ኢዜማ የትግራይ ሕዝብ ሕወሓትን በቃህ ብሎ ከኢትዮጵያዊ ወገኑ ጋር እንዲቆም ጥሪ አቀረበ
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የትግራይ ሕዝብ ከሕወሓት አገዛዝ ነፃ ለመውጣት ለሚያደርገው ትግል ድጋፍ እንደሚያደርግ ገለጸ፡፡
አብን ዓርብ ነሐሴ 20 ቀን 2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ለትግራይ ሕዝብ ባስተላለፈው መልዕክት፣ ‹‹በስምህ የሚነግደው አሸባሪውና ተስፋፊው የትሕነግ ቡድን፣ ከመላው ኢትዮጵያውያን ጋር ያለህን ትስስር ለመበጠስና ከኢትዮጵያዊ ማንነትህ ለመንቀል፣ በማያባራ ጦርነት ውስጥ ከቶሃል›› የሚለው መግለጫው፤ የሽብር ቡድኑ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ በተለይም በአማራና በአፋር ሕዝብ ላይ ካደረሰው ጉዳት ያልተናነሰ ጉዳት፣ በትግራይ ሕዝብ ላይ እንዳደረሰ ምስክር እንጂ አስረጂ እንደማያስፈልግ አስታውቋል፡፡
‹‹ልጆችህን ከጉያህ እየነጠቀ፣ ጥሪትህን እያሟጠጠና አግቶ በመያዝ ከሌሎች ኢትዮጵያውን ጋር በአንድነትና በሰላም እንዳትኖር ጋሬጣ የሆነብህን ደም የማይጠግብ የሽብር ቡድን፣ ከራስህ ላይ አሽቀንጥረህ በመጣል ራስህን ነፃ አውጣ፤›› ሲል ጥሪ ያቀረበው አብን፣ ከሕወሓት ‹‹ዕገታ›› ሕዝቡ ነፃ ለመውጣት በሚያደርገው ተጋድሎ ድጋፍ እንደሚያደርግ ፓርቲው አስታውቋል፡፡
ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሕወሓት ተከፋይ ከሆኑ ሚዲያዎች ሐሰተኛ ፕሮፖጋንዳ ራሱን እንዲጠብቅና በጀግንነት እየተዋጋ ላለው ጥምር ጦርና ለአገር መከላከያ ሠራዊት ሙሉ ድጋፉን እንዲሰጥ አብን ጥሪ አቅርቧል፡፡
የፌዴራልና የክልል መንግሥታት ሕወሓት በየጊዜው የሚደቅነውን የጦርነት ሥጋት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ዕልባት የሚያገኝበትንና የቡድኑን ህልውና መክሰምን ግብ ያደረገ የጦር፣ የዲፕሎማሲና የፕሮፓጋንዳ ዕቅድ ሥራ ላይ እንዲያውሉ ጥሪ አስተላልፏል፡፡
አብን አክሎም ሕወሓት በሚከፍተው የወረራ ጦርነት ኢትዮጵያና ሕዝቦቿ፣ በተለይም የወረራው ቀጥተኛ ገፈት ቀማሽ የሆነው የአማራና የአፋር ሕዝብ ከፍተኛ ዋጋ እየከፈሉ መሆናቸውን በመግለጽ፣ ጦርነቱን የመመከት ድርብ ኃላፊነት ያለባቸው መሆኑን አስረድቷል፡፡
በመሆኑም ጥቃቱ በተከፈተባቸው ግንባሮችና ሌሎች አካባቢዎች የሚገኝው ሕዝብኧ ለሕወሓት ፕሮፓጋንዳ ጆሮ ባለመስጠት፣ ለጥምር ጦሩና ለመከላከያ ሠራዊት ያልተቆጠበ የስንቅና የሞራል ድጋፍ እንዲሰጥ ጥሪ አስተላልፏል፡፡
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ሐሙስ ነሐሴ 19 ቀን 2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫኧ ሕወሓት በተደጋጋሚ ከሰላም በተቃራኒ እየቆመ የኢትዮጵያን ሕዝብ ለመከራ መዳረጉን ገልጿል፡፡
የትግራይ ሕዝብም እየደረሰበት ላለው መከራ ዋነኛ ተጠያቂው ሕወሓት መሆኑን በመረዳት፣ ለተጨማሪ መከራና ብሶት ልጆቹን መገበር፣ ሀብት ንብረቱን ለእኩይ ዓላማው እንዳያውልበት በመከላከል ሕወሓትን በቃህ በማለት ጦርነትን እምቢ ብሎ ከተቀረው ኢትዮጵያዊ ወገኑ ጋር በመቆም፣ ሕወሓት ተገድዶም ቢሆን ወደ ሰላማዊ መንገድ እንዲመጣ ማድረግ እንደሚኖርበት አስታውቋል፡፡
የአገር መከላከያ ሠራዊት የሚጠበቅበትን ኃላፊነትና ግዳጅ ሲወጣ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጎኑ ተሠልፎ ጦርነቱን በአጭር ጊዜ በመቋጨት፣ ሙሉ በሙሉ ወደ ልማትና ሰላም እንዲመለስ የሚጠበቀውን ድጋፍ ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ኢዜማ አስረድቷል፡፡