ባለፈው ሳምንት አጋማሽ ማልጄ ቢሮዬ ስደርስ የሥራ ባልደረባዬ ትክዝ ብሎ ጣራ ጣራውን ሲያይ አገኘሁት፡፡ ለወትሮው ሳቂታና ተጫዋች የነበረው የሥራ ባልደረባዬ በኩባንያችን ውስጥ የሚታወቀው በጨዋታ አዋቂነቱና አዝናኝነቱ ብቻ አይደለም፡፡ በተለያዩ የትምህርት መስኮች የተለያዩ ዲግሪዎችን ያገኘና በሥራው ዓለምም የበርካታ ዓመታት ልምድ ያለው ሰው ነው፡፡ ይህ ለሌሎቻችን አርዓያና መምህር የሆነ የሥራ ባልደረባዬ እንዲህ ክፍትና ትክዝ ያደረገው ምን ይሆን? አንዳንድ ጊዜ እኮ ከስንት አንድ ጊዜ በዚህ ዘመን የምናገኘውን አንፃራዊ ደስታ የሚሻማብን ምን እንደሆነ ግራ ይገባኛል፡፡ በዚህ ሥጋትና ውጥረት በሰፈነበት ጊዜ ትንሹ ደስታችን በድንገት ሲነጠቅ ምሬቱ ከሚታሰበው በላይ ነው፡፡
ለማንኛውም የተለመደውን ሰላምታ ካቀረብኩለት በኋላ ምን እንዳስተከዘው ለባልደረባዬ ጥያቄ አቀረብኩለት፡፡ በንዴት የቀሉ ዓይኖቹን እያንከባለለ ለመናገር ሲሞክር ያ ርቱዕ አንደበቱ ተሳሰረበት፡፡ ከዚህ በፊት የሚፈልገውን መልዕክት ለማስተላለፍ ፈጣን የነበረው አንደበቱ ከመያያዙም በላይ፣ እጆቹና እግሮቹ ከቁጥጥር ውጭ ሆነው እየተንቀጠቀጡ ነበር፡፡ ያመመው ስለመሰለኝ ወደ ክሊኒክ እንደምወስደው ነገርኩት፡፡ በሚንቀጠቀጠው እጁ አለመታመሙን በምልክት ካሳየኝ በኋላ በረጅሙ ተነፈሰ፡፡
ከአፍታ ዝምታ በኋላ፣ “ይኼውልህ እስካሁን ድረስ ከዛሬ ነገ ይስተካከል ይሆናል በማለት በውስጤ አፍኜው የያዝኩት ጉዳይ ነበር፡፡ አሁን ግን ተስፋ የሚያስቆርጥ ደረጃ ላይ መድረሱን ሳውቅ እንቅልፍ ካጣሁ ሳምንታት ተቆጠሩ፡፡ ምግብ አልበላህ አለኝ፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ በጣም የምወዳቸውንና የማከብራቸውን አምስት ዘመዶቼን ፊት ማየት አቃተኝ…” እያለ ሲብሰለሰል ደነገጥኩ፡፡ ምን ሆኖ ይሆን? በሐኪም የተነገረው አሥጊ ሕመም ይኖር ይሆን? ኤችአይቪና ካንሰር የያዛቸው ሰዎች አጋጥመውኝ ስለሚያውቁም ግራ ተጋባሁ፡፡
እንደ ምንም ራሴን ካረጋጋሁ በኋላ፣ “ምን አጋጠመህ?” በማለት እየፈራሁ ጠየቅኩት፡፡ “በእኔና በአምስት ዘመዶቼ ላይ ዝርፊያ ተፈጸመብን፡፡ የእኔስ ዕዳው ገብስ ነው፡፡ ዘመዶቼን ገፋፍቼ አስገብቼ አዘረፍኳቸው…” እያለ ደም ሥሩ ሲገታተር ወባ የያዘው ይመስል ነበር፡፡ “ማን ነው የዘረፋችሁ?” የሚል ጥያቄ አቀረብኩለት፡፡ “አንድ የሪል ስቴት ኩባንያ ነዋ፡፡ ለፍተን ያጠራቀምነውን ገንዘብ ሰብስበን ሰጥተን ከኪራይ ተላቀን የቤት ባለቤት እንሆናለን ስንል ቤት የለ፣ ገንዘብ የለ ባዶአችንን አጨብጭበን ቀረን…” እያለ ሳግ ሲተናነቀው ጉዳዩ ገባኝ፡፡
ይኼ የሥራ ባልደረባዬ የራሱን ሁለት ሚሊዮን ብር ጨምሮ የአምስት ዘመዶቹን ወደ አሥር ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ለአንድ የሪል ስቴት ኩባንያ ማስረከቡን ነገረኝ፡፡ ዘመዶቹ በሊዝ ወይም ከግለሰቦች ላይ ቁራሽ መሬት በሕጉ መሠረት ወስደው ቤት ለመሥራት አቅደው ሲነሱ በማከላከል፣ ከሪል ስቴት ኩባንያው ጋር በማገናኘት ገንዘባቸውን እንዲከፍሉ በማድረጉ በጭንቀት እንቅልፍ መተኛት እንዳልቻለ፣ የዘመዶቹን ዓይን ለማየት ደግሞ ኃፍረት ውስጥ መግባቱን በሐዘን አስረዳኝ፡፡ “የእኔስ ይቅር እነሱ ዕድሜ ልካቸውን ለፍተው ያገኙትን ያለ የሌለ ጥሪታቸውን አስወስጄ ከሰው በታች አደረግኳቸው…” በማለት እዬዬ ብሎ ሲያለቅስ ውስጤ በሐዘን ተኮማተረ፡፡
“ሕግ ባለበት አገር ውስጥ ሕገወጥ ዝርፊያ ተፈጽሞብን የሚታደገን በመጥፋቱ እኔ ሕይወቴን ላጠፋ ነው…” ሲለኝ ደነገጥኩ፡፡ እሱን እያባበልኩና እያረጋጋሁ ሳለሁ ድንገት አንዲት የሥራ ባልደረባችን መጣች፡፡ ሁኔታችንን ስታይ ተደናግጣ፣ “ምን ሆናችኋል?” በማለት ጠየቀችን፡፡ ቁጭ እንድትል ካደረግኳት በኋላ ጓደኛዬ የነገረኝን ዘርዝሬ አስረዳኋት፡፡ “አይ ወንድሜ! አይ ወንድሜ!” እያለች ደረቷን ከደቃች በኋላ የሌሎች ሰዎችን ገጠመኞች ነገረችን፡፡ በአንዳንድ ሪል ስቴት ኩባንያዎች የሚፈጸመውን ሕገወጥ ድርጊት በምሳሌ እያጣቀሰች ነገረችን፡፡ ለዓመታት በተስፋ እየተጠባበቁ ገንዘባቸውን አስረክበው እህህ እያሉ ስለሚኖሩ በርካታ ምስኪኖች ዘረዘረችልን፡፡
ይህች የሥራ ባልደረባችን፣ “ቆይ ይህ ሁሉ ድርጊት ሲፈጸም መንግሥት በአገሩ የለም? የተለያዩ የአክሲዮን ኩባንያዎች ሲቋቋሙ ሰው በሰው እየተመራ ገንዘቡን አፍስሶ አክሲዮን ይገዛል፡፡ የታለ የተጀመረው ሥራ ሲባል ውጤቱ ዜሮ፡፡ እዚህ አገር በኃይለኛ ቁጥጥር ከሚመራው የባንክና የኢንሹራንስ ዘርፍ በቀር እዚህ ግባ የሚባል የአክሲዮን ኩባንያ አለ እንዴ? የአክሲዮን ኩባንያዎች ሲመሠረቱ ሕዝቡን ከጥቃት የሚከላከል ተቆጣጣሪ መንግሥታዊ ተቋም ከሌለ እንዴት ሥራ ይሠራል? እንዴት ተስፋ ይኖራል? ማንም ዘራፊ እየተነሳ ገንዘብ በጠራራ ፀሐይ እየሰበሰበ ሲሰወር እንዴት ዝም ይባላል?” እያለች በኃይለ ቃል ተናገረች፡፡ “አብሮ መብላት እንጂ አብሮ መሥራትና ማደግ ብርቅ በሆነበት አገር የሕግ የበላይነት ከተጣሰ የማፍያዎች ሰለባ መሆናችን አይቀርም…” ስትል የስንቶቻችን ዕጣ ፈንታ አሳሰበኝ፡፡ ሕግን ተማምነው ገንዘባቸውን የሚዘረፉ ዜጎች ሲበረክቱ እኮ ሕገወጥነት ይሰፍናል፡፡ ሕገወጥነት ሲሰፍን ደግሞ ምን ሊከተል እንደሚችል ሁላችንም እናውቀዋለን፡፡
ሌላው ይቅርና በ40/60 እና በ20/80 የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለማግኘት ተመዝግበው አሥር ዓመት እያስቆጠሩ ያሉ ቆጣቢዎችን ማን ዞር ብሎ እያያቸው ነው? ባለፈው ሰሞን ዕጣ ከወጣ በኋላ የመተግበሪያ ዳታው ላይ ማጭበርበር ተፈጸመ ተብሎ ዕጣው ተሰረዘ፡፡ ከአሁን አሁን ይወጣል ተብሎ ሲጠበቅ የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ልዩ ዞን ወሰን ማካለል ተደርጎ፣ እነ ኮዬ ፈጩ ከእነ ኮንዶሚኒየሞቹ ወደ ኦሮሚያ ተካለሉ፡፡ ሌሎቹ ሳይቶች በአግባቡ እየተገነቡ ስላልሆኑ የባከኑት አሥር ዓመታት እንዴት እንደሚካሱ አይታወቅም፡፡ በዚህ ላይ የከተማው አስተዳደር “በልዩ ሁኔታ” እያለ ቤቶችን ለማንም እያደለ እንዴት ባለቤት መሆን እንደሚቻል ግራ ያጋባል፡፡ ገንዘባችን ለአሥር ዓመታት የቆጠብን ሰዎች ገንዘቡን ከባንክ እናውጣ ብንል እንኳ በዋጋ ግሽበት የላሸቀ ነው፡፡ ይህንን ሁሉ ቀንበር ተሸክመን መቼ ባለቤት እንደምንሆን ስለማይታወቅ፣ ፈጣሪ አምላክ ይሁነን ከማለት ውጪ ምንም ማለት የሚቻል አልመስልህ ብሎኛል፡፡
(ኅብረት ናደው፣ ከአዲሱ ገበያ)