የዬል ዩኒቨርሲቲ አንጋፋ መምህርና የአሜሪካ ፌዴራል ሪዘርቭ የቀድሞ ኢኮኖሚስት ስቴፈን ሮች፣ ለሲኤንቢሲ ቴሌቪዥን ጣቢያ ‹‹ፋስት መኒ›› የሰኞ ምሽት ፕሮግራም ካደረገላቸው ቃለ ምልልስ የተወሰደ፡፡ አሜሪካና ቻይና ‹‹ቀዝቃዛው ጦርነት›› ላይ ናቸው ያሉት አንጋፋው ኢኮኖሚስት፣ የሁለቱ አገሮች ፍጥጫ የዓለምን ኢኮኖሚ እንደሚያዘቅጠው አትጠራጠሩ ብለዋል፡፡ ባለፉት አምስት ዓመታት ሁለቱ አገሮች ከንግድ ጦርነት እስከ ቴክኖሎጂ ጦርነት አድርገዋል፡፡ አሁን ደግሞ ወደ ቀዝቃዛው ጦርነት ውስጥ በመግባት ተፋጠዋል ብለዋል፡፡ አሜሪካ የኢኮኖሚ ዝቅጠቱ እንዳያጋጥማት ተዓምር ያስፈልጋታል ያሉት ሮች፣ ቻይናም ብትሆን በኮቪድ ዜሮ ፖሊሲ፣ በምርቶች አቅርቦት ሰንሰለት መናጋትና ከምዕራባውያን ጋር በፈጠረችው ቅራኔ ምክንያት የችግሩ ሰለባ ትሆናለች ሲሉ ተንብየዋል፡፡ አሜሪካ በሥራ አጥነትና እያደር በሚያሻቅበው የዋጋ ግሽበት ሳቢያ የኢኮኖሚ ዝቅጠቱ ያስፈራታል ሲሉም አክለዋል፡፡