Wednesday, October 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የአጥንት ሕክምና ሥርዓትን የማጠናከሩ ጉዳይ ቸል ሊባል አይገባም›› ገለታው ተሰማ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ የአጥንት ሕክምና አደጋዎች ሕክምና ስፔሻሊስቶች ብሔራዊ ማኅበር ፕሬዚዳንት

ገለታው ተሰማ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ የአጥንት ሕክምና የትራዎማ ሕክምና ስፔሻሊስት ብሔራዊ ማኅበር ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በመርሐቤቴ፣ የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በአዲስ አበባ አጠናቀዋል፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስት ኮሌጅ በጠቅላላ ሕክምና የመጀመሪያ ዲግሪ፣ በአጥንት ሕክምና ስፔሻሊቲ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ ወደ ካናዳ አቅንተው በዩኒቨርሲቲ ኦፍ ቶሮንቶ ሦስተኛ ዲግሪያቸውን በአጥንት ሰብ ስፔሻሊቲ ሠርተዋል፡፡ ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት የሆኑት ገለታ (ዶ/ር) በማኅበሩ እንቅስቃሴዎች፣ በአጥንትና በአደጋዎች ሕክምናዎችና ተያያዥ ጤና ነክ ጉዳዮች ዙሪያ ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡

ፖርተር፡- ማኅበሩ ስንት የአጥንት ሕክምና ባለሙያዎችን አቅፏል? ከዚሁ ጋር አያይዘው የአጥንት ሕክምና ደረጃዎችን በተመለከተ ማብራሪያ ቢሰጡን?

ዶ/ር ገለታው፡– ለአጥንት ሕክምና ደረጃዎች ቅድሚያ መስጠት እፈልጋለሁ፡፡ አንድ ሰው ሰባት ዓመታት የጠቅላላ ሕክምና ትምህርት ተከታትሎ ከተመረቀ በኋላ እንደገና ለአራት ዓመታት የአጥንት ሕክምናን ተምሮ ይመረቃል፡፡ በዚህም የአጥንት ሐኪም ወይም የአጥንት ስፔሻሊስት (ኦርቶፔዲክስ ሰርጂን) ይሆናል፡፡ ከዚህ ቀጥሎ ለሰብ ስፔሻሊቲ አንድ ዓመት ተምሮ ማጠናቀቅና መመረቅ አለበት፡፡ ወደ 13 የሚጠጉ ሰብ ስፔሻሊቲዎች አሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል የሕፃናት አጥንት፣ በስፖርት ወይም በተለያዩ ምክንያቶች የመበጠስ አደጋ የሚያጋጥማቸውን ጅማቶች ዳሌና መገጣጠሚያ፣ ሲሰበሩና ውልቃቶችን የሚያክሙ ሰብ ስፔሻሊቲዎች ተጠቃሾች ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ የአጥንት ሕክምናና የአደጋዎች ሕክምና ስፔሻሊስት ብሔራዊ ማኅበር በኢትዮጵያ የሚገኙ 450 የአጥንት ሐኪሞችን ወይም የአጥንት ሕክምና ስፔሻሊስቶችንና ሰብ ስፔሻሊስቶችን በአባልነት አቅፎ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የማኅበሩ አመሠራረትና ለአባላቱ እየሰጠ ያለውን ጥቅም እንዴት ያዩታል?

ዶ/ር ገለታው፡- በኢትዮጵያ ውስጥ የመጀመሪያው የአጥንት ሕክምና የተጀመረው በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ውስጥ ሲሆን፣ የአጥንት ሕክምና ማኅበርም የተወለደው ከሕክምናው ጋር በተያያዘ ነው፡፡ አባላቱም በሆስፒታሉ የአጥንት ቀዶ ሕክምና ዲፓርትመንት ውስጥ የነበሩ የእጥንት ሐኪሞች ብቻ ነበሩ፡፡ ከሆስፒታሉ ውጪ ያሉት የአጥንት ሐኪሞች በማኅበሩ መታቀፍ የጀመሩት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነው፡፡ ክፍሉ በአሁኑ ጊዜ ወደ ማዕከልነት አድጓል፡፡ ስለሆነም በሆስፒታሉ ያለው ይኸው የአጥንት ሕክምና ማዕከል እንደ እናት ሆኖ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ አሥር የመንግሥት ሆስፒታሎች የየራሳቸውን የአጥንት ሕክምና ማዕከል እንዲያቋቁሙ ምክንያት ሆኗል፡፡ ማዕከላቱን ካቋቋሙ መካከልም የጂማ፣ የአዳማ፣ መቀሌ፣ ባህር ዳር፣ ሐዋሳ፣ ሆሳዕና፣ ድሬዳዋ ሆስፒታሎች ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በተረፈ ማኅበሩ ለአባላቱ በርካታ ጥቅሞችን አስገኝቷል፡፡ የውጭ አገር ስፔሻሊስቶችና ሰብ ስፔሻሊስቶችን በመጋበዝ ልምዶቻቸውን እንዲያካፍሉና የዕውቀት ሽግግር እንዲያደርጉ፣ በአጥንት ሕክምና ዙሪያ ጥናትና ምርምር እንዲያካሂዱ፣ የአቅም ግንባታ ሥልጠና እንዲያገኙ፣ ፓናሎች እንዲዘጋጁና በዚህም ትምህርት አዘል ውይይቶች እንዲደረጉ በማስቻል ዕውቀቶችን እንዲቀስሙ ተደርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- በማኅበሩ ከታቀፉት መካከል ሴቶች ስንት ይሆናሉ?

ዶ/ር ገለታው፡- በአገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ በአጥንት ሕክምና ላይ የተሰማሩ ብዙ ሴቶች እስካሁን አልነበሩም፡፡ እኛ ዘንድ ለብዙ ጊዜ አገልግለው በጡረታ በክብር የተሰናበቱ አንድ ሴት የአጥንት ሕክምና ባለሙያ ነበሩ፡፡ ማኅበራችን ለ16ኛ ጊዜ ባካሄደው ዓመታዊ ስብሰባ ላይ የሕይወት ተሸለሚ አድርጓቸዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በማኅበሩ ከታቀፉት አባላት መካከል አሥር ሴቶች አሉ፡፡ የአጥንት ሕክምና ያለምንም ልዩነት ሴቶች ሊሳተፉበት የሚቻል መሆኑን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የአጥንት ሰብ ስፔሻሊቲ ፕሮግራም መጀመሩ ይነገራል፡፡ በዚህ ዙሪያ ማብራሪያ ሊሰጡን ይችላሉ?

ዶ/ር ገለታው፡- የአጥንት ሰብ ስፔሻሊቲ ሥልጠናን ውጭ አገር ሄዶ መከታተል ያስቸግራል፡፡ ምክንያቱም ኢኮኖሚው አቅምን ስለሚፈትን ነው፡፡ ይህንነ ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የአጥንት ሰብ ስፔሻሊቲ ፕሮግራም ተጀምሮ ውጤታማና ስኬታማ በሆነ መንገድ እየተከናወነ ይገኛል፡፡ በዚህም እስካሁን ሁለት የአጥንት ሰብ ስፔሻሊስቶች ተመርቀው ወደ ሥራ የገቡ ሲሆን፣ ሌሎች ሁለት ሰብስፔሻሊቶች ደግሞ በቅርቡ ይመረቃሉ፡፡ ፕሮግራሙን የጎረቤት አገሮችም እንዲቋደሱት ተደርጓል፡፡  በዚህም መሠረት ከታንዛኒያና ከዚምባብዌ የመጡ ሦስት የአጥንት ሕክምና ስፔሻሊስቶች ፕሮግራሙን በመከታተል በሰብ ስፔሻሊቲ ተመርቀው ወደ አገራቸው ሄደዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የአጥንት ሕክምናና የአደጋዎች ሕክምና እንቅስቃሴ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል? ምን ችግርስ ገጠመው?

ዶ/ር ገለታው፡- የአጥንት ሕክምናና የአደጋዎች ሕክምና በደንብ መታየት አለበት፡፡ እኛ አገር የተለመደውና መንግሥትም ትኩረት የሚሰጠው መከላከል በሚቻለውና ተላላፊ በሆኑ በሽታዎች ዙሪያ (ኤችአይቪ፣ ቲቢ፣ ወባ ወዘተ) ነው፡፡ የአጥንት አደጋ መጠን በአሁኑ ጊዜ በጣም ተንሰራፍቷል፡፡ ከፍጥነት በላይ የማሽከርከሩ ሁኔታ ጨምሯል፡፡ ብዙ ሰዎች በየቀኑ በተሽከርካሪ እየተገጩ ለጉዳት ብሎም ለህልፈተ ሕይወት ይዳረጋሉ፡፡ ከዚህም ሌላ ብዙ የሕንፃ ሥራዎችና ግንባታዎች ላይም በርካታ ሰዎች ሲጎዱ ይስተዋላል፡፡ ብዙ ፋብሪካዎችም እየተከፈቱ ሲሆን፣ በዚያው ልክም ከማሽኖች ጋር በተያያዘ አያሌ ሠራተኞች ይጎዳሉ፡፡ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በአሁኑ ጊዜ እየሠራ ካለው የሕክምና ተግባራት ውስጥ ከ97 በመቶ በላይ የሚሆነው ከአደጋ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ስለዚህ የአጥንት ሕክምና ሥርዓት የማጠናከሩ ጉዳይ ቸል ሊባል አይገባም፡፡ ለሕክምናው የሚውሉ ግብዓቶችም ያለምንም ችግር ማቅረብ ግድ ይላል፡፡ ይህ ባለመሆኑ የተነሳ አብዛኛውን ግብዓት የምናገኘው በዕርዳታ ነው፡፡ ይህ ግን ሊቀጥል አይገባም፡፡ በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት ዕርዳታው ሊቋረጥና ሊቆም ይችላል፡፡ ሕክምናውም ባለበት የመቆም አጋጣሚ ይደርስበታል፡፡

ሪፖርተር፡- ግብዓቶችን በዕርዳታ የሚሰጡት የየትኞቹ አገሮች የሕክምና ተቋማት ናቸው?

ዶ/ር ገለታው፡- ወደ ዕርዳታው ከመግባታችን አስቀድሞ ስለ ሕክምናው አሰጣጥ በመጠኑም ቢሆን ባብራራ ጉዳዩን ግልጽ ያደርገዋል፡፡ ቀደም ባሉት ዓመታት በእግሩ ላይ ጉዳት የደረሰበት ታካሚ ያለው ምርጫ በጀሶ መታሰርና ከዚያም የቆሰለ ነገር ካለ ቆርጦ መጣል ብቻ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ሕክምና ቢያንስ አራት ወራት ይፈጃል፡፡ ከአሥር ዓመታ ወዲህ ግን ሕክምናው እየተሻሻለ መጥቷል፡፡ በተጎዳው አካል ላይ ብረት በማስገባት ካለምንም ችግር እንዲራመድ ያስችላል፡፡ ሕክምናውም የሚፈጀው ጊዜ አራት ቀናት ብቻ ነው፡፡ ከተጠቀሰው ቀናት በኋላ በእግሩ ይሄዳል፡፡ በግብዓትነት የገባው ብረት ግን እጅግ በጣም ውድ ነው፡፡ ግብዓቱን የምናገኘው በልመና ነው፡፡ በዚህ በኩል እስካሁን ያልተቋረጠ ዕርዳታ እያደረገልን ያለው አሜሪካ የሚገኘው ‹‹ሰርጂካል ኢንተርናሽናል ጀኔሬሽን ኔትወርክ›› የተባለ ኩባንያ ነው፡፡ ኩባንያው አንድም ጊዜ ሳያቋርጥ ድጋፍ ማድረግ ከጀመረ 12 ዓመት ሆኖታል፡፡ አልፎ አልፎ ከአውስትራሊያና ከስዊዘርላንድ እናገኛለን፡፡

ሪፖርተር፡- አንዳንድ ግብዓቶችን በአገር ውስጥ ለማምረት አልተሞከረም?

ዶ/ር ገለታው፡- አንዳንድ ግብዓቶች እዚሁ የሚመረቱበትን ለማመቻቸት ያላንኳኳንበት በር የለም፡፡ ሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በመከላከያ ሚኒስቴር የቀድሞ ሜቴክ ሁሉ ሄደን አነጋግረናል፡፡ ትልቁ ችግራችን የሆነው አንድ ሰዓት ለይ ሄደን እናገኛቸዋለን እናወራቸዋለን፡፡ እነሱም ፍላጎት ያድርባቸዋል፡፡ ግን ከሰዓት በኋላ ተመልሰን ስንሄድ በቦታው ላይ ሌላ አዲስ ሰው ተተክቶ እናገኛለን፡፡ ጉዳዩ በእንጥልጥል ይቀራል፡፡ ሆኖም ለዚህ የሚውል በጀት አይጠፋም ነበር፡፡ ነገር ግን ለብዙ ነገሮች ሲወጣ ይታያል፡፡ ችግሩ የበጀት ዕጦት ሳይሆን የቁርጠኝነት ችግር ነው፡፡ የአጥንት ሕክምናን በተመለተ የኢንሹራንስ ሥርዓት ያስፈልገዋል፡፡ ይህን ሲስተም ተግባራዊ ለማድረግ ከወዲሁ ሊታሰብበት እንደሚገባው ተናግረን ነበር፡፡ ጉዳዩን ከቁም ነገር የቆጠረ የለም፡፡ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የአጥንት ሕክምና ለማግኘት እስከ 700 የሚሆኑ ታካሚዎች ወረፋ ይጠባበቃሉ፡፡ በየሳምንቱ አገልግሎቱን የሚያገኘው ግን አንድ ሁለት ታካሚ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ችግር ለመላቀቅ ያለው አማራጭ ግብዓቶችን በአገር ውስጥ ማምረት አለበለዚያ ከውጭ እየተገዙ የሚገቡበትን መንገድ ማመቻቸት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በየሆስፒታሎቹ የትራዎማ ማዕከላት እንዲቋቋሙ ማድረግ ግድ ይላል፡፡ አሁን ያሉት ማዕከላት እንደ አገር ሲታይ በቂ አይደሉም፡፡ ይህም የሚያሳየው የትራዎማ ሕክምናችን አደጋ ላይ መሆኑን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የአደጋዎችን መጠን ለመቀነስ ምን መደረግ አለበት ይላሉ?

ዶ/ር ገለታው፡- አደጋ ማከም ብቻ ሳይሆን እንዳይከሰት ያስፈልጋል፡፡ አደጋ መከላከል ላይ ብዙ ሥራዎች መከናወን አለባቸው፡፡ በዚህም ብዙ ለውጥ ማምጣትና የተሽከርካሪንም አደጋ መቀነስ ይቻላል፡፡ መከናወን ከሚገባቸውም ዋና ዋና ሥራዎች መካከል ከሥልጠና ጀምሮ የመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ ላይ ጥንቃቄ ማድረግ፣ የመንገዶችን ደኅንነት ማሟላት፣ የማኅበረሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ ወዘተ ይገኙበታል፡፡ የተሽከርካሪ አደጋ ደርሶባቸው ለሕክምና ከሚመጡት መካከል አንዳንዶቹ ሥልጠናውን በበቂ ሁኔታ ያልተከታተሉ፣ የመንጃ ፈቃዱን በገንዘብ ያገኙ ሲሆን፣ አምስት ሰዎች ጭነው ሲያሽከረክሩ በራሳቸውና በተሳፋሪዎቻቸው ላይ አደጋ የሚያደርሱ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- በተለያዩ ምክንያቶች ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በባህል ሕክምና ወጌሻ፣ የመታሸት ወዘተ ሕክምና ሲያደርጉ ይስተዋላሉ፡፡ በዚህ ላይ ያለዎትን አስተያየት ያካፍሉን?

ዶ/ር ገለታው፡-አሁን ያለው ዘመናዊ ሕክምና ከባህል ሕክምና የመጣና የተወሰደ ነው፡፡ ከዚያም ሳይንስ በአንድ ጊዜ ዘመናዊ የሆነ ሕክምና የለም፡፡ በአገራችን ያለው ባህላዊ ሕክምና ምንም ዓይነት ማሻሻያ ሳይደረግበት አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡ ይኼም ማለት ዱሮ ይደረግ የነበረ ማሸት፣ ማሰር አሁንም ቀጥሏል፡፡ ብዙ ሰዎችም የባህሉን ሕክምና ሲመርጡ ይስተዋላል፡፡ ከዚህም ሌላ አንዳንድ ሰዎች እግራቸው ሲያብጥ ወይም ሲጎዳ በሞቀ ውኃ ይዘፈዝፉታል፡፡ የሞቀው ውኃ ላይም ጨው አክለውበት ይጠቀማሉ፡፡ ይህም አግባብ አይደለም፡፡ ሙቅ ውኃ የደም ሥሮች እንዲያብጥ ያደርገዋል፡፡ መታሸት ደግሞ የደም ሥሮችን ያደማል፡፡ አሁን ደግሞ እየመጣ ያለው ‹‹የታከምኩት ወጌሻ ዘንድ ሄጄ ነው፡፡ ያከመኝም የተነሳሁትን ራጅ ካየ በኋላ ነው›› የሚል የተሳሳተ አስተሳሰብና አመለካከት ነው፡፡ ራጅ ማየትን በተመለከተ ግን ባለወጌሻው ቀርቶ ጠቅላላ ሐኪም የሚያየውና ስፔሻሊስትና ሰብ ስፔሻሊስት ሐኪሞች የሚያዩት ራጅ እኩል ወይም አንድ ዓይነት አይደለም፡፡ የመጀመሪያው ሐኪም ስብራት ያለውን ስፔሻሊስቱ ወይም ሰብ ስፔሻሊሲቱ ስብራት የለውም ሊሉ ይችላሉ፡፡ ምክንያቱም ሙያተኞቹ የተማሩትን ነው የሚያዩት፡፡ ያልተማረውን ሊያይ አይችልም፡፡ የባህል ሐኪም ግን ሕክምና ትምህርት ቤት ገብቶ አያውቅም፡፡ ቤተሰቦቹ ሲያሹ ያየውን እሱም ይህንን ይቀጥልበታል፡፡ በዚህም በተለይ ብዙ ወጣቶች ሲሄዱ ይስተዋላል፡፡

ሪፖርተር፡- የተመረቁ ሐኪሞች ሥራ ያለማግኘትን በተመለከተ እንዴት ያዩታል?

ዶ/ር ገለታው፡- ኢትዮጵያ ውስጥ ከተመረቁ በኋላ ሥራ አጥ የሆኑት የኢንጂነርና የሳይንስ ተመራቂዎች ነበሩ፡፡ አሁን ደግሞ ሕክምና ተተካ፡፡ ይኼ ችግር የተፈጠረው ከፖሊሲ ችግሮች ነው፡፡ በተረፈ ኢትዮጵያ ከበሽታ ነፃ ሆናና ታካሚ ጠፍቶ አይደለም፡፡ እንኳን ኢትዮጵያ አሜሪካም ቢሆን የጤና ባለሙያ የፍላጎት ደረጃው ላይ ገና አልደረሱም፡፡ ለዚህ ነው ከተለያዩ ታዳጊ አገሮች ያሉትን በሳል ሐኪሞች እየሰበሰቡ የሚገኙት፡፡ ከፖሊሲ ችግሮች መካከል አንዱ ብዙ ዩኒቨርሲቲዎች ሕክምና ኮሌጆችን መክፈት አልነበረባቸውም፡፡ ምክንያቱም ያሉት መሠረተ ልማቶች ይህንን የሚያስኬዱ አይደሉም፡፡ ቀደም ባሉት ዓመታታ የሕክምና ኮሌጅ ያላቸው የአዲስ አበባ፣ የጅማና የጎንደር ዩኒቨርሲቲዎች ብቻ ነበሩ፡፡ ከዚያም እንደ ፋሽን ሆነና በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች የሕክምና ኮሌጆች ተከፍተው የተመረቀ ሐኪም ምንም ዓይነት የሥራ ልምድ ሳይኖረው እንዲያስተምር ተደረገ፡፡ ብዙ መመረቅም ተጀመረ፡፡ የተመረቁትንም የሚቀበል ተቋም ጠፋ፡፡ የትምህርቱም ጥራት በዚያው መጠን አሽቆለቆለ፡፡ ሌላው የፖሊሲ ችግር ጤና ጣቢያዎች ሐኪም የሌላቸውና አሁንም በድሮ ፋሽን እያከሙ ያሉት ነርሶች መሆናቸው ነው፡፡ በጤና ጣቢያ ደረጃ ጠቅላላ ሐኪሞች ወይም ፋሚሊ ፊዚሽያን ማስገባት ይቻላል፡፡ በሆስፒታል ደረጃ መታከም ያለበትን ደግሞ ወደ ሆስፒታል ሪፈር ሊያደርጉ ይችሉ ነበር፡፡ ይህ ባለመሆኑ ጤና ማዕከላት እስካሁን የጠቅላላ ሐኪም ክፍተት ይታይባቸዋል፡፡ በተጠቀሰው መንገድ እንዲንቀሳቀሱ ቢደረግ ግን የተመራቂ ሐኪሞች ሥራ የማግኘት ዕድል ይኖራቸው ነበር፡፡  

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች