Tuesday, December 5, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የጦር መሣሪያ ፈቃድ የሚጠይቁ ድርጅቶች ካፒታላቸው ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ መሆን እንዳለበት ተደነገገ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የጦር መሣሪያ  ፈቃድ ለማግኘት የሚጠይቁ ድርጅቶች፣ የተመዘገበ የካፒታል መጠናቸው ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ ሊሆን እንደሚገባና ይህንንም ከሚመለከተው የመንግሥት ተቋም በሚቀርብ ማስረጃ ማረጋገጥ ሲችሉ መሆኑን የፌዴራል ፖሊስ ባወጣው አዲስ መመርያ ተደነገገ፡፡

ድርጅቶቹ በመሥፈርትነት የተቀመጠውን የካፒታል መጠን የሚያሟሉ ቢሆንም፣ ፈቃዱን ለማግኘት ድርጅታቸው ከጦር መሣሪያ ውጪ በማንኛውም ሌላ ዘዴ መጠበቅ እንደማይቻል መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡

ካፒታላቸው አነስተኛ የሆኑ ድርጅቶች የጦር መሣሪያ ፈቃድ ሊያገኙ የሚችሉት፣ ያሉበት አካባቢ የፀጥታ ሁኔታ ምልከታ ተደርጎበት፣ የጦር መሣሪያ  እንደሚያስፈልጋቸው ከተረጋገጠ በኋላ መሆኑን መመርያው ይደነግጋል፡፡

ከሁለት ዓመታት በፊት በወጣው የጦር መሣሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ መሠረት፣ የወጣው የጦር መሣሪያ አስተዳደር፣ አጠቃቀምና ቁጥጥር መመርያ፣ በአዋጁ ላይ በዝርዝር ያልተጠቀሱ የፈቃድና ተያያዥ ጉዳዮችን ያስቀመጠ ነው፡፡ የፌዴራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል መላኩ ፈንታ፣ ከዚህ ቀደም የነበረው የሕግ ክፍተት እንደነበረበትና የመሣሪያ ፈቃድ የሚሰጥባቸውን ዝርዝር መሥፈርቶች እንደማያስቀምጥ ገልጸዋል፡፡ 

አሁን የወጣው መመርያ፣ ‹‹አንድ ሰው ምን ያህል መሣሪያ ሊይዝ ይገባል? ለንብረት ጥበቃ መሣሪያ መያዝ ካስፈለገ ምን ዓይነት ቢዝነስ ያከናውናል? ምን ያህል ካፒታል አለው? የሚለውን በዝርዝር አስቀምጧል፤›› ብለዋል፡፡ የአገሪቱን የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካዊና፣ ማኅበራዊ ሁኔታዎች፣ እንዲሁም ዜጎች ከጦር መሣሪያ ጋር ያላቸውን ‹‹ውህደት›› ከግምት ወስጥ እንደተዘጋጀም አስረድተዋል፡፡

ከዚህ ቀደም የጦር መሣሪያ ፈቃድ የሚጠይቁ ድርጅቶች ያላቸው ካፒታል ፈቃዱን ለማግኘት እንደ ቅድመ ሁኔታ አልተቀመጠባቸውም ነበር፡፡ ይልቁንም ‹‹የድርጅቱ ሕጋዊነት፣ የሚሠራው ለሕዝብና አገር የሚጠቅም መሆኑ፣ የድርጅቱ የኋላ ታሪክ፣ ለአደጋ ተጋላጭነት አለው ወይ? የሚሠራበት አካባቢ ለጥበቃ የማይመች ነገር አለው ወይ?›› የሚሉት ከግምት ውስጥ የሚገቡ ጉዳዮች መሆናቸውን የፌዴራል ፖሊስ ጠቅላይ መምርያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ፍቅሩ ወንዴ ገልጸዋል፡፡

አዲሱ መመርያ የጦር መሣሪያ ለመያዝ የሚፈቀድላቸው ድርጅቶች ለመያዝ የሚችሉት የመሣሪያ ዓይነትና ብዛትን ጠቅሶ አላስቀመጠም፡፡ ለአንድ ድርጅት የሚፈቀደው የጦር መሣሪያ ዓይነትና ብዛት የሚወሰነው ድርጅቱ ለፀጥታ ያለው የሥጋት ተጋላጭነት፣ ከፀጥታ አስከባሪ ተቋማት ያለው ርቀት፣ የሚሰጠው አገልግሎትና ያስመዘገበውን የካፒታል መጠን ግምት ውስጥ በማስገባት ነው፡፡ እነዚህ ጉዳዮችን ለመመዘንም የፌዴራል ፖሊስ ምልከታና ዳሰሳዊ ጥናት መሠረት እንደሚያደርግ ተቀምጧል፡፡

ድርጅቱ ፈቃዱን ካገኘ በኋላ የሚያስታጥቃቸው የጥበቃ ሠራተኞች የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ሊኖራቸው እንደሚገባ፣ ከተቆጣጣሪው ተቋም ጋርም የውል ግዴታ መግባት ይኖርባቸዋል፡፡

በማዕድን ቁፋሮ፣ በጉዞና አስጎብኚ ድርጅት፣ በእርሻ ልማት፣ በእንስሳት ዕርባታና ተዋፅዖ፣ እንዲሁም በዱር እንስሳት ጥበቃና እንክብካቤ ሥራ ላይ የተሰማሩ አካላት በመንግሥት በልዩ ሁኔታ ሊፈቀድላቸው እንደሚችል መመርያው አስቀምጧል፡፡ መመርያው እንደሚያስቀምጠው፣ መሣሪያ  ለማግኘት ፈቃድ የሚጠይቁ ግለሰቦች የአዕምሮ ጤንነትና የጦር መሣሪያን ለመጠቀም የሚያስችል አካላዊ ብቃት ያላቸው፣ እንዲሁም ከጦር መሣሪያ  ጋር በተያያዘ የተፈጸመ የወንጀል ሪከርድ የሌላቸው መሆን አለበት፡፡

በአዲሱ መመርያ መሠረት ለግለሰቦች የሚፈቀደው የመሣሪያ  ዓይነት እንደሚኖሩበት አካባቢ ይለያያል፡፡ ከዞን ከተማና ከዚያ በላይ ባለ የከተማ መደበኛ ነዋሪ የሆነ ፣ ከአነስተኛ ጦር መሣሪያ ውጪ የማይፈቀድለት ሲሆን፣ ከዞን ከተማ በታች ባለ ከተማና የቀበሌ ነዋሪ የሆነ ግለሰብ እስከ ክላሽንኮቭ ድረስ ያለ የጦር መሣሪያ  ሊፈቀድለት ይችላል፡፡

ግለሰቦችም ፈቃዱን ለማግኘት የጦር መሣሪያ አጠቃቀም ሥልጠና ወስዶ የሚሰጠውን ፈተና የማለፍ ግዴታ አለባቸው፡፡ የጦር መሣሪያ  አያያዝና አጠቃቀም ክህሎትና የአጠቃቀም ብቃት ለማሳደግ የሚዘጋጀው ሥልጠና የሚሰጠው በፌዴራል ፖሊስ ሲሆን፣ ሥልጠናው እንደ መሣሪያው ዓይነት ከአምስት እስከ 30 ተከታታይ ቀናት ሊቆይ እንደሚችል መመርያው ይደነግጋል፡፡

ሠልጣኞች ፈቃድ ለማግኘት ከሥልጠናው በኋላ የሚሰጠውን ፈተና ከ65 በመቶ በላይ ማምጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ፈተናውን ያላለፈ ሠልጣኝ በአንድ ዓመት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ተፈትኖ ካላለፈ ከሥልጠናው ሙለ ለሙሉ እንደሚሰናበት መመርያው ላይ ሠፍሯል፡፡ በመመርያው መሠረት አንድ ሠልጣኝ ከዚህ በኋላ ለመሠልጠን ማመልከት የሚችለው ከሁለት ዓመታት በኋላ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች