Tuesday, November 28, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አገልግሎቱን ወደ ጎረቤት አገሮች እያሰፋ የሚገኘው ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኮቪድ-19 ተህዋሲ ወረርሽኝ ሳቢያ ዓለማችን ባለፉት ሁለት ተኩል ዓመታትና አሁንም ድረስ በአያሌ የዓለም አገራት ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ያናጉ ሁነቶችን አስከትሏል። የወረርሽኙ መከሰትን ተከትሎ በዓለም ደረጃ ተጥሎ የነበረው የእንቅስቃሴ ገደብ የፈጠረው ቀውስ፣ በሌላ በኩል ደግሞ አገሮች በወረርሽኙ ምክንያት ከተደቀነባቸው ኢኮኖሚያዊ ችግር በፍጥነት ለማገገም በሚል በተናጠል የወሰዷቸው ዕርምጃዎች የንግድ ሚዛን መዛባትን፣ የወደቦች መጨናነቅን፣ የኮንቴይነር እጥረት መከሰትንና የባህር ማጓጓዣ ዋጋ መናርን በከፍተኛ ሁኔታ አስከትሏል፡፡ 

በሌላ ጎን ከተጀመረ ስድስት ወራቶች ያለፉት በሩሲያና በዩክሬን መካከል የተቀሰቀሰው ጦርነት ዓለም አቀፍ የሎጂስቲክስ ሥርዓቱን ሌላ መልክ እንዲይዝ እያደረገው ይገኛል፡፡ ይህ ሁኔታ አሁን ላይ ያለውን የዓለም አቀፍ ንግድ እንቅስቃሴ ተለዋዋጭ ገጽታን እንዲላበስ በማድረጉ በአጠቃላይ የባህር ትራንስፖርትና የሎጂስቲክስ ሰንሰለት እንቅስቃሴን ለመገመት አዳጋችና ፈታኝ አድርጎታል ይላሉ የዘርፉ አንቀሳቃሾች፡፡ 

ለአብነትም የወቅቱ የባህር ማጓጓዣ ዋጋ /Frieghtos Baltic index/ የ2022 መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ከ2020 ሁለተኛው ግማሽ ዓመት በኋላ የኮንቴነር ፍላጎት በዓለም ላይ በከፍተኛ ሁኔታ እንደጨመረ፣ ነገር ግን የተፈጠረውን ፍላጎት የሚያሟላ የኮንቴነር አቅርቦት አለመኖሩን ያሳያል፡፡

በቅርቡ የተከሰተው የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት በአውሮፓ የንግድ መተላለፊያ መስመር (ኮሪደር) በሆነው በጥቁር ባህር ወደቦች አካባቢ ከተፈጠሩ የንግድ መስተጓጎሎች በተጨማሪ በምዕራቡ ዓለም በሩሲያ ላይ እየተጣሉ ያሉ የኢኮኖሚ ማዕቀቦች በዓለም የንግድ እንቅስቃሴ ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ መሆኑንም ሪፖርቶች ያመለክታሉ፡፡ 

ሩሲያና ዩክሬን የዓለማችን ከፍተኛ የሆነ የሱፍ ዘይት፣ የስንዴ፣ የነዳጅና የብረት ንግድ ማዕከል መሆናቸው የሚታወቅ ሲሆን፣ በአገሮቹና አካባቢያቸው ላይ የተፈጠረው ቀውስ ከሁለቱ አገሮች በዘለለ በጥቁር ባህር ወደቦች የንግድ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ችግር ይፈጥራል። ከዚህም ባሻገር ከላይ የተጠቀሱትን ምርቶች እንቅስቃሴ በጉልህ ሊቀየር የሚችልበት ሁኔታ ሰፊ መሆኑ በግልጽ እየታየ ያለ ጉዳይ ነው፡፡

ለአብነትም የሁለቱ አውሮፓ አገሮች ጦርነት እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ አገሮች ላይ የሚያስከትላቸው ቀውሶች ከወዲሁ ጎልተው መታየት ጀምረዋል። በጠቅላላው በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት  በባህር ትራንስፖርት አገልግሎቱ ላይ የንግድ መስመር ለውጥ እንዲደረግ የሚያስገድዱ ሁኔታዎች መከሰታቸው፣ ከዚህ ቀደም በወረርሽኙ ምክንያት የተጎዳው የዓለም ኢኮኖሚ እያገገመ በሚገኝበት በዚህ ወቅት ላይ የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት መከሰት ዳግም የባህር ማጓጓዣ ዋጋ ንረት መፍጠሩንና ከነዳጅ ዋጋ ንረት ጋር በተገናኘ የባህር አገልግሎት ሥራ ላይ ተጨማሪ ወጪን ማስከተሉን የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት (ኢባትሎአድ) አስታውቋል፡፡

በተለይ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተከሰተ የኮንቴይነር እጥረት፣ የባህር ማጓጓዣ ዋጋ መናር ምክንያት የኢትዮጵያ የገቢና ወጪ ንግድ እንቅስቃሴ በቀጥታ ተጎጂ እንደሆነ ሪፖርቶች ያመለክታሉ። ይህ ሁኔታ በኢባትሎአድ አፈጻጸም ላይ ተፅዕኖ ያሳደረ መሆኑን፣ በተለይም በሌሎች የባህር ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ኩባንያዎች ላይ መጫኛ ቦታ ማጣትና የኮንቴይነር አቅርቦት እጥረት አሉታዊ ተፅዕኖ እንደፈጠረበት ድርጅቱ አስታውቋል፡፡ 

ይህንም ተግዳሮት ለመቋቋም ኢባትሎአድ ጭነቶችን ከመጫኛ ወደቦች ለማንሳት ውል ከገቡ አጓጓዥ የመርከብ ድርጅቶች ጋር በመነጋገር፣ የዋጋና የአገልግሎት ድርድር በማድረግ ችግሩን በመፍታትና ሌሎች አማራጮችን ሁሉ ለመጠቀም ጥረት ማድረጉን በተጠናቀቀው ሳምንት አጋማሽ በዋና መሥሪያ ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አመላክቷል፡፡ በተጨማሪም ድርጅቱ የኮንቴይነር እጥረትን ለመቅረፍ የተለያዩ ጥረቶች በማድረግ በበጀት ዓመቱ ከአምስት ሺሕ በላይ ኮንቴይነሮችን በመግዛት ወደ ሥራ እንዲገቡ ማድረጉንና በዚህም በድርጅቱ መርከቦች ከፍተኛ ውጤት ማስመዘገቡን የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሮባ መገርሳ ገልጸዋል፡፡ 

‹‹የዓለም የባህር ማጓጓዣ ገበያ ዋጋ እየናረ ቢመጣም እስከ 22 በመቶ የሚደርስ የባህር ማጓጓዣ ዋጋ ቅናሽ በማድረግ እያጓጓዝን እንገኛለን፤›› የሚሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ በሌላ በኩል አጓጓዥ ድርጅቶችን በማወዳደርና ድርድሮችን በማድረግ በተሻለ ቅናሽ ዋጋ አገልግሎት የሚቀርብበትን ሁኔታ መፈጠሩን ጠቅሰዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ‹‹በማምረት ሥራ ላይ ለተሰማሩና የወጪ ዕቃ ላኪዎች የአምስት በመቶ የባህርና የ25 በመቶ በየብስ ትራንስፖርት ማጓጓዣ ዋጋ ላይ ቅናሽ በማድረግ አገልግሎት በመስጠት እንገኛለን፤›› የሚሉት አቶ ሮባ፣ እንዲሁም ከጂቡቲ ወደብ ጭነቶችን በቅንጅትና በፍጥነት በማንሳት፣ ባቡርና ከባድ ተሽከርካሪዎች በተቀናጀ መንገድ እንዲሠሩ በማድረግ፣ ኮንቴይነርና የብትን ጭነቶችን በወቅቱ በማጓጓዝ ለተጠቃሚው በወቅቱ በማድረስ ድርጅቱ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የተሳካ ሥራ መሥራቱን ገልጸዋል፡፡  

በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ዓመቱን ያሳለፈው የባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅቱ፣ የበጀት ዓመቱ ሲጀመር የነደፈውን ዕቅድ በመከለስ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በባህር ትራንስፖርት አገልግሎት ዘርፍ ከሚሰጡት አገልግሎቶች ማለትም የድርጅቱን መርከቦችና የኪራይ መርከቦችን ተጠቅሞ በማጓጓዝ፣ በጭነት አስተላላፊነት አገልግሎት በመልቲ ሞዳልና በዩኒ ሞዳል የትራንስፖርት ሥርዓት ኮንቴይነር በማጓጓዝ፣ በወደብና በተርሚናል አገልግሎት ከ7.2 ሚሊዮን ቶን በላይ ገቢና ወጪ ጭነት በማጓጓዝ  51.4 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን፣ ከዚህም ከታክስ በፊት 5.6 ቢሊዮን ብር ትርፍ ማግኘቱ አስታውቀዋል፡፡

ኢባትሎአድ በድርጅቱ መርከቦች ለጎረቤት አገሮች በምጽዋና በበርበራ አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን፣ የድርጅቱን መርከቦች በተሻጋሪ የንግድ (Cross Trade) አገልግሎቶች ላይ በማሰማራት ከሌሎች ጊዜዎች የተሻለ ውጤት መመዝገቡንና የድርጅቱን መርከቦች ትርፋማነትም ማሳደግ መቻሉን አቶ ሮባ ይናገራሉ፡፡

ካቦታጅ በአገር ውስጥና ጠረፍ አገሮች የሚደረግ የባህር ትራንስፖርት አገልግሎት መሆኑ ይታወቃል፣ በኢትዮጵያ መርከቦች ከኢትዮጵያ አልፎ ለሌሎች አገሮች አገልግሎት እየተሰጠ እንደሚገኝም እንዲሁ፡፡

አቶ ሮባ እንደሚናገሩት፣ በምፅዋ በኩል ከኤርትራ የሚወጡ ወጭ ጭነቶች እየተስተናገዱ ሲሆን፣ በተወሰነ ደረጃ ለጅቡቲ መንግስትም ኮንቴይነር ጭነቶችን ጨምሮ ኢባትሎአድ አገልግሎት እየሰጠ ነው። ከዚህ በሻገር ሁለት የኢባትሎድ የጭነት መርከቦች የኮንቴይነርና የብትን ጭነት ትራንስፖርት አግልግሎት በመደበኛነት ለሶማሌንድ እየሰጡ ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በዚህ ወቅት ወደ ኬንያ ናይሮቢ፣ ሞምባሳ የወደብ አገልግሎት በመጀመሩ ሞምባሳን ከሌሎች አገሮች ጋር የማገናኛት ሥራ በሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅቱ መጀመሩን የሚናገሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ከዚህ በሻገር ድርጅታቸው የታንዛንያ ወደቦችን ከሌሎች አገሮች ጋር፣ የደቡብ አፍሪካና አንዳንድ የምዕራብ አፍሪካ አገሮችን ከሌሎች አገሮች ጋር የማገናኛት ሥራ ላይ መበርታተቱን ይገልጻሉ፡፡

‹‹የድርጅቱ መርከቦች ሙሉ በሙሉ ዕዳቸውን ከፍለው ጨርሰው ወደ ትርፍ ገብተዋል፤›› የሚሉት አቶ ሮባ፣ ለአብነትም በ2014 የበጀት ዓመት 1.05 ሚሊዮን ቶን የሌሎች አገሮችን ጭነት ከማጓጓዛቸው ባሻገር፣ 19 ሺሕ ገቢ ኮንቴይነሮች የኢትዮጵያ ጭነቶች እንደተጓጓዙባቸው ያስረዳሉ፡፡ 

እንደ አቶ ሮባ ገለጻ፣ ለድርጅቱ የትርፍ ማደግ አስተዋፅኦ ያደረጉት ድርጅቱ ባለቤትነት የያዛቸው መርከቦች ናቸው፡፡ ከዚህ ቀደም መርከቦቹ በኪሳራ ይሠሩ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ሮባ፣ ይህንን ኪሳራ ያስከተለውም የድርጅቱ የአገልግሎት ትከሩት ኢትዮጵያን ብቻ ማዕከል ያደረገ በመሆኑ ነው። የኢትዮጵያ ጭነት ሲቀንስ የድርጅቱ መርከቦች አገልግሎትም ይገደባል፣ ይህም በድርጅቱ ገቢ ላይ ተጽእኖ ያስከትል እንደነበር ጠቅሰዋል።

አፍሪካ ውስጥ ብቸኛ አገርን የሚወክል (ፍላግ ካርየር) የሆነ የባህር ትራንስፖርት አገልግሎት አቅራቢ ድርጅት ኢባትሎአድ ነው የሚሉት አቶ ሮባ፣ እንደ ሌሎች የአፍሪካ አገሮች ባንዲራ የሚያከራይ ሳይሆን፣ በራሱ መርከቦች ወደ የተለያዩ የመዳረሻ አገሮች አገልግሎት መስጠቱ የተለየ የሚያደርገው ስለመሆኑም ይናገራሉ፡፡

ከትልልቆቹና ግዙፍ ኩባያዎች ጋር ለመወዳደር በሚል የምንሠራው ሥራ የለም የሚሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ድርጅቱ ከሌሎች ተመሳሳይ አገልግሎት ሰጪ ኩባንያዎች መርከቦች የጭነት ቦታ እየተከራየ ጭነቶችን እንደሚያጓጉዝ ገልጸዋል።

ኢባትሎአድ ከሌሎች ዓለም አቀፍ የባህር ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች የጅምላ ዋጋ እንዲሰጡት በማድረግ አብዛኞቹ ዕቃዎችን በዓለም አቀፍ የመርከብ ኩባንያዎች እንዲጓጓዙ እንደሚያደረግ አቶ ሮባ ገልጸዋል። 

ይህም አቀራረብ ኢኮኖሚውን በከፍተኛ ሁኔታ ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ከዚህ በሻገር ኢባትሎአድ መርከቦችን በመከራየት እንደ ማዳበሪያ፣ ስንዴና ስኳር የመሳሰሉ ሸቀጥና ምርቶችን በማጓጓዙ ረገድ ጥሩ አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱን ተናግረዋል። ነገር ግን በአሁኑ ወቅት የስኳር ግዥ ሒደቱ በመቀየሩ ድርጅቱ ይሰጥ የነበረው አገልግሎት እንደሚቋረጥ ጠቁመዋል። የስኳር ግዥ ሂደቱ መቀየር በአቅርቦቱ ላይ ጥሩ ውጤት ያመጣል ብለው እንደማያምኑም አቶ ሮባ አስታውቀዋል፡፡

በጠቅላላው ዓለም ላይ ያለው የመርከብ ማጓጓዣ ዋጋ ጭማሪ፣ ከሁለቱ የአውሮፓ አገሮች ጦርነት ጋር ተያይዞ የተፈጠረው የሸቀጦች ሽሚያና የዋጋ ጭማሪ፣ በወደቦች ያለው የአገልግሎት አሰጣጥና መጨናነቅ አሁንም የባህርና የሎጂስቲክስ ዘርፉን እየፈተነው የቀጠለ ጉዳይ ነው፡፡ 

ኢኮኖሚው እስካደገ ድረስ በዚያው ልክ የባህር ሎጂስቲክስና ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅቱ የሚሰጠውን አገልግሎት የሚደግፍ በመሆኑ፣ ይህንን መሠረት በማድረግና ከግንዛቤ ሊወሰዱ የሚገባቸውን ጉዳዮች ያገናዘበ ስትራቴጂ በመንደፍ፣ የሚገዙ ተሽከርካሪዎች ለአገር ውስጥ ትራንስፖርት አገልግሎት እንዲሰጡ በማድረግ፣ ደረቅ ወደቦች ላይ ተጨማሪ አገልግሎቶችን በማቅረብ የድርጅቱን ውጤታማ አፈጻጸም ለማስቀጠል የሚሠራ ስለመሆኑም ተመላክቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች