Monday, March 4, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምየአፍሪካ የአየር ንብረት ሳምንት በጋቦን ሊበርቪል

የአፍሪካ የአየር ንብረት ሳምንት በጋቦን ሊበርቪል

ቀን:

አፍሪካ ወደ አየር የምትለቀው የካርበን ልቀት መጠን እዚህ ግባ የሚባል ባይሆንም፣ ልቀቱ እየጎዳቸው ከሚገኙ አኅጉሮች ከቀዳሚዎቹ ትመደባለች፡፡

የአየር ንብረት ለውጥን ለመሸከም የሚያስችል ኢኮኖሚ ያልገነቡት በተለይም ከሰሃራ በታች የሚገኙ አገሮች ደግሞ የአየር ንብረት ለውጡ ተጋላጭ ሆነው እያፈራረቀ በሚከሰተው ጎርፍና ድርቅ እየተመቱ ነው፡፡

አፍሪካውያን ለችግሩ መፈጠር ያላቸው አስተዋጽኦ ኢምንት ሆኖ በችግሩ መጎዳታቸው፣ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ በየዓመቱ ሲደረግ የሚነሳ አጀንዳ ቢሆንም፣ ችግሩ አልተፈታም፡፡ የችግሩ ሰለባዎችም የአየር ንብረት ለውጥን የሚያስከትሉ የጋዝ ልቀቶች ምን እንደሆነ የማያውቁ፣ ይህንን የሚያስከትሉ ቴክኖሎጂዎችን የማይጠቀሙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ናቸው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ችግሩን ለመቅረፍ  ዓመታት ያስቆጠረውና በየዓመቱ የሚካሄደው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ዘንድሮም የሚካሄድ ሲሆን፣ ይህ ኮፕ 27 ከመካሄዱ አስቀድሞም ከ42 የአፍሪካ አገሮች የተውጣጡ ልዑካን ቡድኖችና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ባለሥልጣናት በተገኙበት በጋቦን ሊበርቪል የአፍሪካ የአየር ንብረት ሳምንት ጉባዔ ነሐሴ 23 ቀን 2014 ዓ.ም. ተጀምሯል፡፡

በጉባዔው ላይ የተገኙት የጋቦን ፕሬዚዳንት ዓሊ ቦንጎ አንዲምባ፣ የአፍሪካ የአየር ንብረት ሳምንት ጉባዔ ሁሉም የአፍሪካ አገሮች ኮፕ 27 ጉባዔ ላይ ተመሳሳይ አጀንዳ ይዘው እንዲቀርቡ የሚያስችልና አፍሪካውያን የአየር ንብረት ለውጥን በውጤታማነት ለመዋጋት ተጨባጭና ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት አንድ የሚሆኑበት መድረክ ነው ብለዋል፡፡

የዩናይትድ ኔሽን ፍሬምዎርክ ኮንቬንሽን ኦን ክላይሜት ቼንጅ በገፁ እንዳሰፈረው፣ ከሦስት ወራት በኋላ በግብፅ ሻርም አል ሼኪ በሚካሄደው የተመድ የአየር ንብረት ለውጥ ኮንፍረንስ፣ አፍሪካውያን በአየር ንብረት ለውጡ የሚያደርስባቸው ጉዳትና ያሉ መልካም ዕድሎች የሚነሱበት ይሆናል፡፡

በግብፅ የሚካሄደው ኮፕ 27 የአፍሪካ ኮፕ ተብሎ እየተገለጸ ሲሆን፣ ጉባዔው አፍሪካ ወደፊት በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የሚደርስባትን ጉዳት ለመቀነስ አሠራሮች ቅርፅ የሚይዙበት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ለአምስት ቀናት የሚዘልቀው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ የአየር ንብረት ሳምንት ጉባዔ በጋቦን እየተካሄደ የሚገኘው አፍሪካ በተለያዩ የአየር ንብረት ለውጥ ክስተቶች እየተመታች ባለችበት ወቅት ነው፡፡

ለአየር ንብረት ለውጥ ያላቸው አስተዋጽኦ ጥቂት፣ እያስተናገዱ ያሉት ጉዳት ደግሞ ከፍተኛ የሆኑባቸው 54ቱ የአፍሪካ አገሮች ድርቅ፣ ከባድ ጎርፍና ስደት እያስተናገዱም ነው፡፡

ድርቅ

በኢትዮጵያ፣ በሶማሊያና በኬንያ አንዳንድ አካባቢዎች ድርቅ እያስከተለ ያለው ጉዳት እየተባባሰ ነው፡፡ የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት እንደሚለውም፣ ኬንያ፣ ሶማሊያና ኢትዮጵያ ከባድ ለሆነ ሰብዓዊ ቀውስ እየተጋለጡ ነው፡፡

በጂቡቲ፣ በኢትዮጵያ፣ በሶማሊያ፣ በደቡብ ሱዳን፣ በሱዳንና በኡጋንዳ ከ80 ሚሊዮን በላይ ሕዝቦች የምግብ ዋስትና ሥጋት ውስጥ ገብተዋል፡፡

ከየካቲት እስከ ሐምሌ 2014 ዓ.ም. ባለው ጊዜም በኢትዮጵያ፣ በኬንያና በሶማሊያ በድርቅ የተጎዱና የመጠጥ ውኃ ማግኘት ያልቻሉ ሰዎች ቁጥር ከ9.5 ሚሊዮን ወደ 16.2 ሚሊዮን አሻቅቧል፡፡

በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በሳህል ቀጣና የነበረው የውኃ መጠን ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ ከነበረው በ40 በመቶ ቀንሷል፡፡

የጎርፍ መጥለቅለቅ

በሚያዝያ 2014 ዓ.ም. በደቡብ አፍሪካ በካዋዙሉ ናታል አካባቢ የተከሰተው ከባድ ጎርፍና የመሬት መንሸራተት 450 ሰዎች እንዲሞቱ ምክንያት ሆኗል፡፡ በአገሪቷ ታሪክ ከፍተኛ የተባለው ጎርፍ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ሲያፈናቅል፣ ከ12 ሺሕ በላይ ቤቶችን አጥለቅልቋል፡፡ በርካታ ሰዎች ጠፍተው የቀሩ ሲሆን፣ በጎርፍ ተከበው የነበሩ ዜጎች ለሁለት ሳምንታት ያህል በሥፍራው ቆይተዋል፡፡ በወቅቱ የነበረው ከባድ ዝናብና ጎርፍ በመቶ ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ንብረት አውድሟል፡፡

ከደቡብ አፍሪካ በተጨማሪ ሱዳንና ሌሎች የአፍሪካ አገሮችም በጎርፍ ተመተዋል፣ እየተመቱም ነው፡፡

የውስጥ መፈናቀል

በአፍሪካ በርካታ ዜጎች ከግጭትና ከእርስ በርስ ጦርነት ባለፈ የአየር ንብረት ለውጡ እያስከተለ በሚገኘው ድርቅና ጎርፍ ምክንያት ከቀያቸው እየተፈናቀሉ ነው፡፡

የዓለም ባንክ እንደሚለው፣ እ.ኤ.አ. በ2050 ከሰሃራ በታች የሚገኙ የአፍሪካ አገሮች ሕዝቦች ውስጥ 86 ሚሊዮን እንዲሁም ከሰሜን አፍሪካ 19 ሚሊዮን ሕዝቦች የአየር ንብረት ለውጡ እያስከተለ ባለው አውሎ ንፋስና ማዕበል፣ ከፍተኛ ሙቀት፣ ድርቅና ከባድ ጎርፍ ምክንያት ከቀያቸው ይፈናቀላሉ፡፡

ከሰሃራ በታች የሚገኙ አገሮች ሙቀት መጨመርና በረሃማ መሆን፣ የባህር ዳርቻዎች በአግባቡ አለመገንባትና ኅብረተሰቡ በግብርና ላይ የተመረኮዘ መሆን  ለአየር ንብረት ለውጡ ይበልጥ ተጋላጭ ያደርገዋል፡፡

በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በሚከሰቱ ችግሮች ሰዎች ከቀያቸው መፈናቀል ጀምረዋል፡፡ አንጎላ ለዚህ አንድ ማሳያ ነች፡፡ ካለፉት 40 ዓመታት ወዲህ ታይቶ የማይታወቅ ድርቅን ያስተናገደችው አንጎላ፣ በእርሻ ወቅት ዝናብ ባለመገኘቱ፣ በምግብ ዋጋ ውድነትና በምግብ እጥረት ምክንያት በተለይ በአገሪቱ ደቡባዊ ክፍል የሚገኙ ዜጎች ወደ ጎረቤት ናሚቢያ እንዲሰደዱ ምክንያት ሆኗል፡፡

አፍሪካውያን የሚከፍሉት ዕዳ 

በዓለም ከሚመዘገበው የግሪን ሐውስ ልቀት ከመላ አፍሪካ የሚመነጨው አራት በመቶ ያህል ነው፡፡ አፍሪካ የካርበን ልቀቷ በጣም ጥቂት ቢሆንም፣ ምዕራባውያኑ በሚለቁት ከፍተኛ የካርበን ልቀት ምክንያት በሚከሰተው የአየር ንብረት ለውጥ 118 ሚሊዮን ደሃ አፍሪካውያን ለከፋ ድርቅ፣ ጎርፍና ሙቀት ተጋልጠዋል፡፡ በ2030 ደግሞ ችግሩ ይብሳል፡፡ 

ደሃ አገሮች የአየር ንብረት ለውጡን እንዲቋቋሙ የሚሰጥ ገንዘብ

ከፍተኛ የካርበን ልቀት ያላቸው ሀብታም አገሮች በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ እየተጎዱ ያሉ አገሮችን ኢኮኖሚ ለመደገፍ በየዓመቱ 850 ቢሊዮን ዶላር ያህል መስጠት አለባቸው፡፡

ከአሥር ዓመት በፊት ሀብታም አገሮች ደሃ አገሮችን ለመደገፍ በየዓመቱ 100 ቢሊዮን ዶላር ለመስጠት መስማማታቸውም ይታወሳል፡፡ ሆኖም እስካሁን ድረስ ሃብታም አገሮች ደሃ አገሮች በአየር ንብረት ለውጡ ሳቢያ ከሚመጣባቸው  መጠነ ሰፊ የኢኮኖሚ ቀውስ ለማውጣት በዓመት ለመስጠታ ቃል የገቡትን 100 ቢሊዮን ዶላር አልሰጡም፡፡

በአፍሪካ ያሉትን ጨምሮ በርካታ በማደግ ላይ የሚገኙ አገሮችም ለታዳሽ ኃይልና ለኢንዱስትሪዎች የሚውለውን የድንጋይ ከሰል መተኪያ የሚሆን አቅም ለመገንባት ከሃብታም አገሮች ይለቀቃል ተብሎ  የተገባው ገንዘብ ባለመለቀቁ ችላ ብለውታል፡፡

በአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባዔ እነዚህ ሐሳቦች ይነሳሉ፣ የአውሮፓ ኅብረትና ሌሎች የምዕራባውያን ተወካዮች አገሮቻቸው የካርበን ሽያጭ፣ የአረንጓዴ ቴክኖሎጂንና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚያስችል የገንዘብ ድጋፍ ኢንሽየቲቭ እንዲያነሳሱ ይወተውታሉ ተብሎም ይጠበቃል፡፡

(ጥንቅር በምሕረት ሞገስ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...