Saturday, December 9, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

መንግሥት የተፈጥሮ ጋዝ የሚያወጡ ኩባንያዎችን ራሱ እየመረጠ ሊጋብዝ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ሰባት ትሪሊዮን ኪዩቢክ ጫማ የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት መኖሩን ገልጿል

በኢትዮጵያ ደቡብ ምሥራቅ ክፍል በኦጋዴን ቤዚን ስላለው የተፈጥሮ ጋዝና ነዳጅ ክምችት ከአሜሪካው ኔዘርላንድ ስዌል ኤንድ አሶሼትስ ኢንክ ኩባንያ የማረጋገጫ ሰርተፊኬት የተቀበለው መንግሥት፣ ይህንን ሀብት የሚያለሙ ኩባንያዎችን ራሱ እየፈለገ ወደ አገር ውስጥ እንደሚጋብዝ አስታወቀ፡፡

ከዚህ ቀደም በአገሪቱ የተፈጥሮ ጋዝና ነዳጅ ክምችት መኖሩ ቢታወቅም፣ የሀብቱ መጠን ምን ያህል እንደሆነ ባለመታወቁ፣ ኩባንያዎች በራሳቸው እየመጡ ፍለጋ ያደርጉ እንደነበር ተገልጿል፡፡

አሁን ግን የአሜሪካ ኩባንያ ለአራት ወራት ባደረገው ጥናት ለሀብቱ መጠን ማረጋገጫ በመስጠቱ፣ መንግሥት ሰርቲፊኬቱን በመያዝ ‹‹ልምድ እንዲሁም የፋይናንስና ቴክኖሎጂ ሀብት አላቸው” የሚላቸውን ኩብንያዎች በራሱ እንደሚያፈላልግ የማዕድን ሚኒስትር ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) ገልጸዋል፡፡

‹‹ከዚህ በኋላ የኢትዮጵያ መንግሥት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጭምር፣ አቅምና ጉልበታቸው የተመሰከረላቸውን ኩባንያዎች እናስመጣና የተፈጥሮ ጋዛችንን እናመርታለን፤›› ያሉት ሚኒስትሩ፣ የተረጋገጠው የተፈጥሮ ጋዝ ሀብት የአገሪቱን ኢኮኖሚ ‹‹ዕጣ ፋንታ ሊወስን›› የሚችል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ታከለ (ኢንጂነር) ይህንን የገለጹት በኦጋዴን ቤዚን ያለውን ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሀብት ክምችትና የኢኮኖሚ አዋጭነት ጥናት ለማድረግ በመጋቢት 2014 ዓ.ም. ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር ውል የገባው የአሜሪካው ኩባንያ፣ የጥናቱን ሰነድ ዓርብ ነሐሴ 20 ቀን 2014 ዓ.ም. ለሚኒስቴሩ ሲያስረክብ ነው፡፡

ኩባንያው ያደረገው ጥናት በሶማሌ ክልል ኦጋዴን ቤዚን 3,500 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ውስጥ የተከናወኑ የፍለጋና የጥናት ውጤቶችን መነሻ በማድረግ፣ በቤዚኑ ያለውን የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሀብት መጠን የሚያሳውቅና ኢኮኖሚያዊ ግምገማ የሚያሳይ ነው፡፡

ከዚህም ባሻገር ኩባንያው ያደረገውን ጥናት ተመርኩዞ በአከባቢ ላለው የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት የእውቅና ሰርተፊኬት ሰጥቷል፡፡ በኢትዮጵያ ይህ ዓይነቱ ሰርተፊኬት ሲሰጥ የመጀመሪያ እንደሆነ የገለጹት ታከለ (ኢንጂነር)፣ በዚህ ማረጋገጫ መሠረት መንግሥት ያለውን ሀብት ጠቅሶ ከኩባንያዎች ጋር መደራደር እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡

‹‹ይህ ሰነድ ባለመኖሩ ኩባንያዎች እየመጡ የኢትዮጰያን ሀብት እንደፈለጉ ይጫወቱበት ነበር፤›› ያሉት ሚኒስትሩ አክለውም፣ ‹‹ከእነሱ የተሻለ ሀብትና ቁጥር ያለው እኛ ጋ ነው፡፡ ይህንን ቁጥር ይዘን የሚያለማ፣ ከኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ጋር መራመድ የሚችል ኩባንያ ፈልገን እናመጣለን፤›› ብለዋል፡፡

ከ13 ዓመት በላይ ለሆነ ጊዜ የተፈጥሮ ጋዝ ፍለጋ ሲደረግ እንደነበር ጠቅሰው፣ ኩባንያዎች በሚያደርጉት ፍለጋ የሚያገኙት ክምችት ምን ያህል እንደሆነ ለመናገር ፈቃደኛ እንዳልነበሩ አውስተዋል፡፡ ይህም የሚሆነው ስለክምችቱ የነበሩ ጥናቶች የኩባንያዎቹ በመሆኑ እንደሆነ፣ አሁን በአሜሪካው ኩባንያ የተደረገው ጥናት ግን የመንግሥት መሆኑን ታከለ (ኢንጂነር) አክለዋል፡፡

‹‹ከዚህ በፊት ኩባንያው ከሁለት እስከ ሶስት ትሪሊየን ኪዩቢክ ጫማ እንዳለን ሲነግረን ነበር፡፡ አሁን ከዚያ ሦስት እጥፍ እንደሆነ ይህ ሰነድ አረጋግጦልናል፤›› ያሉት ሚኒስትሩ፣ ጥናቱ ሰባት ትሪሊዮን ኪዩቢክ ጫማ የተፈጥሮ ስለመኖሩ ማረጋገጫ መስጠቱን አስታውቀዋል፡፡

አክለውም፣ ‹‹ቢያንስ ሁለት ጉድጓድ ይኖራችኋል ሲሉን በነበር፡፡ አሁን ይህ ኩባንያ የአራት ወር ጊዜ ወስዶ ሰባት ትሪሊየን ጫማ የተፈጥሮ ጋዝና ማንኛውም ኩባንያ ያልነገረን ድፍድፍ ዘይት እንዳለን [አረጋግጧል]፡፡ ምን ያህል ድፍድፍ ዘይት እንዳለን ኩባንያዎች አልነገሩንም፤›› ብለዋል፡፡

ከአራት ዓመት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ነዳጅ መውጣት ልትጀምር መሆኑን ገልጸው የነበረ መሆኑ ተጠቅሶ ጥያቄ የቀረበላቸው ታከለ (ኢንጂነር)፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጊዜው የነዳጅ ምልክት መኖሩን መናገራቸውንና ይህም ትክክል መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ‹‹ይህ ሰነድ ምልክት መኖሩን የሚያረጋግጥ ነው፤›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ታከለ (ኢንጂነር)፣ ‹‹የአሜሪካ ኩባንያ በተለይ በተፈጥሮ ጋዝ ወደ አገራችን ገብቶ ኢንቨስት እንዲያደርግ እንደምናደርግ እርግጠኛ ነኝ፤›› ሲሉ በሥነ ሥርዓቱ ላይ ለተገኙት በኢትዮጵያ የአሜሪካ ተልዕኮ ምክትል ዋና ኃላፊ ፊዮና ኢቫንስ አስታውቀዋል፡፡

የማዕድን ሚኒስቴር በተፈጥሮ ጋዝ ፍለጋና ልማት፣ በማዳበሪያ ፋብሪካና በወርቅ ምርት ላይ ትብብር ለማድረግ ከካሊክ ሆልዲንግ ከተባለ የቱርክ ኩባንያ ጋር በሰኔ 2014 ዓ.ም. ሦስት የመግባቢያ ስምምነቶች መፈራረሙ ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች