በመታሰቢያ መላከ ሕይወት
በዓለማችን ያሉ ሁሉም አገሮች አሁን የያዙትን የቆዳ ስፋት ሊኖራቸው የቻለው በዋናነት በተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎች ሲሆን፣ ደሴት የሆኑ አገሮች ደግሞ ድንበራቸው የተወሰነው በተፈጥሮ ምክንያት ነው፡፡
በብዙ አገሮች የመንግሥት ምሥረታ ከተካሄደ በኋላ መንግሥት የመሠረቱ ኃይሎች ግዛታቸውን ለማስፋት ተግተው የሠሩ መሪዎች ሲኖሩ፣ የያዙትን ትንንሽ መሬት አገሬ ብለው የተቀመጡ ነገሥታትም ነበሩ፡፡ ለምሳሌ እንግሊዞች በዓለም በሁሉም አቅጣጫ ተንቀሳቅሰው ግዛታቸውን ያስፋፉ ቢሆንም፣ የወረሯቸው የመሬት ክፍሎች ከእንግሊዝ መሬት ጋር ኩታ ገጠም ባለመሆናቸው ቀስ በቀስ የእንግሊዞች የበላይነት ተወግዶ፣ እነዚህ የመሬት ክፍሎች ነፃነታቸውን ያወጁበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡
ነገር ግን እንግሊዞች ለረዥም ዘመን የቅኝ ግዛት ወረራ ያካሄዱ በመሆናቸው ቋንቋቸው በመላው ዓለም የተስፋፋ በመሆኑ፣ አሁን የእንግሊዝኛ ቋንቋ የዓለም ቋንቋ እስከ መሆን ደርሷል፡፡ ኩታ ገጠም መሬት የያዙት እንደ ሩሲያ፣ ቻይናና ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች ግን የሰፊ ግዛት ባለቤት በመሆናቸው በቀላሉ ታላቅነትን መፍጠር ችለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ግን በመሪ ዕጦት ከሩሲያና ከቻይና እኩል ታላቅነት መፍጠር አልቻለችም፡፡ ቻይናና ሩሲያ በኢኮኖሚ ማደግ ብቻ ሳይሆን፣ ጠንካራ ወታደራዊ አቅም ገንብተው አሁን አሜሪካንን አዳክመው በዓለም ላይ የበላይነታቸውን ለማረጋጥ እየሠሩ ነው፡፡ ይህ ዕቅድ ደግሞ በእርግጠኝነት ይሳካል፡፡
በዚህ ጽሑፍ ለመዳሰስ የተፈለገው ዋናው አጀንዳ በአንድ የታሪክ አጋጣሚ ትንሽ አገር ለመሆን የተገደዱ አገሮች፣ በመጪው ዘመን ሊገጥማቸው የሚችለው ፈተና ምን ሊመስል እንደሚችል ለመቃኘት ነው፡፡
በመጀመሪያ ትንሽ አገር ስል፣ አንድ አገር ትንሽ የቆዳ ስፋት፣ ትንሽ የሕዝብ ቁጥርና ትንሽ የተፈጥሮ ሀብት ሲኖራት ማለቴ ነው፡፡ አንድ አገር ከላይ የተጠቀሱን ትንንሽ ነገሮች ብቻ ካላት ሊኖራት የሚችለውም ጥንካሬ በዚያው ልክ ትንሽ ይሆናል ማለት ነው፡፡ በወታደራዊ አቅም በማዕከላዊ መንግሥት ጥንካሬ፣ በዲፕሎማሲው መድረክ ሊኖራት የሚችለው ተፅዕኖ ፈጣሪነት በዚያው ልክ ትንሽ ይሆናል ማለት ነው፡፡
በዲፕሎማሲና በወታደራዊ አቅም ሊኖር የሚችለው ጥንካሬ እጅግ አናሳ ከመሆኑ የተነሳ፣ የበለፀጉ አገሮች የተፈጥሮ ሀብት ያላቸውን ትንንሽ አገሮች (አመራሮቹን በቁጥጥራቸው ሥር በማድረግ ከተመቻቸውም እንዲወገዱ ወይም እንዲለወጡ በማድረግ) የራሳቸውን ጥቅም ብቻ ለማስጠበቅ ተግተው ይሠራሉ፡፡ የዚያች ትንሽ አገር ሕዝቦች እንኳን አገራዊ ጥቅማቸውን ሊያስጠብቁ ይቅርና በሰላማዊ መንገድ ድምፃቸውን ማሰማት እንኳን አይችሉም፡፡ ምክንያቱም ማዕከላዊ መንግሥት (አገሪቱ ትንሽ ስለሆነች) በቀላሉ የሕዝብን ድምፅ ፀጥ ማድረግ ይችላል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ያለ ሰፊ አገር ሕዝቦች በተለያየ አቅጣጫ ሕዝባዊ ተቃውሞ ለማሰማት ዕድሉ የተሻለ ነው፡፡
በዓለማችን በቴክኖሎጂ መጥቀው፣ ነገር ግን የትንሽ አገር ባለቤት የሆኑ አገሮች አሉ፡፡ ለምሳሌ ጃፓን፣ ኮሪያና እስራኤልን የመሳሰሉ አገሮች የቴክኖሎጂ ባለቤት ስለሆኑ ኃያል አገር ለመሆን (ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች) ዕድሉ የላቸውም፡፡ እንደ ጃፓን ያሉ በቴክኖሎጂ መጥቀው፣ ነገር ግን ትንሽ ግዛት ያላቸው አገሮች ጦርነት ቀስቅሰው ግዛታቸውን ለማስፋት ሞክረዋል፣ አልተሳካላቸውም፡፡ እነዚህ አገሮች መቼም ታላቅ ወታደራዊ አቅም መገንባት ስለማይችሉ፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ አገር መሆን አይችሉም፡፡ ትንንሽ አገሮች በኃያላኑ የመረሳትና የመናቅ ችግርም አለባቸው፡፡
አንዳንድ አገሮች ደግሞ በጣም ትንሽ አገር ኖሯቸው፣ ከፍተኛ ሀብት የሚያስገኝ የተፈጥሮ ሀብት ያላቸው አገሮች አሉ፡፡ ለምሳሌ ኩዌት፣ ኳታርና ብሩናይ የመሳሰሉ አገሮች የያዙት የመሬት መጠን እጅግ ጠባብ ከመሆኑ የተነሳ ነዳጅ ሸጠው የሚያገኙትን ገንዘብ ኢንቨስት የሚያደርጉበት የመሬት ክፍል እንኳን የላቸውም፡፡ በመሆኑም የእነዚህ አገሮች አመራሮችና ሕዝቦች ከፍተኛ ገንዘብ አባካኞች ናቸው፡፡ እነዚህ አገሮች ከፍተኛ ገንዘብ ስላላቸው የጦር መሣሪያ ሊገዙ ይችሉ ይሆናል፣ ነገር ግን በቂ ሠራዊት ማሠማራት አይችሉም፡፡
እዚህ ላይ በሳዳም ሁሴን ዘመን ኢራቅ ኩዌትን ስትወር የኢራቅ ጦር ኩዌትን ለመውረር የፈጀባት አምስት ሰዓት ብቻ ነበር፡፡ ኩዌቶች ካላቸው ዝቅተኛ የሠራዊት ብዛት የተነሳ ለአንድ ቀን እንኳን ራሳቸውን መከላከል አልቻሉም፡፡ በሌላ አነጋገር አንድ አገር ትንሽ የቆዳ ስፋት ኖሯት ከፍተኛ የገንዘብ ሀብት ቢኖራት፣ ያንን ሀብቷን መጠበቅ የምትችልበት አቅም የሌላት በመሆኑ ትንሽ አገር ሆኖ በተፈጥሮ ሀብት ምክንያት የብዙ ገንዘብ ባለቤት መሆን ብዙም ትርጉም የለውም፡፡
እንደሚታወቀው አንድ አገር ትንሽ የቆዳ ስፋት ቢኖራትና ሌላ አገር ደግሞ ሰፊ የቆዳ ስፋት ቢኖራትም፣ ሁለቱም መንግሥታት የግድ ማዕከላዊ መንግሥት ያስፈልጋቸዋል፡፡ የትንሹም የትልቁም ማዕከላዊ መንግሥት ወጪው ይቀራረባል፡፡ ነገር ግን ሰፊ ግዛት ያላት አገር፣ ሰፊ ግብር ከፋይ ያላት አገር የማዕከላዊ መንግሥትን ወጪ ሸፍና ለፕሮጀክት የሚሆን ገንዘብ የሚተርፉት ሲሆን፣ ትንንሽ አገሮች ግን ከሚሰበስቡት የግብር ገንዘብ ትንሽነት አኳያ ከመደበኛ የመንግሥት ወጪ አልፎ ለፕሮጀክት የሚሆን ገንዘብ ለማግኘት በጣም ይቸገራሉ፡፡ በመሆኑም ትንንሽ አገሮች መቼም የዜጎችን ሕይወት የሚለውጥ ፕሮጀክት ላያዩ ይችላሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ ጥሩ ምሳሌ ኤርትራ ነች፡፡ ኤርትራውያን ጣሊያን የለጠፈባቸውን ማንነት እንደ ትልቅነት ቆጥረውና ተገንጥለው የራሳቸውን አገር ቢመሠርቱም፣ የተጓዙት ወደ ድህነት እንጂ ምንም የተሻለ ነገር ማግኘት አልቻሉም፡፡ ኤርትራውያን እልህ ውስጥ ገብተው ከዛሬ 30 ዓመታት በፊት እጅግ የተሳሳተ ውሳኔ ቢወስኑም፣ ስህተታቸውን ለማረም ምንም ዓይነት ጉዞ አልጀመሩም፡፡ አንድ ኤርትራዊ ትውልድ ከጥቅም ውጪ ሆነ፡፡
በጣም የሚርመው ደግሞ ኤርትራውያን የተሳሳተ ውሳኔ ወስነው በዚህ ደረጃ ችግር ውስጥ ቢገቡም፣ ከእነሱ ስህተት መማር የተሳናቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ የብሔር ልሂቆች አሁንም የኤርትራውያንን ጉዞ ለመጀመር የሚታገሉ አሉ፡፡
ከሁለት አገሮች አንደኛው ትንሽ አገር ቢሆንና ሌላው ደግሞ ትልቅ አገር ሆኖ ሁለቱም በአምባገነናዊ መሪዎች ቢመሩ፣ የትንሽ አገር አምባገነን ከግብር ገቢ የሰበሰበው ገንዘብ ምናልባት ከቤተ መንግሥት ውጪና ከፖሊስ ደመወዝ ላያልፍ ይችላል፡፡
የሰፊ አገር አምባገነን ግን የሚሰበስበው ገንዘብ ከራሱ ፍጆታ ስለሚያልፍ ሕዝብ የሚያገኘው ነገር ይኖራል፡፡ ትንንሽ አገሮች የኦሊምፒክ ኮሚቴ (በገንዘብ ምክንያት) ስለማይኖራቸው በስፖርት መድረክ የሉበትም፡፡
አሁን በምንኖርባት ዓለም በትንንሽ አገሮችና ሰፊ የቆዳ ስፋት ባላቸውና ሰፊ ግብር ከፋይ ማኅበረሰብ ባላቸው አገሮች ውስጥ እየተፈጠረ ያለው ልዩነት በእጅጉ ግልጽ እየሆነ እየመጣ ነው፡፡
እንግሊዝና ፈረንሣይ ዓለምን ወረው በነበረበት ጊዜ ቻይና እጅግ ደሃ አገር ነበረች፡፡ አሁን ከተወሰኑ አሠርት ዓመታት በኋላ ቻይና በኢኮኖሚ ፈርጥማ፣ ከእንግሊዝና ከፈረንሣይ በእጅጉ በልጣለች፡፡ እንግሊዞች ለዘመናት ከመላው ዓለም የሰበሰቡት ሀብት ታላቅነታቸውን ሊያስቀጥልላቸው አልቻለም፡፡ ይህ በግልጽ የሚያሳየን የገንዘብ ሀብት ብቻውን የታላቅነት መለኪያ አለመሆኑን ነው፡፡
በአሁኑ ጊዜ አሜሪካኖች (ምንም እንኳን የሰፊ አገር ባለቤት ቢሆኑም) ታላቅነታቸውን ለቻይና ሊያስረክቡ ተቃርበዋል፡፡ ነገር ግን እልህ ይዟቸው በመታገል ላይ ናቸው፡፡ አሜሪካ 9.8 ሚሊዮን ካሬ ኪሎ ሜትር የሚሆን የቆዳ ስፋት ሲኖራት፣ የሕዝብ ብዛቷ ደግሞ 350 ሚሊዮን ነው፡፡ ቻይና ደግሞ 9.5 ሚሊዮን ካሬ ኪሎ ሜትር የቆዳ ስፋት ሲኖራት የሕዝቧ ብዛት 1.3 ቢሊዮን ነው፡፡
አሜሪካና ቻይና በቆዳ ስፋት እጀግ ይቀራረባሉ፡፡ በሕዝብ ብዛት ግን ቻይና ከአሜሪካ በአራት እጥፍ ገደማ ትበልጣለች፡፡ ያ ማለት ቻይና ከአሜሪካ በአራት እጥፍ የሚበልጥ ታክስ ከፋይ አላት፡፡ በተጨማሪም በጠንካራ ዲሲፕሊን የሚመራ የመንግሥት መዋቅርና መሪ በተቀየረ ቁጥር የፖሊሲ መዋዠቅ የሚባል ነገር የለም፡፡ በተቃራኒው አሜሪካ በየጊዜው መሪ በተቀየረ ቁጥር መሠረታዊ የፖሊሲ ለውጥ እየመጣ አሜሪካውያንና ሌሎች አገሮች በመቸገር ላይ ናቸው፡፡
ከላይ የተጠቀሱትን ነጠብጣቦች አገናኝተን ስንመለከት መጪው ዘመን ያለ ጥርጥር የዓለም ኃያል አገር ሆና ብቅ የምትለው ቻይና ነች፡፡ ምክንያቱም ኃያል አገር ለመሆን የሚያስችላትን መሥፈርቶች ሁሉ ታሟላለች፡፡
ወደ ሩሲያ ደግሞ ስናቀና ሩሲያ በተፈጥሮ ሀብት የተንበሸበሸች አገር ብትሆንም፣ የዓለም ታላቁን የመሬት ክፍል ማለትም 17 ሚሊዮን ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው ግዛት ባለቤት ብትሆንም፣ የሕዝቧ ብዛት 140 ሚሊዮን ብቻ በመሆኑ በወታደራዊና በኢንዱስትሪ ጠንካራ ሆና መውጣት ስለማትችል ከቻይና ጋር ልትገዳደር የምትችልበት ዕድሏ በጣም ጠባብ ነው፡፡
በዚህ ጽሑፍ ለመዳሰስ እንደተሞከረው የቴክኖሎጂ ምጥቀት ብቻውን ታላቅ አያደርግም፣ ሰፊ የቆዳ ስፋት ያለው አገር ባለቤት መሆን ብቻ ታላቅ አያደርግም፣ ሰፊ የሕዝብ ብዛት ባለቤት መሆን ብቻ ኃያል አያደርግም፡፡ ኃያል ለመሆን በሕዝብ ብዛት፣ በቴክኖሎጂ፣ በቆዳ ስፋትና በተፈጥሮ ሀብት መበልፀግ ተደምረው ባለራዕይ መሪና ፓርቲ አገር የሚያስተዳር ከሆነ ኃያል ለመሆን አስተማማኝ መሆን ይቻላል፡፡
ህንድን ደግሞ ብንመለከት የቆዳ ስፋቷ ከኢትዮጵያ በሦስት እጥፍ ይበልጣል፡፡ ሦስት ሚሊዮን ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ሲኖራት፣ የሕዝቧ ብዛት ከቻይና በመቀጠል 1.1 ቢሊዮን ነው፡፡ ህንድ በአሁኑ ጊዜ አስደናቂ የሚባል የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገበች ቢሆንም፣ በደሃውና በሀብታሙ መካከል ያለውን ልዩነት ማጥበብ (በተፈለገው ፍጥነት) አልቻለችም፡፡
ያም ሆነ ይህ ህንድ የኑክሌር ጦር መሣሪያ ባለቤት ከመሆኗ በተጨማሪ ሰፊ ግብር ከፋይ ማኅበረሰብ ያላት በመሆኑ፣ ለእነ አሜሪካ ጭምር አስፈሪ እየሆነች ያለች አገር ነች፡፡ በጠፈር ምርምርና በኢንዱስትሪ ዕድገት እጅግ ፈጣን ዕድገት በማስመዝገብ ላይ ነች፡፡ በተለይ ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆን ሰፊ የሰው ኃይል ባለቤት በመሆኗ፣ የህንድ ኢንዱስትሪ ከቻይና ቀጥሎ ትልቅ ውጤት ማስመዝገቡ አይቀርም፡፡
ዛሬ በመላው ዓለም ሌሉ ሕዝቦች የሰፊ አገር ባለቤት መሆን ከሚገባው በላይ ገብቷቸዋል፡፡ የትንሽ አገር ባለቤት ለመሆን የሚታገሉ ኃይሎች ባላቸው፣ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የግንዛቤ ችግር ባለባቸው አገሮች ውስጥ ብቻ ነው፡፡ ትንሽ አገር በመሆንና የትልቅ አገር ባለቤት በመሆን መካከል ያለው ልዩነት በመኖርና ባለመኖር መካከል እንዳለው ልዩነት ነው፡፡
ኢንቨስተሮች ወደ አንድ አገር ሄደው ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎት የሚኖራቸው፣ ምርት ካመረቱ በኋላ ምርታቸውን ምን ያህል ሕዝብ ይገዛናል ብለው ካጠኑ በኋላ ነው፡፡ ብዙ ምርቶች ተመርተው በቅርብ ርቀት ነው መሸጥ ያለባቸው፡፡ አዋጭ የሚሆኑትም በቀላሉ በአገር ውስጥ መሸጥ ሲቻል ነው፡፡
ለምሳሌ በኢትዮጵያ የቴሌ ሥራ በአሁኑ ጊዜ በመንግሥት እየተከናወነ ያለ ሥራ ነው፡፡ ጂቡቲም ውስጥ ቴሌ አለ፡፡ ነገር ግን የትንሿን ጂቡቲ የቴሌ ገቢና የኢትዮጵያን ቴሌኮም ገቢ ስናነፃፅረው ኢትዮጵያ ሰፊ አገር በመሆኗ የመንግሥትም ገቢ እጅግ በጣም ትልቅ ነው፡፡ ከዚህ ገቢ መላው የአገሪቱን ሕዝብ ተጠቃሚ ያደረገ ሥራ ማከናወን ይቻላል፡፡
በአንድ አገር በገቢ የተጠናከረ ማዕከላዊ መንግሥት ካለ ይህች አገር የማደግ ዕድሏ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ምክንያቱም ብዙ የልማት ሥራዎች በማዕከላዊ መንግሥት ብቻ መከናወን ያለባቸው በመሆኑ፣ የማዕከላዊ መንግሥት ጥንካሬ የዕድገት መሠረት ነው፡፡ ትንንሽ አገሮች ይህንን ማድረግ አይችሉም፡፡ በመሆኑም መሪዎቹ ሁሌም የተንደላቀቀ ኑሮ ይኖራሉ፡፡ የአገሪቱ ሕዝቦች ግን ምንም የሚያገኙ ነገር የለም፡፡
በመሆኑም ትንሽ አገር ለመፍጠር መታገል ሞኝነት ብቻ ሳይሆን ዕብደትም ጭምር ነው፡፡ ቋንቋን እንደ ምክንያት እየወሰዱ ስለአገር የሚያወሩ ብዙ ናቸው፡፡ በእኛ አገር አማርኛን ጨምሮ አንድም የበለፀገ ቋንቋ የለም፡፡ እንኳን በእኛ አገር የሚነገሩ ቋንቋዎች ይቅሩና በሳይንስና በሥነ ጽሑፍ የበለፀጉ እንደ ጀርመንኛ፣ ፈረንሣይኛ፣ ጣሊያንኛና የመሳሰሉ ቋንቋዎች ተፈላጊነታቸው በእጅጉ እየወረደ ነው፡፡
ዛሬ ከላይ የተጠቀሱ አገሮች ሕዝቦች በመላው ዓለም ሠርተው መኖር እንዲችሉ ልጆቻቸውን እንግሊዝኛ እያስተማሩ ነው፡፡ እነሱ የበለፀገ ቋንቋቸውን ወደ ጎን ትተው ልጆቻቸውን እንግሊዝኛ ሲያስተምሩ፣ እኛ የግንዛቤ ችግር ባለባቸው መሪዎች እየተመራን ምንም ያልበለፀጉ የልጅ ልጆቻችን በማይወርሷቸው ቋንቋዎች ምክንያት እርስ በርሳችን እየተናቆርን፣ ይህንን እጅግ አስደናቂ የሆነውን የሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ሥልጣኔ ተጠቃሚ መሆን አልቻልንም፡፡
በተጨማሪም ቋንቋን መሠረት ያደረገ መንግሥት ለመመሥረት ትግል ይካሄዳል እንጂ አንድም ሰው፣ አንድም ቡድን የብሔርን ድንበር ፈልጎ ማግኘት የሚችል የለም፡፡ የብሔር ድንበር ማስመር ከተጀመረ ካለፉት 30 ዓመታት ጀምሮ በርካታ ሙከራዎች የተካሄዱ ቢሆንም፣ እስካሁን መደበኛው ሕዝብ የፖለቲካ መሪዎቻችን እንኳን የብሔር ድንበር የቱ ጋ እንደሆነ የሚያውቅ የለም፡፡
እርግጥ ነው የፖለቲካ መሪዎቻችን ለቦታው የማይመጥኑ በመሆናቸውና ሠርተው የዜጎችን ሕይወት መለወጥ ስለማይችሉ፣ ሕዝቡ መሠረታዊ መብቱን እንዳይጠይቅ ሁሌም ሕዝቡን እንደ ብሔር ፖለቲካ ዓይነት አጀንዳ እያስጨበጡ ዕድሜያቸውን ለማራዘም ተግተው እየሠሩ ነው፡፡ ይህንን አካሄድ ምን ያህል መቀጠል እንደሚችሉ አብረን የምናየው ይሆናል፡፡ ችሎታ ያለው ሰው ሥልጣን ሲይዝ ሠርቶ የዜጎችን ሕይወት መለወጥ ስለሚችል፣ በተጨማሪ ዜጎችን በልማት አጀንዳ ማሳተፍ ስለሚችል፣ ለብሔር ፖለቲካ የሚሆን ምንም ጊዜም፣ ቦታም አይኖርም ነበር፡፡
በመጨረሻም በርዕሱ እንደተጠቀሰው መጪው ዘመን እጅግ በርካታ ፈተናዎችን ይዞ ስለሚመጣ፣ ለትንንሽ አገሮች የሚሆን ምንም ቦታ አይኖርም፡፡ ትንንሽ አገሮች ልክ እንደ ሰፋፊ አገሮች የሉዓላዊ ሥልጣንና መብት ቢኖራቸውም፣ መጪው ዘመን ይዞት የሚመጣውን ፈተና በተዓምር መቋቋም አይችሉም፡፡ ሩሲያ በየጊዜው የተጣለባትን ማዕቀብ ተቋቁማ እንደ መንግሥት መቀጠል የቻለችው የሰፊ አገር ባለቤት ስለሆነች ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንድም ቦታ ኢትዮጵያ ሉዓላዊት አገር ነች አይልም፡፡ ሉዓላዊነትን ለክልሎች ነው የሰጠው፡፡ ሉዓላዊነት ማለት አንድ አገር የማንንም ፈቃድ ሳትጠይቅ በርካታ መብቶችን የሚያጎናፅፍ ማዕረግ ነው፡፡
አንድ አገር ሉዓላዊ ከሆነች በዓለም አቀፍ ማኅበረሰብና ተቋማት እንደ አገር ዕውቅና ይኖራታል፡፡ በተጨማሪ ፓስፖርት ማተም፣ ገንዘብ ማተም፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዕውቅና ማግኘት፣ ዓለም አቀፍ ውሎችን መዋዋል፣ በሕግ መክሰስና መከሰስ የመሳሰሉ መብቶች ይኖራታል፡፡ ትንንሽ አገሮች የሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤት በመሆናቸው ብቻ ሊመጡ የሚችሉ ማናቸውንም ጫናዎች መቋቋም የሚችሉበት አቅም መቼም አይኖራቸውም፡፡ ወደፊት በምንኖርበት ዓለም የነዳጅና የምግብ ዋጋ መናር፣ የሕዝብ ቁጥር መጨመር፣ የከባቢ አየር ሙቀት መጨመር፣ የተለያዩ የተፈጥሮ አደጋዎች በተከታታይ መከሰታቸው አይቀርም፡፡፡ ይህንን መቋቋም የሚቻለው የሰፊ አገር ባለቤት በመሆንና አንደኛው የአገር ክፍል ሌላውን የአገር ክፍል እየደገፈ መኖር ሲችል ብቻ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ከላይ እንደተጠቀሰው በመጪው ዘመን ብቁ ተወዳዳሪ መሆን የሚቻለው፣ ማንኛውንም ችግር መጋፈጥ የሚችል ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት ሲኖር ነው፡፡
እኛ ኢትዮጵያውያን ለክልሎች የሉዓላዊነት ሥልጣን ሰጥተን፣ ቋንቋን መሠረት ያደረገ አደረጃጀት ፈጥረን፣ ልጆቻችንን በፍፁም በማይጠቅምና በመላው ዓለም ያሉ ሕዝቦች ከገባቸው ትክክለኛ መንገድ በተቃራኒ እየተጓዝን ነው፡፡ መቼ ይሆን ልክ እንዳልሆንን እንኳን የሚገባን?
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡