Tuesday, February 27, 2024

የዩኒቨርሲቲ መምህራን በጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ ቅሬታ እንደተሰማቸው ተናገሩ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በመንግሥት ዩኒቨርሲቲ የሚያስተምሩ መምህራን በተደጋጋሚ እየጠየቁ ላሉት ደመወዝ፣ የሥራ ደረጃ ዕድገትና የተለያዩ ጥያቄዎች ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የሰጡት ምላሽ በርካታ የዩኒቨርሲቲ መምህራን ቅሬታ እንደተሰማቸው ተናገሩ፡፡

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በንግድ ባንክ አዲሱ ሕንፃ አዳራሽ በተካሄደው የጠቅላይ ሚኒስትሩና ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ ወጣቶች የውይይት መድረክ ላይ ከአንድ ተሳታፊ የዩኒቨርሲቲ መምህራንን ጥያቄ በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ማብራሪያ ምክንያት ነው የዩኒቨርሲቲ መምህራኑ ቅሬታቸውን ያሰሙት፡፡

መምህራኖቹን ያስቆጣው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ ሲሰጡ የተናገሩት አንደኛው ጉዳይ የስታንዳርድ አለመኖር ሲሆን፣ በሴሚስተር አራትና አምስት ማስተማርያ ሰዓታት (credit hour) ብቻ የማስተማር፣ የዩኒቨርሲቲ መምህር መባል እንደማይገባ ነበር፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲገልጹ አንዳንድ መምህራን ከአራት ሰዓት በማይዘል በሳምንት በማስተማር እንዲሁም በሳምንት አንድ ቀን ብቻ ዩኒቨርሲቲ በመቀመጥና ሌላውን ቀን ሌላ ቦታ በመዋል ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ አድማ እናደርጋለን የሚሉ አሉ ሲሉ ነበር የተናገሩት፡፡

‹‹ጥያቄው አግባብ ነው፡፡ ደመወዝም በቂ ነው ለምን ጠየቁ አልተባለም፡፡ ደረጃ በደረጃ እየመለስን ብንሄድ ለሁላችንም ይጠቅማል፡፡ ከአገር አንፃር ኢትዮጵያን በሚያሳድግ ሁኔታ መታየት አለበት፣ አድማ ቢደረግ ዩኒቨርሲቲው ይዘጋል፣ ገንዘብም ይከስራል›› ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

በአደጉ አገሮችና ጎረቤት ኬንያ ካሉ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በማነፃፀር፣ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪ እየቀለቡ እንዲሁም ለአስተማሪ ደመወዝ እየጨመሩ መቆየት ስሜት እንደማይሰጥ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ዩኒቨርሲቲዎች ራሳቸውን ማስተዳደር መጀመር እንዳለባቸው፣ እንዲሁም ከመንግሥት በጀት ሳይጠይቁ የራሳቸውን ገቢ በማስገባት መተዳደር እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡ በሰሞኑ በትምህርት ሚኒስቴር በኩል እንደተለጸው፣ ዩኒቨርሲቲዎች ራሳቸውን የማስተዳደር ሁኔታ በቀጣይ እንደሚጀመርና በሁለት ዓመት ውስጥም አሥር ዩኒቨርሲቲዎች በዚህ እንሚያልፉ ተገልጾ ነበር፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም ከሚመጣው የትምህርት ዓመት ጀምሮ በዚህ የሚያልፍ ይሆናል፡፡

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ JEG መተግበር ከተጀመረ ጀምሮ በመንግሥት ላይ 30 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት እየመጣበት ነው፡፡ ‹‹ጥያቄያቸውን አቅም በፈቀደ መጠን እንመልሳለን፣ ከእነርሱ ግን ድጋፍ እንፈልጋለን›› ሲሉ አክለዋል፡፡

በ2011 ዓ.ም. ተግባራዊ ተደርጎ የነበረው የመንግሥት ሠራተኞች የሥራ ምዘናና ደረጃ ማስተካከያ (Job Evaluation and Grading-JEG) የዩኒቨርሲቲ መምህራን ላይ ምንም ለውጥ ባለማምጣቱ ምክንያት፣ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ መምህራኖቹ የተለያዩ ጥያቄዎችን ሲጠይቁ ቆይተዋል፡፡ ከባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ጀምሮም በጥያቄዎቻቸው ዙሪያ ከመንግሥት ኃላፊዎች ጋር በተደጋጋሚ ሲወያዩም ነበር፡፡

በቂ መልስ ባለማግኘታቸው በዚህ ዓመት ግንቦት ወር ላይ የዩኒቨርሲቲዎች መምህራን ማኅበራት ኃላፊዎች ከሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን፣ ትምህርት ሚኒስትር፣ ገንዘብ ሚኒስትር፣ ገቢዎች ሚኒስቴርና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰው ሀብትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) ጋር መወያየታቸውን፣ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህራን ማኅበር ፕሬዚዳንት ተስፋዬ ከበደ (ዶ/ር) ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

‹‹አዘጋጅተናቸው የነበሩት 16 ጥያቄዎች በሦስት ዘርፍ፣ በአጭር ጊዜ የሚመለስ፣ በመካከለኛ ጊዜ የሚመለስና በረዥም ጊዜ የሚመለስ›› በማለት ‹‹በኃላፊዎች ተይዘው እንደሚመለስልን ተነግሮን ነበር፤›› በማለት በተጨማሪም አሥር አማራ ክልል ያሉ ዩኒቨርሲቲዎች መምህራን ማኅበራት ሕዝብ ግንኙነት የሆኑት ተስፋዬ (ዶ/ር) ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በአጭር ጊዜ ከሚመለስ ውስጥ የገቡት ጥያቄዎች፣ የቤት አበል ክፍያ ማስጀመር፣ የሥራ ደረጃ ማስተካከልና የJEG ደረጃን ማስተካከል ሲሆኑ፣ በቤት አበልና በJEG ለውጥ በኩል ያሉት ጥያቄዎች እስካሁን መልስ አላገኙም በማለት ተስፋዬ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡ ከገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ጋር በነበራቸው ውይይትም ሚኒስትር ዴኤታው በጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ታዘው ከሐምሌ 1 ጀምሮ የቤት አበል መክፈል እንደሚጀመር የተነገራቸው ቢሆንም እስካሁን ምንም አለማግኘታቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በማስተማሪያ ሰዓት (credit hour) ትንሽ መሥራትን በተመለከተ ተስፋዬ (ዶ/ር) ለሪፖርተር ሲገልጹ፣ አይደለም አራትና አምስት ሰዓት ምንም ሰዓት የማያስተምር መምህር ሊኖር እንደሚችልና ይህም የፖለቲካ ተቀጣሪ ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲ መምህራን ዝቅተኛ ማስተማርያ ሰዓት (credit hour) በሳምንት 12 ሰዓት ሲሆን መምህራኖች ይህን ያህል ጊዜ የሚያስተምሩ ከሆነ ራሱ መንግሥት መጠየቅ ሲኖርበት፣ ሁሉንም መምህራን መውቀስ ተገቢ አይደለም በማለት ተናግረዋል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ በመከፋት በርካታ መምህራኖች በማኅበራዊ ሚዲያም ሐሳባቸን እየገለጹ ነው፡፡ ከመምህራኖቹ አንደኛውና የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ መምህራኖች ማኅበር ፕሬዚዳንት የሆኑት አቶ ጋሻው ዓለሙ ይገኙበታል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ እንዲህ እንደሚሆን አለመጠበቃቸውንና ‹‹አመክኖያዊ ባልሆነ ማብራሪያ›› መታለፉም አግባብ እንዳልሆነ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲያቸው ከ1000 በላይ መምህራን ያሉ ሲሆን፣ ከ800 በላይ የሚሆኑት የእነሱ አባላት ናቸው፡፡

ጥያቄያቸውን ለተለያዩ የመንግሥት ኃላፊዎች እንዳስገቡ፣ እንዲሁም ምንም ምላሽ ሳያገኙ በትዕግሥት መቆየታቸውንና የአገሪቱ ችግርንም ከማንም በላይ እነርሱ እንደሚሰማቸው የገለጹት አቶ ጋሻው፣ ምላሾቹ እንዳናደዳቸው ተናግረዋል፡፡ ‹‹ምንም ትንሽ ገንዘብ ብትሆንም የቤት አበልን በተመለከተ አንድ መልስ እንኳን አልተሰጠንም›› ሲሉ ከሐምሌ 1 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ይተገበራል የተባለውን የቤት አበል አለመተግበሩን ተናግረዋል፡፡

ሌላኛው በእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የመምህራን ማኅበር ፕሬዚዳንት የሆኑት አቶ ፈለቀ ወርቁ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ጥያቄያቸው የፖለቲካ እንዳልሆነና ተገቢው መልስ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ነው፡፡ የተሻለ ሕይወት ለመኖር የሚጠይቅ ተገቢ የመብት ጥያቄ ስለሆነ፣ መምህራኖቹ ተገቢ መልስ ካላገኙ በገቢ በኩል ወደ ተሻለ ሥራ ሊሄዱ እንደሚችሉ ያላቸውንም ሥጋት አቶ ፈለቀ ገልጸዋል፡፡ በእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ሥር ከ500 በላይ መምህራን አሉ፡፡

‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ በግልጽ ይቅርታ መጠየቅ አለባቸው›› ሲሉም አቶ ፈለቀ አክለዋል፡፡

የሦስቱም ዩኒቨርሲቲ መምህራን ማኅበር ፕሬዚዳንቶች ለሪፖርተር እንደገለጹት ከሆነ፣ ለማንኛውም የዩኒቨርሲቲ መምህራኖች በተናጠል ለሚወስኑት ውሳኔ ኃላፊነት ይወስዳል፡፡ በመምህራኖቹ በተናጠል እየታቀደ ያለውን የአድማ መምታት ቅስቀሳዎችን የማይደግፉ ሲሆን፣ እየሠሩ ጥያቄያቸውን መጠየቅ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -