Sunday, December 3, 2023

እንደገና ያገረሸው ጦርነት

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ጦርነቱ ወደ ሦስተኛ ዙር ምዕራፍ የተሸጋገረ ይመስላል፡፡ የሕወሓት ኃይልና የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ዳግም ወደ ተኩስ ልውውጥ ማምራታቸው እየተነገረ ነው፡፡ በትግራይና በአማራ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች፣ እንዲሁም በትግራይና በአፋር ክልሎች አጎራባች ቀጣናዎች እንደገና ጦርነት ማገርሸቱ ተነግሯል፡፡

ራሱን ‹‹የትግራይ ሠራዊት ወታደራዊ ኮማንድ›› ብሎ የሚጠራው ኃይል ባወጣው መግለጫ፣ መንግሥት ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነቱን ጥሶ በትግራይ ላይ ጦርነት አውጇል ሲል ከሷል፡፡ ቡድኑ በመግለጫው ዳግም ጦርነቱ መጀመሩን ያረጋገጠ ሲሆን ለተዋጊዎቹ ጠንክረው እንዲዋጉ ማሳሰቢያም ሰጥቷል፡፡

በመንግሥት በኩል በተሰጡ መግለጫዎች ጊዜያዊ የተኩስ አቁሙን በመጣስ፣ የሕወሓት ኃይል ሦስተኛ ዙር ጦርነት ማወጁ ተገልጿል፡፡ ሕወሓት ጦርነት በማወጅ ዳግም ወደ አማራና አፋር ክልሎች ወረራ ለማካሄድ ጥረት መጀመሩን የመንግሥት መግለጫ ያትታል፡፡

ሕወሓት ‹‹ድርድሩ አስቀድሞ ከሽፏል›› በማለት ጦርነቱ መጀመሩ እንደማይቀር ሲናገር እንደነበር፣ ‹‹ከበባውን እንሰብራለን›› በሚል ዛቻም በተደጋጋሚ ሲያደርገው የቆየውን ትንኮሳ ገፍቶበት ከነሐሴ 18 ቀን 2014 ዓ.ም. ሌሊት 11 ሰዓት ጀምሮ በምሥራቅ ግንባር በቢሶበር፣ በዞብልና በተኩለሽ አቅጣጫ ጥቃት ከፍቷል ሲል የመንግሥት መግለጫ ይፋ አድርጓል፡፡

ጦርነቱ ተጀመረ በተባለ ምሽት ኢትዮጵያን ሚዲያ ሰርቪስ (EMS) ለተባለው የዩቲዩብ ሚዲያ የስልክ አስተያየት የሰጡት የአገር መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ እንደገና ስለተቀሰቀሰው ውጊያ ሰፊ ገለጻ አድርገዋል፡፡

‹‹መከላከያ ትግራይ የመግባት አንዳችም ፍላጎት የለውም፡፡ መከላከያ አንድ ኢንች መሬት ከነበረበት ቦታ አልተንቀሳቀሰም፤›› ሲሉ የተናገሩት ፊልድ ማርሻሉ፣ እንደገና ውጊያና ወረራውን የጀመረው ራሱ የሕወሓት ኃይል ነው ብለዋል፡፡ የጊዜ ጉዳይ እንጂ ሕወሓት መጥፋቱ የማይቀር ቡድን መሆኑን አስረግጠው ገልጸው፣ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ‹‹ታሪካዊ ጠላት ከሆኑ አገሮች›› መሣሪያ ጭኖ መቀሌ ለማረፍ የሞከረ አውሮፕላን መትቶ መጣሉንም አረጋግጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ከሱዳን ባለሥልጣናት በአውሮፕላኑ ጉዳይ ማብራሪያ መጠየቅ እንደሚኖርበትም፣ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹሙ ከዚሁ ጎን ለጎን ተናግረዋል፡፡

ዓርብ ነሐሴ 20 ቀን 2014 ዓ.ም. የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ያወጣው መግለጫ፣ መንግሥት መረር ያለ አቋም እየያዘ መምጣቱን ያሳያል፡፡ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሕወሓትን ከጥቃት እንዲያስቆመው የሚጠይቀው መግለጫው፣ በአስቸኳይ ይህ ካልሆነና ሕወሓት ጥቃቱን የሚቀጥል ከሆነ ግን መንግሥት በሕግ የተጣለበትን ግዴታ ለመወጣት ሲል ማንኛውንም ዕርምጃ ለመውሰድ የሚገደድ መሆኑን ያሳውቃል በማለት ነበር፣ የመንግሥት ትዕግሥት መሟጠጡን መግለጫው ያተተው፡፡

መንግሥት ይህን ቢልም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ግን ግጭቱን ለማስቆም ከመሞከር ይልቅ፣ ሙሉ ትኩረቱን ሕወሓት ዘረፈው በተባለው ነዳጅ ላይ ያደረገ ነው የሚመስለው፡፡ በትግራይ ግጭት ጠንካራ ተፅዕኖ አላቸው የሚባሉ ተቋማትና መንግሥታት ባለሥልጣናት አንዴ በሊትር ሌላ ጊዜ በጋሎን አኃዙን እያቀያየሩ በመጥቀስ፣ የተዘረፈው ነዳጅ ያሳሰባቸው መሆኑን የሚጠቁም መግለጫ በማውጣት ተጠምደው ከርመዋል፡፡

የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅት (USAID) ኃላፊ ሳማንታ ፓወር፣ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ኃላፊ ዴቪድ ቢስሊ፣ የዓለም ምግብና እርሻ ድርጅት (FAO) እና ሌሎችም አካላት የተሰረቀው ነዳጅ በእጅጉ እንዳሳሰባቸው ሲናገሩ ተሰምተዋል፡፡ ጦርነቱ ሊያስከትል የሚችለውን ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት ወደ ጎን ብለው ግጭቱ በአስቸኳይ እንዲቆም ከመጠየቅ ይልቅ፣ ነዳጁ በአስቸኳይ እንዲመለስ በማሳሰብ ላይ የተወጠሩም ይመስላል፡፡

የሕወሓት ኃይሎች ለዚህ በሰጡት ምላሽ ነዳጁ ከዚህ ቀደም በብድር ለዓለም አቀፍ ድርጅቶች የሰጡት እንጂ፣ የዘረፉት እንዳልሆነ ማስታወቃቸው መነጋገሪያ ሆኖ ነበር፡፡ በዚህ መሀል ግን የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ‹‹ቴድሮስ አድኃኖም (ዶ/ር) የሚሰጡትን አስተያየት በጉጉት እየጠበቅን ነው፤›› የሚል የትዊተር መልዕክት በትዊተር ገጿ የለጠፈችው ጋዜጠኛ አን ጋሪሰን፣ እየተራበ ነው ሲባል በቆየው ትግራይ ክልል ይህ ሁሉ ነዳጅ ተከማችቶ መዘረፉ መመርመር ያለበት ጉዳይ መሆኑን ጠቅሳለች፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊና የቀድሞ የሕወሓት አመራሩ ቴድሮስ (ዶ/ር)፣ በማኅበራዊ ገጻቸው ባወጡት መረጃ ስለነዳጁ ዘረፋም ሆነ ስለጦርነቱ ሳይሆን፣ ሕወሓትን ወይም ታጋይነትን የሚያወድስ ጥቅስ መለጠፍ ላይ ሲያተኩሩ መታየታቸው በብዙዎች ዘንድ ገረሜት ፈጥሯል፡፡

ሐሙስ ነሐሴ 19 ቀን 2014 ዓ.ም. በርዕዮት የዩቲዩብ ሚዲያ ቆይታ ያደረጉት በውጭ አገር የሕወሓት ዋና ተደራዳሪ የሆኑት ፍስሐ አስገዶም (አምባሳደር)፣ ባለፉት ወራት ጦርነቱ እንዲቆም መደረጉ በሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎች መካከል የፈጠረውን ተፅዕኖ እንዲገመግሙ ተጠይቀው ነበር፡፡ ጦርነቱ ለአምስት ወራት መቆሙን በሁለት መንገድ እንደሚገመግሙት ሲናገሩ፣ በአንድ ወገን የዓብይ (ዶ/ር) መንግሥት ራሱን የበለጠ አጠንክሮበታል የሚለውን ግምት እንደሚቀበሉት አስረድተዋል፡፡

‹‹የሰላሙን ጊዜ በተወሰነ መንገድ እኛም ራሳችን እንፈልገው ነበር፡፡ ለተወሰኑ ወራት ራሳችንን ለማጠናከር፣ ከሕዝባችን ጋር ለመወያየትም ሆነ የሰላም ሒደቱ ካልተሳካ ለቀጣዩ ጦርነት ለመዘጋጀት የተወሰነ ጊዜ ያስፈልገን ስለነበር ለራሳችን ተጠቅመንበታል፤›› በማለት ነው ከሰላሙ ጥረት እኩል የጦር ዝግጅት እንደነበር የተናገሩት፡፡

ጦርነቱ ተጀምሮባቸዋል ከተባሉ ግንባሮች የሚወጡ መረጃዎችን ሪፖርተር ለማጣራት እንደሞከረው ከሆነ፣ የአሁኑ ጦርነት ግብታዊ በሆነ መንግድ በድንገት የተጀመረ ሳይሆን ታስቦበትና በቂ ዝግጅት ተደርጎበት የሚካሄድ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

የወሎ ፋኖ ሚዲያ ክፍል ኃላፊ ነኝ ያለው ቴዎድሮስ አያሌው በዋጃ ግንባር ባለፉት አምስት ወራት የፋኖ ኃይል ሲጠብቅ መቆየቱን ይናገራል፡፡ ‹‹በቂ የስንቅና የትጥቅ ድጋፍ ከመንግሥት ወገን ባያገኝም የወሎ  ፋኖ ቤትና መሬት ጭምር ሸጦ ራሱን አስታጥቆ ለአገሩ ተሠልፏል፤›› ሲል ያስረዳል፡፡ ‹‹በዲቪ፣ በወርቄ፣ በዞብል፣ በጊራና፣ በሶዶማና በጋፍራ የጠላት ኃይልን ወጥሮ የያዘው የፋኖ ኃይል ነው፤›› ሲልም በግንባር ላይ ያለውን አሠላለፍ አስረድቷል፡፡

ፋኖ በተሠለፈበት በዚህ የሰሜን ወሎ ዋጃ ግንባር ሐሙስ ለመጀመርያ ጊዜ ከሕወሓት ጋር ውጊያ መደረጉን የተናገረው ቴዎድሮስ፣ የጠላት ኃይል ተመቶ መመለሱን ተናግሯል፡፡ በመረጃም ሆነ በጦር ዝግጅት በአስተማማኝ ሁኔታ የፋኖ ኃይል መደራጀቱን የተናገረው ቴዎድሮስ፣ ከመንግሥት ኃይልና ከመከላከያ ጋር ጥብቅ ቁርኝት በመፍጠር  ተናበው እየሠሩ መሆኑን ጠቁሟል፡፡  

በዚሁ የዋጃ ግንባር የተሠለፈው ፋኖ ያሲን በበኩሉ፣ ‹‹በእኛ አቅጣጫ የጠላት ኃይል አያልፋትም፤›› ሲል ነው የተናገረው፡፡ ‹‹ከመንግሥት ጎን ቆመን እየተዋጋን ነው፡፡ መንግሥትም ከእኛ ጎን እንዲቆም ነው የምንጠይቀው፤›› ሲልም አክሏል፡፡

በዚሁ በሰሜን ወሎ (ራያ) ግንብር የፋኖ ሕዝባዊ ኃይልን የሚመሩት የ68 ዓመቱ አርበኛ ሀሰን ከረሙ ከድሬ ሮቃ ሶዶማ ተነስተው፣ በዋጃ ግንባር የፋኖ ኃይል ይዘው መሠለፋቸውን ተናግረዋል፡፡ በተከታዮቻቸው ‹‹ጄኔራል›› የሚል ማዕረግ የተሰጣቸው አርበኛ ሀሰን፣ ‹‹እኛ በውጊያው ሜዳ ያለን ምንም አይመስለንም፣ ዳር ዳሩን ያለው ይጭነቀው እንጂ፤›› በማለት ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

የሕወሓት ኃይልን  አሠላለፍ ጠንቅቀው እንደሚያውቁና በቂ መረጃ እንዳላቸው የተናገሩት አርበኛ ሀሰን፣ ‹‹እንኳን መከላከያ ገብቶበት አይደለም ጠላት የእኛን አቅምም የመቋቋም አቅም የለውም፤›› ብለዋል፡፡ ከመከላከያና ከልዩ ኃይሉ ጋር ጥሩ መግባባት ፈጥረው የራሳቸው ግንባር ተሰጥቷቸው ሕዝባዊ የፋኖ ኃይሎች መሠለፋቸውን የጠቀሱት አርበኛው፣ ‹‹ፈቃድ ካገኘን ነገ አላማጣ እንገባለን፤›› ብለዋል፡፡

‹‹አምናም ሆነ አሁን ሕወሓቶች እያካሄዱ ያሉት ሕዝብ የሚያሠልፉበት ዘመቻ ነው፡፡ በአንድ ቡድን የተነሳ ደሃ አርሶ አደር አርሶ መብላት እያቃተው እስከ መቼ ይቀጥላል?›› ሲሉ የተናገሩት አርበኛ ሀሰን፣ ሕዝባዊ የፋኖ ኃይሉ ማንንም ለመዝረፍ ወይም ማንንም ለመውጋት ብሎ ሳይሆን ‹‹ሚስቱን፣ አገሩን፣ ቤቱንና ንብረቱን ለመጠበቅ ሲል የዘመተ የደሃ ገበሬ ጦር ነው፤›› ብለዋል፡፡

በራማ ግንባር ለሁለት ተከታታይ ቀናት ሕወሓት ውጊያ መክፈቱን የተናገሩት አርበኛ ሀሰን፣ በሦስት አቅጣጫዎች ሕወሓት ጥቃት ከፍቷል ብለዋል፡፡ ‹‹ድንኩል የሚባለው ኃይል በእኛ አቅጣጫ ሙጃ ድረስ ገብቷል፡፡ ታደሰ ወረደ የሚመራው ብዙ ኃይል ይዞ በአፋር በኩል ሲሠለፍ፣ በወልቃይት ግንባር ደግሞ ፃድቃን ገብረ ትንሳዔ የሚመራው ጦር ነው የተሠለፈው፤›› በማለትም አርበኛው የጠላትን አሠላለፍ አመላክተዋል፡፡

ረቡዕ አመሻሽ ሕወሓት ለሦስተኛ ዙር ጦርነት መክፈቱ ሲሰማ፣ በማግሥቱ ሐሙስ በወልዲያ ከተማ ሼክ አል አሙዲ ስታዲየም የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፍአለ (ዶ/ር) በተገኙበት፣ በጎ አስተዋጽኦ ለአካባቢው ያበረከቱ ሰዎች የሚሸለሙበት ደማቅ ሥነ ሥርዓት ሲካሄድ ውሏል፡፡

በዚህ ዝግጅት ላይ የታደሙት የሕግ ምሁሩ አሰፋ አዳነ (ዶ/ር)፣ ‹‹እኛ ወልዲያ በገባንበት ወቅት የከባድ መሣሪያ ጩኸት በርቀት ይሰማ ነበር፤›› ብለዋል፡፡ የአሁኑን ጦርነት አነሳስ፣ የሕወሓት  ኃይልን ለመከላከል የተደረገውን ዝግጅትና የሰላም ጥረቱን ማብቃት ያስረዱት አሰፋ (ዶ/ር)፣ ከጦርነቱ በስተጀርባ የውጭ ጠላቶች መሠለፋቸውንም ተናግረዋል፡፡

‹‹ኢትዮጵያ ሰላም ከሆነችና ወደ ልማት ፊቷን ካዞረች ታላቁ የህዳሴ ግድብን መጨረስ ብቻ አይደለም፣ በዓባይ ወንዝ ላይ ብቻ ሰባትና ስምንት ግድቦችን መገንባት ትችላለች፤›› በማለት ጦርነቱ ጂኦ ፖለቲካዊ መሠረት ያለው መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ ‹‹ይህ ደግሞ ግብፆችን ያስከፋል፡፡ ይህም ምዕራባውያን ኃይሎች ከግብፅ ጎን እንዲሠለፉ ያደርጋቸዋል፡፡ ስለዚህ ወያኔ በራሱ ከከፈተው ይልቅ በውጭ ኃይሎች ግፊት ነው ወደ ጦርነት እየገባ ያለው፤›› በማለትም የሕግ ምሁሩ ያስረዳሉ፡፡

‹‹ሕወሓት ወልቃይትን መልሶ እንደማያገኝ ያውቃል፡፡ መሬት የሚባል  እንደማያገኝ ያውቃል፡፡ ሆኖም መሬት በነፃ ቢሰጠውም ጦርነት መልሶ መክፈቱን አይተውም፤›› ሲሉ የሚያክሉት አሰፋ (ዶ/ር)፣ ቡድኑ አሳማኝ ምክንያት ኖሮት ሳይሆን በሌሎች ግፊት ወደ ጦርነት መግባቱን ገልጸዋል፡፡

‹‹ወሎ ገራገሩ እንደ ከዚህ ቀደሙ አይደለም፤›› ሲሉ በአካል ተገኝተው ስለአካባቢው የታዘቡትን ሁኔታ የተናገሩት አሰፋ (ዶ/ር)፣ በሁሉም አቅጣጫ ተደራጅቶና ተዘጋጅቶ ኅብረተሰቡ እየጠበቀ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ‹‹ሕወሓት በሕዝባዊ ማዕበል እንደ ከዚህ ቀደሙ ገስግሶ ለመግባት በወሎ ግንባር አይችልም፡፡ አሁን የሚጠብቀው የተዘጋጀና ምሽግ ይዞ የሚዋጋ ኃይል ነው፤›› ሲሉ የጦርነቱን ዝግጅት አስረድተዋል፡፡

ከሕወሓት መሠረታዊ ባህሪ እንዲሁም ከኋላ ከሚገፉት ኃይሎች ፍላጎት አንፃር ቡድኑ ለሰላም ዝግጁ ይሆናል የሚል እምነት እንደሌላቸው የሚናገሩት አሰፋ (ዶ/ር)፣ የሰላም አማራጭን የሚቀበል ከሆነ መጠቀም እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡ ይሁን እንጂ በሰላምና በድርድር ግጭቱን ለመፍታት ሕወሓት ፍላጎት አለው ተብሎ መዘናጋት አደገኛ መሆኑን አሳስበዋል፡፡ ‹‹መንግሥት የሰላም አማራጭ ሊኖር እንደማይችል በማመን የትግራይ ሕዝብና የኢትዮጵያን ሕዝብ ሥቃይ አጭር ቢያደርገው ይበጃል፤›› የሚል ማሳሰቢያ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

አሁን ለትግራይ ችግር ጦርነት መፍትሔ ይሆናል የሚለው መላምት ሚዛን እያገኘ የሄደ ይመስላል፡፡ ብዙዎች ሰላም በሌለበት ሁኔታ ግጭትና ቁርሾን እያከኩ ለረዥም ጊዜ ከመኖር፣ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ችግሩን የሚያስወግድ ጦርነት በማድረግ  ከዚህ ቀውስ በአጭር ጊዜ መውጣት እንደሚሻል እያሳሰቡ ነው፡፡

ይሁን እንጂ ለረዥምም ሆነ ለአጭር ጊዜ ቢሆን ይህች አገር ጦርነትን የሚሸከም አቅም አላት ወይ የሚለው ጥያቄ አሳሳቢ ምላሽ የሚሰጥበት ጉዳይ ሆኗል፡፡

ዘ ኢትዮጵያን ኢኮኖሚስት ቪው በተባለው የፌስቡክ ገጽ በርካታ የኢኮኖሚ ርዕሰ ጉዳዮችን የሚያነሳው የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ዋሲሁን በላይ፣ ኢትዮጵያ ከጦርነት የምታገኘው አንዳችም የኢኮኖሚ ዕድል እንደሌለ ነው የሚናገረው፡፡

‹‹እንኳን እኛው እርስ በርስ ተዋግተን አይደለም በብዙ ሺሕ ኪሎ ሜትር ርቀውን ያሉት ሩሲያና ዩክሬን ጦርነት በመጀመራቸው ብዙ ፈተና እያየን ነው የምንገኘው፤›› በማለት የሚናገረው ኢኮኖሚስቱ፣ በሁለት ዓመታት ለሦስተኛ ጊዜ እየተካሄደ ያለው ጦርነት ከባድ ቀውስ በአገሪቱ ላይ ሊያስከትል እንደሚችል ይተነብያል፡፡

‹‹ጦርነት በሁለት መንገዶች ፈንድ ይደረጋል›› የሚለው ዋሲሁን፣ በጦርነቱ የሚካፈሉ ወገኖች በቀጥታ ብዙ የሰብዓዊና ቁሳዊ መስዋዕቶች እንደሚከፍሉ ይገልጻል፡፡ የደጀኑ ኃይል መደበኛ እንቅስቃሴውን ገቶ ሙሉ ትኩረቱንና ድጋፉን ወደ ጦርነቱ እንዲያደርግ ጦርነት እንደሚያስገድድም ያክላል፡፡

‹‹ቱሪዝምና ብዙ የአገልግሎት መስኮች በጦርነቱ መዘዝ ተጎድተዋል፡፡ በግጭት ቀጣና ያሉ ወገኖች ማምረት የሚችሉበትን ዕድል አጥተዋል፡፡ ስደትና መፈናቀል በጦርነቱ መዘዝ ጨምሯል፤›› ሲል ግጭቱ አገሪቱን እያስከፈላት ያለውን ዋጋ ይዘረዝራል፡፡ ከውጭ ሊመጣ የሚችል የልማት ዕርዳታንና ብድርን ጦርነቱ እንዳደረቀው ያስረዳል፡፡

ከዚህ በመነሳት አገሪቱ ጦርነት የሚሸከም ኢኮኖሚ እንደሌላት የሚናገረው ዋሲሁን፣ ‹‹በአንዳንድ አገሮች ጦርነት የኢኮኖሚ ዕድል ይፈጥራል ቢባልም፣ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ደሃ አገሮች ግን ጦርነት ይዞ የሚመጣው አንዳችም የኢኮኖሚ ዕድል የለም፤›› ይላል፡፡ ጦርነቱን በአጭር ጊዜ መቋጨት የሚለው ጉዳይ የሚያግባባ ቢሆንም እንኳ፣ ‹‹ጭላንጭልም ቢሆን ከተገኘ ግጭቱን በሰላም መፍታት የበለጠ አዋጭ›› ሆኖ እንደሚታየው ነው የተናገረው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -