Wednesday, October 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉመልካም አስተዳደርና ዴሞክራሲ የራቃት አገር

መልካም አስተዳደርና ዴሞክራሲ የራቃት አገር

ቀን:

በኢሳያስ ፈለቀ

‹‹ኢትዮጵያ እንድትመጭ ስንት ቀን ይበቃል?›› ብሎ የተጫወተው ዕውቁ አርቲስት እውነቱን ነው። እኛ ሁላችንም የምናውቅሽ ኢትዮጵያ መቼ ይሆን መምጫሽ? በመከራውና በደስታው ተቻችለን ተከባብረን የምንኖርብሽ አገራችን ከወዴት ይሆን ያለሽው? ቀርተሽ ይሆን ወይስ እየመጣሽ? መቼም ይህን ጽሑፍ ለመከተብ ብነሳ እኔ የማውቃት ብቻ ሳይሆን ብዙዎቻችን የመቻቻል፣ የመከባበርና የመዋደድ ተምሳሌት ኢትዮጵያችን የጠፋችብን የምንጋራው ይመስለኛል፡፡

ኢትዮጵያ ማለት የነፃነት፣ የእኩልነት፣ የአልሸነፍ ባይነትና በአጠቃላይ የጥንካሬ ምልክት እንደሆነች እኛ ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳንሆን ድፍን የጥቁር ሕዝብ የማሸነፍ ምልክት አድርጎ ያውቀዋል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ምዕራባውያንም ምን ዓይነት ብርቱ ሕዝብ እንደሆንን ጠንካራ ክንዳችንን አቅምሰናቸዋል፣ ማን እንደሆንን ያውቁናል። ለዚህም የአውሮፓ ቁንጮ የሆነውን ሞሶሊኒን (ጣሊያንን) አዋርደን እንደመለስን ዓለም የማይዘነጋው ሀቅ ነው፡፡ ይህም ከአፍሪካ አገሮች ብቸኛዋ በክንዳችን፣ ነፃነታችንና አንድነታችንን ለዘመናት ጠብቀን የቆየን ሕዝቦች መሆናችንን ዓለም ያውቀዋል።

ዳሩ ምን ዋጋ አለው? አገራችንን ከወራሪ ለመታደግ ያደረግነው ርብርብ መልካም ሆኖ ሳለ፣ ዓለም እየተማረበት ያለውን እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባቱን ችላ ብለን በመቆየታችን ለዘመናት የተዳፈኑ ጥቃቅን ቁርሾዎችና ጥላቻዎች አድገውና ጎልብተው ከድጡ ወደ ማጡ እየወሰዱን ነው፡፡ ያኔ በድህነታችን ባንበላም ባንጠጣም ተከባብረን ተዋደን የኖርንባትን ኢትዮጵያችንን ለመናፈቅ አብቅቶናል።

እውነተኛ ዴሞክራሲ በወረቀት ወይም በሐሳብ ሊፈጸም አይችልም፡፡ እውነተኛ ዴሞክራሲ ቁርጠኝነትን ይጠይቃል፡፡ ይህም አንድን አገር የሚመራ አካል እውነተኛ የአገር ፍቅር ሊኖረው ይገባል። በእኔ ዕድሜ ያየሁት የኢሕአዴግ መራሹ ስብስብ ኢትዮጵያን እየጠሉ ኢትዮጵያን የሚመሩ አካላት ስብስብ እንደሆነ ሁላችንም እናውቃለን። ይህንንም ለመረዳት ብዙ አስረጂ አያሻውም፡፡ በአፍሪካ የነፃነት ቀንዲል የሆነችውንና ግዙፍ የቆዳና የሕዝብ ብዛት ባለቤት የሆነችውን አገራችንን የባህር በር አልባ አድርገው ማስቀረታቸው የሁላችንም ኢትዮጵያውያን ቁጭት ነው፡፡ የ27 ዓመታት የኢሕአዴግ መራሹ ስብስብ ያደረሰውን ሰብዓዊ ውድመትና አገር መከፋፈል፣ እንዲሁም በሙስናና በብልሹ አሠራር ያሠፈነው ሥርዓት አይረሳም፡፡ በዋነኛነት ይኼው ሥርዓት ሲያራምደው የነበረው በዘር ላይ የተመሠረተ የመንግሥት አወቃቀር፣ አሁንም ድረስ ለገባንበት በየቦታው ለሚፈጠር የሰላምና የደኅንነት ዕጦት የአንበሳውን ድርሻ እንደሚወስድ ግልጽ ነው።

ይህም አገራችንን ወደኋላ ያስቀረና በኢትዮጵያዊነቱ ድርድር የማያውቀውን ሕዝባችንን ለመከፋፈልና አገሪቱንም ለማፍረስ የተከናወነ እኩይ ሥራ ለመሆኑ አጠራጣሪ አይደለም፡፡ በእጅግም የሚያስቆጨው አሁንም ካለፈው የረዥም አገረ መንግሥት ግንባታችን ወቅት እያሳለፍን የመጣነውን ውጣ ውረድ መማሪያ ማድረግ ሲገባን የመለያያና የጥላቻ፣ እንዲሁም በአሳዛኝ ሁኔታ ምንም የማያውቁ ንፁኃን ዜጎቻችን እዚህም እዚያም በአሰቃቂ ሁኔታ ሲገደሉ መመልከት የተለመደ መሆኑን ሲታይ፣ ወዴት እያመራን እንደሆነ ግራ የሚያጋባ እየሆነ መምጣቱ በሚገባ እየተስተዋለ ነው።    

ከምንም በላይ በኢትዮጵያ በየአካባቢው ክቡር የሆነው የሰው ልጅ እንደ ቀልድ እየታረደ፣ እየተገደለና መፍትሔ ማጣቱ እየቀጠለ መሆኑ አሳዛኝ ክስተት እየሆነ መጥቷል፡፡ አገሪቱን እየመራ ያለው የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ብልፅግና ፓርቲ የዜጎችን ደኅንነትና በሰላም ወጥቶ መግባት ማስከበር እንደተሳነው በግልጽ ይታያል። እንደ ማሳያም በየአካባቢዎቹ በጅምላ እየተገደሉ፣ እየታፈኑና እየተፈናቀሉ ያሉ ንፁኃን ዜጎችን ማንሳት በቂ ነው። ይህም በፓርቲው ውስጥ የተበላሸና ከቀድሞው የኢሕአዴግ ሥርዓት እየተንከባለለ የመጣ ዓይን ያወጣ የሙስናና የዘረኝነት አመለካከት፣ በመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ሳይቀር እየተስተዋለ መሆኑን በይፋ እየተመለከትን እንገኛለን።

ይህንንም ለመረዳት በየቦታው ንፁኃን ሲገደሉ የመንግሥት ባለሥልጣናት እጅ እንዳለበት፣ ከተለያዩ ምንጮች የሚወጡ ሪፖርቶችና ከግድያው የተረፉ ዜጎች  በግልጽ የሚያንፀባርቁት ነው፡፡ በተጨማሪም ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በሙስና ውስጥ እንደተዘፈቁ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ለአብነት ያህልም የፓርቲው ከፍተኛ አመራር የሆኑት የብሔራዊ የአደጋና ሥጋት አመራር ኮሚሽነር የነበሩትን ግለሰብ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ይህም የገዥውን ሥርዓት በሙስና፣ በብልሹ አሠራር የተተበተበ መሆኑ ዋነኛ ማሳያ ነው፡፡ በመላ አገሪቱ በተለይም በሕገወጥ የመሬት ንግድና ሥልጣንን ያላግባብ በመጠቀም ሀብት መሰብሰብ እየተለመደ መምጣቱን መመልከት፣ የዕለት ተዕለት ተግባር መሆኑን መገንዘብ ይቻላል::

ሁሉንም ነገር አስከፊ የሚያደርገው ደግሞ ሥርዓቱ የተዘፈቀበትን ብልሹ አሠራር ለምን ብለው የሚጠይቁትን የአገሪቱን ዜጎች በጠራራ ፀሐይ በመንግሥት የደኅንነት ኃይሎች እየታፈኑ መሰወራቸው ነው፡፡ ሥርዓቱንና የፍትሕ ሥርዓቱን ምን ያህል ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ እንደሚሆን አንድ ማሳያ ማድረግ ይቻላል። ከጋዜጠኞች እስከ ተራ ግለሰብ በመንግሥት የደኅንነት ኃይሎች የሚደረገው የእስርና የማገት ክስተት የማያቆም ከሆነ፣ መንግሥት መንግሥትነቱን ጥያቄ ምልክት ውስጥ እንደሚከተው የመንግሥት ባለሥልጣናት ሊገነዘቡት የሚገባ ይመስለኛል፡፡ በመሆኑም በዚህ አካሄድ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥርዓት ብዙ ርቀት ስለማይወስደው፣ ዜጎችን የማዋከብና ያለ ሕግ ትዕዛዝ የማሰር ድርጊት ሊያቆም ይገባል።

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመገረም እየተመለከቱ አገኟቸው]

ምንድነው እንዲህ ቀልብሽን የሳበው? ስለሰላም ኖቤል ሽልማት ዜና እየተመለከትኩ ነበር። እና...

የወሎ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ መመሥረትና የአማራ ክልል ጥያቄ

አማራ የኢሕአዴግ አንዱ መሥራችና አጋር ከሆነው ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ...

የሽንኩርት ዋጋ ሰማይ የነካበት ምክንያት ምንድነው?

ባለፉት ሁለትና ሦስት ሳምንታት የሸማቾችን ኪስ ካስደነገጡ መሠረታዊ ከሚባሉ...

የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ኤግዚቢሽን ማዕከልን እንዲያስተዳድር የተሰጠው ኮንትራት ለምን ተቋረጠ?

በአዲስ አበባ ከተማ ለንግድ ትርዒት ዝግጅት ብቸኛ በመሆን የሚጠቀሰው...