Friday, September 22, 2023

የዳኞች ዓለም አቀፍ ሕግ ዕውቀት ዝቅተኛ መሆን የባለሥልጣናትን ተጠያቂነት ዝቅተኛ እንዳደረገው ተገለጸ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በኢትዮጵያ የፍርድ ቤት ዳኞች የዓለም አቀፍ ዕውቀታቸው አነስተኛ መሆን፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት የዓለም አቀፍ ሕግጋትና ግዴታዎችን እንዲወጡ የማዘዝና የመጠየቅ አቅማቸውን እንደገደበው ተገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል የድኅረ 2010 ዓ.ም. የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ሁኔታን አስመልክቶ፣ ነሐሴ 19 ቀን 2014 ዓ.ም ይፋ ባደረገው ጥናት፣ የዳኞች የአቅም ውስንነት ኢትዮጵያ ከፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ ሕጎች ጋር የሚጋጭና በኢትዮጵያ የሚተገበሩ ገዳቢ ሕጎችን የመቃወምና እንዲሻሩ የመጠየቅ ዕድልን ዝቅተኛ እንዳደረገው አመላክቷል፡፡

ባለፉት አራት ዓመታት ‹‹የሚያስደንቁ›› የሕግ ማሻሻያዎች ቢደረጉም፣ በሰብዓዊ መብቶች ረገድ በድፍረትና በግልጽ የሚሟገቱትን የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾችን አፍ ለማስያዝና ለማፈን፣ የተሟጋችነትን ሥራ ወንጀል አድርገው የሚደነግጉ ሕጎች መውጣታቸውን በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ለሚያከናውኗቸው ሥራዎች ዕውቅና የሚመጥንና ጥበቃ የሚያደርግላቸው የሕግ ማዕቀፍ አለመኖሩን በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ማነው የሚለው በግልጽ አለመታወቁን ሪፖርቱ አስረድቷል፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ግለሰብና ድርጅት ማነው የሚለው ጥያቄ ያልተመለሰና ለመወሰን አስቸጋሪ መሆኑን ያብራረው ጥናቱ፣ ጥያቄውን ለመመለስ አስቸጋሪ ከሆኑባቸው ምክንያቶች መካከል አንዱ የሰብዓዊ መብቶች አንቂነት ከፖለቲካ አንቂነትና ከማኅበራዊ ጉዳዮች አቀንቃኝነት ጋር የተጠላለፈና የተቀላቀለ በመሆኑ እንደሆነ ተብራርቷል፡፡

በሌላ  በኩል እየተንሰራፋ የመጡት ግጭቶችና ጦርነቶች የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋችነትን መወሰኛ መስመር በማደብዘዛቸው የተነሳ፣ እነ ማን የሰብዓዊ መብት ተሟጋች እንደሆኑ በግልጽ ለመለየት በጣም አስቸጋሪ እንደሆነ በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡

ያለፉት ሦስት ዓመታት በኢትዮጵያ ታሪክ የሰብዓዊ መብቶች እሴቶች ወደ ጎን የተተውበት ምዕራፍ መሆኑን፣ በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍሎች በተደጋጋሚ ተወሳስበው በተፈጠሩ የተራዘሙ ግጭቶች ምክንያት፣ የሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ አገርን ከማፍረስ ማዳን ቀጥሎ የሚመጣ ነው የሚል አስተሳሰብ መፍጠሩን፣ ይህ ዕሳቤ ለሰብዓዊ መብቶች መጠበቅ መነጋገር የሚቻለው የአገር ሕልውና በተረጋገጠበት ሁኔታ ነው የሚል ሌላ አስተሳሰሰብ እንደፈጠረ በሪፖርቱ ተካቷል፡፡

በሪፖርቱ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ግለሰብና ድርጅትን ለመለየት ተግዳሮት እንደሆነ እንደ ምክንያት የተጠቀሰው ሌላኛው ምክንያት፣ ብሔርን መሠረት ያደረገ የፖለቲካ ትርክት ነው፡፡ ይህ ጉዳይ የአገሪቱን ፖለቲካና የሰብዓዊ መብቶች አረዳድ እንዳዛባው ተገልጿል፡፡

በየትኛውም ሁኔታ ላይ ሆነው በራሳቸው መንገድ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር የሚጥሩ ሰዎች፣ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ተብለው ቢጠሩም፣ የሰብዓዊ ተሟጋችነት የተምታታባቸው አካላት፣ ጠዋት ለሰብዓዊ መብት ሲሰብኩ ውለው ከቀትር በኋላ ጥላቻን ሲያንፀባርቁ የሚያመሹ መሆናቸውን፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ኃይለ ማርያም ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -