የአሜሪካ መንግሥት ኢትዮጵያን ከአጎዋ (የአፍሪካ ነፃ የገበያ ዕድል) ተጠቃሚነት ማገዱን ተከትሎ ምርታቸውን ወደ አሜሪካ ሲልኩ የነበሩ በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሚገኙ አምራቾች በገበያ ዕጦት ያሰናበቱዋቸው ሠራተኞች ቁጥር ከአምስት ሺሕ በላይ ማለፉ ተገለጸ፡፡
ከኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌደሬሽን (ኢሰማኮ) ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ኢትዮጵያ የአጎዋ ዕድል ተጠቃሚ እንዳትሆን በአሜሪካ መንግሥት ዕገዳ ከተጣለባት ወዲህ በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ብቻ አምስት የጨርቃ ጨርቅ አምራቾች በገጠማቸው የገበያ ዕጦት ሠራተኞችን መቀነሳቸውንና በመቀነስ ላይ ይገኛሉ፡፡ በአጎዋ ዕድል ተጠቅመው ወደ አሜሪካ ከቀረጥ ነፃ ምርቶቻቸውን ሲያስገቡ ከነበሩ ኩባንያዎች ውስጥ ሁለቱ ሙሉ በሙሉ ሥራ ያቆሙና ሠራተኞቻቸውን ያሰናበቱ ሲሆን ሦስቱ ደግሞ ሠራተኞቻቸውን ቀንሰው ከማምረት አቅማቸው በታች እያመረቱ ነው፡፡
ሙሉ በሙሉ ሥራ ካቆሙት ኩባንያዎች ውስጥ ፒቪኤች 1,400 እና ቻርቸርስ 22 ሠራተኞች ነበሯቸው፡፡ ቤስት፣ ኤፔክና ኳድራንት የተባሉት ኩባንያዎች ደግሞ ሥራቸውን ሙሉ በሙሉ ባያቆሙም እንደ ቅደም ተከተላቸው 3,000፣ 1,200 እና 161 ሠራተኞች እንደቀነሱ መረጃው ያመለክታል።
በጥቅሉ ከላይ የተጠቀሱት አምራች ኩባንያዎች 5,783 ሠራተኞችን እንደቀነሱ ታውቋል። እነዚህ ኩባንያዎች የተለያዩ የገበያ አማራጮችን በማፈላለግ በአጎዋ ያጡትን ገበያ ወደ ሌሎች አገሮች በመላክ እንዲሁም ታክስ በመክፈል ወደ አሜሪካ ምርቶቻቸውን በመላክ ጭምር እየሠሩ ቢሆንም አሁንም የገበያ እጥረቱ እየፈተናቸው ነው፡፡
ከኢትዮጵያ የጨርቃ ጨርቅ አልባሳትና የመሳሰሉት ሠራተኞች ኢንዱስትሪ ፌዴሬሽን ያገኘው ተጨማሪ መረጃ እንደሚያመለክተውም፣ ከአጎዋ ተጠቃሚነት ዕገዳ በኋላ በተለይ በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ያሉ ኩባንያዎች ችግር ውስጥ መሆናቸውንና አማራጭ ገበያ በማጣታቸው ተጨማሪ ሠራተኞች ሊቀነሱ ይችላሉ የሚል ሥጋት አይሏል፡፡
ከገበያ ዕጦት ጋር በተያያዘ እነዚህ ኩባንያዎች በአሜሪካ መንግሥት የተጣለው ክልከላ ካልተነሳ ወይም አዲስ ገበያ የማያገኙ ከሆነ ተጨማሪ የሠራተኞች ቅነሳ ሊያደርጉ የሚችሉ መሆኑንም የፌደሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ አንገሶም ገብረ ዮሐንስ ሥጋት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
ለዚህም እንደማሳያ ኤፔክ የተባለው ኩባንያ ተጨማሪ 100 ሠራተኞች ለመቀነስ እንደሚችል በዚህ ሳምንት ማስታወቁን ጠቁመዋል፡፡ አንፑቺንና ሔላ ሱብሪን የተባሉት ሁለት ኩባንያዎች ደግሞ 400 ለሚደርሱ ሠራተኞቻቸው ከክፍያ ጋር አስገዳጅ የዓመት ፈቃድ መስጠታቸውን ጠቅሰው፣ ይህም በቀጣይ ምን ሊከተል እንደሚችል አመላካች መሆኑን ገልጸዋል።
ይህ አካሄድ በሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞችን የሥራ ዋስትና እያሳጣ በመሆኑ ጉዳዩ እጅግ አሳሳቢ እንደሆነባቸው የገለጹት የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌደሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ፣ ኢትዮጵያ ከአጎዋ ተጠቃሚነት እንድትወጣ በመደረጉ በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ብቻ ወደ ስድስት ሺሕ የሚጠጉ ሠራተኞች ሥራ ማሳጣቱን ገልጸዋል።
ጉዳዩን የበለጠ አሳሳቢ የሚያደርገው ደግሞ የሠራተኞቹ ከሥራ መሰናበትን ተከትሎ፣ በሥራቸው የሚተዳደሩ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ቤተሰቦቻቸውን ችግር ውስጥ እየከተተ መሆኑ ነው ብለዋል፡፡
በአሜሪካ መንግሥት የተወሰነው ውሳኔ አግባብ ያለመሆኑን የሚገልጹት አቶ ካሳሁን ዕርምጃው መንግሥትን ሳይሆን በይበልጥ እየጎዳ የሚገኘው ሠራተኞችን በመሆኑ በአሜሪካ ከሚገኙ የሠራተኞች ማኅበራት ጋር በመሆን ዕገዳው እንዲነሳ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረገ መሆኑን አቶ ካሳሁን ገልጸዋል፡፡
ባለፈው ወርም የኢሰማኮ ልዑካን ወደ አሜሪካ በማምራት በኢትዮጵያ ላይ የተጣለው ዕገዳ እያስከተለ ያለውን ጉዳት በማስረዳት፣ ይህ አሳሳቢ ጉዳይ በአሜሪካ ሠራተኛ ማኅበራት በኩል ጥያቄው ለሚመለከተው የአሜሪካ መንግሥት አካል እንዲቀርብ ማድረጋቸውንም አቶ ካሳሁን አመልክተዋል፡፡
ኢሰማኮ ቀደም ብሎም ቢሆን በኢትዮጵያ የአጎዋ ተጠቃሚነት ላይ የተጣለው ዕገዳ ተፈጻሚ እንዳይሆን አሜሪካ ከሚገኘው አጋር ማኅበር ጋር በመሆን እስከ ኮንግረስ ድረስ በመሄድ ግፊት ሲያደርግ እንደነበርም ይታወሳል፡፡
አሁን ያለውን ችገር ለመቅረፍ የአሜሪካ መንግሥት የጣለውን ዕገዳ እንዲያነሳ የኢትዮጵያ መንግስትም እየጠየቀ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ካሳሁንም፣ ኢሰማኮም ከአሜሪካ ተቋማት ጋር ያለውን ግንኙነት በመጠቀም የዕገዳው እንዲነሳ የጀመረውን ጥረት እንደሚቀጥልበት ገልጸዋል፡፡ በመንግሥት በኩል ለእነዚህ ፋብሪካዎች አማራጭ ገበያ ለማፈላለግ የተጀመረው ጥረት ሠራተኞችን ከብተና ሊያድን የሚችል መሆኑን በጥንካሬ አንስተው ተጠናክሮ እንዲቀጥል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
አቶ አንገሶም እንዳመለከቱት፣ ደግሞ በሐዋሳ ያለው ሥጋት በሌሎች ኢንዱስትሪ ፓርኮች ላይም እየታየ ነው፡፡ ለዚህም ከአጎዋ ገበያ ጋር ግንኙነት ያላቸው የኮምቦልቻና የቦሌ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ያሉ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎችን በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡
በመሆኑም እነዚህ ሁለቱ ኢንዱስትሪዎችና በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ያሉ የጨርቃ ጨርቅ አምራቾች አሁን እየተገዳደራቸው ያለው የገበያ ዕጦት እስከ ጥቅምት 2018 ዓ.ም. ድረስ ካልተፈታ እስከ 60 በመቶ የሚሆኑ ሠራተኞች ሊቀንሱ ይችላሉ የሚል ሥጋት እንዳላቸው አመልክተዋል፡፡ በሌላ በኩል ግን በአጎዋ ምክንያት እንዲህ ያሉ ችግሮች ቢታዩም በሐዋሳም ሆነ በሌሎች የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ያሉ የቻይና ኩባንያዎች ምርቶቻቸውን ወደ ቻይና መላክ በመጀመራቸው ችግሩን በአንፃራዊነት መቋቋማቸው ተጠቅሷል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን ሰሞኑን እንዳስታወቀው፣ የሚያስተዳድራቸው 92 የኢንዱስትሪ ፓርኮች የ2014 ዓ.ም. አፈጻጸም መልካም የሚባል ነው፡፡ ሆኖም ካጋጠሙት ተግዳሮቶች ውስጥ አንዱ ኢትዮጵያ ከአጎዋ ተጠቃሚነት በመታገዷ ፓርኮቹ የተሻለ የሥራ አፈጻጸም እንዳያስመዘግቡ ተፅዕኖ ፈጥሯል፡፡ ቢሆንም በ2014 የምርት ገበያ 13ቱ ኢንዱስትሪ ፓርኮች 196.3 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘታቸውን፣ እነዚህ ፓርኮችም ለ57 ሺሕ ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን በመግለጽ፣ በአጠቃላይ የአገሪቱ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ሥር የተቀጠሩ ሠራተኞች ቁጥር ከ81 ሺሕ በላይ መድረሱንም አሳውቋል፡፡