በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የወጣውና ከወር በፊት ተግባራዊ የሆነው የሲሚንቶ ግብዓት ሥርጭት መመርያ ቁጥር 908/2014 ተግባራዊ ባለመደረጉ፣ ሰሞኑን ለተከሰተው የሲሚንቶ መጥፋት ምክንያት መሆኑን የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ አስታወቀ፡፡
ይህ መመርያ በሚተገበርበት ወቅት ግን የግል ጥቅማቸውን በማስቀደም ከተቀመጠው መመርያ ውጪ ችግሩን የሚያባብሱ ግለሰቦችና ድርጅቶች መኖራቸውን የጠቀሱት የንግድ ቢሮው ኃላፊ አቶ አደም ኑሪ፣ ችግሩን በሚያባብሱ ግለሰቦችና ድርጅቶች ላይ ዕርምጃ እንደሚወሰድ ገልጸዋል፡፡
መመርያው ተግባራዊ ሲደረግ ሲሚንቶ በኤጀንቶች፣ አከፋፋዮችና በችርቻሮ መሸጫ በኩል መሸጥ እንዳይችሉ የሚያደርግ ነው፡፡
ግብይቱን መስመር ለማስያዝ ለመንግሥት ፕሮጀክቶችና ሌሎች ቅድሚያ ለሚሰጣቸው የግል ፕሮጀክቶች በቀጥታ፣ ከኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶችና ልማት ድርጅትና ከኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ብቻ ምርቱ እንደሚከፋፈል አቶ አደም አስረድተዋል፡፡
አዲሱ መመርያ ሲሚንቶ የማከፋፈል ኃላፊነት ከተሰጣቸው ውጪ ሌሎች አካላትን ከገበያ እንዲወጡ እንደሚያደርግ ደንግጓል፡፡ ለአሥር ዓመት ያህል በሲሚንቶ ችርቻሮ ንግድ ላይ የተሰማራች ነጋዴ ለሪፖርተር እንደተናገረችው፣ ከነሐሴ ወር ጀምሮ ሙሉ በሙሉ የሽያጭ ሱቋን በመዝጋት ከገበያ ወጥታለች፡፡
የኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ግርማ ሀብተ ማርያም፣ አዲሱ መመርያ ተግባራዊ እስከሚሆን ድረስ ክፍተት ይኖራል ብለዋል፡፡
በመመርያው መሠረት በፌደራል መንግሥት ሥር ያሉ ፕሮጀክቶች የሚያስፈልጋቸውን የሲሚንቶ መጠን ለኮንስትራክሽን ባለሥልጣንና ለንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር እንዲያሳውቁ ተደርጎ፣ ከየፋብሪካው በሚመደብ ኮታ መሠረት ለሲሚንቶ አቅራቢዎች ይሰጣል፡፡
‹‹አቅራቢዎች በመመርያው መሠረት ኮታቸው እስከሚታወቅ ድረስ ሲሚንቶ ከፋብሪካ ማውጣት ካልቻሉ የሰሚንቶ እጥረት ይፈጠራል፡፡ መመርያውን በማይተገብሩ የማይመለከታቸው ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች አማካይነት የሚወጣ ሲሚንቶ ከ1,600 ብር በላይ ይሸጣል፡፡ ሰሞኑን የተከሰተው እጥረትም መመርያው ተግባራዊ እስኪሆን የተፈጠረ ክፍተት ነው፤›› ሲሉ አቶ ግርማ ገልጸዋል፡፡
የሲሚንቶ እጥረት በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ያጋጠመ አይደለም የሚሉት ደግሞ፣ የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አበጀ አየው ናቸው፡፡
አዲሱ መመርያ ከወጣ በኋላ የአማራ ክልል የራሱ የሆነ የማስፈጸሚያ መመርያ ማውጣቱን የገለጹት አቶ አበጀ፣ በመመርያው መሠረት ክልሉን የሚወክሉ 24 የሲሚንቶ አቅራቢዎች ተመርጠው ወደ ሥራ መግባታቸውን አስረድተዋል፡፡
ለአማራ ክልል በወር የተመደበው የሲሚንቶ ኮታ መጠን 610 ሺሕ ኩንታል እንደሆነ፣ በሐምሌ ወር 2014 ዓ.ም. ለክልሉ የደረሰው 260 ሺሕ ኩንታል ብቻ መሆኑን አቶ አበጀ ገልጸዋል፡፡ አቅራቢዎቹ ለክልሉ የተመደበውን ኮታ ከሰባት ፋብሪካዎች እንደሚያገኙ፣ ለክልሉ የሚያስፈልገውና እየደረሰ ያለው የሲሚንቶ መጠን አነስተኛ የሆነበት ምክንያት መኖሩን አስረድተዋል፡፡
ለአማራ ክልል ሲሚንቶ ከሚያቀርቡት ሰባት ፋብሪካዎች መካከል ኢስት ሲሚንቶ በማሽን ብልሽት ምክንያት ምርት እያቀረበ አለመሆኑን፣ ሙገር ሲሚንቶ ለኮይሻ ፕሮጀክት በትዕዛዝ እያቀረበ ስለሆነ ለክልሉ ማቅረብ አለመቻሉን፣ ከፋብሪካዎቹ የወጡት ሲሚንቶዎች በተለያዩ ምክንያቶች መንገድ ላይ ረጅም ጊዜ መቆየታቸው ከምክንያቶቹ መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ ከሁለት ዓመታት በፊት ለጀመረው የሲሚንቶ እጥረት ምክንያት ፋብሪካዎቹ ማምረት ከሚችሉት በታች ማምረታቸው፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረትና የኃይል መቆራረጥ ችግሮች ይጠቀሳሉ፡፡
በአገሪቱ በዓመት የሚያስፈልገው የሲሚንቶ መጠን ከ15 እስከ 17 ሚሊዮን ቶን ሲሆን፣ በሥራ ላይ የሚገኙት 13 የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በአጠቃላይ የሚያመርቱት 6.3 ሚሊዮን ቶን ብቻ ነው፡፡