Wednesday, October 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የካሳና የመሬት ይገባኛል ጥያቄዎች ለኢንዱስትሪ ፓርኮች ፈተና ሆነዋል ተባለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በሚያስተዳድራቸው ፓርኮች ላይ የሚስተዋሉ የካሳና የይገባኛል ጥያቄዎች፣ አሁንም ፈተና እንደሆኑበት አስታወቀ፡፡

የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሳንዶካን ደበበ እንደተናገሩት፣ የካሳና የይገባኛል ጥያቄዎች ላለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ ሳይሆን፣ ኮርፖሬሽኑ ሀብት ማስተዳደር ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ መጠናቸው ይቀያየር እንጂ አሁንም እንደቀጠሉ ነው፡፡

ኮርፖሬሽኑ በዚህ ወቅት ትልቅ ሥጋት የሆነበት በተወሰኑ አካባቢዎች ያሉ የካሳ ጥያቄዎች መልካቸውና መጠናቸው ማየሉ ነው ያሉት አቶ ሳንዶካን፣ ይህ ክስተት ከሚስተዋልባቸው አንዱ የአዲስ አበባ ከተማ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሁሉም የኢንዱስትሪ ፓርኮች የተሰጣቸው መሬት የሚታወቅና የይዞታ ማረጋገጫ ያላቸው ቢሆኑም፣ ነገር ግን የኢንዱስትሪ ፓርኮቹን ይዞታ በማስከበር ረገድ እክሎች ማጋጠማቸው ከዚህ ቀደም ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ በተጨማሪም በአዲስ አበባና በድሬዳዋ የከተማ አስተዳደሮች የሚገኙ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በማስተዳደር ረገድ እክሎች መጋጠማቸው ሲገለጽ ነበር፡፡

አቶ ሳንዶካን እንዳስረዱት፣ በአዲስ አበባ ከተማ አራት ኢንዱስትሪ ፓርኮች አሉ፡፡ እነዚህም ቂሊንጦ፣ ቦሌ ለሚ፣ አይሲቲ ፓርክ፣ እንዲሁም አዲስ ኢንዱስትሪ መንደር ናቸው፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ቂሊንጦ 279 ሔክታር፣ ቦሌ ለሚ ምዕራፍ አንድና ሁለት ከ300 ሔክታር በላይ፣ እንዲሁም አይሲቲ ፓርክ ከ200 ሔክታር በላይ መሬት ላይ ያረፉ ናቸው፡፡

የፓርኮቹ መሬቶች ኮርፖሬሽኑ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር ስምምነት ፈርሞ ሊዝ ያደረጋቸው መሆናቸውን የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ባሉት የፖለቲካ ሁኔታዎች፣ በተቋማት የማስፈጸም አቅምና መሰል ጉዳዮች፣ የይገባኛል ጥያቄዎችና የመሬት ጥያቄዎች (ወረራዎች) እየተስፋፉ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

ይህንን ለማስቆም ኮርፖሬሽኑ የውስጥ የፀጥታ አቅሙን ከማሳደግ በተጨማሪ  የፌዴራል ፖሊስ ለኢንዱስትሪ ፓርኮች ብቻ ተለይቶ ዲፓርትመንት እስከ ማቋቋም ደረጃ ተደርሷል ተብሏል፡፡ በአሁኑ ወቅት በሁሉም የኢንዱስትሪ ፓርኮች ከውስጥ ጥበቃና ከክልል ልዩ ኃይሎች በተጨማሪ፣ የፌዴራል ፖሊሶች በፓርኮች ውስጥ እንደሚኙ ተገልጿል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ይህን ያደረገው ከግለሰቦችና ከአካባቢው ማኅበረሰብ የተሳሳተ ዕይታ የሚመነጩ ክፍተቶች ካሉ በመግባባት ለመፍታት፣ በፀጥታ መዋቅሩ የሚመለሱትን ደግሞ በዚያው አግባብ ለመፍታት በማሰብ መሆኑን አቶ ሳንዶካን ተናግረዋል፡፡

የኮርፖሬሽኑ ትልቁ ሀብት መሬትና መሠረተ ልማት በመሆኑ ከመሬት ወረራና ከካሳ ክፍያ ጋር ያሉ ከፍተኛ ጫናዎች የኢንዱስትሪ ፓርኮች በልማት ሥራቸው ላይ ትኩረት አድርገው እንዳይሠሩ ፈተና ሆነው መቆየታቸው ተገልጾ፣ ድርጊቱ በመልክና በመጠን እንደተበራከተ ተጠቁሟል፡፡

‹‹በአዲስ አበባ ከተማ ከአስተዳደሩ የምንፈልጋቸውን ድጋፎች በበቂ ሁኔታ እያገኘን ነው የሚል ግምገማ የለንም፤›› ያሉት አቶ ሳንዶካን፣ ተከታታይ ውይይቶች መደረጋቸውን፣ ጥረቶች በስፋት ሲደረጉ መቆየታቸውንና በቂ አለመሆናቸውን አስገንዝበዋል፡፡

በዚህ ወቅት የኮርፖሬሽኑ ቦርድ የወሰደው አንዱ ትልቁ ኃላፊነት ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመሆን ማኅበረሰቡ ሳይጎዳ የሚያነሳው ጥያቄና የሚገባው ምላሽ ካለ ምላሽ እየተሰጠ፣ ነገር ግን ጉዳዮቹ የኢንዱስትሪ ከባቢ ሁኔታ በማይረብሽ ሁኔታ መፈታት አለበት የሚል ነው ተብሏል፡፡

ከካሳ ክፍያና መሬት ወረራ ጋር የተያያዙትን ችግሮች ለማረም ከፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽኑ ቦርድ ጋር ሰፊ ሥራ እየተሠራ ነው ያሉት  ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ በሚቀጥሉት ዓመታት መፍትሔ እየተበጀለት ካልተሄደ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ በሚሠሩትም ሆነ በኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ህልውና ላይ ትልቅ ተፅዕኖ የሚፈጥረው የመሬት ወረራና ካሳ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡   

በአዲስ አበባ ከተማ ከታችኛው እስከ ላይኛው መዋቅር  ያለውን አደረጃጀት በተለያየ አግባብ ለማነጋገር የተደረገውን ጥረት የተናገሩት አቶ ሳንዶካን፣ ውጤት ያመጡና “የተሻገርናቸው” እንዳሉ ሁሉ እስካሁን ደግሞ ተስፋ ያልተገኘባቸው ችግሮች ስለመኖራቸው አመላክተዋል፡፡

በ2015 የበጀት ዓመት ከዚህ ቀደም በተጀመረው ውይይት ችግሮችን ለመፍታት ጥረት እንደሚደረግ የተነገረ ሲሆን፣ ነገር ግን ጉዳዩ  ከኮርፖሬሽኑ አቅም በላይ ከሆነ መንግሥት ገብቶበት ይፈታል የሚል እምነት መያዙ ተብራርቷል፡፡

በድሬዳዋ የኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ የውኃ ጉድጓዶችን ለመቆፈር የውኃ መስመር በሚያልፍበት ቦታ ላይ ያሉ ለካሳና ለይገባኛል ጉዳዮች ምላሽ ለመስጠት ጊዜ መውሰዱን፣ በዚህም ምክንያት ፓርኮቹ ውስጥ የሚገኙ አልሚዎችን ወደ ሌሎች ፓርኮች እስከ መዘዋወር ያደረሰ ችግር ተፈጥሮ እንደነበር ከዚህ ቀደም መገለጹ ይታወሳል፡፡

በድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከውኃና ከመንገድ ጋር የተያያዘ ችግር እንደነበረበት ተገልጾ፣ የከተማ አስተዳደሩ በተሻሻለ መነሳሳትና ቅንጅት ችግሩን ለመፍታት ጥረት እያደረገ ነው ተብሏል፡፡ ከዚህ ቀደም በከተማው ከካሳ ችግር ጋር ተያይዞ ለሁለት ዓመታት የቆየው የውኃ አቅርቦት ችግር፣ ከመንገድ ግንባታ ጋር ተያይዞ ያልተቋጨው ጉዳይ የነፃ ቀጣናው ሥራ ከመጀመሩ ጋር ተያይዞ በአጭር ጊዜ ውስጥ መፍትሔ ይሰጠዋል ተብሏል፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ የከተማ አስተዳደሮች ለፓርክ ልማት የሚሆን መሬት ካሳ ከፍለው፣ የምትክ መሬት ካስፈለገ ሰጥተውና ከይገባኛል ነፃ አድርገው ያዘጋጃሉ የሚል ድንጋጌ ስለመስፈሩ ሪፖርተር በጉዳዩ ላይ ያነጋገራቸው የኮርፖሬሽኑ ኃላፊዎች መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ ኮርፖሬሽኑ ከእያንዳንዱ የከተማ አስተዳደር ጋር መሬትን በፕላን ፎርማት ሲረከብ የሚገባ ውል እንዳለ፣ በውሉ ላይ እንደተቀመጠው የካሳ ክፍያና መሬትን ከይገባኛል ነፃ አድርጎ የማስረከብ ኃላፊነት የከተማ አስተዳደሮች መሆኑ ተገልጾ ነበር፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች