Friday, December 1, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

አደፍርስና የተጠላው እንዳልተጠላ ከጥናትና ምርምር አንፃር

በያሬድ ነጋሽ

‹‹ምቀኛ አታሳጣኝ›› ይላል የአገሬ ሰው፡፡ እ.ኤ.አ. መጋቢት 14 ቀን 1958 ነበር አሜሪካ የመጀመሪያውን ወታደራዊ ማዕቀብ በኩባ ላይ የጣለችው (በባቲስታ ዘመነ መንግሥት)፡፡ ይህም ማለት ከኩባ አብዮት ሁለት ዓመት ቀደም ብሎ፡፡ ከዚህ በኋላም በተለይም ኩባ ከሶሻሊስት አገሮች ጋር የጀመረቻቸውን ግንኙነት ተከትላ አሜሪካ የፊደል ካስትሮን አስተዳደር ለመጣል አለኝ የምትለውን ጫና ሁሉ ማድረግ ጀመረች፡፡ የኩባ መደበኛ የግብርና ምርት የሆነውን የሸንኮራ አገዳና ቀይ ስኳር ግብይት አቋረጠች፡፡ ምግብና መድኃኒት ወደ ውጭ እንዳትልክ አገደች፡፡ የኩባ መንግሥት የአሜሪካ ነዳጅ አፈላላጊ ድርጅቶችን ከወረሰ በኋላ አሜሪካ እ.ኤ.አ. ከ1964 እስከ 1975 ባለው ጊዜ ውስጥ የተለያዩ የተናጠል ማዕቀቦችን ጣለች፡፡ እ.ኤ.አ. በ1982 ፕሬዚዳንት ሮናልድ ሬጋን ሌሎች የንግድ ማዕቀቦች አሳረፉባት፡፡

በዚህ ያልበቃት አሜሪካ የኩባ ባለሥልጣናትን ሕይወት ለመቅጠፍ ሴራ መጎንጎን፣ የዓመት የሸንኮራ አገዳ ምርቷን ‹‹ሞዛይክ›› በሚባል በሽታ ማውደም፣ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ኩባ በነበሩበት ወቅት ተቆጣጥራው የነበረውን የሥጋ ደዌ ሕመም ዳግም እንዲያገረሽ ማድረግ፣ በርካታ የኩባ ዜጎችን ለተለያዩ የዓይን ሕመሞች በሚዳርግ ተውሳክ መምታት፣ በመድኃኒት ማዕቀቡ ሳቢያ መድኃኒት ከቻይና ለማስመጣት በሚደረግ ጥረት ለከፍተኛ ወጪ መዳረግ፣ የኩባን የአየር ቀጣና በደቂቃዎች ውስጥ አቋርጦ በሚያልፍ የስለላ አውሮፕላን ጓዳ ጎድጓዳዋን መበርበርና ሌላም፣ ሌላም ኩባ ወገቧ እንዲጎብጥ በጎረቤቷ አሜሪካ ጉልበተኛነት የተሸከመቻቸው ቀንበሮቿ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ  ፕሬዚዳንት ኦባማ ሃቫና በመድረሳቸው እንኳን ሊረግብ ባልቻለ ውጥረት ኩባ ኢኮኖሚዋን በሚያደቅ፣ የባለሥልጣናቷንና የዜጎቿን ዝውውር በሚገታ ማዕቀብ ውስጥ እንድትኖር ተፈርዶባት 60 ዓመታትን አሳልፉለች፡፡ ይህም የማዕቀብ ቆይታ በዓለም ቀዳሚው ሲሆን፣ አንድ አገር በዚህ ሁሉ ማነቆ ውስጥ ህያው ሆና መቀጠሏ የሚያስደንቅ ነው፡፡

ሆኖም ነገሩ ኩባን አንገት የሚያስደፋ ሳይሆን ‹‹ምቀኛ አያሳጣኝ›› እንዲሉ፣ በብርታት ያቆማትና ያለ እንቅልፍ ሥራዋ ላይ እንድታተኩር ያደረጋት መልካም አጋጣሚ አድርጋ የምትወስደው ሆነላት፡፡ የአገራችንን ትንሽ ግዛት የምታህል ይህች አገር በቀደመ ጊዜ ከራሷ ተርፋ 60 ሺሕ አፍሪካውያን ነፃ የትምህርት ዕድል ሰጠች፣ ውቅያኖስ አቋርጣ የወታደራዊ ድጋፍ ለአንጎላ፣ ለኮንጎና ለኢትዮጵያ አደረገች፡፡ የጤና ተቋማቷም ቢሆኑ በተጠንቀቅ የቆሙ ሲሆኑ፣ በጤና ሳይንስ ምርምር ካደጉት አገሮች ተርታ እንደማታንስ በሚመሰክር ሁኔታ ለኮቪድ-19 ወረርሽኝ መቆጣጠር ሒደት እንኳን አራት ዓይነት ክትባት በማምረት ግልጋሎት ላይ አውላለች (በማዕቀብ ምክንያት ወደ የትኛውም አገር እንዳትልክ ብትታገድም)፡፡ 485,000 የጤና ባለሙያዎችና 100,000 ዶክተሮች ያሏት ሲሆን፣ ከዜጋ ምጣኔዋ ዘጠኝ ዶክተሮች ለአንድ ሺሕ ሰዎች ይደርሳሉ፡፡ 50,000 ዶክተሮችን ወደ 67 አገሮችም እንደላከች ይነገራል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2019 በሰው ሀብት ልማትና ማብቃት (Human Development Index) ረገድም ከ189 አገሮች 70ኛ ደረጃን ይዛለች፡፡

በኢኮኖሚ ደረጃም ቢሆን በነዳጅ፣ በኒኬልና በኮባልት ማዕድናት፣ በትምባሆና በሸንኮራ አገዳ ግብርና ዘርፍ በሚደጎመው ኢኮኖሚ ለራሷ የምታንስ አገር አይደለችም፡፡ በላይኛው መደብ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ የምትመደበው ይህች አገር፣ የምትከተለው ቅይጥ ኢኮኖሚ በማኅበር የሚሠሩትንና ሥራ ፈጣሪዎችን የሚያበረታታ ነው፡፡ ወደ አሥራ አንድ ሚሊዮን ለሚጠጋው ዜጋዋ ዝቅተኛ የሆነ የመኖሪያ ቤትና የትራንስፖርት ወጪ እንዲኖር ድጎማን ማድረግ ጨምሮ ብዙ ነገር የተመቻቸለት ነው፡፡ በአጠቃላይ ጀርባዋ ላይ እንደተሸከመችው የአሜሪካ ማዕቀብ ልክ የጎበጠች እንዳልሆነችና ይበልጥ የበረታች አገር እንደሆነች መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ኩባን እንቅልፍ ነስቶ በብርታትና በኅብረት ያቆመው ባላጋራና ምቀኛ እኛስ የለን ይሆን? በአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ሕዝብን በረሃብና በበሽታ የጨረሰው ክፉ ቀን፣ ተፈሪ መኮንን በአልጋ ወራሽነት ዘመናቸው እንኳን ለሕመም ለመዳረግ ያልቦዘነው ቸነፈርና ችጋር፣ የ1966 ዓ.ም. እና የ1977 ዓ.ም.  የድርቅ፣ የረሃብና የችጋር ወቅት የማን ባላጋራ ነበሩ? የማንንስ ስም አጠፉ? የማንንስ ምሥል አቆሸሹ? በዘመናችንስ የተከሰተው የምሥራቁና የደቡብ ምሥራቁ ድርቅ ማንን ይጠብቃል? በብርታት ለመቆም የጠለሸውን ስማችን ለማፅዳት፣ በረሃብ አንገቱና ሆዱ ብቻ ከብዶ አጥንቱ ለገጠጠ ሕፃን ርዝራዥ ወተት ጠፍቶ ቆዳውን እንዲምግ ልጇን ያቀፈች እናት፣ የስንዴ ዕርዳታው ሠልፍ ሁለት ኪሎ ሜትር ያህል የረዘመበትና ጠኔ ያገረጣው ዜጋ ላለማየት እንዴት እንቅልፍ አልነሳንም? እንዴት ለለውጥ አልተነሳንም? እያሉ የጠየቁ በየዘመን የተነሱ አሰላሳዮችና ስለኢትዮጵያ ያሉ ተቆርቋሪዎች፣ ከንግግርም አልፈው ድርሳን ጽፈውና መፍትሔ የሚሉትን ከትበው ለአንባብያን ያደረሱ ደራሲያንን እስካለንበት ጊዜ ድረስ ተመልክተናል፡፡

በዚህ ቁጭት ከተዘጋጁና በይዘታቸው ነባር አስተሳሰብን ለመነቅነቅ ከሞከሩ ሥራዎች መካከል የትናንቶቹን ወገን ወካይ አድርገን ዳኛቸው ወርቁ በ‹‹አደፍርስ›› ድርሰቱ፣ ላለንበት ጊዜ ተጠሪ ሆኖ ዓለማየሁ ገላጋይ ‹‹የተጠላው እንዳልተጠላ›› የሚል ሥራውን ከጥናትና ከምርምር አንፃር ልንመለከታቸው ወደድን፡፡

ዳኛቸው ወርቁ በ‹አደፍርስ› እና ዓለማየሁ ገላጋይ በ‹የተጠላው እንዳልተጠላ›፣ የሚያምኑበትንና የልባቸውን ክፋይ በልብ ወለድ ቀይጠው በተለያየ ይዘት እንዳቀረቡልንም፣ ነባር አስተሳስብንም ለመነቅነቅ እንደሞከሩም እንረዳለን፡፡ ሁለቱ ደራሲያን ድርሰታቸውን ለማዘጋጀት ለአገር ዕድገትና ለውጥ ካላቸው ቀናዒነትና የትንሳዔዋን ጊዜ ናፋቂነት የበኩላቸውን አበርክተው ለማለፍ ካላቸው ተነሳሽነት የመነጨ እንደሆነና  ቅዱስ ዳዊት ልጁ ሰለሞንና ክርስቶስ ለእየሩሳሌም እንዳሉት ሁሉ፣ ሁለቱ ደራሲያንም ስለአገራቸው ኢትዮጵያ ቅናት በልቷቸው እንደተነሱ እንገነዘባለን፡፡ ለዚህም ማረጋገጫ ይሆን ዘንድ በየመጻሕፍቶቻቸው ቁጭታቸውን ያሠፈሩባቸውን ሥፍራዎች እንመልከት፡፡

ዳኛቸው በ‹‹አደፍርስ›› ሥራው ውስጥ የኢትዮጵያ ሕማማት ይበቃታል እንዲል በገጸ ባህሪው አደፍርስ አንደበት፣ ‹‹ከቃላት ሁሉ ደስ የሚሉኝ ዕንቢ! አሻፈረኝ! ዕንቢ! አሻፈረኝ! ናቸው (አደፍርስ ገጽ 106)›› ይለናል፡፡ ኢትዮጵያ የያዘችው ነባር አስተሳሰብ ሳይነካ ዘመናዊው ቢቀየጥበት ስለሚገኘው ውጤት ሲቃትት፣ ‹‹ይህንን በአገር ቤት ያለውን ሃይማኖታዊ ርኅራኄ፣ ገርነት፣ ሰው አፍቃሪነት፣ እንግዳ ተቀባይነት፣ ዘመናዊ ትምህርት የቀላቀልሽበት እንደሆን እንዴት ይመስልሻል? ውጤቱ አይናፍቅሽም? አያስቀናሽም?… የኢትዮጵያ ሕዝብ ምንኛ በተበራከተ! ምንኛ በተራመደ (አደፍርስ ገጽ 112)›› ይለናል፡፡ በአባ ዮሐንስ አንደበት ኢትዮጵያ በእጇ የያዘችው ሥውር ሀብት ይገለጥላት ዘንድ በመመኘት፣ ‹‹የተደበቀባት ይገለጥ ዘንድ ታዲያ ምድር ምንኛ በተሻሻለች፣ የሰው ልጅ ምንኛ በተራቀቀ እንደ አቡየ ጻዲቁ እውነትን ፈልፍለው የሚያወጡ ጻድቃን ቢፈጠሩ ገጽ 222›› በሚል ያስነብበናል፡፡

ዓለማየሁ በ‹‹የተጠላ እንዳልተጠላ›› ድርሰቱ ላይ በብሉያት ምዕራፉ ውስጥ በዶ/ር አሮን ዕርዳታ አፈላላጊነት ተመፅዋች ሆና አገሩን ሲመለከታት፣ ‹‹ኢትዮጵያውያን መቼ ይበረታሉ? (ገጽ 6)›› እያለ ያመሰኳል፡፡ ከዓለም በፊት ቀድመን ነቅተን ኋላ ስለመቅረታችን ሲቆጭ፣ ‹‹እግዚአብሔር በመጀመርያ አምርቶ የክብር ቦታ ያኖረን ሕዝቦች ነን አልን፡፡ ታዲያ እዳሪና ብካች የበዛበት ቦታ ከእሪያዎች ጋር ማን ደባለቀን? (ገጽ 75)›› እያለ ይቆጫል፡፡ አገሬው የምድር ቆይታውን እጁን አጣጥፎ እያሳለፈ ሲመስለውና ሳይሠራ ተስፈኛ ቢበዛበት፣ ‹‹ስለምን በሥራችሁ ከለላ የሀብት ጥሪት አታበጁም? (ገጽ 69)››፣ ‹‹ሰነፍ ሰው ግን ሐሰተኛ ሕልምን በከንቱ ተስፋ ያደርጋል ተብሎ አልተጻፈምን? (ገጽ 79)›› እያለ ይቆጣል፡፡ ወገኑ የተሰጠውን መክሊት ሳይሠራበት ቆፍሮ እንደቀበረው ሲሰማው፣ ‹‹ፈጣሪ ያስጨበጣችሁ የልጅነት ፀዳል ከወዴት አለ? (ገጽ 68)›› እያለ በአራጣ አበዳሪው አንደበት ይጠይቃል፡፡ ከጸሐፊ ትዕዛዝ ገብረ ሥላሴ ከኢትዮጵያ የረሃብ ጊዜ ትርክት መጣጥፍ ላይ፣ ‹‹እናትና ልጅ የሚለያይ ብርቱ ረሃብ ሆነ፣ ፈረስና በቅሎ ተበላ፣ ከረሃቡና ከበሽታው የተረፈውን ጦር ፈጀው›› የሚለውን ጠቅሶ፣ የአለቃ ለማ ኃይሉን መዝገብ አስከትሎ፣ ‹‹ልጆቻቸውን ጥቃቅኖቹን የበሉት ብዙ ናቸው፡፡ ሰው ቅጠል በላ፣ ያልተበላ ቅጠል የለም፡፡ ይህ ቅጠል ቀረ የሚባለውን ነገር አላውቅም›› የሚለውን የኢትዮጵያ የረሃብ ዘመን ትውስታ ያወሳንና፣ ‹‹ይህ የሆነበት ባለታሪክ እንዴት የተከደነበትን አይገነጣጥልም? (ገጽ 94)›› እያለ ‹‹ከዚህ ሌላ ምቀኛ ከየት ይምጣልን›› በማለት ይጠይቃል፡፡

በሃዲሳት ምዕራፉ በባለ ዋሻው አንደበት የተሰጠንን መክሊት ሳንሠራበት ይዘን እንደተቀመጥንና በውጤቱ ፈጣሪ ከእኛ ነጥቆ ለሠሩበት እንደሚጨምር ሲያበክር፣ ‹‹እግዚአብሔር ሊያተርፍባችሁ ዕውቀቱንና ጊዜውን እንዳፈሰሰባችሁ ዘነጋችሁትን? ታዲያ ስለምን የሰጣችሁን መክሊት ቆፍራችሁ ለመቅበር ደፈራችሁ? (የተጠላ እንዳልተጠላ ገጽ 102)›› ይለናል፡፡ ዛሬን በትጋት ያሳለፈ ለድካሙ ወቅት ጥሪት እንደቋጠረ ሲጠቁም፣ ‹‹ለሥራ የዋለ ባርነት በመከራ ጊዜ ታዳጊያችሁ አይደለምን? (የተጠላ እንዳልተጠላ ገጽ 151)›› ሲል ያስነብበናል፡፡ በሐዋርያት ምዕራፉ ከጥበበኛ አባቶቻችን መንፈስ እንዳልተካፈልንና መንፈሳቸውን በእኛ ውስጥ ዘርተን ሺሕ ሆኖ አለመብቀሉን ሲነግረን፣ ወይም የአክሱምና የላሊበላ ሥልጣኔ በጎተራ ተቀመጠ እንጂ መሬት ወድቆ በስብሶ ሺሕ ሆኖ እንዲያፈራ አላደረጋችሁም በሚል፣ ‹‹በአንድ ዘር መውደቅ ሺሕ እንዲዘረዝር አታውቁምን? (የተጠላ እንዳልተጠላ ገጽ 178)›› እያለ ይጠይቃል፡፡ በአጠቃላይ ሁለቱም ደራሲያን ከበጎ መሻት በመነሳት መጽሐፍቱን እንዳዘጋጁት እንረዳለን፡፡

ሆኖም ደራሲያኑ ኢትዮጵያ ለገጠማት ምስቅልቅልና ላለችበት ችግር መንስዔ ያደረጉትና መፍትሔ ይሆን ዘንድ መላውን እንካቹ ያሉት በምን አግባብ ነው? ከኢትዮጵያዊነትና ከዜጋው የፀና ኑባሬ ጋር ምን ያህል የተጣጣመ ነው? ጥናትስ ምን ይላል? ለሚለው ጥያቄ፣ ዶ/ር ሰሎሞን በላይ በቶሮንቶ ዩኒቨርስቲ ለፒኤችዲ ዲግሪ ማዕረጉ፣ ‹‹በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ አካባቢያዊና ባህላዊ እሴቶችን ወደ ሳይንስ ትምህርት መልሶ ማምጣት›› በሚል ርዕስ ያዘጋጀው የጥናትና የምርምር ሥራውን ወደ አማርኛ መልሶ ካሳተመበት፣ ‹‹ከዶክተርነት፣ ደብተራነትና ወልይነት›› ከሚለው መጽሐፍ አንፃር ለመመዘን ስንሞክር፣ ጥናቱ ማስረገጥ ከፈለገው አራት ጉዳዮች መካከል ሁለትን እንዋሳለን፡፡

አንደኛው የጥናቱ ጥያቄ ‹‹ኢትዮጵያውያን መንፈሳዊና ባህላዊ እሴቶችን እንዴት እየተገነዘቡ ይተገብራሉ?›› የሚል ነው፡፡ በዚህ ርዕስ ሥር ካሉ የተለያዩ ወጎች መካከል አንዱን እንመልከተው፡፡ እንግዳው፣ አንድ እንግዳ ሰው ከአንዱ መንደር ወደ ሌላው ይጓዛል፡፡ ቀኑ መጨለም ሲጀምር ጎኑን ማሳረፍ ስለሚያሻው በቅርቡ ባገኘው ቤት ያንኳኳል፡፡ የቤት ባለቤት ‹‹ማን ልበል›› ይላል፡፡ ‹‹የመሸበት የእግዚአብሔር እንግዳ›› እንግዳው ይመልሳል፡፡ ባለቤት ‹‹የእግዚአብሔር እንግዳ – አይቁም ከሜዳ፡፡ ቤት የእግዚአብሔር ነው›› በሚል እንዲገባ ፈቃዱን ይቸረውና ቤተሰቡ ከተቀመጡበት ተነስተው በአክብሮት ይቀበሉታል፡፡ ባለቤቱ ‹‹ኖር ኖር››፣ እንግዳው ‹‹በእግዚአብሔር ተቀመጥ››፡፡ እንግዳው በምቹ ሥፍራ ይቀመጣል፡፡ እራት ቀርቦ ከፍ እስኪል ድረስ ማንም በጥያቄ አያጣድፈውም፡፡ ለእንግዳው የሚቀርበው ምግብና መጠጥ ከወትሮ የተለየ፣ የጣፈጠና ለድንገተኛ እንግዳ የተቀመጠ ይሆናል፡፡ ከጥፍጥናው የተነሳ ልጆች እንግዳ የሚመጣበትን ዕለት እስኪናፍቁ ድረስ፡፡ ቡና ከተጠጣ በኋላ፣ ‹‹ከየት መጡ? ወዴት ይሄዳሉ?›› የሚል ጥያቄ ይከተላል፡፡ አንዱ የቤቱ ልጅ የእንግዳውን እግር ለማጠብ በገበቴ ውኃ ይዞ ይቀርባል፡፡ ይህም ‹ክርስቶስ የደቀ መዛሙርቱን እግር አጠበ› የሚለውን የትህትናና የአገልግሎት ምሳሌ ነው፡፡ እግር ያጠበው ልጅ በእንግዳው፣ ‹‹እግዚአብሔር ይባርክህ፣ ትምህርትህን ይግለጥልህ›› ሲባል ይመረቃል፡፡ ባለቤት አልጋውን (መደቡን) ለእንግዳው ይለቃል፡፡ እንግዳው አሻፈረኝ ብሎ ቁርበት አንጥፎ ለመተኛት ይወስናል፡፡ እንግዳው ቁርበት ላይ ከተኛ በኋላ ተባይ እንዳይነካውና ሙቀት እንዲያገኝ የቤቱ ልጆች ከበውት ይተኛሉ፡፡ ጠዋት፣ ‹‹እግዚአብሔር ይስጥልኝ፣ እግዚአብሔር ያክብርልኝ›› ብሎ ባለቤቱን መርቆ እንግዳው ይወጣል (ከዶክተርነት፣ ደብተራነትና ወልይነት ገጽ 14)››፡፡ የወጉ መነሻም መዳረሻም በእግዚአብሔር ስም ጠይቆ በእግዚአብሔር ስም መቀበል፣ ወይም በእግዚአብሔር ስም ተጠይቆ ስለእግዚአብሔር መስጠትን ይመለከተዋል፡፡

ጥናቱ የዚህ መሰል የተለያዩ ወጎችን አስደግፎ፣ የተለያዩ ጸሐፍትን ሥራ አንተርሶ፣ ግለሰቦችን ቃለ መጠይቅ አድርጎና የአጥኚውን ግንዛቤ ደምሮ ምላሹን ሲያስቀምጥ፣ ‹‹በኢትዮጵያውያን የሕይወት መንገዶች ታላቁን ህላዌ ማመንና እሱን መፍራት በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ሕዝቡ ‹ይህ ከፍተኛ ህላዌ ከኢትዮጵያ ጋር ልዩ የሆነ ቁርኝት አለው› ብለው በፅኑ ስለሚያምኑ ‹የኢትዮጵያ አምላክ› በማለት ይጠሩታል፡፡ በእሱ ላይ ያላቸው እምነት፣ እንዲሁም የእሱን ፍርኃትና አክብሮት የኑሯቸው ሚዛን ይሆን ዘንድ ይሻሉ፡፡ መጥፎ ወይም የጥሩ ምንነት በእግዚአብሔር እምነት ሚዛን ነው የሚለካው፡፡ ‹‹ነውር›› የሚለው ቃል የሚያሳየው ከእግዚአብሔር ጋር የማይጣጣሙ አስተሳሰቦችና ድርጊቶችን ነው፡፡ በግለሰቦች መካከል የሚካሄደው መስተጋብርና ጭውውት በሙሉ እግዚአብሔር በሚለው ቃል የተሞላ ይመስላል፡፡ ‹‹…ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዕውቀትን በመፍጠርና በመተግበር ሒደት ውስጥ የእግዚአብሔር ማንነትና ባህሪያትን ጽንሰ ሐሳብ ችላ ማለት አይችልም›› (ከዶክተርነት፣ ደብተራነትና ወልይነት ከገጽ 31-32)፡፡

‹‹የኢትዮጵያውያን መንፈሳዊና ባህላዊ እሴቶች የሚመነጩት የእግዚአብሔርን መኖር ከማመንና ፈቃዱን ለመፈጸም ካለ ፍላጎት ነው፡፡ ማንኛውም ሳይንሳዊ ትምህርትን ጨምሮ ይህንን መሠረታዊ ሀቅ የሚገዳደር ከሆነ ኢትዮጵያውያን ሊደክሙለት አይገባም፡፡ የልጆች ትምህርት በቤታቸውና በማኅበረሰባቸው ባህል ላይ መመሥረት አለበት ብለን የምናምን ከሆነ፣ ከመንፈሳዊና ከባህላዊ ጥያቄዎች ጋር እንዲጋፈጡ ማድረግ ይገባናል፡፡ የሳይንስ ትምህርታችን ኢትዮጵያውያን የሚያምኑበትንና የሚኖሩበትን መለኮታዊና ባህላዊ ዕውቀቶችን ቢመረምር ይመረጣል›› ይላል (ከዶክተርነት፣ ደብተራነትና ወልይነት ገጽ 37)፡፡

ከጥናቱ ምላሽ አኳያ የደራሲ የዳኛቸው ወርቁ ‹አደፍርስ› የተሰኘው ሥራና ለችግሮቻችን አማራጭ የመፍትሔ ሐሳብ ያደረገውን ስንመለከት፣ ወይም ሥር ነቀል ለውጥ የሚሻውና የዚያ ትውልድ አባል ከሆነው አደፍርስ አንደበት ሥር የሚነቀንቁ ሐሳብ እንዲመነጭ ያደርግና በሌሎች ገጸ ባህሪያት ምላሽ ያበጃል፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያውያን ስለሆኑ ጉዳዮች ሲያወሱ፣ ‹‹ሥልጣኔ እንደ ተቀባዩ ነው? (አደፍርስ ገጽ 227)›› ለሚለው የአደፍርስ ጥያቄን አቶ ጥሶ ሲመልሱ፣ ‹‹የኢትዮጵያውያን ጉጉት የላቀና የመጠቀ መሆን ይገባዋል፡፡ ውስጣዊውን ሰብዕና ወልውሎ በሚያሳይ በመንፈስ ጥበብ በልፅጎና በመንፈሳዊ ኃይል ጎልብቶ ለመገኘት መጣጣር፡፡ በእውነት እልሃለሁ አደፍርስ አጣንም፣ ቆረቆዝንም፣ የበታችም ሆንን ብለን ማዘን የሚገባን ይህ በውስጣችን ሲንቦለቦል የኖረው መንፈሳዊ የሰብዓት ሕይወት ፈሳሽ ያለ መኖር መሰናክል ይገጥመውና የደረቀ የተመጠጠለት እንደሆነ ነው›› (አደፍርስ ገጽ 234)፡፡

አዲስ አስተሳሰብን ልንቀበልበት ስለሚገባው መንገድ ሲወሳ፣ ‹‹ኢትዮጵያውያን አዲስ ነገርን እንዴት ሊሰበኩ ይገባቸዋል?›› ለሚለው የአደፍርስ ጥያቄ አቶ ወልዱ ሲመልሱ፣ ‹‹ስለእኩልነት ስንሰብከው፣ ሰው በእግዚአብሔር አምሣል ስለተፈጠረ በፈጣሪው ፊት እኩል ነውና የእኩልነቱ ሁኔታ ሃይማኖቱን አስታኮ ካስተማሩት እንደ አዲስ ግንጥል ጌጥ ስለማይቆጥረው ይቀበለው ይሆናል፡፡ …ነፃነቱንም፣ ‹የራስህ የምትለው ነገር እንዲከበርልህ፣ ሌላ ሰው የራሴ የሚለውን ማክበር ይኖርብሃል ማለት ነው፡፡ የራስህን ርስት ይዘህ የሌላ ሰው ርስት ካሻህ ደግሞ፣ የራስህን ንብረት አስፋፍተህ የሌላ ሰው ንብረት ከደፈርክ የነፃነት ጠላት መሆንህ ነው› ብለው ካስረዱት እንደ አዲስ ግንጥል ጌጥ ስለማይቆጥረው ይቀበለው ይሆናል (አደፍርስ ገጽ 253)›› ይላሉ፡፡ ከላይ ያየናቸውን ሁለት የመጽሐፉ አንኳር ሐሳቦች ስንጠምራቸው፣ ‹‹ኢትዮጵያውያን ሞትን የሚሉት ከመንፈሳዊውና ባህላዊ ሕይወት የተለዩ እንደሆነና ማኅበረሰቡ ለውጥ ያስፈለገው እንደሆነም፣ መንፈሳዊ ምልከታውን አስታከን የምንመግበው ሊሆን እንደሚገባ ያበክራል፡፡ ከዚህ አኳያ ከላይ ካየነው ዶ/ር ሰሎሞን፣ ‹‹ኢትዮጵያን ሁሉን ነገር በመንፈሳዊ ዓውድ ይመለከቱታል›› ከሚለው የመጀመሪያው የጥናት ውጤት ጋር የተጣጣመ ተዛምዶ እንዳለው እንረዳለን፡፡

በአንፃሩ የዓለማየሁ ገላጋይ ‹‹የተጠላው እንዳልተጠላ›› ድርሰት ለችግሮቻችን አማራጭ ሐሳብ አድርጎ ያቀረበውን ጉዳዮች ስንመለከት፣ መንፈሳዊ ሀብታችንን በመተውና ባለመተዋችን ላይ ዕድገታችን ይበሰራል ወይም የምዕራባውያኑ ዕድገትና ሥልጣኔ የመነጨው ከመንፈሳዊ መንገድ ተገንጥለው ወጥተው የተጓዙት መንገድ እንደሆነ ሲያበክር፣ ‹‹ሰዎች ሲበረቱ እግዚአብሔር ያፈገፍጋል፡፡ ከህሊናቸው ከመንፈሳቸው ይወጣል፡፡ ፍርዳቸውን፣ ግንኙነታቸውን፣ ሀብታቸውን፣ ከተሞቻቸውን ሁሉ ለእነሱ ይተዋል (ገጽ 1)››፡፡ ‹‹ኢትዮጵያውያንስ መቼ ይበረታሉ? እግዚአብሔር የሚያፈገፍገው ቀኑ መቼ ነው? ከህሊናችን፣ ከመንፈሳችንና ከነፍሳችን የሚወጣው? (ገጽ 2)››፡፡ ‹‹አዕምሮውና አካሉ በልምሻ እንደተመታ ልጅ፣ እንዲሁም እግዚአብሔር የኢትዮጵያ የዘለዓለም ሞግዚት ሆኗል (ገጽ 3)››፡፡ ‹‹ሥራችሁንና ኃላፊነታችሁን ቁጭ ብሎ ለሚውለው አምላካችሁ አሳልፋችሁ ሰጣችሁ፡፡ የኖርኩባቸው የባዕድ ከተሞች አካላቸውን የሚያደክሙት ከፆም ሳይሆን ከሥራ ብዛት ነው (ገጽ 3)›› ይለናል፡፡

የኢትዮጵያ የችግሯ ቁልፍ መነሻ ደግሞ መለኮታዊ ጥገኝነት እንደሆነ ሲያትት፣ ‹‹እትብታችሁን ከተቀበረበት የነቀላችሁ ረሃብና እግዚአብሔር አይደሉምን (ገጽ 11)››፡፡ መፍትሔውን ሲያስቀምጥ፣ ‹‹ከመካከላችሁ ብርቱዎቹ አሮጌ ቤተ ፀሎታችሁን ያፍርሱ፡፡ በፈረሰው ቤተ እምነታችሁ ፈንታ ሰማይ ጠቀስ ጎተሮችን ገንቡ፣ ጥጋብ እስኪሆንም ለእነሱ ብቻ ስገዱ (ገጽ 76-77)››፡፡ ‹‹አምልኳችሁ በጎተራዎቻችሁ አፀድ ውስጥ ለእህል ማጠራቀሚያዎቻችሁ ይሁን (ገጽ 180)፣ (እግዚአብሔር በቁጣው ረሃብ ቢያመጣ፣ ከጎተራው ትመገባላችሁ እንደ ማለት)›› ይለናል፡፡ መላ ኢትዮጵያውያን በምድር ባይደላቸውም ከሞት በኋላ ተስፋ ስለሚያደርጉት መንግሥተ ሰማያት ሲያወሳ፣ ‹‹እናንተ የምድር ዘሮች የምድራችሁን ራቁትነት፣ የስንፍናችሁን እፍረት እዩ፡፡ በመንገዳችሁ ጫፍ ያለው ሞት ብቻ ነው፡፡ አንድስም ሌላ ነገር የለም፡፡ ሰማይን በበዘበዝሁ ጊዜ ተስፋችሁ ከንቱ እንደሆነ አየሁ (የተጠላው እንዳልተጠላ ገጽ 179-180)›› ይለናል፡፡

ዓለማየሁ የችግራችን መንስዔ ያላቸውንና መፍትሔ አድርጎ ያስቀመጠውን ሐሳቦች ጥሬ ቃሉን ወስደን፣ ‹‹ዘመናትን የፈጀው የሕዝቡ መንፈሳዊ ሀብትና ተስፋ ይፍረስ ወይም ከንቱ ነው አለ›› ባንልም፣ ወይም ደካማ የሥራ ባህላችንን እየተቸ እንደሆነ ብንረዳም፣ ወይም ደራሲው ከዚህ ቀደም የፍሬደሪክ ኒቼ፣ ‹‹እግዚአብሔር ሞቷል›› የሚለውን ሐሳብ በመቃወም፣ ‹‹እግዜር ከሞተ ኒቼ ሕይወቱ እንዴት ቀጠለ?›› የሚለውን ጥያቄ ለማስረዳት፣ ሐሰተኛው በእምነት ስም በሚለው ሥራው ውስጥ ዋናው ገጸ ባህሪይ የሆነው የታለ? ‹‹ዓለማየሁ ገላጋይ ሞቷል›› እንዲል በማድረግ፣ ‹‹ዓለማየሁ ገላጋይ ከሞተ ‹ቀጣዩ የታለ› ታሪክ ማን ጻፈው ታዲያ?›› ከሚል አነፃፅሮ በመለስ፣ ከመለኮት ህልውና ጋር የተቃረነ ምልከታ እንደሌለው እንድናስታውስ ቢያስገነዝበንም፣ ሆኖም በዚሁ ‹‹የተጠላው እንዳልተጠላ›› መጽሐፍ ውስጥ ከላይ ካቀረብነው የዶ/ር ሰሎሞን ጥናትና ምርምር ግኝት አንፃር ከኢትዮጵያውያን ሥነ ልቦና የራቁ መፍትሔዎችን ሲጠቁም ይስተዋላል፡፡ በተለይ ከልብ ወለድነቱ ይልቅ ጥሬ ቃሉን ለወሰደው ሰው ኢትዮጵያውያንን ከአለቱ ላይ ነቅሎ በአሸዋ መሠረት ላይ ለማፅናት የሞከረው አድርጎ ሊወስደው ይችላል፡፡ ጥናቱ፣ ‹‹ኢትዮጵያውያን ሁሉን ነገር በመንፈሳዊ ዓውድ ይመለከቱታል›› እንደሚለው ከሆነ፣ ኢትዮጵያውያን ለዓለማየሁ ድርሰት ‹‹ሰው ዓለምን ሁሉ ቢያተርፍ፣ ነፍሱን ግን ቢያጣ ምን ይጠቅመዋል? (ማቴዎስ 16:26)›› የሚል ምላሽ መስጠታቸው አይቀሬ ነው፡፡

ሁለተኛው የጥናቱ ጥያቄ ኢትዮጵያውያን የኢትዮጵያውያን ብቻ ብለው የሚቆጥሯቸው እሴቶች የትኞቹ ናቸው? የሚል ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ አንዱ፣ ‹‹ለኢትዮጵያውያን ሳያካፍሉ መብላት ነውር ነው፡፡ ተጋባዡ እንግዳ እንኳ ቢሆን ‹‹እንብላ›› የሚል ጥያቄ ማቅረብ የታወቀ ልማድ ነው፡፡ …የሚበሉት በቂ ነገር ሳይኖር ከሌሎች ጋር መካፈል የክርስቶስንና የመሐመድን ቃላትና ምግባር የሚያሳይና ማኅበረሰባዊ ወዳጅነትን የሚያጎላ ነው፡፡ ተካፍሎ መብላት በጣም የተለመደና ብዙ ጥረት የማይፈልግ ስለሆነ ብዙም ‹አመሠግናለሁ› አያስገኝም (ከዶክተርነት፣ ከደብተራነትና ወልይነት ገጽ 57)፡፡

የአደፍርስ ድርሰት አብዛኛውን ክፍል የሚያጠነጥነው ኢትዮጵያዊ አብሮነትንና የአኗኗር መልክ በሚዘክር መንገድ ወ/ሮ አሰጋሽ ቤት እንግዳ ሆነው በመጡት አቶ ጥሶ፣ አደፍርስ፣ ፍሬዋ፣ ክብረቴ፣ አልፎ አልፎ የሚከሰተው ጎርፉ፣ አባ አዲሴ፣ አባ ዮሐንስ፣ የወ/ሮ አሰጋሽ ወንድም አቶ ወልዱ፣ ወርዶፋ፣ ሮማን፣ አንድ ላይ ሆነው ባሳለፉት የአብሮነት፣ የመጨዋወት፣ የመሟገት፣ የመበሻሸቅ፣ የመብላት፣ የመጠጣት፣ የመዝፈን፣ ወዘተ የዕለት ተዕለት መስተጋብር ውስጥ ነበር፡፡ ከዚህ አኳያ የዳኛቸው ወርቁ አደፍርስ ድርሰት ከዶ/ር ሰሎሞን፣ ‹‹ኢትዮጵያውያን ተካፍሎ መብላት መገለጫቸው ነው›› በሚል በጥናቱ ካሰፈረው ሐሳብ ጋር የተስማማ ነበር፡፡

ደራሲ ዓለማየሁ በ‹‹የተጠላ እንዳልተጠላ›› ሥራው ውስጥ ‹‹ሠራተኛው ጥቂት በላተኛው ብዙ ሆኗል›› ወይም፣ ‹‹የጥገኝነቱ መጠን (Dependency Ratio) ከፍተኛ ነው›› የሚለውን እንዳበከረ ብንረዳም የአብሮነት፣ የዝምድናና የመረዳዳት ባህላችንን ለመናድ እንዲህ በማለት ያመሰኳል፡፡ ‹‹አንቺ ሴት የዝምድናው ሸክም አድክሞሻልና አውርጂው፡፡ ዝምድና ሸክም ብቻ ሳይሆን ቅንቅንም ነውና ታጠቢው፡፡ …የቅንቅኑም ዝምድና ይህንን ይመስላል እናት፣ አባት፣ ልጅ፣ ወንድም፣ እህት፣ አጎት፣ አክስት፣ ሚስት፣ የሚስት ዘመድ… ስለእነዚህ ሞት ዕድሮቻችሁ አይርዱ፡፡ ጀርባዋ ላይ የዝምድና ኮርቻ የሌለባትን ሌጣ ንብ ተመልከት፡፡ የእሷ ወላጅ ማን ይሆን? ስለምን ከምንዥላትህ ጋር የተቋጠረ መቀነትህን በጥሰህ ከማርህ ጋር አትዛመድም? ዘመዶችህ በጭስ አባረው ማርህን መከናነብ ለምደዋልና እነሱ የቤተ ዘመድ ጉባዔያቸውን ያፈርሳሉ ብለህ አትጠብቅ፡፡ በዘመድ የሚመኩ የሥራ ሾተላይ ያለባቸው ናቸው፡፡ የቤተ ዘመድ ማዕድ የመቆጣጠሪያ ኬላ የለውምና ሰነፎች አጥብቀው ይሹታል፡፡ ዘመዶች ድመቶች ናቸው የሚባሉት በሥራ የጋመ አካልህን ተጠግተው ስለሚሞቁ ነው፡፡ ዘመድህን በራቅኸው ቁጥር ይበርደዋል፡፡ የአንተ ዘመድህ ስትቀርበው የሚሞቅህ ሥራህ ብቻ ይሁን (የተጠላው እንዳልተጠላ ገጽ 151-152)››፡፡ ዓለማየሁ አሁንም የአውሮፓውያኑን የግለኝነት አባዜ መፍትሔ ሲያደርግና ዶ/ር ሰሎሞን፣ ‹‹ኢትዮጵያውያን ተካፍሎ መብላት መገለጫቸው ነው›› ከሚለው የጥናትና የምርምር ውጤት አንፃር ኢትዮጵያውያን በእጄ የሚሉት ወይም ከኑባሬያቸው የራቀ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡

በሁለተኛው የጥናቱ ጥያቄ ሥር ያለው ሌላው የጥናቱ ምልከታ፣ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የሐሳብ ግራና ቀኙ ይታይ ዘንድ ወይም ሐሳብ በትግል ዳብሮ ሁሉንም የሚያስማማ ማዕከላዊ ደረጃ ላይ እንዲደርስ፣ ነገርን በወግ መልክ መጠረቅ የተለመደ መሆኑን ለመግለጽ፣ ‹‹በነገራችን ላይ ታሪክ ስንናገርም ሆነ ስንተነትን በሰዎች ሕይወት ውስጥ ያለውን ማዕከላዊ ሥፍራ በሚገባ ተገንዝበን መሆን አለበት፡፡ …ወጎችን ማዳመጥ፣ እንደገና መተረክና ከእነዚያም በትንታኔ ዓይን ማየት በተለያዩ መንገዶች ይነካኩናል፡፡ …ወግ ጥረቃ ራሱን በራሱ የሚያሟላበት ትንቢት ነው፡፡ ለስኬቱ ድርጊትን የሚያነሳሳና አቅጣጫ የሚያመላክት ነው፡፡ ለወደፊት የሰዎች ኑሮ የውይይቱ ርዕስ የሚያኖር ነው›› (ከዶክተርነት፣ ደብተራነትና ወልይነት ገጽ 104-105)፡፡

በአደፍርስ ድርሰት ውስጥ ‹‹ዕንቢኝ››፣ ‹‹አሻፈረኝ›› የሚወደው አደፍርስ፣ ሥር ለመንቀል የሚጣደፉ ሐሳቦቹን ብቻ አንብበን እንድንጨርስ ሳይሆን፣ ሐሳቡ ክብ ሠርተው ወግ በሚጠርቁ ሰዎች መሀል የሚነሳና ማዕከላዊ የሆነውን ሐሳብ እንድንይዝ ባለጋራ በሆኑ ነቃፊዎች ይተች ነበር፡፡ ለምሳሌ ያህል አደፍርስ የትናቱን በአዲሱ ለመተካት በሚቃጣው ወቅት፣ ‹‹ኢትዮጵያ ታዲያ ምን ተጠቀመች፣ የማንንም እከሌን የማይባል ልጅ ሰብስበው አይደል እንዴ ንጉሡ መከራቸውን የሚያዩት (ገጽ 100)›› ተብሎ በአባ አዲሴ አንደበት ሊገሰጽ፣ ራሱን እንደ አማላይ ማየት ሲቃጣው፣ ‹‹የምልህ ምንድነህ አንተ? ራስህን ከፍ ከፍ አድርገህ ስለምታይ አይመስልህም? (ገጽ 183)›› በሚል በሠዓሊው ክብረት ይነቀፋል፡፡ ቀለም ቀመስነቱ ሲያኩራራው፣ ‹‹ንጉሡ አሁን የእናንተ ሥራ በቃኝ፣ አያስፈልገኝም፣ እንደ ገበሬው፣ እንደ ነጋዴው፣ እንደ ወታደሩ እየሠራችሁ ኑሩ የቢሮ ሥራ አልጠቀመኝም፣ ሂዱ ውጡ ከተራው ሰው ተደባለቁ ቢልዎት ምን ይውጥዎታል? (ገጽ 201)›› በመባል በጎርፉ ይፌዝበታል፡፡ የጎርፉ በተማረ ሰው ላይ መዘባበት ሲበዛ አደብ ለማስያዝ፣ ‹‹የተማረ ሰው እስከ እዚህ እጅ እግሩ የታሰረ አይምሰልህ›› በማለት የዒላማ ውርርዱን ከጎርፉ ጋር እኩል መሆኑን ያስመሰከረው አደፍርስ ይናገራል፡፡ የአደፍርስ መንቻካነት የበዛባት የአቶ ጥሶ ልጅ ፍሬዋ፣ ‹‹ባይሆን እያወቅህ አላውቅም ወይም አልቀበልም በል እንጂ ጨርሰህ አላውቅም የምትለውን ነገር አልሰማም (ገጽ 216)›› ስትል እናነባለን፡፡ አባ ዮሐንስ አደፍርስ ስለጻድቃን ያለውን አፍራሽ አስተያየት ተከትለው ‹‹የጸላኤ ሠናያት መጠጋት! ጸላኤ ሠናያት ቢቀርብህ ነው እንጂ ተክለ ሃይማኖት የጻዲቅ ጻዲቅ ናቸው (ገጽ 217)›› በሚል ይገስጹታል፡፡ አቶ ጥሶ አደፍርስ ለጥንታዊ አስተሳሰብ ስላለው አመለካከት ሲያነውሩ ‹‹ጥንታዊቷ ኢትዮጵያ …ከዘመናዊ የሰብዕና ወራሪዎቹ ሊያድኗት የሚታገሉላት ደግሞ በዱሮው መንፈስ የጠነከሩት አስተሳሰቦቿ ናቸው (ገጽ 228)›› ሲሉት እንመለከታለን፡፡ አደፍርስ ስለለውጥ ሐዋሪያነቱና ስለእሱ መሰሎች፣ ‹‹ሰዎች ምን ይሉናል?›› በሚል ለአቶ ወልዱ በጠየቃቸው መሠረት፣ ‹‹ወላጅ የመድፈር፣ ሃይማኖት የማፍረስና ሥልጣንን የመናቅ ሁኔታዎች ይታይባችኋል፡፡ ከቤተሰቦቻቸው ራቁ፣ አጉል የገለልተኛነት መንፈስና ኑሮ ፈጥረዋል ይሏችኋል (ገጽ 231)›› በማለት እንቅጩን ይነግሩታል፡፡ የትናንቱን ስለማነወሩ አደፍርስን ሲገስጹት ደግሞ፣ ‹‹ያለፈውን ካለው፣ ከጊዜው ጥዩቅ ጋር አስተያይቶ፣ ሙሉነቱንና ጎዶሎውን ለማመዛዘን እንኳን ቢሆን ነበርን ማወቁ ይበጅ ይመስለኛል (ገጽ 233)›› ሲሉት ይነበባል፡፡ ከዚህ አኳያ አደፍርስ ጥናታዊ በሆነው የኢትዮጵያውያን ወግ ጠርቆ ማዕከላዊ የሆነውን ሐሳብ ይዞ ለመጓዝ የተሞከረበት የውይይት ድርሰት እንደነበር እንረዳለን፡፡

ዓለማየሁ ገላጋይ በተጠላ እንዳልተጠላ ሥራው ላይ ያላንዳች ተሟጋች ማስረፅ የፈለገውን የመጨረሻ ጽንፍ የረገጠ ሐሳብ ማዕከላዊነትን በሚፈጥሩ ወግ ጠራቂዎች ሳይከብ እንዳሻው ይጓዛል፡፡ እዚህ ላይ ማየት የሚገባን ነገር ቢኖር የዓለማየሁ ሥራ ከአደፍርስ ጋር የይዘት ልዩነት ሲኖረው ዓለማየሁ መጽሐፉ ከመውጣቱ በፊት፣ በሸገር 102.1 ሬዲዩ ሸገር ካፌ ፕሮግራም ላይ ቀርቦ (2014 ዓ.ም. የዓብይ ፆም ውስጥ)፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ዓይነት አተራረክን ይዞ የተደረሰ ሥራ በአገራችን እንደሌለ በጠቀሰው መሠረት፣ መጽሐፉ የመጽሐፍ ቅዱሳዊ ይዘትና አተራረክ ተላብሶ የቀረበ የመጀመሪያው ሥራ እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ሆኖም የመጽሐፍ ቅዱሱ ክርስቶስም ቢሆን ለሐሳቡ ባላጋራ መጥቶበት የተሞገተበት እንደነበሩ አንብበናል፡፡ ለምሳሌ፣ ‹‹ሴትየዋም ግሪካዊት፣ በትውልዷም ሲሮፊኒቃዊት ነበረች፡፡ እሷም ኢየሱስ ጋኔኑን ከልጇ እንዲያስወጣላት ለመነችው፡፡ እርሱ ግን፣ ‹የልጆችን እንጀራ ወስዶ ለውሾች መጣል ተገቢ ስላልሆነ፣ መጀመርያ ልጆቹ ጠግበው ይብሉ› አላት (ማርቆስ 7፡26-27)›› በሚል ፊት ሲያዞርባት፣ ‹‹አዎን፡፡ ጌታ ሆይ! ውሾችም ከገበታ በታች ሆነው የልጆችን ትራፊ ይበላሉ›› አለችው (ማርቆስ 7፡28)›› በሚል ስትሟገት እናነባለን፡፡ ሆኖም ዓለማየሁ መጽሐፍ ቅዱሳዊ የአተራረክ ይዘት ባለው ሥራ ውስጥ ነገሮችን አራት ዓይና ሆነን እንድናይ ወይም ማዕከላዊ ሆነን እንድንገነዘበው፣ ወይም ኢትዮጵያውያን በመንፈሳዊ ምልከታቸው ያጡትን እንጂ ያተረፉትን እንድንመለከት በሚያስችለን ኢትዮጵያዊ የወግ መጠረቅ ሥልትን አለመከተሉን ከዶ/ር ሰሎሞን ጥናት አንፃር መናገር እንችላለን፡፡

በአጠቃላይ ዳኛቸው ወርቁ በ‹‹አደፍርስ››፣ ዓለማየሁ ገላጋይ በ‹‹የተጠላው እንዳልተጠላ›› (ከጥሬ ቃሉ በስተጀርባ ደካማ የሥራ ባህላችን እንደተተቸ ይረዳዋል) ሥራቸው በቀናይነት ተነስተው ለታዘቡት የአገራችን ችግሮች መፍትሔ ይሆን ዘንድ የበኩላቸውን እንዳካፈሉን (ሁለቱም ሥራዎች አብዮት የማስነሳት አቅም እንዳላቸው ይረዳዋል) ብንረዳም ለማኅበረሰቡ የቀረቡበት መንገድ ግን፣ ‹‹በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ አካባቢያዊና ባህላዊ እሴቶችን ወደ ሳይንስ ትምህርት መልሶ ማምጣት›› ከሚለው የዶ/ር ሰሎሞን በላይ ጥናትና ግኝት አንፃር፣ ከ‹‹የተጠላው እንዳልተጠላ›› ይልቅ ‹‹አደፍርስ›› ለኢትዮጵያውያን ሥነ ልቦና የቀረበና በእውነተኛው ኑባሬ የተዋዛ ነበር ማለት ያስችለናል፡፡ በመጨረሻም ከዶ/ር ሰሎሞን የጥናት ማጠቃለያዎች መካከል ሁለት ነገር አንስተን እናብቃ፡፡

‹‹ዘጠና ሰባት በመቶ የአገሪቱ ሕዝብ በእግዚአብሔር መኖር በሚያምንበትና ባለው ትርፍ ጊዜ በየቤተክርስቲያኑ፣ በየመስጊዱና በሌሎች የማምለኪያ ሥፍራዎች በሚሄድባት አገር፣ በተጨማሪም በከፍተኛ ሁኔታ በሕዝብ ሆነ በመገናኛ ብዙኃን ትኩረት ተሰጥቷቸው የሚከበሩት የሕዝብ በዓላት ሃይማኖታዊ ሆነው ሳለ፣ ሃይማኖት አብዛኛውን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቶችን በሚቀርፅበት አገር፣ የእግዚአብሔር ስምና አምልኮ ከመንግሥትና ከትምህርት ልቦና ማጥፋት ወንጀል ይመስለኛል፡፡ …የኢትዮጵያ መከራ የጀመረው ሃይማኖተኛና ፃድቅ አገር ተብላ በመታወቋ ብዙዎች በአክብሮት በባዶ እግራቸው የተረማመዱባትን አገር ሕዝብ የትምህርት ፖሊሲ፣ በእግዚአብሔር መኖር የማያምኑ ሰዎች ያወጡት (የጻፉት) ቀን ነው (ከዶክተርነት፣ ደብተራነትና ወልይነት ገጽ 151)››፡፡

‹‹እንደ ኢትዮጵያ የመሰለ ብዙ አቅም ያለው አገር በዓለም ዕውቀት የመፍጠርና የማሠራጨት ሒደት ውስጥ ሳይሳተፍ፣ የተሻለ ዓለም ለመፍጠር ያስቸግራል ብዬ አምናለሁ፡፡ ኢትዮጵያ እንደ ተለያዩ የሰውነት ክፍሎች በውስጧ ያለውን የሁሉንም ብሔረሰቦች ማንነት አጥርታና አደራጅታ፣ ከዚያም ለብሔራዊ መታወቂያ የሚሆናትንም እንዲሁ መዝና ስታበቃ በዓለም መድረክ ልዩ ማንነት ይዛ መቅረብ ትችላለች (ከዶክተርነት፣ ከደብተራነትና ከወልይነት ገጽ 179)፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል [email protected] አድራሻቸው ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles