፖሬሽኑ በሁለት ዓይነት መንገዶች የተገበራቸው የሪፎርም ሥራዎች እንደነበሩት ያስረዱት አቶ ሳንዶካን፣ የመጀመርያው የበጀት አጠቃቀም፣ የአሠራር ሥርዓት፣ ወጪዎችንና መሰል ጉዳዮችን ለማሻሻል የተሠራው ሥራ ነው ብለዋል፡፡ የንግድ (ኮሜርሻል) ኢንቨስትመንት ከመሆን ይልቅ የፖሊሲ ኢንቨስትመንት በሆነው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት አገልግሎት፣ ከፍተኛ ድጎማ ተደርጎ የሚያቀርባቸውን አገልግሎቶች በማስፋት 340.3 ሚሊዮን ብር ትርፍ መገኘቱን ተናግረዋል፡፡

በ2014 በጀት ዓመት ዓለም አቀፍ ጫናዎች፣ በአገር ውስጥ የተከሰቱ የፀጥታ ችግሮች፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ ከአጎዋ ነፃ ዕድል መሰረዝ፣ በሩሲያና በዩክሬን መካከል በተፈጠረው ጦርነት ሳቢያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢንዱስትሪ ግብዓቶች ዋጋ መናር ኮርፖሬሽኑ በበጀት ዓመቱ አጋጠሙኝ ካላቸው ተግዳሮቶች ተጠቃሾቹ መሆናቸውን አቶ ሳንዶካን በሰጡት መግለጫ አስረድተዋል፡፡

በኢንዱስትሪ ፓርኮች በበጀት ዓመቱ 14 ሼዶችን ለማከራየት ታቅዶ 13 ሼዶች ማከራየት መቻሉ የተገለጸ ሲሆን፣ በጠቅላላው ኮርፖሬሽኑ ካሉት 177 ሼዶች 15 የመቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሼዶችን ሳይጨምር 136 ሼዶች በባለሀብቶች የተያዙ መሆናቸውንና የማምረቻ ሼዶች የመያዝ ምጣኔ 83.9 መድረሱ ተመላክቷል፡፡

     ኮርፖሬሽኑ 357 ሚሊዮን ዶላር ግምት ያላቸው ምርቶች ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ቀርበዋል ያለ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ 161 ሚሊዮን ዶላር ግምት ያላቸው ምርቶች የቀረቡት ለአገር ውስጥ፣ 196 ሚሊዮን ዶላር ግምት ያላቸው ምርቶች ደግሞ ለውጭ መላካቸው ታውቋል፡፡ ይህ ይሆነውም የመቀሌ፣ የባህር ዳርና የሰመራ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ሥራ ላይ ባልነበሩበት ሁኔታ ውስጥ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

ከአገር ውስጥ ምርት አቅራቢ ድርጅቶችና አርሶ አደሮች ጋር በተፈጠረ የገበያ ትስስር ከ69 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጣ ግብዓት፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ለተሰማሩ የውጭ ኩባንያዎች በበጀት ዓመቱ መቅረቡን አቶ ሳንዶካን በመግለጫቸው ተናግረዋል።

 በሁሉም የኢንዱስትሪ ፓርኮች ለ75,200 ዜጎች በ2014 ዓ.ም. የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታስቦ እንደነበር፣ ነገር ግን ማሳካት የተቻለው 57,189 እንደሆነና እስከ ሰኔ 30 ቀን 2014 ዓ.ም. ባለው መረጃ መሠረት በኢንዱስትሪ ፓርኮች በጠቅላላው 80,867 የሥራ ዕድል እንደተፈጠረላቸው የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡

የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነትን ተከትሎ አሜሪካ ለአፍሪካዊያን የሰጠችው ከኮታና ከቀረጥ ነፃ የንግድ ዕድል (አጎዋ) መታገዷ ኢትዮጵያን እንደጎዳ የገለጹት አቶ ሳንዶካን፣ ነገር ግን ዕገዳውን ተከትሎ ከአገር የተሰደደ ኩባንያ አለመኖሩን አረጋግጠዋል።

‹‹የታገደው የአጎዋ ዕድል እንዲነሳ ከአሜሪካ መንግሥት ጋር ምክክሮችና ውይይቶች ተካሂደዋል፤›› ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ከዚያው ጎን ለጎን የገበያ ዕድሎችን ለማስፋት ሥራዎች መቀጠላቸውን ጠቁመዋል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች