በሰሜን ኢትዮጵያ በሕወሓት አማካይነት ሕዝብን አደጋ ላይ ለመጣል የሚመጣ ማንኛውንም ትንኮሳ፣ የፌደራል መንግሥት ያሉትን አማራጮች ተጠቅሞ ሕግ እንዲያስከብር ሦስት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ባወጡት መግለጫ ጠየቁ፡፡
መኢአድ፣ እናት ፓርቲና ኢሕአፓ ዓርብ ነሐሴ 20 ቀን 2014 ዓ.ም. ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ፣ ጦርነቱ አገሪቱን ዋጋ እያስከፈላት በመሆኑ፣ መንግሥት ችግሩን ለመፍታት እስከ መጨረሻው አማራጭ ድረስ በመሄድ ዘላቂ መፍትሔ እንዲሰጠው ጠይቀዋል፡፡
የፌደራል መንግሥት አሁንም ወደ ፖለቲካ ድርድር ሲገባ የአፋርና የአማራ ክልሎችን ጨምሮ የሕዝብን ጥቅም ሊያስከብሩ የሚስችሉ አካላትን የድርድሩ አካል እንዲሆኑ ማድረግ እንደሚጠበቅበት የጠየቀው የፓርቲዎቹ መግለጫ፣ በትግራይ በኩል ከሕወሓት ውጪ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሌሎች ይመለከተኛል የሚሉ አካላት እንዲሳተፉበት ጥሪ አቅርቧል፡፡
ሕወሓት በዚያ በኩል የትግራይን፣ በሌላ በኩል ቀሪውን የኢትዮጵያ ሕዝብ አደጋ ውስጥ ቢጥልም፣ ብዙውን ጊዜ እየተወራ ያለው በፌደራል መንግሥት የሚነሳው ጉዳይ በመሆኑ፣ የትግራይ ሕዝብ ተጠርንፎ አደጋ ውስጥ በገባበት በዚህ ጊዜ ሁለቱንም ወገኖች ለማዳን ሲባል ሕግን የማስከበር ዕርምጃ መውሰድ አለበት ሲሉ ፓርቲዎቹ በመግለጫቸው ገልጸዋል፡፡
ከወራት በፊት በሰሜን ኢትዮጵያ በተካሄደው ጦርነት፣ የሕወሓት ታጣቂዎችን ከአማራና ከአፋር ክልሎች ድንበር አባሮ የትግራይን ሕዝብ አሸባሪ ተብሎ ለተጠራ አካል፣ የትግራይ ሕዝብ ጥሎ መመለሱ፣ ከጅምሩ ጤናማ እንዳልነበር ፓርቲዎቹ በመግለጫቸው አስታውቀዋል፡፡
የትግራይ ሕዝብ በአሸባሪነት የተሰየመውን ኃይል ብቻውን ተሸክሞ መኖር የለበትም ያሉት ፓርቲዎቹ፣ የፌደራል መንግሥት ሕግን የማስከበር ዕርምጃ ተከትሎ፣ እስከ መጨረሻው አማራጭ በመሄድ ሰላም መረጋገጥ አለበት ብለዋል፡፡
መንግሥት ይህን ሁሉ ችግር ለትግራይን ሕዝብ ተወጡት ብሎ መተው እንደሌለበትና ሕዝቡን፣ ‹‹ከዚህ ጤናማ ካልሆነና ከታመመ ቡድን›› ነፃ ማውጣት እንደሚያስፈልግ አክለው ጠይቀዋል፡፡
መንግሥትም ሆነ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሰላም ጎዳናን መምረጥ እንዳለባቸውና ሁለቱም ሕዝቦች ጦርነት በቃ ሊሉ እንደሚገባ የጠየቁት ፓርቲዎቹ፣ ምንም እንኳ ሕወሓት በታሪክ በጠረጴዛ ዙሪያ ቁጭ ብሎ በድርድር ችግሮችን የፈታበት መድረክ ባይኖርም፣ እንደ መንግሥት የሰላም መንገድን መምረጡ አስፈላጊ መሆኑን አሳስበዋል፡፡
ፓርቲዎቹ ጦርነቱ እንደገና ሊጀመር እንደሚችል በተለያዩ መንገዶች ሲያስጠነቅቁ እንደነበር ገልጸው፣ ይሁን እንጂ አሁንም በተጀመረው ጦርነት የትም ቦታ የሚሞተው የደሃ ልጅ እንጂ የመሪዎች ልጆች ወይም ራሳቸው መሪዎች አይደሉም ብለዋል፡፡ በመሆኑም ሕወሓት ከቋሚ የጦረኝነት ባህሪው የማይመለስና በዚህ ሒደት በሰላም መቀጠል ስለማይችልና ለድርድር ያልታደለ በመሆኑ፣ የፌደራል መንግሥት እስከ መጨረሻው ጥግ ሄዶ ሰላም የማስከበር ግዴታ አለበት ብለዋል፡፡