Monday, December 4, 2023

የአማራ ክልል መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ሠራተኞች የገቢ ግብር ሊሰበስብ ነው

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶችና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ በሥራቸው ከሚገኙ ሠራተኞች የሚቆረጠውን የገቢ ግብር ለክልሉ እንዲከፍሉ ትዕዛዝ ተላለፈ፡፡

የክልሉ የገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ፀጋ ጥበቡ (ዶ/ር) ማክሰኞ ነሐሴ 17 ቀን 2014 ዓ.ም. በጻፉት ደብዳቤ፣ ‹‹እነዚህ ሠራተኞች ተቀጥረው ከሚያገኙት ገቢ ላይ የሥራ ግብር መክፈል ያለባቸው ለክልሉ እንደሆነ ታምኖበታል፤›› ሲሉ የክልሉን የገቢ መምርያዎች አዘዋል፡፡ ትዕዛዙ የተላለፈላቸው የክልሉ 12 የዞንና ስምንት የከተማ አስተዳደር ገቢዎች መምርያዎች አፈጻጸሙን ‹‹በጥብቅ›› እንዲከታተሉም ኃላፊው በደብዳቤው አሳስበዋል፡፡

የቢሮው ኃላፊ ፀጋ (ዶ/ር) በክልሉ የሚገኙ ‹‹አንዳንድ›› የገቢዎች መምርያዎች መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅት ሠራተኞች የገቢ ግብር መሰብሰብ ላይ ትኩረት ሰጥተው እየሠሩ ባለመሆኑ፣ ይኼ ደብዳቤ እንደተላለፈ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ከዚህም ባሻገር በክልሉ ሠራተኞች ቀጥረው የሚያሠሩ የገቢ ግብር ግን ለፌዴራል መንግሥት የሚከፍሉ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዳሉ ኃላፊው ሲያስረዱ፣ ‹‹አንዳንዶቹ ደግሞ በተመሠረቱበት በፌዴራል አካባቢ ነው የምንከፍለው ብለው የሚከፍሉ አሉ፡፡ [ደብዳቤው የተላላፈው መምርያዎች] እነሱን ሁሉ አግባብተው ማስከፈል እንዲችሉ ነው፤›› ብለዋል፡፡

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን መረጃ እንደሚያሳየው፣ ዋና መሥሪያ ቤታቸውን በአማራ ክልል ያደረጉ ቢያንስ 117 አገር በቀልና ሰባት የውጭ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ፈቃድ ወስደዋል፡፡ ይኼ ቁጥር ዋና መሥሪያ ቤታቸውን በሌሎች አካባቢዎች አድርገው በክልሉ የተለያዩ ፕሮጀክቶች የሚያከናውኑ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን አያካትትም፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት ቢያንስ 50 በመቶ የሚሆነውን ወጪውን ከሚሰበሰብው ገቢ ለመሸፈን ያቀደው የክልሉ መንግሥት፣ ከዚህ ቀደም እምብዛም ያልታዩ የግብር ዘርፎች ላይ ትኩረት አድርጓል፡፡ ከሳምንት በፊትም የሃይማኖት ተቋማት ከሕንፃ ኪራይና ከሆቴል ንግድ ሥራ ከሚያገኙት ገቢ ላይ ግብር እንዲከፍሉ የሚያዝ ደብዳቤ፣ ለስምንት ሪጆኦፖሊታን ከተሞች ገቢዎች መምርያዎች መተላለፉ ይታወሳል፡፡

የክልሉ ገቢዎች ቢሮ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን አስመልክቶ በሥሩ ለሚገኙ መመርያዎች አዲሱን ትዕዛዝ ያስተላለፈው፣ በ2008 ዓ.ም. የወጣውን የክልሉን የገቡ ግብር አዋጅና በ2013 ዓ.ም. የፀደቀውን የዚሁ አዋጅ ማሻሻያ በመጥቀስ ነው፡፡ የገቢ ግብር አዋጅ ማሻሻያ 276/2003 አንቀጽ ሁለት ንዑስ አንቀጽ 2 (ሀ) ማንኛውም ሰው በክልሉ ወስጥ በሚያገኘው በማናቸውም ገቢ ላይ የገቢ ግብር ተፈጻሚ እንደሚሆን መደንገጉ በደብዳቤው ላይ ተጠቅሷል፡፡ መጀመርያ የወጣው የገቢ ግብር አዋጅ 240/2008 ደግሞ በአንቀጽ አምስት ንዑስ አንቀጽ አንድ ነዋሪነትን ሲደነግግ፣ በክልሉ ዞኖች ከተማ ውስጥ የሚገኝ ማንኛውም ግለሰብና ድርጅት፣ እንዲሁም የክልሉን መንግሥት እንደሚያካትት ያስታውቃል፡፡

የገቢዎች ቢሮው ከዚህ አዋጅ ባሻገር መንግሥታዊ የሆኑት ድርጅቶች በክልሉ ውስጥ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ሲያከናውኑ፣ ለሠራተኞቻቸው የሚከፍሉትን ደመወዝና የሥራ ማስኪጅያ ወጪያቸው ለክልሉ ብለው ከመደቡት ሀብት የሚከፈል መሆኑ በምክንያትነት ተጠቅሷል፡፡

‹‹ድርጅቶቹ ሠራተኞችን ቀጥረው ለክልሉ ተብሎ ከተመደበው ሀብት ውስጥ የሚከፈል በመሆኑ፣ እነዚህ ሠራተኞች ተቀጥረው ከሚያገኙት ገቢ ላይ የሥራ ግብር መክፈል ያለባቸው ለክልሉ መሆን እንዳለበት ታምኖበታል፤›› የሚል ሐሳብ በደብዳቤው ላይ ሰፍሯል፡፡

ደብዳቤው አክሎም መምርያዎች ለክልሉ ብለው ከመደቡት ሀብት ውስጥ ሠራተኞችን ቀጥረው የሚያሠሩ መሆንናቸው እየተለየ የሥራ ግብር እንዲያስከፍሉ ትዕዛዝ ተላልፏል፡፡

በገቢዎች ሚኒስቴር የታክስ ሥርዓት ማጣጣምና የክልሎች ድጋፍ ዳይሬክተር አቶ መሐመድ ሃሶ፣ ክልሉ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ሠራተኞች የሚቆረጥ የገቢ ግብር ለመሰብሰብ ትዕዛዝ ማስተላለፉ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ተገቢ መሆኑን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ሕገ መንግሥቱ በክልሎች ውስጥ ከሚገኙ ድርጅቶች የሚቆረጥ የሠራተኞች የገቢ ግብር የመሰብሰብ ሥልጣን የክልሎች እንደሆነ መደንገጉንና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በዚሁ ውስጥ እንደሚካተቱ አስረድተዋል፡፡ ነገር ግን ሕገ መንግሥቱ ይኼንን ቢደነግግም አተገባበር ላይ ‹‹ክፍተቶች›› መኖራቸውን አክለዋል፡፡

‹‹መሬት ላይ ክፍተት ሊኖር ይችላል፣ በተለይ ከለውጥ በኋላ ባለው አካሄድ እነዚህ ነገሮች እየተሻሻሉ የሕጉ ዕሳቤ እየመጣ ነው፤›› ብለዋል፡፡

የሕግ ባለሙያው ታደሰ ሌንጮም (ዶ/ር) ይኼ ገቢ የክልሎች መሆኑንና አተገባበር ላይ ክፍተቶች መኖራቸውን ይስማሙበታል፡፡ ‹‹በቅርቡ በፌዴራል የተመዘገበ አንድ የውጭ ኩባንያ የሠራተኞቹን ገቢ ግብር ለፌዴራል ሲከፍል ቆይቶ የሚሠራበት ሐዋሳ ከተማ ደግሞ ክፍለኝ ብሎት አለመግባባት ነበር፤›› ሲሉም ምሳሌ ጠቅሰዋል፡፡

ይሁንና የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ይኼንን ትዕዛዝ ሲያስተላልፍ፣ ድርጅቶቹ ደመወዝ የሚከፍሉት ለክልሉ ከሚመድቡት ሀብት ላይ መሆኑን በምክንያትነት መጥቀሱን አይስማሙበትም፡፡

‹‹የሕግ አረዳዱ ግን ልክ አይደለም፤›› ያሉት ታደሰ (ዶ/ር)፣ የሠራተኛ ገቢ ግብር ለፌዴራል መንግሥት የሚከፍሉት እንደ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያሉ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ለክልሉ ሀብት ስለመደቡ ተመሳሳይ ጥያቄ ማንሳት እንደማይቻል አስረድተዋል፡፡  

ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የሚባሉት አገሮች አባል የሆኑባቸው እንደ አፍሪካ ኅብረትና የተባበሩት መንግሥታት ያሉት ድርጅቶች ናቸው፡፡ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 96 ንዑስ አንቀጽ ሁለት በዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተቀጣሪዎች ላይ የሥራ ግብር የመጣልና የመሰብሰብ ሥልጣን የፌዴራል መንግሥት መሆኑ ተቀምጧል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -