Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትለሙያና ለኃላፊነት መታመንን ከየት እናምጣው?

ለሙያና ለኃላፊነት መታመንን ከየት እናምጣው?

ቀን:

በገነት ዓለሙ

ለሙያና ለኃላፊነት መታመን ከየት ይገኛል? በትምህርትና በሥልጠና የተገኘ ሙያ የሚያሸክመው ኃላፊነት የሚጠይቀውን ጨዋነትና ባህርይ ከየት ይመጣል? የፍልስፍና ጥያቄ አይደለም፡፡ በየዕለቱ፣ በየቦታው ከማጀት እስከ ሥራ ቦታ፣ ከጓዳ ጉድጓዳችን እስከ አደባባይና በዓለም አቀፍ መድረክ ሁሉ ጥቃታችን፣ ሕመማችን፣ ትግላችን ውስጥ የአገር ውጋትም፣ ቁርጠትም ሆኖ የሚያንገላታን ጥያቄ ነው፡፡ የአገራችን ሰው በየቋንቋውና በየእምነቱ ‹‹ከእንጨት መርጦ ለታቦት፣ ከሰው መርጦ ለሹመት›› ዓይነት አባባልና ምሳሌያዊ አነጋገር አለው፡፡ ‹‹እንደ ምሰሶ የመሃል፣ እንደ ዳኛ የወል››ም ይላል፡፡ እነዚህንና ሌሎችም አባባሎች በየትኛውም ደረጃ ቢሆን ሙያዎች ሁሉ፣ ሰዎች የሚጫወቷቸው ሚናዎች ሁሉ፣ ዕውቀት ብቻ ሳይሆን ሥነ ምግባር ባላቸው ይበልጥ በላቁ ሰዎች እንዲሞሉ ወይም እንዲያዙ ማድረግ የተለመደ አሠራር ነው፡፡ የተለመደ ብቻ ሳይሆን በሕግ የሚገዛ ረዥም ዘመን ያለው አሠራር ነው፡፡ እንዲህ ያለ ሕገ መንግሥትን ጭምር ወደ የሚገዛበት፣ መንግሥትንም ጨምሮ ከሕግ በታች ወደ የሚያደርግበት ሥርዓት (ወደ ዴሞክራሲ) የመሸጋገር ትጋትና ጥረት ያለው አገር ደግሞ (በዓለም አቀፍ ደረጃም ያለው ትግል የሚለው ይህንኑ ነው)፣ የሕዝብ ሉዓላዊነት የሚለው ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ ይህንን የትምርት ዕውቀት፣ የሥራ ልምድ፣ የጨዋነትና የማለፊያ ባህርይ አስፈላጊነት የግድ ያደርገዋል፡፡ የመንግሥት ሥልጣን ባለቤትነት የሚገለጸው ነፃትክክለኛና ፍትሐዊ ምርጫ ባሰባሰባቸው ምርጥ እንደራሴዎች ብቻ ሳይሆን፣ እነሱም በሚያቋቁሙትና በሚያደራጁት በላቀ ባለሙያነቱና የግል ጥቅሙን ንቆ በተወ አስተዳደር ልክና መልክ ነው፡፡ ስለዚህም እንደራሴያዊ ዴሞክራሲ ባለሙያነትንና ለሙያና ለኃላፊነት መታመንን የማረጋገጥ የበለጠ አደራ እንጂ፣ ዴሞክራሲ ካለ ሌላው ትርፍ ነው የሚሉበት ሥርዓትና አሠራር አይደለም፡፡

ይህንን ለሙያና ለኃላፊነት መታመንን ከየት እናገኘዋለን? የሚለውን በውስጥም በውጭም የአገር ሕመም የአገር ሆድ ቁርጠት የሆነውን ጉዳይ ይበልጥ ግልጥልጥ አድርጎ ለማሳየት ባለፈው ሳምንት ከታዘብኩት ‹‹ገጠመኝ›› ውስጥ ተነስቼ የአምቡላንስ ሾፌር ሙያና ኃላፊነት ምንድነው ብለን እንጠይቅ፡፡ ይህን ጥያቄ መነሻ አድርገው፣ ጥያቄውን ተከትለው የሚመጡ ምላሾችና አስተያየቶች ምክንያት አድርገው የሚግተለተሉ ጉዳዮችም አሉ፡፡ የአምቡላንስ ሾፌር ያልኩትን የሥራ መደብ በአጠቃላይ በመንገድ ትራፊክ ደንብና ሕግ፣ በኢትዮጵያም ሕግ ጭምር፣ የአደጋ አገልግሎት ተሽከርካሪ ከሚባሉት ውስጥ የአንዱን የአምቡላንስ ተሽከርካሪ ሾፌርን ወስጄ ነው፡፡ ከ50ዎቹ አጋማሽ ጅምሮ ሥራ ላይ በነበረውና በአንፃራዊነት በቅርቡ በ2003 ዓ.ም. በወጣው አዲስ ተኪ የአገር ‹‹የትራንስፖርት ደንብ›› መሠረት የአደጋ አገልግሎት ተሽከርካሪ ማለት የአምቡላንስ፣ ለጦር ኃይል ወይም ለፖሊስ ኃይል የሚያገለግል ተሽከርካሪ ወይም ለእሳት አደጋ መከላከያ የሚያገለግል ተሽከርካሪ ነው፡፡ እንዲህ ላለ ለአደጋ አገልግሎት ተሽከርካሪ የአገር የመንገድ ሕግ በመላው ዓለም የተለመደውንና በወጥነት የሚሠራበትን ልዩ ደንብ፣ ልዩ ‹‹መብት›› ሰጥቶታል፡፡ ይህም፣ የዚህ ዓይነት ተሽከርካሪ የሚዘዋወረው የአደጋ ጊዜ አገልግሎት ተግባሩን ለመፈጸም ሆኖ፣ ስለመታወቂያውም በግንባሩ አቅጣጫ ሳያቋርጥ ብልጭ ብልጭ የሚል ቀይ ወይም ሰማያዊ የመብራት ምልክት ማሳየት ወይም ለማስጠንቀቂያ ተስማሚ የሆነ የድምፅ ምልክት የማሰማት ግዴታውን እየተወጣ፣ ግን በየትኛውም የአገር ሕግና ደንብ የተደነገገውን ግዴታ ሳይጠብቅ ተሽከርካሪውን ለማቆም፣ አደጋ እንዳይደርስ በሚበቃ አኳኃን የተሽከርካሪውን ፍጥነት ቀንሶ ቁም በሚል ምልክት ላይ ሳይቆም ለማለፍ፣ በሕግ ከተወሰነው ፍጥነት በላይ ለመንዳት፣ ተግባሩን ለመፈጸም በሚያስፈልገው መጠን ስለትራፊክ የወጡትን ደንቦችና ምልክቶች ሳይመለከት በፈቀደው አቅጣጫ ለመጠምዘዝ የተፈቀደለት ተሽከርካሪ ነው፡፡ ይህን የመሰለ ልዩ ‹‹ፈቃድ›› ወይም ልዩ ‹‹መብት›› ከመስጠት በተጨማሪ እንዲህ ያለው ተሽከርካሪ ልዩ ጥበቃም አለው፡፡ ለምሳሌ በዚሁ በጠቀስነው ሕግ መሠረት ቀድሞ የሚሄደው የአደጋ አገልግሎት ተሽከርካሪ በሚፈጽመው ተግባር ወይም በሚሰጠው አገልግሎት ተካፋይ የሆነ የሌላ የአደጋ አገልግሎት ተሽከርካሪ ነጂ ካልሆነ በስተቀር፣ ማናቸውም ሰው ከአንድ መቶ ሜትር ባነሰ ርቀት ከአንድ የአደጋ አገልግሎት ተሽከርካሪ ኋላ ተጠግቶ እንዳይነዳ ክልክል ነው፡፡

የምንነጋገረው ለሙያና ለኃላፊነት መታመንን ከየት እናገኘዋለን የሚል አንገብጋቢ ጥያቄ አንስተን ነው፡፡ ይህንን ጥያቄ በሙያ ጠበብ ለማድረግ የአደጋ አገልግሎት ተሽከርካሪ ነጂን (ሾፌርን) ለሙያና ለኃላፊነት የመታመን ነገር እንዴት አድርገን ማረጋገጥ እንችላለን? ብሎ ማዋቀርም ይቻላል፡፡ የአደጋ አገልግሎት ተሽከርካሪዎች ዓይነትም ልዩ ልዩ ነውና (የአምቡላንስ ተሽከርካሪ፣ ለፖሊስ አገልግሎት፣ ለእሳት አደጋ መከላከያ አገልግሎት የሚውል ተሽከርካሪ አለና) ጥያቄውን በአምቡላንስ ተሽከርካሪ ሾፌር ላይ ብቻ እንገታዋለን፡፡ በዚህ መሠረት የአምቡላንስ አገልግሎት ተሽከርካሪ ሾፌርን ለሙያና ለኃላፊነት የመታመን ብቃትና ጥረት፣ ወዘተ እንዴት እናረጋግጣለን? ብለን በጉዳያችን እንቀጥል፡፡

ይህንን ጥያቄ ለመመለስ ወይም ጥያቄውን ይዞ ትርጉም ያለው ውይይትም በሉት ገለጻ ለማድረግ መጀመርያ የዚህ ዓይነት የአደጋ አገልግሎት ተሽከርካሪ፣ ሾፌር/ነጂ (የአምቡላንስ ሾፌር) ሙያ ምንድነው? ብሎ የሙያ ተግባሩን፣ የሥራ ባህርይውን አፍታትቶ ፍቺውን/ትርጉሙን መስጠት፣ እንዲሁም ከዚሁ በመነሳት ተፈላጊውን የትምህርት ደረጃ፣ ሥልጠናና የሥራ ልምድ መመልከት ያስፈልጋል፡፡ ጉዳዩን አጭር ለማድረግ አምቡላንስ የሚባል የአደጋ ጊዜ አገልግሎት ተሽከርካሪ ሾፌር/ነጂ የትምህርትና የሥልጠና ተፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎችን የፀና የመንጃ ፈቃድ፣ ከተፈላጊ ደረጃና የሥራ ልምድ ጋር በማቅረብ የሚወጡት ግዴታ ነው? ወይስ የአምቡላንስ ሾፌርነት ‹‹ፓራሜዲክ›› መሆንን ጭምር (ወይም ባለሙያዎች ሲሉ እንደምንሰማው በCPR ወይም BLS ሰርቲፋይድ የሆነ) ይጠይቃል? ወይስ ይህንን የመሰለ የቅድመ ሆስፒታል የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ የሕክምና አገልግሎትን ‹‹ደረቅ›› ሾፌርን ከነርስ ጋር በማጣመድ የሚሠራ ሥራ ነው?

ጥያቄዬን የሚመልስልኝ መረጃ አገኝ እንደሁ ብዬ ወርልድ ዋይድ ዌብ ውስጥ የተሰባሰቡና ተደራሽ የሆኑ በአገራችን ውስጥ የሚገኙ የአምቡላንስ ሾፌር ቀጣሪ ድርጅቶች አንዳንድ የቅጥር ማስታወቂያዎችና ተዛማች ሰነዶችን ገረፍ ገረፍ አድርጌ ዓይቻለሁ፡፡ በአገራችን የአምቡላንስ አገልግሎት የሚሰጡ፣ በዚህ አገልግሎት ሰጪነታቸው ብቻና ጭምር ከሚታወቁ የአገር ተቋማት፣ ማኅበራት፣ የግል ኩባንያዎች፣ የመንግሥታቱ ድርጅት፣ የጤና ማዕከላት፣ ወዘተን አግባብ ያላቸውና በጠቀስኩት መንገድ በእጄ የገቡ ሰነዶች የገለጹልኝንና የገባኝን ያህል እንደተረዳሁት የትኛውም የአምቡላንስ አገልግሎት ሰጪ ተቋም የአምቡላንስ ሾፌርና የጤና ባለሙያ እንደ ዱባና ቅል አበቃቀላቸው ለየቅል ባይሉም ነርስ ሌላ፣ ሾፌር ሌላ ብለው ባይማማሉም የአምቡላንስ ሾፌር ለመሆን የፀና የመንጃ ፈቃድ ከመያዝ ሌላ የጤና ባለሙያነት ‹‹ጥቂት›› ዕውቀት ተጨማሪ ቅድመ ሁኔታ ተደርጎ ሲፈለግና ሲወሰን ማየት አልቻልኩም፡፡ ይህንን የምለው ግን ይህንን ጽሑፍ ስጽፍ፣ ‹‹እቤቴ ቁጭ ብዬ ባጠራሁት›› ልክ ብቻ መሆኑን ግልጽ ማድረግ አለብኝ፡፡

እና የአምቡላንስ ተሽከርካሪ ሾፌርን ለሙያና ለኃላፊነት መታመንን እንዴት እናረጋግጣለን የሚለውን ጥያቄ በመፈተሽ ሒደት ውስጥ ደግሞ መመልከት ያለብን፣ አላየነውም የማንለው አንድ ሌላ ጉዳይ አለ፡፡ የአገር ሕግ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የታወቀና በመላው ዓለም ባሉ አገሪቱ ሁሉ የወል የሆነ ሕግ ከአምቡላንስ ሾፌር ከዚህ በላይ ከፕሮፌሽናል ሾፌርነት በላይ ተጨማሪ ይጠይቃል፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ ‹‹በአደጋ ላይ የሚገኝ ሰውን አለመርዳት››ን ይቀጣል፣ የሰውን ሕይወት፣ አካል ወይም ጤንነት ለአደጋ በማጋለጥ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ውስጥ ይፈርጃል፡፡ በዚህ መሠረት የ1949 ዓ.ም. የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ በቁጥር 547፣ አሁን ደግሞ የ1997 ዓ.ም. የወንጀል ሕግ በአንቀጽ 575፣

 አንደኛ ማንኛውም ሰው በራሱ ወይም በሦስተኛ ወገኖች ላይ አደጋ በሚያደርስ ሁኔታ በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ መንገድ ሊረዳው ሲችል በሕይወቱ፣ በሰውነቱ ወይም በጤንነቱ ላይ ሊደርስ በሚችል ከባድ አደጋ ላይ የሚገኘውን ሌላ ሰው አስቦ ሳይረዳው የቀረ እንደሆነ ከስድስት ወራት በማይበልጥ ቀላል እስራት ወይም መቀጮ ይቀጣል፡፡

ሁለተኛ ጥፋተኛው

ሀ. በማናቸውም ሁኔታ ወይም ዘዴ ይሁን በተጎጂው ላይ ጉዳት ያደረሰው ራሱ ተከሳሹ እንደሆነ ወይም፣

ለ. ተጎጂውን ለመታደግ ወይም ለመርዳት የሙያ ወይም የውል፣ የሕክምና፣ የባህር ወይም ሌላ ሕጋዊ ግዴታ ያለበት እንደሆነ [ቅጣቱ ይጠነክርና] ከአንድ ወር እስከ ሁለት ዓመት በሚደርስ ቀላል እስራትና በመቀጮ ይቀጣል ይላል፡፡

አንድ ሰው በአደጋ ላይ በሚገኝበት ጊዜ አለመርዳትን ወንጀል የሚያደርገው የአገራችን ሕግ ለተራውና ለመደዴው ሰው መከራከሪያና መከላከያ አለው፡፡ ያልረዳሁት በራሴ ላይና ወይም በሌላ ሰው ላይ አደጋ ስለሚያደርስ ነው ማለት ይችላል፡፡ ሌላው ግን የሙያ ወይም የውል፣ የሕክምና ወይም ሌላ ሕጋዊ ግዴታ ያለበት ግን፣ ይህን መከራከሪያና መከላከያ ማቅረብ አይችልም፡፡ አምቡላንስ የአስቸኳይና የድንገተኛ አደጋ ፈጥኖ ደራሽ ምላሽ ሥራ ዋና ተዋናይ ነው፡፡ በዚህ ሕግ ተፈጻሚነት መሠረት ማንም ሰው ለምሳሌ ክፉኛ እየደማ ያለውን ሰው መኪናውን እየነዳ ዝም ብሎ ቢያልፈው የተጠቀሰውን ሕግ በመጣሱ ይጠየቃል፡፡ ያው ሰው እንዲህ ያለውን ሰው ዓይቶ መኪናውን አቁም ክፉኛ እየደማ ያለውን ሰው አፋፍሶ ወደ ሆስፒታል ሲወስደው፣ ሆስፒታል ከመድረሳቸው በፊት ደም ፈሶት ቢሞት፣ ይህ ሰው ከመጠየቅ የሚድነው ተራ ሰው፣ ለሕክምና ሙያ ማይም፣ ባዳና እንግዳ የሆነ ሰው ሲሆን ነው፡፡ የዚህ ምክንያት ሙያው፣ የሕክምና ሙያው ክፉኛ ደሙ እየፈሰሰ ያለን ሰው መጀመርያ ደሙ እንዲቆም የመጀመርያ ዕርዳታ (ድሬሲንግ) ከመስጠቱ በፊት ማንቀሳቀስ አይችልም ማለትን ይህ ተራ መደዴ፣ ለሕክምና ለሙያ ማይም የሆነ ሰው አያውቅምና ነው፡፡ ይህን ያደረገው ማለትም ያንን ክፉኛ እየደማ ያለውን ሰው አፋፍሶ በመኪና ጭኖ ወደ ሆስፒታል ላድርሰው ያለው ድንገት አንድ ሐኪም ቢሆን ግን ይጠየቃል፡፡ በአደጋ ላይ የሚገኘውን ሰው በሚገባ፣ ሙያው በሚጠይቀው ልክና መንገድ አይደለም ተብሎ፡፡ እና አምቡላንስን የመሰለ የድንገተኛና የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ መኪና አሽከርካሪ ሆኖ የእኔ ሥራ መኪና መንዳት ብቻ ነው ማለት፣ በግለሰብም ሆነ በተቋም ደረጃ ለሙያና ለኃላፊነት መታመንን ከማሟላት ጋር ይጣላል፡፡

ለምሳሌ ያነሳነው የአምቡላንስ ተሽከርካሪ ሾፌር ለሙያና ለኃላፊነት የመታመን ልክና መልክ ግን በዚህ ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ መኪናውም፣ አምቡላንሱም፣ ባለ አምቡላንሱም፣ የአምቡላንስ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቱም፣ እንዲሁም ሾፌሩ ጭምር ይህንን የመሰለ ሙያና ኃላፊነት አለባቸውና አገርና ሕግ ለአደጋ አገልግሎት ተሽከርካሪዎች ልዩ ‹‹መብት›› ሰጥቷል፡፡ የመኪናው መንገድና የትራፊኩ ብዛት በፈቀደው ልክ አገሩን፣ ከተማውን እያተራመሱ የመንገድ ትራፊክ ሕግ ሳይከተሉ፣ ሳይቆሙና ሳይፈተሹ እንዲሄዱ ይፈቀድላቸዋል፡፡ የአደጋ አገልግሎት ተሽከርካሪ ናቸው ብሎ ሕግ ይህን ሁሉ ያመቻቸላቸው፣ ሌላው አሽከርካሪም እግረኛም ሰው የማዳን አገልግሎት እየሰጡ ነው ብሎ መንገድ የሚለቅላቸው፣ የሚቆምላቸው፣ ቅድሚያ የሚሰጣቸው እነዚህ ተሽከርካሪዎች ግን ኮንትሮባንድ ዕቃ እያሸጋገሩ፣ የሽብር የወንጀል ድርጊት እየፈጸሙ ቢሆንስ? መከላከያውና መጠበቂያው ምንድነው? ለሙያና ለኃላፊነት መታመንን የት እናገኘዋለን? እንዴትስ እናረጋግጠዋለን? የሚለው ጥያቄያችን ትርጉም እያገኘ የሚመጣው እንዲህ ያለ ነገርም መኖሩን ስንረዳ ነው፡፡ ለአምቡላንስ ሾፌርነት መኪና የማሽከርከር ችሎታና ልምድ ብቻ ሳይሆን፣ የሚሠሩበትን ተቋምም ሙያ ሕክምናውንም ማወቅና መካን ያስፈልጋል ብሎ መወሰን ይቻላል፡፡ ለሌላውም የመሃላ ቃል መፈጸምን ግዴታ ማድረግ የተለመደ ነው፡፡ በአገር ደረጃም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያን ሕመምና በሽታ የምንገላገለው ግን ለሥራ መደቡ የሚያስፈልጉትን የትምህርት ደረጃዎችና የሥራ ልምዶች በሰፊውና በዝርዝር በመደንገግ፣ እንዲሁም ለሥራ ቦታው የተመደበውን ሰው የመሃላ ቃል በማረጋገጥ አይደለም፡፡ የተለያዩ የሥራ መደቦችና ሙያዎች የሚጠይቁትን ለሥራ አደራ የመታመን ጥንካሬን፣ ኃላፊነት የማክበር ጨዋነትን የምናገኘው ገለልተኛ ተቋማት የመገንባት ሥራችን የሁሉንም የጋራ መግባባት ሲጎናፀፍ ነው፡፡

በአገር ውስጥ ተጋድሏችን እንዲህ ያለው ትግል ከብዙ አቅጣጫ የተጀማመረ ቢሆንም፣ ዋናው የሲቪል ሰርቪስ ተቋም ግን ከለውጥ በፊት በነበሩት ያለፉት 27 ዓመታት ‹‹የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም›› በቃኝ ያለ ይመስላል፡፡ የአገራችንን መንግሥታዊ አውታራት ከገዥው ፓርቲ መለየት እስኪሳነን ድረስ ተንሰራፍቶ የኖረው የአንድ ፓርቲ አገዛዝ፣ ሲቪል ሰርቪሲ ውስጥ ሥር ነቀል ዕርምጃ ባለመወሰዱ ዛሬም ሲፈልገውና ሲያሰኘው በተለያየ ድምፅ አለሁ፣ አለሁ ማለቱን አልተወም፡፡ ዛሬም በቋሚው ሲቪል ሰርቪስና መንግሥት በምርጫ በተቀያየረ ቁጥር በሚለዋወጡት በፖለቲካ ተሿሚዎች መካከል ልዩነት ያበጀ ሕግና ለውጥ አላየንም፡፡ እዚህ ላይ እያልከሰከስንና ደጋግመንም በአረም እየተመላለስን የሠራነው የቢወቅጡት እምቦጭ ሥራ፣ ዓለም አቀፋዊ ተቋማት ወይም ድርጅቶች ውስጥ እየተንፀባረቀ ጉድ አድርጎናል፡፡

እንደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያሉ ዓለም አቀፋዊ ተቋማት (IOs ይባላሉ) የማኅበርተኞች ድርጅቶች ናቸው፡፡ ማኅበርተኞች፣ አባል አገሮች፣ ማኅበርተኞች ሆነው ያቋቋማቸው፣ በጠቅላላ የአባላት ጉባዔ ደረጃና እዚያ በተወከሉ በተገኙ ልዑካን ወይም ዲፕሎማቶች አማካይነት የየአገራቸውን የላቀ እንደራሴያዊ ፖለቲካ የሚያስተጋቡበት፣ የሚገልፁበት መድረክ ነው፡፡ ይህ ብቻም አይደለም፣ የአገር ድምፅ በእንደራሴዋ አማካይነት የሚሰማበት ቦታ ብቻ ሳይሆን፣ አባል አገሮች ከሞላ ጎደል ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ ዓለም አቀፋዊ ማኅበር ሠራ የሚያካሂዱና በዚሁ ተቋም የተቀጠሩ ዜጎቻቸውን የሚያቀርቡበት ተቋማት/ድርጅቶች ወይም ማኅበራት ናቸው፡፡ የእነዚህ ሁለት ነገሮች የየብቻ ባህርይ ግን በዝምታ የታለፈ አልነበረም፡፡ በዚህ ምክንያት ከሊግ ኦፍ ኔሽንስ ጀምሮ፣ በተለይም ደግሞ ከተመድ መቋቋም ጋር ዓለም አቀፋዊውን ሲቪል ሰርቪስ፣ ሲቪል ሰርቪሱን ከማገሩት ሰዎች የዜግነት አገር ተፅዕኖ ለመከላከል ዝርዝርና ቁልጭ ያሉ ግልጽ ሕጎች ወጡ፡፡ ይህን መርህ ያቋቋመው የመንግሥታቱ ድርጅት ቻርተር አንቀጽ 100 እና በእሱም መሠረት የወጡ ሌሎች ድንጋጌዎች ናቸው፡፡ በዚህ ኢንተርናሽናል ሲቪል ሰርቪስ ሕግ መሠረት ለምሳሌ አንቶንዮ ጉተሬስ የመንግሥታቱ ድርጅት ከፍተኛ ቅጥር ሠራተኛ እንጂ፣ የፖርቹጋል ወኪል ወይም አባል የነበሩበት የሶሻሊስት ፓርቲ ‹‹የእኛ ሰው በUN›› አይደሉም፡፡ የፖርቹጋል በተመድ ቋሚ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር አሁን አና ፓውላ ዘካሪያስ ናቸው፡፡ ፖርቹጋላዊው የተመድ ቋሚ መልዕክተኛ የሹመት ደብዳቤያቸውን ለአንቶንዮ ጉተሬስ ሲያቀርቡ፣ ሲነጋገሩ ይህም ‹‹ተራ›› ዜና ሲሆን ያየነው ቢያንስ ቢያንስ በንድፈ ሐሳብ ደረጃ ገለልተኛነትን የአንድ አገር ዜጋ በመሆን/አለመሆን ላይ እፈልጋለሁ ማለት፣ ሌላው ቢቀር ፖርቹጋል ውስጥ ለፖርቹጋል የሥልጣኔ ደረጃ ወራዳ ነገር በመሆኑ ነው፡፡

እኛ አገር ግን ይህን መሠረታዊና መነሻ ነገር አልጨበጥንም፡፡ ሲጀመር ገና ከመነሻው እንዲህ ያለ ነገር ሲገጥመን፣ የኢትዮጵያ ሰው የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ሲሆን፣ በጄኔቫ መቀመጫውን ባደረገው በኢትዮጵያ የጄኔቫ ቋሚ መልዕክተኛችንና በዓለም የጤና ድርጅት ኢትዮጵያዊው የሥራ ውል ቅጥር ሠራተኛ (ባለሥልጣን) መካከል ያለው ልዩነት ሁሉም አልገባውም፡፡ ኢትዮጵያውያን ኢንተርናሽናል ሲቪል ሰርቪስ ውስጥ በብዛት መግባታቸውን ማድነቅ፣ በዚህ መደሰት፣  ለዚህም መትጋትና እሱኑም ማበረታታት አንድ ነገር ነው፡፡ ይህንን ከአገር ‹‹ውክልና›› ወይም እንደራሴነት ሥራና አደጋ ጋር ማምታታት ግን ስህተትና ጥፋት ነው፡፡ ይህንን የትም ቦታ፣ በማንም ዜጋ ደረጃ የሚገኝ አለማወቅ፣ ግን ሙሉ በሙሉ በሕወሓት ቁጥጥር ሥር በነበረ መንግሥታዊ አውታራት ላይ ሆኖ ለብቻው ይገዛ የነበረውና አገሪቱን የምርኮ ሲሳይ፣ የዘርፊያ ማሳ ያደረጋት ገዥ ቡድን መንግሥትና ፓርቲ የሚባል ነገር ሳያሰናክለው፣ የጎጠኛ ፓርቲውን ወኪል ዓለም አቀፍ ድርጅት ውስጥ ሲተክል ያኔ ቀርቶ ዛሬ ከብዙ ኢትዮጵያውን ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፋዊውን ሲቪል ሰርቪስ ክፉኛ የጎዳ ጥፋት በኋላ እንኳን ደረስኩላችሁ ያለን የሥርዓት መጠበቂያ አላገኘንም፡፡ አገራችንም ዓለም አቀፋዊው የጤና ድርጅትም ውስጥ ኃላፊነትን የማክበር ጨዋነት ለሙያና ሙያው ለሚጠይቀው የባህርይ አረማመድ የመታመን ክብርና ሰውነት ፖለቲካዊ ዝንባሌን፣ የብሔር ሠፈርን፣ የጎጥ ፖለቲካን በልጦ እስኪጠና ድረስ አለመገንባቱን መሰከርን፡፡

ዳይሬክተር ጄኔራሉ ለሁለተኛ ጊዜ መሃላ ፈጸሙ፡፡ የሁለተኛው የሥራ ዘመናቸው አገስት 16 ቀን 2022 (ነሐሴ 10 ቀን 2014 ዓ.ም.) ወዲህ ደግሞ ግልጽና ከዚህ በኋላ በጭራሽ መመስጠር ወይም በሥውር ወይም መሸፋፈን የሌለበትን ፀረ የኢትዮጵያ ዘመቻ በአዲስ መልክ ሥራ ጀምረናል ብለው በግልጽና ዋና ሥራቸው አድርገው ገፉበት፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥስ እሺ! ዓለም አቀፋዊው ሲቪል ሰርቪስ ተቋም ውስጥ ለሙያና ለኃላፊነት መታመን እንዲህ ክህደት ሲፈጸም፣ ከሊግ ኦፍ ኔሽንስ ጀምሮ መቶ ዓመት ተገነባ የተባለው ሥርዓት ምን ነካው?

የዓለም የጤና ድርጅት፣ በሰፊው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሥርዓት ማዕቀፍ ውስጥ የሚገኝ የተመድ ስፔሻላይዝድ ኤጀንሲዎች ከሚባሉት መካከል አንዱ ሆኖ፣ ጤና ላይ የሚሠራ በይነ መንግሥታዊ የማኅበርተኞች ድርጅት ነው፡፡ አባል አገሮች ወይም ማኅበርተኞች በእንደራሴዎቻቸው አማካይነት ለየትኛውም አባል ወይም ማኅበርተኛ አገር በማያዳላ ወይም በማያዳልጥ የተስተካከለ ሜዳ ጥቅማቸውን የሚገልጹበትና የሚያስከብሩበት መድረክ ነው፡፡ ይህንን ዋነኛ ሥራውን የሚሠራበት፣ የሚያደራጅበትና የሚያካሂድበት በሕግ ተወስነው የተደነገጉና በምርጫ የሚቋቋሙ የሥልጣን አካላት አሉት፡፡ ዋነኛውና የጤና ድርጀቱ ከፍተኛው የሥልጣን አካል ሁሉም አባል አገሮች እንደራሴዎች የሚገኙበት ጄኔቫ ውስጥ በዓመት አንድ ጊዜ የሚሰበሰበው ጉባዔው ነው፡፡ የዚህ ከፍተኛ የሥልጣን አካል አስፈጻሚ አካል 34 አባላት ያሉት ከአባል አገሮች መካከል በምርጫ የተደራጀ ቢያንስ በዓመት ሁለት ጊዜ የሚሰበሰበው ቦርድ ነው፡፡ አስተዳደራዊ አካሉ ደግሞ በዳይሬክተር ጄኔራሉ የሚመራው ጽሕፈት ቤት ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ ሕግና ሥርዓት አላቸው፡፡ ተቋሞቹም በምርጫ የተቋቋሙትን ልዩ ልዩ የሥልጣን ተቋማትን የማገሩትንም አገሮችን፣ እንዲሁም ግለሰቦችን ጭምር የባህርይ አረማመዳቸውን፣ ጨዋነታቸውን የሚገዛ በሕግና በደንብ የተደገፈ ወግና ባህል አለው፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ራሱ እንዳለም ሆነ በዚህ ሥርዓት ውስጥ የሚገኘው እያንዳንዱ ተቋም፣ ለምሳሌ የዓለም የጤና ድርጅት አገሮች በአባልነት ያቋቋሙት ድርጅት ነው፡፡ ሥርዓት ካልያዙ፣ በግልጽ የተወሰነ መተዳደሪያና የባህርይ መረማመጃ ካልተበጀላቸው፣ በተለይም መረን ከተለቀቁ የጉልበተኞች መጫወቻ የልዩ ጥቅም ማምረቻ ለም መሬት የሚያበጁ ሁለት ነገሮች አሉ፡፡ ኢንተርናሽናል በይነ መንግሥታዊ ተቋማት የአገሮች እንደራሴዎች የተወከሉበት መድረክ ነው፡፡ ትልቁና ከፍተኛው የሥልጣን አካልም ይኸው ነው፡፡ ይህን ዋነኛ ሥራና አደራ ቀን ተቀን ለመወጣት የተቋቋመው ጽሕፈት ቤትና አስተዳደርም ከአባል አገሮች የተመለመሉ ‹‹ዜግነት›› ያላቸው ሠራተኞች የማገሩት ነው፡፡ እነዚህን ሁለቱን በእኛ ሁኔታ እንደምናየው፣ የሆነ ጊዜ የሰጠው፣ ሀይ የሚለውም የጠፋ ‹‹ደንቆሮ›› ካገኛቸው ጠላት መጉጃ፣ ወዳጅ ማሻሪያ መሣሪያ ያደርጋቸዋል፡፡ ጠቀምኩ ከሚለው በላይ ጉዳቱ ይከፋል፡፡ የማኅበርተኛ አገሮችን ሥርዓትም ያጠፋል፡፡ የአምቡላንስ ሾፌርን ለሙያውና ለኃላፊነቱ የመታመን ክብርን እንዴትና ከየት ‹‹አባታችን›› እናገኛለን ብለን በምሳሌነትና ለማብራሪያነት ያነሳነው ጉዳይ ተራና ቀላል ነገር አይደለም፡፡ የአደጋ ጊዜ አገልግሎት ተሽከርካሪዎችን በልዩ ዓይን የሚያይ ሕግ የሚወጣው፣ በእነዚህ ተሽከርካሪዎች ላይ ልዩ የብቃትና የደረጃ መሥፈርት የሚጣለው፣ በአሽከርካሪዎች ብቃት ላይ ተጨማሪ ሁኔታዎች ተፈላጊ ሆነው የሚደረደሩት በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ቴሌኮሙዩኒኬሽን ሕግ ውስጥ እያንዳንዱ የዓለም አቀፍ ቴሌኮሙዩኒኬሽን ኅብረት አባል የሆነ አገር የግድ ሊያከብረው በሚገባ ሁኔታ ‹‹የልዩ ቁጥር አገልግሎትን›› የሚገዛ ሕግ አለ፡፡ አገራችንም ይህንን እንደ ነገሩ የሚደነግግ ሕግ አላት፡፡ በዚህ ሕግ መሠረት በአጠቃላይ ለአደጋ ጊዜ የሚያገለግሉ ልዩ ቁጥሮች ይመደባሉ፡፡ ለእሳት አደጋ መከላከያ፣ ለአምቡላንስ አገልግሎት፣ ለፖሊስ ጣቢያዎችና ለሌሎች የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ ለሕዝብ የሚሰጡ ተቋማት ናቸው ብሎ አግባብ ያለው የመንግሥት ተቋም ለሚወስናቸው ድርጅቶች የሚደረጉ ጥሪዎች ከክፍያ ነፃ ናቸው፣ ወዘተ ይላሉ፡፡ የቴሌፎን ቁጥሮችም ከመደበኛው የሚለዩ የሚያስታውቁ በሦስት አኃዝ ብቻ የተወሰኑትም በዚህ ምክንያት ነው፡፡ እንዲያም ሆኖ ልዩ ልዩና የተጠቃቀሱት ጥረቶቻችን ሁሉ ሥርዓት ወደ ማደላደል የግንባታ ሥራ ውስጥ ተቀናጅተው የፈሰሱና የተቀላቀሉ ባለመሆናቸው ሕግ የማስከበር፣ በሥራ ላይ የማዋል ጥረታችን የቢሻን በመሆኑ የጠቀስናቸው የሕግ ዓይነቶች ተራ ‹‹ቅራቅንቦ›› ሆኑ እንጂ፣ የአጠቃላይ አገርም ሆነ የአደጋ አገልግሎት ሥራችን ግንባታ ግብዓት አልሆኑም፡፡

የሥርዓት ግንባታችን ጥሩ የአምቡላንስ ሾፌር ማለትም ከመደበኛው መኪና ነጂ የተለየና ሻል ያለ የሾፌርነት ችሎታና ብቃት ያለው የሚሠራበትን የአደጋ አገልግሎት ሥራ ባህርይ የሚያውቅ የዚያም ዕውቀት ያለው መሆኑን የሚያረጋግጥ ብቻ ሳይሆን፣ እንዲህ ሆኖም ይህንን አሟልቶም የተቀጠረ ሾፌር ድንገት በዚህ ሙያዬና ኃላፊነቴ ቁማር ልጫወት፣ ለካስ ማመንዘር ይቻላል፣ ወዘተ ቢል ይህንን አሽትቶና አነፍንፎ ማስጠንቀቂያ የሚያሰማና አፈናጥሮ ከቦታው የሚያስወግድ ሆኖ መሠራት ይጎድለዋል፡፡ ተመድ ውስጥ ከአንድ መቶ ዓመት በላይ ዕድሜ ያለው የገለልተኛ የሲቪል ሰርቪስ ሕግና ባህል ግንባታ አለ፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን በዓለም የጤና ድርጅት ጽሕፈት ቤት ውስጥ ነፍስ የኢንተርናሽናል ሲቪል ሰርቪስ የሥነ ምግባር ደንብና መሃላን ሽራ የአንድ የፖለቲካ ፓርቲ ንብረት ሆና እስክታገለግል ድረስ የተዘቀጠው፣ ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ እያየ እንዳላይ ሆኖ ዝም በማለቱ ጭምር ነው፡፡ በታላላቅ አገሮች በጎ ፈቃድና ቁርጠኝነት ላይ የተመሠረተም ‹‹ተቋም›› ያልተገነባ ያህል በመሆኑ፣ ከዚህ ተምረንና አደጋ ላይ የወደቀውም በሕግ የመገዛት ወግና ባህሉ ሁሉ በመሆኑ ከአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ አፍሪካን ይዛ፣ በቀድሞ የፀረ ፋሽስት ትግሉ ጊዜ ለኢትዮጵያ አሸናፊነትና ለራሳቸውም ነፃነት የታገሉትን ጥቁር ሕዝችና ፀረ ኢምፔሪያሊቶች ከጎኗ አሠልፋ ከጄኔቫም፣ ከኒውዮርክም፣ ወዘተ በይፋ ድምጿን ማሰማት፣ አቤት ማለት አለባት፡፡              

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...