በኢትዮጵያ እየታየ ያለውን የኑሮ ውድነት ለመግታት መንግሥት የተለያዩ አሠራሮችን ቢዘረጋም፣ ዘርፉ ላይ የተሻለ ለውጥ መጥቷል ማለት ይቸግራል፡፡ በተለይም በዘርፉ ላይ የሚታየውን ችግር ለመቅረፍ መንግሥትም ሆነ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋሞች ኤግዚቢሽንና ባዛርን እንዲሁም ደግሞ የእሑድን ገበያ እንደ አማራጭ ማቅረባቸው ይታወቃል፡፡
ነገር ግን የማኅበረሰቡን ጥያቄ ከመፍታት ይልቅ የራሳቸውን ጥቅም በማስቀደም እንደዚህ ዓይነት ድግሶችን የሚካፈሉ ነጋዴዎች ቁጥር ከፍተኛ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ሆኖም በዓል በመጣ ቁጥር በየዓመቱ ኤግዚቢሽን፣ ባዛርና ሲምፖዚየም እየተካሄደ ይገኛል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኤግዚቢሽንና የገበያ ልማት ድርጅት የዘመን መለወጫ በዓልን አስመልክቶ ለ22 ቀናት የሚቆይ ኤግዚቢሽንና ባዛር ቅዳሜ ነሐሴ 14 ቀን 2014 ዓ.ም. በይፋ አስከፍቷል፡፡
የኤግዚቢሽንና ባዛር ማዕከል የገበያ ልማት ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጥላሁን ታደሰ እንደገለጹት፣ ከነሐሴ 14 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ለ22 ቀናት የሚካሄደው ኤግዚቢሽንና ባዛር ላይ 500 የሚሆኑ ነጋዴዎች ምርትና አገልግሎታቸውን ያቀርባሉ፡፡
በኤግዚቢሽንና ባዛሩ ከተለያዩ አገሮች የተውጣቱ ነጋዴዎች ምርቶቻቸው ይዘው መቅረባቸውን የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚው ያቀረቧቸውን ምርቶችን ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ ለማኅበረሰቡ በመሸጥ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚደረግ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ኤግዚቢንና ባዛሩን 500 ሺሕ የማኅበረሰብ ክፍሎች ይጎበኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅና ማኅበረሰቡም የተለያዩ ምርቶችን በቀላሉ የሚያገኝበት እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኩነት አዘጋጆች የኪራይ ዋጋ በማናር እንዲሁም የጎብኚዎችን የመግቢያ ዋጋ በመጨመር ከዚህ በፊት በተከናወኑ ኤግዚቢሽንና ባዛሮች ግብይት ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ እንዲታይ መደረጉን አክለው ገልጸዋል፡፡
በዚህም መሠረት ሸማቹን ማኅበረሰብ እያማረረ ያለውን የንግድ ሥርዓት ለመቀልበስ ድርጅቱ በአዋጅ የተሰጠውን ኃላፊነት በመጠቀም፣ ኤግዚቢሽንና ባዛሮች ካለፉት ዓመታት ጀምሮ በደማቅ ሁኔታ ማዘጋጀት መጀመሩን አቶ ጥላሁን ተናግረዋል፡፡
የንግድ ትርዒትና ባዛሩ በተለይ የግሉን ዘርፍ የንግድ ተወዳዳሪነት በማሳደግ ከደንበኞቻቸው ጋር ዘለቄታዊ ግንኙነት እንዲኖራቸው ምቹ ሁኔታዎችን ይፈጥራል ያሉት አዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ ናቸው፡፡
ኤግዚቢሽንና ባዛሩም የተሰባጠረ የምርት አገልግሎትና አቅርቦትን ወደኋላ በመተው፣ የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎችን በአንድ በማስተሳሰር ከሰፊው ሕዝብና ሸማች ጋር የገበያ ትስስር የሚፈጠርበት ቴክኖሎጂም የት እንደደረሰ የሚማሩበት መድረክ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡
በተለይም በተለያዩ የሥራ ዘርፎች የተሰማሩ ድርቶች ምርቶቻቸውንና አገልግሎቶቻቸውን በተሻለ ሁኔታ የሚያስተዋውቁበት ከዚያም አልፎ ለቱሪዝም፣ ለመዝናኛ፣ ለሆቴልና ለትራንስፖርት ዘርፍ መነቃቃትን በመፍጠር ጉልህ ሚና የሚያበረክቱበት ነው ብለዋል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞም በኤግዚቢሽንና ባዛር ዝግጅት የእሴት ሰንሰለት ውስጥ በርካታ ዜጎች ተጨማሪ የሥራ ዕድል የሚያገኙ መሆኑን የገለጹት ወ/ሮ መሰንበት፣ ‹‹ይህም ከተማዋ የኤግዚቢሽን ማዕከልም የእሴት ፈጠራና የአካባቢያዊ ቢዝነስ ማዕከል ማሳያ ሆና እንድትታይ ያደርጋታል፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡